የአባቶች በጎነት – ለሀገርና ሕዝብ አበርክቶ

ዜና ሐተታ

ለአንድ አካባቢ የመልካም ሕይወት ህልውና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች ሊዳብሩ፣ ሕዝቦች በአንድ መንፈስ ሊተሳሰሩና ዘለቄታዊ በሚባል የሰላም ድር ሊጋመዱ ግድ ይላል። ይህ አይነቱ ጤናማ ማንነት ዕውን ይሆን ዘንድም ተሰሚነት ያላቸው የህብረተሰብ አካላት አስተዋጽኦ የላቀ ነው።

የሃይማኖትና የጎሳ መሪዎች.፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የዕምነት አባቶች በህብረተሰቡ መካከል ሲገኙ ክፉውን በበጎ የመለወጥ ሃይል አላቸው። እነዚህ አካላት በማንኛውም ጊዜ ተደማጭ በመሆናቸው ለአርቅና ሰላም ፣ ለአንድነትና ፍቅር ተምሳሌትነታቸው የጎላ ይሆናል።

በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል ሆነው የዘለቁ ነባር እሴቶችን ወደ ትውልድ ለማሻገር የእነዚህ ወገኖች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። ቤተሰብ፣ አካባቢና ሀገር እንዳይበተን፣ ጦርነት ፣ ግጭትና ብጥብጥ እንዳይሰፋ በምክር፣ በባህላዊ ዳኝነትና በሽምግልና ልማድ እየታገዙ ከመፍትሔው ያደርሳሉ። አንዳንዴ ሕዝብ ከመንግሥት፣ ብሔር ፣ ከብሔር ፣ ጎሳ ከጎሳ ግጭት በፈጠሩ ጊዜም ለሀገርና ወገን ደህንነት እንደ ድልድይ ሆነው ሰላማዊ ሕይወት እንዲቀጥል አቅም ይሆናሉ።

አባ ገዳ በቀለ ሻንቆ ነዋሪነታቸው በባቱ ከተማ ነው። በአካባቢው ተወልደው እንደማደጋቸው የህብረተሰቡን ሃይማኖት፣ ባህልና ወግ ጠንቅቀው እንደሚያውቁ ይናገራሉ። አባ ገዳ በቀለ በአካባቢው ለዓመታት በአበባ እርሻ ልማት ከሚታወቀው የሼር ኢትዮጵያ ዝዋይ ሮዝስ ኩባንያ ጋር የማሕበራዊ ተሳትፎ አላቸው።

ኩባንያው በተለይ ከአምስት ዓመታት ወዲህ ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር የመሥራት ባህልን እያዳበረ ይገኛል ይላሉ። በአባገዳው አገላለጽ ለዚህ መልካም

ግንኙነት መጎልበት እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የሀገር ሽማግሌዎችና የዕምነት አባቶች ድርሻ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የአካባቢው ነዋሪና የአበባ እርሻ ልማቱ ዕለት በዕለት ባላቸው ማህበራዊ ትስስር እነ አባገዳ በቀለ በቅርብ የመከታተል ልማድን አዳብረዋል።

አብዛኞቹ ሠራተኞች የአካባቢው ነዋሪ እንደ መሆናቸው ተቀጥረው የመሥራት ዕድላቸው ሰፍቷል። እንደሳቸው አገላለፅም አንዳንዴ በእርሻ ልማቱና በሠራተኞች መሃል ለሚኖረው ጥያቄ የእነሱ መገኘት በመፍትሔነት መልስ ሆኖ ይገለጻል።

የዝዋይ ሮዝስ ኩባንያ ሠራተኞችን ቀጥሮ ከማሠራት ባሻገር ለአካባቢው ማህበረሰብ በርካታ ማሕበራዊ ኃላፊነቶችን እየተወጣ ይገኛል። አባገዳው እንደሚሉትም በትምህርት፣ በጤና፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ ፣ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታና በሌሎችም የልማት እንቅስቃሴዎች የእሳቸውና የሌሎች አባቶች ተሳትፎ በቅርበት ይተገበራል።

የአካባቢውን ማህበረሰብ ጥያቄዎችና የአበባ እርሻ ልማቱን ምላሽ በአንድ አስታርቆ ውጤት ለማግኘትም እስካሁን የአባገዳዎች፣ የዕምነት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አስተዋጽኦ በስኬት ተመዝግቧል። ባለመግባባት ግጭት ቢፈጠርና ምላሽ ቢዘገይ እነዚህ አባቶች ለሁለቱም ወገኖች አንደበት በመሆን መላ እንደሚፈጥሩ አባገዳው ይናገራሉ።

ቀደም ሲል በአበባ እርሻ ልማቱ የኬሚካል አጠቃቀምና የውሃ አወጋገድ ላይ ስጋት ለነበረው የከተማው ነዋሪ ሂደቱን በግልጽ በማሳየትና በአካል ተገኝቶ በማረጋገጥ እውነታውን እንዲረዳ ተደር ጓል። ለዚህ ግልጽነት መኖርም ነዋሪው አምኖ የሚያከብራቸውና ከልብ የሚቀበላቸው አባቶች እጅ እንዳለበት ይገልጻሉ።

በአሁኑ ጊዜ በአበባ እርሻ ልማቱና በነዋሪው መካከል መልካምና ሰላማዊ ግንኙነት ተፈጥሯል የሚሉት አባገዳ ፤ በስብሰባና በተለያዩ መድረኮች ሁሉ አባቶች ተገኝተው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በመሠራቱ ከፍተኛ ለውጥ መገኘቱን ይገልፃሉ።

የባቱ ከተማና ዙሪያው የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ ነው የሚሉት አባገዳ በቀለ፤ በአካባቢው ሁሉም እንደባህሪው ተቻችሎ እየኖረ መሆኑን ይናገራሉ። በሼር ኢትዮጵያና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የዳበረው መልካምና ሰላማዊ ግንኙነት ሠርቶ በማግኘትና ተምሮ በመለወጥ የሚገለጽ እንደሆነም ያሰምሩበታል።

ፓስተር ሆቢቾ ደበሎ ለዓመታት ኑሯቸውን በባቱ ከተማ ያደረጉ የእምነት አባት ናቸው። ፓስተሩ በአካባቢው ከሃያ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የሼር ኢትዮጵያ የአበባ እርሻ ልማት ሥራ በጀመረ ሰሞን በህብረተሰቡ ዘንድ ፈጥኖ ተቀባይነት ለማግኘት ፈተና እንደገጠመው ያስታውሳሉ።

ውሎ አድሮ እርሻ ልማቱ ባሳየው ልማታዊ ተሳትፎ ግን ብዙዎች የሥራ ዕድል በማግኘት የበርካታ ማህበ ራዊ እገዛ ተጠቃሚዎች ለመሆን መብቃታቸውን ይናገራሉ። የአካባቢው የዕምነት አባቶችና አባገዳዎች ከከተማው አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ህብረተሰቡንና ኩባንያውን የማገናኘት ሥራን ሲተገብሩ መቆየታቸውን ፓስተር ሆቢቾ ይገልጻሉ ።

እንደሳቸው አባባል ይህ አይነቱ ግንኙነት ሁሌም በበጎ አመለካከት የተቃኘ ነው። እንዲህ መሆኑ ነዋሪው በኩባንያው ተግባራት ላይ አመኔታ እንዲኖረውና በልማት ሥራው የእኔነት ስሜትን እንዲፈጥር አስች ሏል። ፓስተሩ ይህ እውነታ በእጁ ያለውን ሰፊ ሀብት እንደባለቤት ይዞ ደህንነቱን ለመጠበቅ የሚያደርገውን ተሳትፎ የላቀ አድርጎታል ይላሉ። ይህም በአንድ ወቅቱ በአካባቢው በተነሳው ድንገቴ ግጭት በተግባር የተረጋገጠ ነው።

እሳቸው እንደሚያስታውሱት በወቅቱ የተፈጠረው ብጥብጥ የበርካታ ባለሀብቶችን ቤትና ንብረት ሰለባ አድርጓል። የግለሰቦችን ቤት አውድሟል። ይሁን እንጂ ክፉ አጋጣሚው በእርሻ ልማቱ ላይ እንዳይከሰት የአካባቢው ወጣቶች ደጀንነትና ጥበቃ ለዛሬው ህልውና አብቅቶታል። እንደ ፓስተር ሆቢቾ አገላለጽም ለዚህ የአመለካከት ለውጥ መዳበር የታላላቅ አባቶች ምክርና ተግሳጽ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ሀገራችን በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች እንደመገለጧ በሃይማኖቶችና ባህሎች፣ በታሪኮችና ዕምነቶች ግማድ ትስስሯ የጠበቀ ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም በመቻቻልና አብሮነት የመኖር ባህልን አዳብሮ ዘመናትን ተሻግሯል። ልዩነትን በአንድነት አጣምሮ ሰላማዊ ግንኙነትን ዕውን ለማድረግም የእነዚህ መሰል ድንቅ አባቶች ታላቅ አበርክቶ የሚኖረው ድርሻ ላቅ ያለ ይሆናል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You