
አዲስ አበባ፡– አዲስ ሕይወት ጠቅላላ ሆስፒታል መንግሥት በፈቀደለት አንድ ሺህ 408 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሜዲካል ቱሪዝምን ታሳቢ ያደረገ የህክምና አገልግሎት ማስፋፊያ ሊያደርግ መሆኑን ገለጸ። የተመሰረተበትን ሃያ አምስተኛ የብር እዮቤልዩ በዓል በልዩ ልዩ ዝግጅት እያከበረ መሆኑንም ጠቁሟል።
የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ኪሮስ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ፤ ሆስፒታሉ በስምንት ሀኪሞችና በባለ ሶስት ወለል ህንፃ ሥራውን እንደጀመረ አስታውሰዋል። ዛሬ ላይ ደግሞ ሆስፒታሉ ከ50 በላይ የስፔሻሊቲ ሀኪምና አገልግሎቶችን፣ ከ100 በላይ ስፔሻሊስትና ሰብ ስፔሽያሊስት ሀኪሞችን፣ 90 የመታከሚያ ክፍሎችን ፣ 500 ቋሚ ሠራተኞችን፣ 500 የትርፍ ጊዜ ሠራተኞችን በማካተት በባለ ሰባት ወለል ህንፃ ላይ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግሥት በፈቀደለት ሆስፒታሉ ከሚገኝበት አጠገብ ባለው አንድ ሺህ 408 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ባለ 16 ወለል ህንፃ በመገንባት ሜዲካል ቱሪዝምን ታሳቢ ያደረገ የህክምና አገልግሎት ማስፋፊያ ለማድረግ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
ሆስፒታሉ ለማስፋፊያ በተፈቀደለት ቦታ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታል በመገንባት ዘመናዊ ህክምና ለመስጠትና በተለይ ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ ዜጎችን እዚሁ ለማስቀረት ውጥን ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ከጎረቤት ሀገራትም ጭምር ሰዎች ወደ ሆስፒታሉ መጥተው የሚታከሙበትን ሁኔታ ለመፍጠርና የሜ ዲካል ቱሪዝምን ለማስፋፋት ታላሚ ባደረገ መልኩ የህክምና አገልግሎት ማስፋፊያ ቦታው ከመንግሥት እንደተፈቀደለትም አመልክተዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ ሆስፒታሉ የተመሠረተበትን ሃያ አምስተኛ የብር እዮቤልዩ በዓል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እያከበረ እንደሚገኝ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገልፀው፤ ይህንኑ በማስመልከት በሆስፒታሉ አካባቢ ለሚገኙ ሁለት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና አንድ ጤና ጣቢያ ግምታቸው 200 ሺህ ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።
በጤና ጣቢያው ውስጥም የአልትራ ሳውንድ፣ የኤም አር አይና የሲቲ ስካን ምርመራ ለሚያስፈልጋቸው ህሙማን ይህንኑ አገልግሎት መስጠቱንና አሁንም የምሥረታ በዓሉን አስመልክቶ ወደ ሆስፒታሉ ለሚመጡ ህሙማን በተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች ላይ በቀላሉ በማይገመት ዋጋ ቅናሽ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ሜዲካል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም