ያልተሰማው የአትሌቶች ድምፅ

ከሳምንት በፊት በተካሄደው የግራንድ ስላም ትራክ ውድድር ተሳታፊ የነበሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባስመዘገቡት ደረጃ መሠረት የተበረከተላቸው የገንዘብ ሽልማት በጥቅሉ 305ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነበር:: ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገና ከዓለም ላይ እየጠፋ ነው በሚል ስጋት ላሳደረው የመካከለኛና ረጅም ርቀት የመም ሩጫ ተስፋን ያጫረ ውድድር የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ በእጅጉ ስቧል:: ከጅምሩ ድንቅ ፉክክር የታየበትና የስፖርት ቤተሰቡን የሳበ ውድድር እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የአትሌቶች ሀገር ተጨማሪ የውድድር ዕድልን የሚፈጥር፤ ሀገርም በአትሌቶቿ አማካኝነት ከፍተኛ የሚባል የውጪ ምንዛሬ የምታገኝበት ነው::

በእርግጥ እንደ ኦሊምፒክ፣ የዓለም ቻምፒዮና፣ የቤት ውስጥና የሀገር አቋራጭ ቻምፒዮናዎች፣ ዳይመንድ ሊግ ካሉ ታላላቅ ውድድሮች ባለፈ በየሳምንቱ በተለያዩ የዓለም ከተሞች የሚደረጉ ውድድሮች ከፍተኛ መጠን ያለው የውጪ ምንዛሬ በሽልማት መልክ ይገኛል:: ኢትዮጵያ ካላት የአትሌቶች ቁጥር እንዲሁም የተደራጀና ራሱን የቻለ አሠራር በዚህ ረገድ ባለመኖሩ ምን ያህል ገቢ በስፖርቱ እንደሚገኝ ማወቅ አይቻልም:: ነገር ግን ከውድድሩና ከተወዳዳሪዎቹ አንጻር መገመት አያዳግትም:: በአሜሪካዊው አትሌት የተጀመረው ይህ ውድድር ደግሞ በዓመት ውስጥ አራት ጊዜ እንደመከናወኑ አንድ አትሌት በእያንዳንዱ ውድድር ቢያሸንፍ 400ሺህ ዶላር እንደሚያገኝ ማስላት ይቻላል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተቸረችው ይህ የአትሌቲክስ ሀብት ታዲያ በትኩረት ቢሠራበት የክብሯ መሠረት ብቻም ሳይሆን የኢኮኖሚዋም የጀርባ አጥንት ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነው:: በርካታ ሀገራት ለተሳትፎ ብቻ ሲሉ በሚካፈሉበት እንደ ኦሊምፒክ ባሉ የስፖርታዊ ውድድር መድረኮች ኢትዮጵያ በርካታ ታሪክ ልታስመዘግብ ችላለች:: አንድ ልኡክ ሊያሳካ ያልቻለውን ድልም አንድ አትሌት በግሉ ማሳካት መቻሉንም በተደጋጋሚ መመልከት ችለናል:: ታዲያ ይሄ ሁሉ አቅምና ስጦታ ያላት ኢትዮጵያ ስፖርቱን በምን መልኩ እየደገፈችው ይገኛል የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ነው::

አትሌቲክስ ለኢትዮጵያ የመልካም ገጽታዋ መታያ ሆኖ ሳለ የሚገባውን ባለማግኘቱ ግን የተበደለ ስፖርት ነው:: በሺዎች የሚቆጠሩና ነገ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ከፍ ለማድረግ ለሚተጉ አትሌቶች ቢቻል በየስፍራው በብዛትና በጥራት ትራክ/መሞችን ማዘጋጀት በተገባ ነበር:: ይሁንና ቀድሞ የነበረውን የአዲስ አበባ ስታዲየም መም እንኳን በእድሳት ምክንያት በመዘጋቱ እነሆ ለዓመታት አትሌቶችና መም የተራራቁ ሊሆኑ ችለዋል:: ፌዴሬሽኑ ለሚያዘጋጃቸው ውድድሮችና የብሄራዊ ቡድን ሥልጠናዎች የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚን መም የሚዋስ ቢሆንም ከጫና ብዛት በመጎዳቱ ምክንያት ከጥቅሙ ጉዳቱ እየጎላ መጥቷል:: በመሆኑም አትሌቶች መደበኛ ልምምዳቸውን ለመሥራት ሱሉልታ የሚገኘውን የአትሌት ቀነኒሳ በቀለን መም እንደ አማራጭ የሚጠቀሙ ቢሆንም ከቁጥራቸው አንጻር በሚፈለገው ልክ እየተገለገሉ አይደለም:: በክልል የሚገኙ ስታዲየሞች ያሉ መሞችም ቢሆኑ አትሌቶች በስፋት ከሚገኙባቸው ሥፍራዎች የራቁና የአየር ሁኔታውም እንደሚፈለገው ባለመሆኑ ግልጋሎታቸው እምብዛም ነው::

በዚህም ምክንያት አትሌቶች ብቻም ሳይሆኑ በዓለም ላይ ያስጠራንና ክብርን ያጎናጸፈን ብቸኛው ስፖርታችን በእጅጉ እየተጎዳ ይገኛል:: እንደ ጅቡቲ ያሉ ስፖርት እምብዛም የማይነገርባቸው ሀገራት ሳይቀሩ ዓለም አቀፍ ሚቲንጎችን (የአንድ ቀን ውድድር) ሲያስተናግዱ እንደ ኢትዮጵያ ያለችው ባለ ግዙፍ ስም ያላት የአትሌቲክስ ሀገር ግን ሌላውን ዓለም ለመጋበዝ ቀርቶ ለራሷም አልበቃችም:: በእርግጥ አትሌቲክስ እንደ እግር ኳሱ አልተሰደደም እንጂ አስከፊ ሁኔታ በማሳለፍ ላይ ነው::

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በስፖርቱ ውጤታማ ለመሆን አትሌቶች ከሚያደርጉት ጥረት ባለፈ በተፈጥሮ የታደለችው የአየር ሁኔታና የቦታ አቀማመጥ ከፍተኛ ሚና አለው:: በተለይ እንደ በቆጂ ያሉ ሥፍራዎች ደግሞ እጅግ በርካታ ጀግና አትሌቶችን በማፍራት አሁንም ድረስ የሀብት ምንጭ ናቸው:: ታዲያ ይህ ድንቅ አካባቢ በውጪ ሀገራት ጎብኚዎችና የስፖርቱ አፍቃሪያን ሊታይ የሚፈለግ ብቻም ሳይሆን ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ፊልም ሠሪዎች መዳረሻቸው ሊያደርጉት የሚፈልጉት ነው:: የሌሎች ሀገራት ሯጮችም ጭምር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ካገኙት የተፈጥሮ ብርታት ለመቋደስ አካባቢውን ያዘወትራሉ::

ይህም አካባቢውን ከፍተኛ የስፖርት ቱሪዝም መስህብ ሊያደርገው የሚችል፣ ኢትዮጵያም እንደሌሎች ሀገራት የኢኮኖሚ መሠረት ልታደርጋቸው ከምትችላቸው ዘርፎች መካከል ነው:: ነገር ግን ሥፍራው ለዘመናት ከነበረ ተፈጥሯዊ አቀማመጡ ባለፈ በመም ላይ ዝግጅት ማድረግ የማይታሰብበት ነው:: የአሸናፊነት ታሪክ የተጻፈበትን ይህን ድንቅ ሥፍራ መንግሥትም ሆነ ከሥፍራው የወጡ ምርጥ አንጋፋ አትሌቶች የሚበጃትን አልሠሩላትም:: ይህ ታዲያ የታሪካዊዋ በቆጂ ነባራዊ ሁኔታ ብቻም ሳይሆን በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ያለ እውነታ ነው:: የማሠልጠኛ ማዕከላትም በየሥፍራው የተገነቡ ቢሆንም ሠልጣኞች ከመም ጋር የሚተዋወቁት በውድድር አሊያም አካዳሚዎችን ሲቀላቀሉ ብቻ ነው::

ይህ ሁኔታ መደበኛው ሥልጠና ላይ ምን ያህል ተጽእኖ እንደሚያሳርፍም በቅርቡ በተካሄደው የኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣቶች ስፖርታዊ ውድድር ላይ የታየ ነው:: ክለቦችም ቢሆኑ ለመሰል እጣ ፋንታ የተዳረጉ በመሆኑ ሥልጠናዎቻቸውን በተለያዩ የቦታ አቀማመጦች እንዲሆም ጎዳና ላይ ለማድረግ ተገደዋል:: በዚህም ለመኪና አደጋ ተጋልጠው ለሞት የተዳረጉት አትሌቶች ጥቂት አይደሉም:: በመሆኑም አትሌቶች እየተበታተኑና በለጋ እድሜያቸው ከመም ወደ ጎዳና ውድድር እየተሸጋገሩ ይገኛሉ:: ይኸው ሁኔታ ተስፋ ያስቆረጣቸውና እንዳሰቡት ስመጥር አትሌቶችን ለመፍጠር አዳጋች የሆነባቸው በርካታ አሠልጣኞች ሀገር ጥለው እየተሰደዱ መሆናቸው በተለያዩ መድረኮች ላይ ይነሳል::

ይህ ሁሉ ባለበት ሂደት ግን መንግሥት ትኩረቱን ከውጤታማው መም ይልቅ ለእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ አድርጓል:: በዚህም ምክንያት እንደ አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ያሉና ለስፖርቱ በብዙ መንገድ መፍትሄ ይሆናል በሚል ተስፋ የተጣለበት የመም ሥራ ፌዴሬሽኑ በራሱ ተነሳሽነት የውጪ ምንዛሬ አውጥቶም ሥራው ግን ተፈጻሚ ሊሆን አልቻለም:: በእርግጥ ስፖርቱን የሚመራው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር በተደጋጋሚ ለሚቀርበው የስፖርቱ ባለሙያዎች ሮሮ ቅድሚያ እንደሚሰጥና የመም መሥሪያ ግብዓቱም ጉምሩክ መግባቱን በተደጋጋሚ አስታውቋል:: ነገር ግን ሥራው በቅርቡ ይጀመራል የተባለው መም ጠብ ያለ ነገር ሳይኖር የኢትዮጵያ ቻምፒዮና እና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለመካሄድ ተቃርበዋል::

ስለዚህም ውድድሩን ለማካሄድም ይሁን ብሄራዊ ቡድንን ለማዘጋጀት አሁንም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስጋት ማገርሸቱ አይቀርም:: ከስፖርቱ በብዙ የተጠቀሙት መንግሥትና አትሌቶችም በጉዳዩ ላይ ዝምታን መርጠዋል:: ታዲያ በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሜዳሊያዎች ቁጥር አንሷል ድሉም ተቀዛቅዟል በማለት እንደከዚህ ቀደሙ ቅሬታችንን ለማቅረብ ሞራሉ ይኖረን ይሆን? የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ እያሽቆለቆለ ከሽልማት የሚገኘው የውጪ ምንዛሬ እያነሰ መምጣቱስ አይገደን ይሆን?

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You