
ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ከሆኑ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ተጠቃሿ ናት:: ያላት ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና ወጣት የሰው ሃይል፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ምቹ እንድትሆን ካደረጓት መካከል ይጠቀሳሉ::
በፍጥነት እየጨመረ የመጣው የህዝብ ብዛቷ፣ ለአፍሪካና ለመካከለኛው ምስራቅ ያለችበት ስትራቴጂክ ስፍራም በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ይበልጥ ተመራጭ ያደርጋታል:: ሀገሪቱም ከቅርብ አመታት ወዲህ ለኢንቨስትመንቱ ምቹ ምህዳር በመፍጠር በትኩረት እየሠራች መሆኗም ሌላው ምቹ የሚያደርጋት ነው::
ባለፉት የለውጥ አመታት ብቻ የኢንቨስትመንት አዋጅ እስከ ማሻሻል የዘለቀ ሪፎርም አድርጋለች:: በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ በገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም ለዘርፉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል:: የውጭ ባንኮች ወደ ሀገሪቱ ገብተው እንዲሠሩ አሠራር ተቀምጧል፤ ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ የነበሩ የችርቻሮና ጅምላ ንግድ ሥራዎች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ተደርገዋል::
በዘርፉ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን ለመጠቀምም የሀገር ውስጥ እና የውጪ ባለሀብቶችን በዘርፉ እየተሰማሩ ይገኛሉ:: ይህን ተከትሎም በተለያዩ ዘርፎች ለውጦች እየተመዘገቡ ናቸው::
መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በሀገሪቱ በተካሄደው ሪፎርም ውጤት የታየባቸው ተብለው ከሚነሱት ውስጥ የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ይጠቀሳል:: ኢንቨስትመንቱ ከ2015 ጀምሮ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ ይገኛል:: ለአብነት ያህል በ2016 ዓ.ም ከአጠቃላይ ጂዲፒ የኢንቨስትመንቱ ዘርፉ 20 በመቶ መያዙ እንዲሁም በ2017 ደግሞ ይህ አሀዝ ወደ 23 ከፍ ማለቱን መረጃዎቹ ጠቁመዋል::
በቅርቡ የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በተገመገመበት ወቅት የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ በሰጡት ማብራሪያ በኢንቨስትመንት ዘርፉ የታዩ ለውጦች ተጠቁመዋል::
ሚኒስትሯ በተለይ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ዋነኛ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ማሳያ መሆኑን አመልክተው፣ በ2017 በጀት አመት ስምንት ወራት ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳቡን ገልጸዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ በስምንት ወራቱ 363 የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፍቃዶች ለተለያዩ ዘርፎች ተሰጥተዋል፤ እነዚህም በዝርዝር ሲታዩ በግብርና 10፣ በማኑፋክቸሪንግ 207፣ በአገልግሎት ዘርፍ 146 ፍቃዶች ናቸው የተሰጡት::
ይህ አፈጻጸም በባለቤትነት ሲገለጽ ብለው እንዳብራሩትም፤ ለ143 የውጭ ኢንቨስተሮች ፍቃድ ተሰጥቷል፤ በጥምረትም እንዲሁ 44 ለሚሆኑ ኢንቨስተሮች ፍቃድ ተሰጥቷል:: 33 የሚሆኑ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃዶች ወጥተዋል::
ወደ ማምረት እና አገልግሎት መስጠት የተሸጋገሩ ኢንቨስትመንቶች እንዳሉም ገልጸው፣ በእቅድ ደረጃ መስሪያ ቤታቸው 161 ኢንቨስትመንቶች ወደሥራ ይገባሉ ብሎ ያቀደ ቢሆንም 141 የሚሆኑት በአሁኑ ሰዓት ሥራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል::
ኢትዮጵያ እንዳለፉት አመታት ሁሉ አሁንም የኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ለማድረግ እየሠራች ትገኛለች:: የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንደ ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ ያሉ ሁነቶችን፣ የውጭ ሀገር ጉብኝቶችን፣ ወዘተ እያደረገ ባለሀብቶችን ለመሳብ መሥራቱን አጠናክሮ ቀጥሏል::
ይህ ኢንቨስት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም ባለፉት ዓመታት ሁለት ጊዜ ተካሂዷል:: ዘንድሮም ለሶስተኛ ጊዜ በመጪው ግንቦት ይካሄዳል::
መድረኩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የልማት አጋሮች በቅርቡ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ መድረኩ በከፍተኛ ደረጃ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከመላ ዓለም የሚመጡ ባለሀብቶችን፣ የንግዱን ማኅበረሰብ፣ ፖሊሲ አውጭዎችን፣ ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያገናኝና የኢትዮጵያን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም አውጥቶ ለማሳየት የሚያስችል ነው:: ለዘርፉ አዋጪ የሆኑ አማራጮችን በመጠቀም ኢትዮጵያን የቀጣዩ ጊዜ የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል::
በመግለጫው ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የካናዳ ኢምባሲ ተወካይ እና የልማት አጋር ቡድኑ ምክትል ሊቀ መንበር አሽሊ ሙልሮኒ እንዲሁም የአፍሪካ የልማት ባንክ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ሊያንድሪ ባሰሊ ተገኝተዋል::
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፤ ሀገሪቱን የመጪው ዘመን የኢንቨስትመንት ማዕከል የማድረጉ ጥረት ፍሬያማ ወደ መሆን መቃረቡን ጠቅሰው፣ ብዙ የዓለም ባለሀብቶች ሀገሪቱን ምርጫቸው አድርገው የእንሥራ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ አመልክተዋል:: እየታየ ያለው የኢኮኖሚ መነቃቃት ተስፋ እንደተጣለበትም ተናግረዋል::
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ሀገሪቱ አንድ ሀገር ሊኖራት የሚገባው የኢንቨስትመንት መስፈርት ታሟላለች:: እንደ ሀገር ያልተሠሩትን በመሥራት ተመራጭና የባለሀብቶችን ቀልብ የምትስብ ሆና እንድትገኝ ለማድረግ አሁንም ሥራዎቿን አጠናቃ እንግዶቿን ለመቀበል ተዘጋጅታለች::
ኮሚሽነሩ እንዳሉት፤ ፎረሙ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቶች እንዲታዩ የሚደረግበት ብሎም ለኢንቨስትመንቱ ያላትን ምቹነት እና ፍቃደኝነት ለውጭው ማህበረሰብ የሚገለጽበት ነው:: የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና አማካሪዎች እንደዚሁም የልማት ድርጅቶች የኢትዮጵያን እምቅ የኢንቨስትመንት እድል የሚመለከቱበት ይሆናል::
በፈረንጆቹ 2023 የተካሄደው ሁለተኛው ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም ብዙ መልካም እድሎችን ይዞ መጥቶ እንደነበርም አስታውሰዋል:: ኢትዮጵያን ያስተዋወቀ፣ ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንቱ ያላትን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ማሳየት የተቻለበት እንደነበር አመልክተዋል::
ሀገሪቱ ያላትን ምቹ ስነምህዳር በማስተዋወቅ ተፈጥሮና ኢንቨስትመንት ያላቸው ብርቱ ቁርኝት በተግባር የታየበት እንደነበር ጠቅሰው፣ ከ750 በላይ የዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ መሪዎች እንደዚሁም ፖሊሲ አውጪዎች እና አማካሪዎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች እና አጋር የልማት ድርጅቶች እንደተሳተፉበት አብራርተዋል::
ኮሚሽነሩ በሁለተኛው ዙር የቢዝነስ ፎረም ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ፍሰት ማግኘት እንደተቻለም ጠቅሰው፣ ይሄ እንደ ሀገር ጥሩ እመርታ ነው ብለዋል::
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው እንዳስታወቁት፤ እንደ አትሌቲክሱ ሁሉ ሀገሪቱን በኢንቨስትመንቱም በአጠቃላይም በኢኮኖሚው መስክ ለማስተዋወቅ እንዲሁም ተጨማሪ ገቢ እንዲገኝ ለማድረግ እየተሠራ ነው:: መንግስት የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲነቃቃ ለማድረግ የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ማስፋት፣ የፖሊሲ እና የህግ ማሕቀፎችን ማሻሻል፣ አሠራርን ማዘመን ላይ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል::
በፓርላማ የጸደቁ እና እየጸደቁ ያሉ የኢንቨስትመንት ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በማዕድን፣ በኢነርጂ በሌሎችም ዘርፎች ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥስራዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል:: ይሄን ምቹ ሁኔታ አቀናጅተን በመያዝ አጋር ድርጅቶችን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትን አካተን በመሥራት በኢንቨስትመንቱ ላይ ለውጥ በማምጣት ላይ እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል::
በትጋት ከተሠራ ለውጥ ሁሌም አለ ያሉት ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ በመንግሥት የተያዙ እቅዶች ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል:: ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ኃላፊነት እንዳለበት ተቋም ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ለተሻለች ኢትዮጵያ በተሻለ ሞራል እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል::
ሶስተኛው ኢንቨስት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም የፊታችን ግንቦት አራት እና አምስት በስካይ ላይት ሆቴል ይካሄዳል::
ሶስተኛው የቢዝነስ ፎረም ካለፉት ሁለት ፎረሞች በተሻለ ሁኔታ ኢትዮጵያን በከፍታ ላይ ሊያስቀምጥ ይችላል፤ ለዚህም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ አጋር የልማት ድርጅቶች በጥምረት እየሠሩ ይገኛሉ:: ይህ የአጋርነት ጥምረት ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ያለመም መሆኑም በመድረኩ ተመላክቷል::
ፎረሙን አስመልክቶ የወጣው መረጃ እንዳመለከተው፤ ፎረሙ የተለያዩ ግቦችን አስቀምጧል፤ በዋናነት ግን አዳዲስ ባለሀብቶችን መሳብ፣ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ማሳየት እንዲሁም አዲስ የወጡ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማሳወቅ በዋናነት የሚጠቀሱ ግቦች ናቸው::
የባለሀብቶችን ተሳትፎ ለመጨመር፣ በኢንቨስትመንትና ፖሊሲ ማውጣት ላይ ውሳኔ ሰጪ ለመሆን የሚያስችሉ እንዲሁም የዘርፎች ስኬቶችን የተመለከቱ ውይይቶች ለሁለት ቀናት እንደሚካሄዱበትም ተጠቁሟል::
ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና በኢነርጂ በአይሲ እንዲሁም በጤና በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በቱሪዝም እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኗ የተጠቀሰ ሲሆን፣ መድረኩ የውጭ ባለሀብቶች ከሀገር ውስጥ ኢንተርፕረነሮች እና የመንግሥት አካላት እንዲቀራረቡ ለማድረግ እንደሚጠቅም ታምኖበታል:: ባለህብቶቹ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ በቅርቡ የተደረጉ ለውጦች እንዲመለከቱ፣ ከኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸው ጋር በአጋርነት ሊሠሩ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች እንደሚፈጥሩ እንደሚያስችልም ተነግሯል::
የዘንድሮው ሶስተኛው ፎረም ከ700 በሚበልጡ አዳዲስና ነባር ባለሀብቶች ፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት አጋሮች፣ ታዋቂ የቢዝነስ መሪዎች፣ እንደሚሳፉበት ይጠበቃል፤ በቀጣይ ዓመታት ከሶስት ቢሊየን ዶላር በላይ የሚገመቱ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ እንደሚያስችልም ታምኖበታል::
መድረኩ ኢትዮጵያ የፋይናንሻል ዘርፍ በተለይ የውጭ ምንዛሬ ግብይቱ በነጻ ገበያ እንዲመራ ማድረግን ጨምሮ ወደ ሙሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ መግባቷን እንዲሁም ቁልፍ የኢኮኖሚው ዘርፎችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጋቸውን ተከትሎ የሚካሄድ ነው:: ይህም የኢትዮጵየ መንግሥት ኢኮኖሚውን ትራንስፎርም ለማድረግ እያከናወነ ባለው ተግባር በኢንቨስትመንት ዘርፉ ይታዩ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት የኢንቨስትመንት ዘርፉን አማራጮች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ለማስተዋወቅ እያደረገ ያለውን ጥረት ያመለክታል::
ኮሚሽነሩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት አመታት በርካታ ለውጦችን ማስመዝገቧን ጠቅሰው፣ በተለይ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ የተዘጉ እድሎችን ለውጪ ሀገር ባለሀብቶች ክፍት በማድረግ ጠንካራ ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል::
የኢንቨስትመንት ህግን በማሻሻል ረገድ የተወሰዱ ርምጃዎች ከዚህ ቀደም ለውጪ ባለሀብቶች ተገድበው የቆዩ ዘርፎችን የከፈተ መሆኑን በመጠቆም የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ቦርድ የውጪ ኩባንያዎች በጅምላ፣ ችርቻሮ፣ እንዲሁም በወጪና ገቢ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ መፍቀዱን አስታውቀዋል:: ይህን ተከትሎ ለ40 የውጭ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል:: 66 የሚሆኑት ደግሞ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል::
እንደኢትዮ ቴሌኮም እና የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ የመሳሰሉ ከዚህ በፊት ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ በነበሩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉባቸው መደረጉን ገልጸዋል:: የኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከፍተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ለአብነትም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከአምናው የሁለት ነጥብ አራት በመቶ እድገት ያለው ፍሰት መሳብ ማስቻሉን ገልጸዋል::
የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጣና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ስራ ከጀመረ ወዲህ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለሀብቶችን ወደቀጣናው እንዲገቡ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል:: አስራ አንድ የሚሆኑ ባለሀብቶች መግባታቸውንና አንዳንዶቹም ሸቀጦችን እያመጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል::
እንደ ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ /ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም / ያሉ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ውይይቶችን ማካሄድ ሀገራችንን ለተቀረው ዓለም በይበልጥ የማስተዋወቅ ሥራ መሆኑን ጠቁመዋል::
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ለእነዚህ ግንቦት 4 እና 5 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄደው ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ ፎረም / ኢንቨስት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም/ እንዲሳካ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲሁም መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል::
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም