“እኔ ለእናቴ ሮጣለሁ!”

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ሕዳር ወር ላይ ከሚያካሄደው ዝነኛ የአስር ኪሎ ሜትር በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ውድድሮችን ያከናውናል። ከነዚህ ውድድሮች መካከልም ኤሊት አትሌቶች የማይሳተፉበትና በጤና ሯጮች ተሳትፎ ብቻ የሚታወቁ ውድድሮች ይገኙበታል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየጊዜው እነዚህን ውድድሮች የሚያዘጋጀውም ስፖርትን ተጠቅሞ የተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ማሕበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንደሆነ ይታወቃል።

የፊታችን ቅዳሜም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የእናቶች ቀንን በእንጦጦ ፓርክ በሚካሄድ የሩጫ ውድድር እንደሚያከብር ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አመልክቷል። የውድድሩ ተሳታፊዎች ምዝገባ መጀመሩም ታውቋል።

በታላቁ ሩጫ ወርኃዊው የእንጦጦ ፓርክ “ሲቢኢ ሩጫ” ላይ የዘንድሮውን ዓመት የእናቶች ቀን የፊታችን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ጠዋት 1፡30 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄድ የሩጫ ውድድር ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በመደበኛነት በየወሩ የሚያካሂደው የእንጦጦ ፓርክ ሲቢኢ ሩጫ የዘንድሮ ዓመት ስድስተኛ ውድድሩ መሆኑን በማስታወስ፣ የፊታችን ቅዳሜ በሚኖረው ውድድርም እናትና ልጅ በጋራ እንደሚሮጡ ጠቁሟል። አብሮ በመሮጥ ቀዳሚ የሚሆኑት ደግሞ ልዩ ሽልማት ይበረከትላቸዋል ብሏል።

በተጨማሪም በውድድሩ የሚሳተፉ እናቶቻቸውን ይዘው መምጣት ባይችሉም ሩጫቸውን ለእናቶቻቸው መታሰቢያ የሚያደርጉ ተሳታፊዎች በራሳቸው መንገድ የመሮጫ ቁጥራቸውን በመሥራት ይሸለማሉ ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪ በየወሩ በውድድሩ እንደሚደረገው በሁለቱም ጾታ የጤና ሯጮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች መሀከል የሚደረጉት ውድድሮች እንደተጠበቁ ይቀጥላሉ።

የእናቶችን ቀን “እኔ ለእናቴ ሮጣለሁ!” በሚል መርህ እንዲከናወን ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር አብሮ የሚሠራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሕል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ለሚያሳድሳቸው የአቅመ ደካሞች ቤቶች ገቢ ማሰባሰቢያ እንዲሆን በውድድሩ አጋር ድርጅቶች እና ሆቴሎች በውደድሩ ላይ እንደሚሳተፉ ታውቋል። በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሕል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ለሚያሳድሳቸው የአቅመ ደካሞች ቤቶች ገቢ ማሰባሰቢያ የሚሆን የሆቴሎች ውድድርም ይኖራል።

በሲቢኢ ብር ላይ በሚደረገው ምዝገባ ከልጃቸው ወይንም ከእናታቸው ጋር ለመሮጥ ለሚመዘገቡ ተሳታፊዎች የአንዳቸው መመዝገቢያ በነጻ ይሆናልም ተብሏል።

ውድድሩ ለተሳታፊዎች ከሚሰጠው የጤና እና በሩጫ የመዝናናት ጥቅም ባሻገር እንጦጦን የስፖርት ቱሪዝም መዳረሻዎች ማዕከል ለማድረግ እንደሚሠራ የገለፀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣ ለእናቶች ቀን በሚደረገው ውድድር እያንዳንዱ ተሳታፊን ለውድድሩ መመዝገቢያነት የሚያስከፍለውን አንድ መቶ ብር (100 ብር) በቀጥታ እንጦጦ እና አካባቢው የሚገኙ እናቶችን ለማገዝ በማዋል ማሕበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አሳውቋል።

ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መደበኛ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው ወርኃዊው የእንጦጦ ፓርክ ሲቢኢ ሩጫ በሕዳር ወር 2017 ዓ.ም. መጀመሩ የሚታወስ ነው።

ከተጀመረ 25ኛ ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ሕዳር 14 /2018 ዓ.ም. ይካሄዳል። የብር ኢዮቤልዩ ላይ የደረሰው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ሊከናወን ሰባት ወራት የቀሩት ሲሆን፣ ሕዳር 16 ቀን 1994 ዓ.ም. ጅማሮውን ማድረጉ ይታወሳል። ከአፍሪካ ትልቁ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር የሆነው ዝግጅቱ ባለፉት 24 የውድድር ዓመታት ወደ 760 ሺህ አካባቢ ሰው በ10 ኪሎ ሜትር ውድድሩ ላይ አሳትፏል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዘንድሮ ውድድር በተጠናቀቀ ማግስት የ25ኛ ዓመት ክብረበዓሉን አስመልክቶ ለቀጣዩ ዓመት 500 ቀዳሚ ተሳታፊዎች በነጻ ምዝገባ ያከናወነ መሆኑ ይታወሳል። ለሌሎች የውድድሩ ተሳታፊዎች ምዝገባ ሐምሌ ወር ላይ እንደሚከናወን ተገልጿል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You