
አዲስ አበባ፡- የወረቀት ኢንዱስትሪዎች ተረፈ ምርትን ብቻ ሳይሆን ጥሬ ግብዓትን ተጠቅመው ማምረት እስከሚጀምሩ ድረስ የህትመት ሚዲያዎች በወረቀት መወደድ ምክንያት እንዳይጠፉ ይታገዛሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር በነበራቸው ውይይት በተለይም የህትመት ዘርፉን ማነቆ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በወረቀት መወደድ ምክንያት የህትመት ሚዲያዎች እንዳይጠፉ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።
እስከ አሁንም የዘርፉን ችግር ለመፍታት መንግሥት ሲሠራ እንደነበር አውስተው፤ ለሁለትና ሶስት ባለሀብቶች በነጻ ቦታ በመስጠት የወረቀት ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
እስከ አሁን ኢንዱስትሪዎቹ ወረቀት የሚያመርቱት ከተረፈ ምርት ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጥሬ ግብዓቶችን ተጠቅመው ወረቀት እስከሚያመርቱ ድረስ የህትመት ሚዲያው የሚታገዝ መሆኑን አመልክተዋል።
ሚዲያዎችን ሁሉ በፋይናንስ መደገፍ አስፈላጊ እንደሆነ፤ ነገር ግን ብዛታቸው ችግሩን በቀላሉ ለመፍታት አዳጋች እንደሚያደርገው ጠቅሰው፤ ያም ሆኖ ከክልል አመራሮች እና ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጋር በመነጋገር ችግሩ የሚፈታ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ሁሉም ሚዲያዎች የሚሠሩት ለሀገር በመሆኑ ከልመና እና ከተረጂነት ወጥተው መርህ ላይ ቆመው መሥራት እንዲችሉ እንደየሥራ ባህሪያቸው እና እንደየ ይዘታችው ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል። ኢትዮጵያ የራሷ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሳተላይት እንዲኖራት እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የሚዲያው ኢንዱስትሪ አራተኛው የመንግሥት አካል ተብሎ የሚጠራ እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ዋናው ተልዕኮውም ማህበረሰባዊ ንቃት መፍጠር እንደሆነ ጠቅሰዋል። የነቃ ማህበረሰብ ብሄራዊ ጥቅሙን፣ ጠላቱን ፣ወዳጁን፣ ፍላጎቱን ፣ አቅሙን ፣ ዓለምን እንዲሁም ራሱን ያውቃል ነው ያሉት።
ሚዲያው የጋራ ራዕይ እና የጠራ አስተሳሰብ ኖሮት መገንባቱ ተልእኮውን ለመፈጸም ያስችለዋል ብለዋል።
ጋዜጠኞች ከሚነገራቸው ነገር በላይ አሻግረው ካልተመለከቱ ጥፋት ይመጣል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንድ ጋዜጠኛ ስለሰማ ወይም ስለአየ ብቻ ሳይሆን ከሰማውና ካየው ጀርባ መተንተን የሚችል መሆን አለበት ነው ያሉት። ጉዳዩ ለሀገራዊ ጥቅም ምን ፋይዳ አለው ብሎ መመልክት እንደሚገባውም ጠቅሰዋል።
ጋዜጠኛ ምክንያትና ውጤትን መተንተን የሚችል፤ ለክስ እና ለወቀሳ ያልቸኮለ መሆን እንደሚገባውም አመልክተዋል ጋዜጠኝነት ዜግነት እንደሌለው ተደርጎ መታሰብ እንደሌለበት ጠቁመው፤ ልክ እንደወታደር፣ እንደ ሀኪም፣ እንደመምህር፣ እንደደህንነት ሠራተኛ ሁሉ ጋዜጠኝነትም ዜግነት ያለው ነው ብለዋል። ጋዜጠኝነት ብሄራዊ ፍላጎት፣ የሚቆምለት ሀገር እና ባህል ያለው መሆኑን አስረድተው፤ ያን እያሰቡ ለእውነት ቆሞ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
እንደሀገር ሀገራዊ ፍላጎትና ጥቅም ላይ በጋራ ያለመቆም ችግር የሚስተዋል መሆኑንም ጠቅሰዋል። ሀገርን ከጥይት በፊት የሚያፈርሳት ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ አመልክተው፤ ጋዜጠኞች ሀገራዊ ጥቅምና ፍላጎትን መሠረት በማድረግ እውነትን እየገለጡ ሀገርን ከጥፋት መታደግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የሚዲያ ውግንናው ለእውነት እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ስንዴን በስፋት ታመርታለች የሚለውን ሀቅ የሚሞግቱ አካላት መኖራቸውን ለአብነት ጠቅሰው፤ እንዲህ አይነት ጉዳዮች ሲነሱ ሚዲያዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች ተሰማርተው እውነታውን ለሕዝብ የመግለጽ ልምድ እንዲኖራቸው አሳስበዋል።
ሚዲያዎች ከአካባቢያዊነት ወጥተው በተለያዩ ቋንቋዎች ለወንድምና እህት ጎረቤት ሕዝቦች ተደራሽ በሚሆኑባቸው ጉዳዮችም ላይ ትኩረት ሰጥተው ቢሠሩ ተመራጭ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የአየር ሰዓት (ፍሪኩየንሲ) በጣም ውድ ሀብት እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን ውድ ሀብት እንደኢትዮጵያ ያለ ደሃ ሀገር ለልማትና ለመንቃት ፣መጠቀም ሲገባው፤ ለአልባሌ ወሬ ካባከነው ገንዘብ እንደማባከን ይቆጠራል ብለዋል።
ሀገር ውስጥ ያሉ አንዳንድ የዩቱዩብም ይሁን ብሮድ ካስት ሚዲያዎች ከሰፈር እና ከመንደር ጉዳይ ያልወጡ፤ ቁምነገር የማይገኝባቸው መሆናቸውን እና ለሚዲያ ሥራ የተሻለ ቅርብ ናቸው የተባሉ ውጭ አሉ የሚባሉትም የጎደለንን እውቀት የሚሞሉ ሳይሆኑ የሚበጠብጡ እንደሆኑ ተናግረዋል።
በሚዲያ ተቋም ውስጥ ያለ አብዛኛው ጋዜጠኛም መረጃ አነፍናፊ በመሆን እውነተኛ እና ተጨባጭ መረጃን ተደራሽ ማድረግ የተፈላጊነቱን ደረጃ ማሳደግ ይኖርበታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም