“በሶስት ክልሎች የሚገኙ ቅርሶችን በሰላም ተንቀሳቅሰን መጎብኘት ችለናል”- አቶ ኤልያስ ሽኩር

– አቶ ኤልያስ ሽኩር የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር

ጊኒር (ምስራቅ ባሌ)፡- በሶስት ክፍሎች የሚገኙ ቅርሶችን ቀንና ማታ በእግር እና በፈረስ ተጉዘው መጎብኘታቸውን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋናዳይሬክተር አስታወቁ። በጉብኝታቸው ያጋጠማቸው የሰላም ችግር እንደሌለም አመለከቱ። ምክትል ዋና ዳይሬከተሩ አቶ ኤልያስ ሽኩር ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ጉብኝቱ አስደሳች እና ቅርሶችን ከመጎብኘትም በላይ የሰላም ጉዞ ነበር፡፡ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ወደ ሙሉ ሰላሟ እየተመለሰች መሆኑን ተጨባጭ ማሳያ ነው ።

‹‹በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው የሰላም እጦት መሬት ላይ የሌለ አሉባልታ ነው›› ያሉት አቶ ኤልያስ ‹‹አራት ቀን ሙሉ የተለያዩ አካባቢዎችን ያዳረሰ በእግር በፈረስ ጉዞ አድርገን የጠበቀን ፍቅርና ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ብቻ ነው›› ብለዋል፡፡

በለውጥ ጎዳና ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ለቅርሶች ልማትና ጥበቃ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ አምስት ቅርሶች በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል ፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የሁሉም አካባቢ ነዋሪ በፍቅር ከመቀበል በዘለለ ምንም አይነት የፀጥታ እክል እንዳልገጠማቸው፤ ሕዝቡ በሰላም የዕለት ተዕለት ኑሮውን እየኖረ እንደሆነ መታዘባቸውን ገልፀዋል፡፡

‹‹የሰላም መደፍረስ ሲያጋጥም ወደ ቅርሶች የሚመጣው የጎብኚ ቁጥር ከመቀነሱም ባሻገር ቅርሶች ከሰው ልጅ ባልተናነሰ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል›› የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ወደ ሙሉ ሰላሟ የተመለሰች መሆኑ ከሰሞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ያደረግነው ጉብኝት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በጎበኘንባቸው አካባቢዎች ሁሉ ወጣቱ ሥራው ላይ ነው ያለው›› የሚሉት ኃላፊው፤ በከተሞች አካባቢ የሚገኘው ማህበረሰብ ከስጋትና ከአሉባልታ ወሬዎች መውጣት አለበት፤ ጉብኝቶች ለማድረግ አስተማማኝ ሰላም እንዳለ ተረድቶ እራሱን ለጉብኝት ማዘጋጀት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

‹‹ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችን ያካተተ እና የእግር ጉዞ ጭምር ያለበት ጫካዎችን እና ስምጥ ሸለቆዎችን ሳይቀር የዳሰሰ ጉብኝት አካሂደናል›› ያሉት አቶ ኤልያስ፤ ‹‹የተለመደው ኢትዮጵያዊ መስተንግዶና ፍቅር የተመላበት አቀባበል በሄድንበት ሁሉ ሲያጅበን ነበር እንጂ ያጋጠመን እንቅፋትም ሆነ የፀጥታ ችግር የለም›› ብለዋል፡፡

በጎበኟቸው ቅርሶችና የቱሪስት መዳረሻዎች ሁሉ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በብዛት ሲጎበኙ መታዘባቸውን የነገሩን አቶ ኤልያስ፤ ይህም አስተማማኝ ሰላም መኖሩን ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል ፡፡

እንደ አቶ ኤልያስ ገለፃ፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በማልማት፣ በመጠገን እና በማስተዋወቅ የጎብኚ ቁጥር ለማሳደግ እና የየአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን በስፋት እየሠራ ነው፡፡ ከሴክተሩ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የተረጋጋ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን የሚገልፁ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ማህበረሰቡ አሁን ያለውን የተረጋጋ ሁኔታና ሰላም አጠናክሮ በመቀጠል ተጠቃሚነቱን ማሳደግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ባዘጋጀው የጉብኝት መርሀ-ግብር በኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን የመልካ ቁንጡሬ እና የባልጪት የቅድመ-ታሪክ መካነ ቅርስን መነሻ በማድረግ የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርን በደቡብ ኢትዮጵያ፣ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክንና በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኘው የድሬ ሼህ ሑሴን ጥንታዊ መካነ ቅርስን ደግሞ በኦሮሚያ ክልልን ያካተተ ጉብኝት ተደርጓል፡፡

ጉብኝቱ ከአራት ቀናት በላይ በመኪና የተደረገ ሲሆን ከንጋቱ አስር ሰአት እስከ ምሽቱ ሦስትና አራት ሰአት ድረስ ጉዞ በማድረግ የተከናወነ ነበር፡፡

ዳርጌ ካሕሳይ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You