የንግድ ሥርዓትን ለማዘመን የኢ-ኮሜርስ የግብይት ሥርዓት ይተገበራል

ቢሾፍቱ፡የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ሊያግዝ እንደሚችል ተስፋ የተደረገበት የኢ-ኮሜርስ የግብይት ሥርዓት ወደ ትግበራ ለማስገባት እየሠራ እንደሚገኝ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ሚኒስቴሩ ሀገራዊ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ዘርፍ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸምን ትናንት ሲገመግም እንደገለጹት፤ የግብይት ችግርን ለመቅረፍና የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን ኢ-ኮሜርስ አደረጃጀት ወደ ትግበራ እንዲገባ ይደረጋል ብለዋል። ትግበራው ቻይናን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ውጤታማ የሆኑበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በግብይት ሥርዓት ወቅቱን የሚመጥኑ የፖሊሲ ሰነዶች እየተዘጋጁ መሆናቸውን በመጠቆምም፣ የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ እና የኢትዮጵያ ጥራት ፖሊሲ ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ፖሊሲዎቹ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የተዛመዱ የወደፊት አቅጣጫን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ ገቢ ከአምስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አንስተው፤ በቀሪ ጊዜ ገቢውን በማሳደግ በ2017 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ከሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ ትኩረት መሰጠቱንም አመልክተዋል።

በ2010 ዓ.ም ከወጪ ንግድ የገባው ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደነበርም አስታውሰዋል። መንግሥት የንግዱን ዘርፍ ተወዳዳሪ እና ተገማች ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ካሳሁን (ዶ/ር) ተናግረዋል። ተገማች የገበያ እድሎችን በማስፋት ጥራት ያላቸውን ምርቶችን በማቅረብ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ሥራ መሥራት ተገቢ መሆኑን በማመን እንቅስቃሴ መጀመሩን አመልክተዋል፤ የወጪና ገቢ ንግድ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው ጥራትን ማዕከል ሲያደርግ መሆኑን የጠቆሙት ካሳሁን (ዶ/ር)፣ ዘንድሮ ስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ የተገነባው የጥራት መንደር ተመርቆ አገልግሎት መጀመሩ ለተግባሩ በበጎነት እንደሚጠቀስ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ባካሄደችው 5ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት የሥራ ቡድን ስብሰባ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል መሆን እንደምትችል የታየበት መሆኑን አመልክተው፤ የእሁድ ገበያዎችን በማስፋፋት ሸማቹ በቀላሉ ዋጋ ምርትና አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል ተጨማሪ 374 የገበያ ማእከላት መገንባታቸውን ጠቁመዋል።

የነዳጅ ግብይት መቃወስ መታረም ያለበት መሆኑን ጠቁመው፤ ጠንካራ የነዳጅ ግብይት ሬጉላቶሪ ሥርዓት በመዘርጋትና በመተግበር አላግባብ ለመክበር በተንቀሳቀሱ የነዳጅ ማደያዎች እና ኩባንያዎች ላይ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ቅጣት መጣሉንም ተናግረዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት ማሕቀፍ የሙከራ ንግድ ትግበራም በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከሀገር ውስጥ ንግድ አፈጻጸም አንጻር በኦንላይን ከ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶች ለንግዱ ማህበረሰብ መሰጠታቸውን፤ ተግባራቱም አዲስ ንግድ ፍቃድ ማውጣት፣ የንግድ ምዝገባ፣ ነባር የንግድ ፍቃድ ማደስና መሰል አገልግሎት በኦንላይን እንደተሰጡም ካሳሁን (ዶ/ር) አመልክተዋል።

ዘንድሮ በክልሎች በተጀመረው የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን አገልግሎትም ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ የንግድ ፈቃድ ኢንስፔክሽን መከናወኑንም ነው የተናገሩት።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You