“አሠሪና ሠራተኛ ባላንጣ ሳይሆኑ ከአንድ መዓድ የሚበሉ ቤተሰቦች ናቸው” – አቶ ካሳሁን ፎሎ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ከተቋቋመበት አላማ ዋናው የሰራተኞችን ደህንነት በመጠበቅና የተለያዩ ቅሬታዎቻቸውን በመፍታት መብታቸውን እንዲያውቁ ግዴታቸውንም እንዲወጡ ማድረግ ነው:: ተቋሙም ላለፉት በርካታ ዓመታት ይህንን ሥራ ሲሠራ ውጤትም ሲያመጣ ቆይቷል:: ነገር ግን ሠራተኞች በተለያያ ጊዜያት የተለያዩ ችግሮችና ጫናዎች ያሉባቸው በመሆኑ ሁሌም ከሠራተኞች ጎን ቆሞ አሠሪዎችን እንዲሁም የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት ጫና በማሳደር ሥራዎችን መሥራቱን እንደቀጠለ ነው::

እኛም ዓለም አቀፉን የሠራተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ ከኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት ከአቶ ካሳሁን ፎሎ ጋር ቆይታ አድርገናል::

አዲስ ዘመን፦ ኢሠማኮ የሠራተኞችን መብት በማስከበር በኩል የሠራቸው ዋና ዋና ተግባራት ምንድን ናቸው?

አቶ ካሳሁን፦ እንደ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን በርካታ ሥራዎችን እንሠራለን:: አንደኛው ሠራተኞችን ማደራጀት ሲሆን ይህ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ የሚሠራ የማይቋረጥ ሥራ ነው:: ሁለተኛው ለተደራጁት ሠራተኞች ግንዛቤ መፍጠር እና ለተመረጡት የማኅበር መሪዎች ተመሳሳይ ስልጠና መስጠት ነው:: ሶስተኛው ሠራተኛው ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን በተለይም ከሠራተኛ ማኅበራት አልፎ እኛ ጋር ሲደርሱ ከካምፓኒዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት በማድረግ ለመፍታት መሞከር ሲሆን በተለያዩ ደረጃዎች የመንግሥት አካላትንም በመጨመር ውይይቶች ማድረግ ነው፡፡ በውይይት መፈታት ካልተቻለም ወደ ፍርድ ቤት የምንወስድ ይሆናል:: በዚህ ደረጃ እኛ ጋር የደረሱ ጉዳዮች ሲኖሩም ማኅበሩ በነጻ የሕግ ባለሙያዎችን አቅርቦ ይከራከራል::

በሌላ በኩል ግን የኮንፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ የሆነው ሠራተኞችን በማኅበር የማደራጀት ጉዳይ ግን ሁሌም ችግር እንደገጠመው ነው:: አሠሪዎች መደራጀቱን ስለማይፈልጉ የማኅበራት መሪዎች ይባረራሉ፤ ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ፤ ከደረጃ እድገት ይቀነሳሉ :: ነገር ግን በ2015 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመወያየትና እነዚህን የሠራተኛውን የመብት ጥያቄዎች በማቅረባችን በቀጣይ ዓመት ሥራና ክሕሎት ሚኒስቴር እቅድ ሲያወጣ እንድንሳተፍ አድርጎናል:: እኛም ለቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቻችን አውርደን በጋራ እየሠራን ነው:: ይህም ሆኖ አሁንም ችግሩ አልተፈታም::

አዲስ ዘመን፦ አሠሪዎች የሠራተኛውን በማኅበር መደራጀት ለምንድን ነው እንደ ሥጋት የሚቆጥሩት? በእናንተ በኩል ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ካሳሁን፦ እኛም በተቻለን መጠን ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራን ለመሥራት እንሞክራለን ነገር ግን እኛንም የሠራተኛው ወገን ናቸው ብለው ስለሚያስቡ ለስብሰባ ስንጠራቸው እንኳን አይመጡም:: በመሆኑም እንደ አዲስ አማራጭ በዚህ ዓመት የያዝነው በመንግሥት አካላት በኩል ግንዛቤ ፈጠራው እንዲሰጥልን የማድረግ ሥራ ነው::

ነገር ግን በብዙ ጉትጎታ የመጡ አሠሪዎች የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠናውን ወስደው ሲመለሱ በጣም ነው የሚገረሙት “እኛ እኮ መብት ብቻ የምትጠይቁ ስለሚመስለን ነው” በማለት ይደነቃሉ:: በመሆኑም እዚህ ጋር መታወቅ ያለበት ነገር ድርጅቱ ከሌለ ሠራተኛው የለም ኮንፌዴሬሽኑ የሠራተኞች መብት እያለ ብቻ ድርጅቱ እንዲጠፋ ወይም እንዲከስር አይሰራም::

አዲስ ዘመን፦ የሙያ ደህንነትና ጤንነት እንዲጠበቅ የሚወጡ መመሪያና ሕጎችን አሠሪዎች ምን ያህል ተግባራዊ እያደረጓቸው ነው? ተግባራዊ እየተደረገ ካልሆነስ መፍትሔው ምንድን ነው?

አቶ ካሳሁን፦ አንዱ ቁልፍ ችግር የሙያ ደህንነትና ጤንነት ሕጎች አለመከበራቸው ነው:: በዚህ ምክንያት በአንዳንድ ፋብሪካዎች በተለይም ደግሞ በኮንስትራክሽን ቦታዎች ላይ አደጋዎች ይደርሳሉ:: በሚገርም ሁኔታ አንዳንዶቹ የሚደርሱት ማስቀረት በሚቻል ትንሽ ጥንቃቄ በማድረግ ብቻ ሊፈታ በሚችል ችግር ነው::

አሠሪዎች ሕግ ባለማክበር ጥቂት ወጪን ላለማውጣት ብዙ ሰዎች ለሞትና አካል ጉዳት እየተዳረጉ ያሉበት ዘርፍ ኮንስትራክሽን ነው:: እንደ ማሕበር እነዚህን ኮንስትራክሽኖች እንዳናስገድድ ብዙዎቹ የማሕበር አባል አይደሉም:: የሠራተኛ ማሕበርም የላቸውም:: ነገር ግን ማሕበሩ ላይ የሉም ብለን ዝም አንልም፣ ይልቁንም ዘርፉን የሚቆጣጠረው አካል ለሠራተኞች ደህንነት ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጥ ሁልጊዜ የምንጠይቀው ጥያቄ ነው::

በነገራችን ላይ የሥራ ላይ ደህንነት የማይነካው አካል የለም:: ሰዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ አስፈላጊው የሥራ ላይ ደህንነት ትጥቅ ተሟልቶላቸው መሥራት ካልቻሉ እንደ ሀገር ቀውሱ ከባድ ነው:: ይህንን በምሳሌ ብናይ አንድ ሰው በዚህ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ቤተሰብ እያስተዳደር በጥንቃቄ ጉድለት ሕይወቱ አደጋ ላይ ቢወድቅ ቤተሰቡ ለችግር ይጋለጣል፤ አሠሪው በሥራው ልምድ ያለውን ባለሙያውን ያጣል፤ መንግሥትም ተጎጂ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የሥራ ላይ ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው::

አዲስ ዘመን፦ በአሠሪዎችና በሠራተኛው መካከል ጤናማ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ምን ይመስላል? ሊጠቀሱ የሚችሉ ውጤቶችስ ተገኝተዋል ?

አቶ ካሳሁን፦ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ያለው ግንኙነት የሰመረና ጤናማ እንዲሆን እንፈልጋለን:: ከዚህ አንጻር ሥራው እስካለ ድረስ ጥያቄዎች ሊነሱ እና በዚህም ምክንያት አለመግባባቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፤ ሆኖም እነዚህ ችግሮች በማኅበራዊ ምክክሮሽ መፈታት አለባቸው ብለን እናምናለን፤ በዚህም ሁለቱ አካላት በምን መልኩ ይመካከሩ የሚለውን ስልጠና እንሰጣለን:: ከስልጠና ባሻገርም ከአሠሪዎቹ ጋር በመነጋገር ችግሮቹ ወደ አደባባይ ሳይወጡ በውስጥ እንዲቀረፉ እንሰራለን::

በርካታ ነገሮችን ስለምንሠራ ውጤት ያመጣንባቸው እነዚህ ናቸው ብሎ መጥቀስ መረጃ ይፈልጋል:: ነገር ግን እንደ አጠቃላይ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ እኛ ጋር ከመጡቱ 85 በመቶ ያህሉ በውይይት ነው እልባት ያገኙት:: ወደ ፍርድ ቤት የደረሱት በጣም ጥቂት ጉዳዮች ናቸው::

አዲስ ዘመን፦ የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን ከአሠሪው፤ ከሠራተኛው እንዲሁም ከመንግሥት ምን ይጠበቃል ይላሉ?

አቶ ካሳሁን፦ ይህ መሰረታዊ ነገር ነው:: የሥራ ቦታ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም አካላት መብትና ግዴታቸውን በውል ሊረዱ ይገባል :: አንዱ የሌላውን መብት ማክበር መቻል አለበት:: መንግሥትም የተረጋጋ የሥራ አካባቢ እንዲፈጠር የሚፈልግ ከሆነ በአሠሪና ሠራተኞች መካከል ለሚኖር ግንኙነት የሚወጡ ደንብና ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል::

አሁን ላይ ችግሩ በተለይም በእኛ በኩል በማኅበራዊ ምክክሮሽ ዙሪያ ለአሠሪዎች የምንሰጠው ስልጠና ክፍተት አለበት፤ ነገር ግን አንዱ አንዱን ካከበረና ያስፈልገኛል በሚል ስሜት ሥራውን መሥራት ከቻለ ችግር ይፈታል የተረጋጋ የኢንደስትሪ ሰላም ይፈጠራል :: ምርትና ምርታማነት ያድጋል፤ ሠራተኛውም አሠሪውም እንዲሁም መንግሥት ተጠቃሚ ይሆናሉ::

አንድ መታወቅ ያለበት ነገር እንደ ኢትዮጵያ የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽንም እንደ ኢንደስትሪ ፌዴሬሽንም ሆነ መሰረታዊ ማኅበራት እያንዳንዱ ኢንደስትሪ በሥራው ላይ ትርፋማ ሆኖ እንዲቆይ እንጂ እንዲጠፋ የሚፈልግ ማኅበር የለም፤ በመሆኑም ተሳስቦና ተናቦ መሥራቱ ለተሻለ እድገት ወሳኝ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል::

አዲስ ዘመን፦ ዝቅተኛ የሠራተኞችን ደመወዝ ለመወሰን የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፤ አሁን ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?

አቶ ካሳሁን፦ ዝቅተኛ የሠራተኞችን የደመወዝ ስኬል ውሳኔ አለማግኘቱ ሠራተኛው በልቶ እንዳያድር አድርጎታል:: የደመወዝ ስኬሉ አሁን የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ብቻ አይደለም መሸከም ያልቻለው ከዚህ በፊትም ሠራተኛው የሚከፈለው ደመወዝ እየበቃው አልነበረም:: ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዲያልፍ እየተገደደ ነበር:: አሁን ደግሞ እንደ ሀገርም በዓለም አቀፍ ደረጃም ባለው የዋጋ ንረት ወትሮም ያልሞላለት ደሞዝተኛ አሁን ኑሮ ጫናውን አብዝቶበታል ማለት ይቻላል::

ይህንን ሁኔታ ደግሞ ከለውጡ በፊትም ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ይወሰን ብለን በተደጋጋሚ ስናነሳ ነበር ፤ በዚህም መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 1156/2011 የገበያውን ሁኔታ የኢኮኖሚውን ሁኔታ እየተከታተለ የሚወስን የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም የሕግ ማሕቀፉን ይዞ እንዲገባ ሆኗል::

ይህ በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያ ቢሆንም ተፈጻሚነቱ ላይ ግን እስከ አሁን የታየ ለውጥ የለም:: እኛም ያለማቋረጥ ግፊት እያደረግን ቆይተናል:: በተለያየ ጊዜ ውይይቶች ይደረጋሉ ግን መሬት ላይ ወርደው ሲተገበሩ አይታይም :: በ2015 ዓ.ም ምናልባትም የዛሬ አንድ ዓመት ከ 6 ወራት በፊት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፕሮግራም ይዘውልን ስንወያይ ያነሳነው ይህንን ጉዳይ ነበር:: እሳቸውም ያለውን ነገር ተረድተው ለሚመለከታቸው አካላት አቅጣጫ ቢሰጡም አሁንም ምላሽ የተሰጠው ጉዳይ አይደለም:: አሁን ከሥራና ክሕሎት ሚኒስቴር ጋር ይህንን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ያሉ ቢሆንም በፍጥነት ተጠናቀው ችግር ውስጥ ያለውን አነስተኛ ተከፋይ የሚታደጉበት ቀን ግን ይናፍቃል::

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ 1 ሺ ብር ፣1 ሺ 2 መቶ ብር እያገኘ ሰው እንዴት ወር ሙሉ ሊቆይ ይችላል ተብሎ ይታሰባል:: ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ ኢንደስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ የማምረቻ ድርጅቶች ውስጥ ነው፤ በመሆኑም ይህ ደመወዝ እንኳን አንድ ወር አንድ ቀን የሚያቆይ ባለመሆኑ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መወሰኑ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ ሊሆን አይገባም::

ይህ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እኮ ለሠራተኛው ብቻ ሳይሆን ለአሠሪውም ጥቅም እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል:: የራበውን ቤቱ ልጆቹንም መመገብ ያቃተውን ሠራተኛ ይዞ ውጤት ለማምጣት ማሰብ አይቻልም:: ማንም ሰው ሳይበላ መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ሳይሟሉለት ልጆቹን መመገብ ሳይችል ሥራው ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል ማለት ዘበት ነው:: በመሆኑም እንደ ሀገር ምርታማነታችን ማደግ አለበት ካልን ይህንን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ወደ ተግባር ማስገባት ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆን አለበት::

በሌላም በኩል ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን እንደ ሀገር ተግባራዊ ማድረግ ከቻልን በየጊዜው ወደ ስደት እየሄዱ ባሕር ገብተው የሚሞቱትን ወገኖቻችንንም ማትረፍ እንችላለን::

አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች ዝቅተኛ የደመወዝ ወሰን ማስቀመጥ ሥራ አጥነት እንዲስፋፋ ያደርጋል ይላሉ፤ ነገር ግን ይህ ትክክል አይደለም፤ የትኛውም የውጭም ይሁን የውስጥ ባለሀብት ፋብሪካ አቋቁሞ የሰው ኃይል የሚፈልገው በአቅሙና በሥራው ልክ ነው እንጂ ሀገራችን ደሃ ስለሆነች አንድ ሺ ሰው ሊቀጥር የመጣው ሁለት ሺ እቀጥራሉ ብሎ አይነሳም ፤ እሱም የሚፈልገው ትርፍ አለ ፤ በመሆኑም ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ማንም አይጎዳም::

ለምሳሌ ጎረቤታችን ኬንያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን ተግባራዊ አድርጋለች፤ ነገር ግን የሸሸባት ባለሀብት የለም:: እንደውም ጥቅሙን በጣም ይረዱታል:: ወደፊት አውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም ሌሎች ሀገሮች እቃ ሲላክ አስገዳጅ የሆኑ ደንቦች እየተቀመጡ ነው፤ አንዱ ሠራተኛው የሚያኖረውን ክፍያ ያገኛል ወይ ? ሲሆን ሌላው የአካባቢ ጥበቃ ነው:: እነዚህ ካልተሟሉ ምርቱ በሄደበት ሀገር ላይ ችግር ይገጥመዋል:: ይህ እንግዲህ በፈረንጆች ቀጣይ ዓመት ተግባራዊ የሚሆን ነው:: ታዲያ እኛ ይህ አስገዳጅ ሁኔታ እስኪመጣ እየጠበቅን ነው? የሚለው ለእኔም ጥያቄ ይሆንብኛል::

በመሆኑም ይህ ጥያቄ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ በረድ እያለ ጊዜ የሚወስድ መሆን የለበትም መልስ ማግኘትና ወደ ሥራ መግባት ያስፈልጋል::

አዲስ ዘመን፦ ከሠራተኛው ላይ የሚቆረጠው ግብር ከፍተኛ በመሆኑ ጫና ስለማሳደሩ በተደጋጋሚ ይነሳል፤ ይህንን ችግር መልክ ለማስያዝ በእናንተ በኩል ምን ተሠራ?

አቶ ካሳሁን፦ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረን የውይይት ጊዜ ካነሳናቸው ጉዳዮች አንዱ ይህ ነበር:: እሳቸውም ጥያቄው ትክክል ነው የሚመለከታቸው አካላት መልስ ይስጡበት ብለው አቅጣጫ ሰጥተዋል:: ከዚያም በኋላ በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን እያቀረብን ነው:: ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገ እንቅስቃሴም ሆነ ወደ እኛ የመጣ ምላሽ የለም:: የሚመለከታቸው የተባሉትም አካላት በደብዳቤ በአካልም ሄደን ለመጠየቅ ሞክረናል ግን መልስ አላገኘንም ::

ግብር ለሀገር እድገት ወሳኝ ነው ምንም ጥያቄ የለውም:: ነገር ግን እነዚህ ግብሮች ከማን ላይ ነው እየተቆረጡ ያሉት ? የኑሮውስ ሁኔታ ታይቶ ሊወሰን አይገባም ወይ? ፍትሐዊ የሆነ የግብር አከፋፈል ሥርዓትስ ለምን አይኖርም? የሚለው ሊታይ ይገባል::

ለምሳሌ እስከ 6 መቶ ብር ያለ ገንዘብ ከግብር ነጻ ነው :: ግን ይህ ሕግ የዛሬ ስንት ዓመት የወጣ ነው? ይህ ሕግ በወጣበትና በአሁኑ ጊዜ ያለው የኑሮ ሁኔታ ተመሳሳይ ነው? ምናልባት በወቅቱ 6 መቶ ብር ለአንድ ሰው የወር ቀለቡን ይችል ነበር፤ አሁን ግን ጊዜው ተቀይሯል:: ከዚህ አንጻር ሠራተኛው የኑሮ ውድነቱን አልቻለም:: አንደንዶች ግብር ስለተነሳ ወይም ስለተቀነሰ የኑሮ ውድነት አይቀንስም ይላሉ አዎ ምናልባት ግን አንዱ የኑሮ ማቅለያ ነው የሚል ሀሳብ ነው ያለን::

በመሆኑም እንደ ኮንፌዴሬሽን ግብር መክፈል ሙሉ በሙሉ ይቅር ሳይሆን ይቀነስ 6 መቶ የነበረው ከፍ ይበል እያልን ነው::

እዚህ ላይ አንድ ማሳያ ላስቀምጥ ቤት የሚያከራዩ ሰዎች እስከ 7 ሺ 2 መቶ ብር ድረስ ግብር አይቆረጥባቸውም:: ከ 7 ሺ 2 መቶ እስከ 15 ሺ ብር ድረስ 10 በመቶ እንዲከፍሉ ነው የሚገደዱት:: የመንግሥትና የግል ሠራተኛውስ የተባለ እንደሆነ ደመወዙ ከ 10 ሺ 9 መቶ ብር በላይ ከሄደ 35 በመቶ ግብር እንዲከፍል ይገደዳል :: በመሆኑም ይህ አካሄድ ፍትሐዊ አይደለም፤ ሰዎች በሚያገኙት ገቢ ልክ ይክፈሉ የኮንፌዴሬሽኑ ጥያቄ ነው፤ በመሆኑም አሁን ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር እንኳን ታይቶ የሥራ ግብር ቢቀነስ ይሻላል:: ይህንንም ሃሳባችንን ከየትኛውም የመንግሥት አካላት ጋር ለመወያየት እኛም ያለንን አሳማኝ ነገር ለማቅረብ በእነሱም በኩል የሚነሱ ሃሳቦችን ለመስማት ዝግጁዎች ነን::

አዲስ ዘመን፦ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመሳሳይ ማሕበራት ጋር ያላችሁ ትስስር ምን ይመስላል ?

አቶ ካሳሁን፦ በዓለም አቀፍ የሠራተኛ ኮንፌዴሬሽን ውስጥ የአፍሪካ አሕጉር አለ፤ በዛ ላይ አባል ና የምክር ቤት አባልም ነን፤ብዙ ነገሮችንም አብረን እንሠራለን:: ከዓለም አቀፍ ሠራተኛ ኮንፌዴሬሽን ጋርም በአባልነት እየሠራን ነው :: እንደ አጋጣሚም የዚሁ ኮንፌዴሬሽን የኦዲት ኮሚቴ አባልም ነን:: በተጨማሪም የዓለም ሠራተኞችን በመወከል በዓለም ሥራ ድርጅት የአስተዳደር አካሉ ላይ በሥራ እንሳተፋለን:: ሌላው የአፍሪካ ቀንድ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ተቋቁሟል፤ የኢጋድ አባል ሀገራት ይሳተፉበታል :: መቀመጫውም አዲስ አበባ ሲሆን እኛም ዋና ጸሀፊ በመሆን እየሠራን ነው::

በዚህ ተሳትፏችንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ኮንቬንሽኖች ሲወጡ በየሀገራቱ ያሉትን ችግሮች እየተነጋገርን የሚፈታ ውሳኔ የሚሰጥ አካል እንደ ኢትዮዸያ የሠራተኛ ማኅበር ኮንፌዴሬሽን የተወከልነው በአፍሪካ ደረጃ ጥሩ ግንኙነት ስላለን ነው::

በመሆኑም ፌዴሬሽኑ በሀገር ውስጥ ለሚደራጁ የሠራተኛ ማኅበራት ያልተቆራረጠ ስልጠና የሚሰጠውም በእንደዚህ አይነቱ ተሳትፎ ከሚገኝ ገቢ ነው::

አዲስ ዘመን፦ ዛሬ ለሚከበረው የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን መልዕክቶን ያስተላልፉ፤

አቶ ካሳሁን፦ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ስናከብር የመረጥነው መሪ ቃል ” መንግሥት ላቀረብናቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ይስጠን ” የሚል ሲሆን ከላይ ያነሳናቸው የሠራተኛው ጥያቄዎች ቶሎ እንዲመልሱልን ያለመ ነው::

በዓሉም በአዲስ አበባ ደረጃ በኢሠማኮ ቅጥር ግቢ ውስጥ ይከበራል:: በሌሎች ስምንት ቅርንጫፎች ደግሞ በፓናል ውይይት ይከበራል:: በአዳማ ቅርንጫፍ ግን ሜይዴይ ስፖርት ውድድር ተዘጋጅቷል::

የኢትዮጵያ ሠራተኞች በሙሉ እንኳን ለሜይዴይ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን :: አሠሪና ሠራተኛ ባላንጣ ሳይሆኑ ከአንድ መዓድ የሚበሉ ቤተሰቦች ስለሆኑ ሁላችንም ተከባብረን መብትና ግዴታችንን አውቀን ለጋራ ጥቅም በጋራ እንሥራ ማለት እወዳለሁ ::

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ

አቶ ካሳሁን፦ እኔም አመሰግናለሁ::

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You