
ኢትዮጵያዊቷ ድንቅ የማራቶን ኮከብ አትሌት ትዕግስት አሰፋ በለንደን ማራቶን አዲስ የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብ አሸንፋለች። የዓለም ኮከብ የማራቶን አትሌቶች የሚፋለሙበት የለንደን ማራቶን ትናንት ሲካሄድ ትዕግስት በአስደናቂ ብቃት 2:15:50 ማጠናቀቅ ችላለች። ይህም በሴት አሯሯጮች በተካሄደ ውድድር የተመዘገበ አዲስ የዓለም ክብረወሰን ሆኗል።
ከዓመት በፊት በዚሁ ውድድር ላይ ክብረወሰኑን ይዛ የነበረችው ኬንያዊቷ አትሌት ፔርስ ጂፕቺርቺር ነበረች። ትዕግስት የቀድሞውን ክብረወሰን በ26 ሰከንድ ባሻሻለችበት ድንቅ ብቃት ተፎካካሪዎቿን ከሶስት ደቂቃ በበለጠ ልዩነት ማሸነፏ ብዙዎች ያልጠበቁት ነው። ባለድሏን አትሌት ተከትላ ኬንያዊቷ ጆይስሊን ጂፕኮስጌ 2:18:43 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ጂፕኮስጌ አምና 2:16:16 በሆነ ሰዓት አሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል።
ዘንድሮ ግን አምና ካሸነፈችበት ሰዓት በሶስት ደቂቃ ዘግይታ ነው ሁለተኛ ሆና የፈፀመችው። የዘንድሮዋ ባለድል ትዕግስት አሰፋ አምና በዚህ ውድድር ሁለተኛ ሆና ብታጠናቅቅም ኬንያዊቷን አትሌት በማሸነፍ ቁጭቷን በክብረወሰን በታጀበ ድል ተወጥታለች። የትናንቱ የለንደን ማራቶን ትዕግስት ሌላም ቁጭት በድል የተወጣችበት ነበር። ባለፈው የፓሪስ ኦሊምፒክ በማራቶን ለጥቂት ቀድማት የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችውን የኔዘርላንድስ ኮከብ አትሌት ሲፈን ሀሰንን ለንደን ላይ አሸንፋታለች። ትዕግስት በክብረወሰን በደመቀችበት ፉክክር የርቀቱ የኦሊምፒክ ባለድል ሲፈን ከሶስት ደቂቃ በላይ ዘግይታ በ2:18:59 ሰዓት ሶስተኛ ሆና ነው ማጠናቀቅ የቻለችው።
ትዕግስት በውድድሩ ኦሊምፒክ ላይ በአጨራረስ ቀድማት ወርቁን ያጠለቀችው አትሌት ሲፈን ለንደን ላይ ተፎካካሪ እንደመሆኗ ፓሪስ ላይ የገጠማት ተመሳሳይ ነገር ይገጥመኛል ብላ ስጋት አድሮባት እንደሆን ለቀረበላት ጥያቄ፣ “ውድድሩን እንዳጠናቀኩኝ ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ፣ በማንኛውም መንገድ ለማሸነፍ ዝግጁ ነበርኩ፣ መጨረሻ ላይ ታግዬ ለማሸነፍም ይሁን ረጅም ርቀት ከፊት እየመራሁ ለማሸነፍ ተዘጋጅቻለሁ፣ ዋናው ነገር በደንብ መዘጋጀት ነው፣ ያደረኩትም ይህንኑ ነው፣ በፓሪስ ኦሊምፒክ ለጥቂት ሁለተኛ ሆኜ ካጠናቀቅኩ በኋላ ዛሬ ለማሸነፍ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ፣ ለዚያም ጠንክሬ ተዘጋጅቻለሁ፣ የልፋቴን ውጤት በማግኘቴም በጣም ደስተኛ ነኝ” በማለት በስፍራው ለነበሩ መገናኛ ብዙሃን አስተያየቷን ሰጥታለች።
ትዕግስት በሴት አሯሯጮች የዓለምን ክብረወሰን ባሻሻለችበት ለማመን የሚከብድ ብቃት በእንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ለረጅም ዓመት ተይዞ የቆየውን የለንደን ማራቶን ክብረወሰን (2:15.25) ለማሻሻል ተቃርባ የነበረ ቢሆንም ለጥቂት አልተሳካላትም። የኦሊምፒክ ማራቶን የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ብርቱ አትሌት ትናንት ያስመዘገበችው ሰዓት በማራቶን የውድድር ታሪኳ ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ነው።
ትዕግስት 2022 ላይ በበርሊን ማራቶን ስታሸንፍ 2:15:37 የሆነ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገቧ ይታወቃል። በቀጣይም ዓመት በበርሊን ማራቶን በወንድ አሯሯጮች ታግዛ በተፎካከረችበት ውድድር 2:11:53 በማጠናቀቅ በርቀቱ አዲስ የማራቶን የዓለም ክብረወሰን ጨብጣ ዓለምን ማስደነቅ ችላ ነበር። ያ ክብረወሰኗ ግን በ2024 ቺካጎ ማራቶን በኬንያዊቷ አትሌት ሩዝ ቺፕንጌቲች 2:09:56 በሆነ ሰዓት ተሻሽሏል።
ተጠባቂ በነበረው የለንደን ማራቶን የወንዶች ፉክክር ኬንያዊው ሳባስቲያን ሳዌ 2:02:27 በመግባት አሸናፊ ሆኗል። ዩጋንዳዊው ኮከብ ጃኮብ ክሊሞ በ2:03:37 የሀገሩን ክብረወሰን አሻሽሎ ሁለተኛ በመሆን ፈፅሟል። ሌላኛው ኬንያዊ አሌክዛንደር ሙቲሶ በ2:04:20 ሰዓት ሦስተኛ፣ ኔዘርላንዳዊው አብዲ ናጋዬ በ2:04:20 አራተኛ ደረጃን ይዟል። ለድል ታጭቶ የነበረው የኦሊምፒክ ማራቶን አሸናፊው አትሌት ታምራት ቶላ 2:04:42 ሰዓት አምስተኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም ያስመዘገበው ሰዓት ለቀጣዩ የዓለም ቻምፒዮና ኢትዮጵያን ለመወከል ያበቃዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም