
አዲስ አበባ፡- የግሉ ሴክተር ከመንግሥት ጋር በመተባበር ወጣቶችን በማብቃት የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት በማሳደግ ረገድ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ የግብርና ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።
የግብርና ሚኒስቴር አማካሪ አለማየሁ መኮንን አዩቴ አፍሪካ ቻሌንጅ ኢትዮጵያ 2025 የተሰኘ ግብርናን በማዘመን ሥራ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የቴክኖሎጂ ውድድር ማጠቃለያ መርሀግብር ትናንት ሲካሄድ እንደተናገሩት ፤ መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ወደ ውጤታማነት ለማሸጋገር ከሚያከናውናቸው በርካታ ተግባራት በተጨማሪ የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ትብብርን ይሻል። በዚህም የግሉ ዘርፍም ከመንግሥት ጋር በትብብር በመሥራትና ወጣቶችን በማብቃት የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ዘርፍ ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።
ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን መደገፍ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ያሉት አማካሪው፤ የተከናወነው የፈጠራ ውድድርም በግብርና ዘርፍ ያሉ ችግሮችን የሚፈቱ ሃሳቦች ያሏቸውን ወጣቶች በማውጣት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።
የሀይፈን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ አየለ በበኩላቸው፤ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታትና ማብቃት በምግብ ራስን የመቻል ግብን እውን ለማድረግ ይረዳል ሲሉ ገልጸዋል።
በምግብ ራስን ለመቻል የመፍትሄ ሃሳብ የሚያመጡ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን መደገፍ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበው፤ ተቋማቸው በግብርናው ዘርፍ ያሉ ሥራ ፈጣሪዎችን የማበረታታትና ማብቃት ሥራውን የሚቀጥልበት ስለመሆኑ አንስተዋል።
የግሮውዝ ቲፕ ኮንሳልቲንግ ሥራ አስኪያጅ ሀምዴኖ ሚዴሶ በበኩላቸው፤ ይህ የወጣቶች የግብርና እና ቴክኖሎጂ ውድድር ግብርናን ከማዘመን ባለፈ ሥራ ፈጣሪ እና ችግር ፈቺ ወጣቶችን ለማበረታታት ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ዩቲ ወጣቶች የግብርና ተግዳሮትን ለመፍታት የሚያስችሉ የመፍትሄ ፈጠራዎችን እንደሚደግፍ የተገለጸ ሲሆን፤ የግሉ ዘርፍም የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍና ወጣቶችን ለማብቃት እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
እስከ አሁን በተደረጉ ሶስት ዙር ውድድሮች ከ1ሺህ 500 በላይ የፈጠራ ሃሳቦች የቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ዘጠኝ ያህሉ መሸለማቸው ተመላክቷል። በአሁኑ ውድድር አሸናፊ የሆኑት ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች የገንዘብ ሽልማት ብቻ ሳይሆን የፈጠራ ሃሳባቸው እንዲተገበር ድጋፍ ይደረግላቸዋል ተብሏል።
በውድድሩ ከ 1 እስከ 10 የወጡ ተወዳዳሪዎች እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን ከአንድ እስከ አምስት ለወጡት የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል። በዚህም መሠረት 1ኛ አማረ አዲስ 15ሺህ፣ 2ኛ ዶክተር በአምላክ ካሳሁን 10ሺህ፣ 3ኛ ማህደር ሰለሞን 7ሺህ 4ኛ ሁንዱማ አቶምሳ 5ሺህ 5ኛ ቤተልሄም ጥላሁን እና ጀቤሳ ጫላ 2ሺ 500 የአሜሪካን ዶላር መሸለማቸው ታውቋል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም