የቆቅ ንቃት የጀግና ብርታት ያልፈሰሰ መቅኔ፤ ያልደበዘዘ ወኔ፤ ተላብሰው ከገጻቸው ሳነብ የዘጠና አንድ ዓመት አዛውንት መሆናቸው ግምቴን አዛንፎ ጥርጥር ሲገባኝ የወጋቸው ፍትፍት አንጀቴን አርሶ ሲያረጋግጥልኝ የእኔስ የወጣትነት እድሜ ምን ላይ ዋለ? ስል ፈተሽኩት። መናኛ ቤታቸው ዘልቄ ዙሪያ ገባውን ስቃኝ የተሰቀለ አልበም ተመለከትኩና በልጃቸው እስጢፋኖስ አማካኝነት ከዘመን ሰርክ ከሕይወት መልክ ሃሳብ ልዘግን ከፎቷቸው ጋር ተፋጠጥኩ። በኮሪያ መሬት ለፈጸሙት ጀብዱ የሕዝብ ተወካዮችና ባለሀብቶች ጉልበት እየሳሙ እጅ መንሻ ሲያቀርቡ ያሳያል፤ ቀጠልኩና በወታደርነት ሕይወታቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚገልጡ ወረቀቶችን ከራስጌ እስከግርጌ በዓይን ገረፍኳቸው፤ የተዘሩት ቃላትም ልሳናቸውን ፈትተው እንዲህ ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጡኝ።
የኮሪያ ጦር አርበኞችን ለማክበር የተዘጋጀ። አንዳችሁም አልተረሳችሁም፤ ይህ ለደቡብ ኮሪያ ሰላምና ነጻነት ለከፈላችሁት ጀግንነት፣ ለተሞላውና ወደር የለሽ መስዋእትነታችሁ ለማስታወስ የተበረከተ ስጦታ ነው። ሁልጊዜ እናስታውሳችኋለን።
ለኢትዮጵያ የጦር ጀግኖች። በኮሪያ ልሳነ ምድር የተካሄደው ጦርነት በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ ቀውስ አስከትሏል፤ ይሁን እንጂ ከሩቅ ሆነው የሀገራችንን ሕመም እንደራስዎ ተረዱ፤ ደም አፍስሰው ሕዝባችንን ለመታደግ እዚህ ታግለው ለከፈሉት መስዋእትነትና ለታላቅ ቁርጠኝነት የኮሪያ ሪፐብሊክ እንደነጻ ዲሞክራሲ በጽናት በመቆም ታላቅ ሀገር ሆናለች፤ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በዋነኛነት በእግዚአብሔር ቸርነት ነው፤ እናም የሀገራችንን ስቃይ እንደራሳችሁ በመቁጠር ደማችሁን በጦርነት በማፍሰስ ለከፈላችሁት መስዋእትነት ምስጋና መሆኑን እንገነዘባለን።
እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ጀግኖች ወደሀገራችን እንደላካቸው እናምናለን፤ ሕዝባችንን ለመታደግ ያደረጋችሁት ጥረትና መስዋእትነት ከንቱ አልነበረም፤ ለእርስዎ ማድረግ የምንችለው ብዙ ላይኖር ይችላል፤ ነገር ግን እንጸልይሎዎታለን። ላልተወሰነው የኢትዮጵያ ልማትና ለቀሪ ዓመታትዎ በረከቶችን እንዘረጋለን።
ሽበትን ያቆነጀ ከፍተኛ የሙያ ዲሲፕሊን ምግባርን ከሥራ አስማምቶ እኔነታቸውን ውብ ታሪክ ሸለመና በየደረሱበት እኛነትን እንዲያጎሉ አቅም ሆናቸው።
“ኢትዮጵያ ይሏታል ስሟን አሳንሰው፣
ከድንጋይ ይበልጣል ለተሸከመው ሰው።”
እያሉ ለዱር ገደሉ ስንኝ ያቀበሉት የዛሬ እንግዳዬ ስለሀገራቸው ዳር ድንበር መከበር ስለሕዝባቸው የነገ ሕልውና መሻገር ትናንታቸውን የገበሩ ቅን ዘብ አደር ናቸው ሻለቃ አስፋው ተክለማርያም።
ሻለቃ አስፋው ተክለማርያም ከአባታቸው አርበኛ ተክለማርያም ሃብተየስና ከእናታቸው ከወይዘሮ ዘብይደሩ ይታጠቁ በወርሃ ጥር 1926 ዓ.ም በምእራብ ሸዋ ሙገር በከልቻ መንደር ተወለዱ። አባታቸውን አርበኛ ተክለማርያምን ከጣሊያን ጋር በነበረው ጦርነት ከተነጠቁ በኋላ የልጅነት ህልማቸውን ዳዋ እንዳይውጠው የእህታቸው ባለቤት መምህር ጉግሳ ወልደመድህን ወሰዷቸውና የቆሎ ተማሪ ቤት አስገቧቸው፤ መምህሩም በእግራቸው ተተክተው ደብሩን እንዲያገለግሉ አስበው ነበርና በጊዜው የኢትዮጵያ ጳጳስ ከነበሩት ከግብጻዊው አቡነሰላማ ዘንድ መናገሻ ማርያም ደብር ክህነት እንዲቀበሉ ሲያደርጉ እሳቸው ግን በድቁና ተቀጥረው ከሚያገኙት ደመወዝ ይልቅ ያስኳላ ተማሪ መሆን ነውና መሻታቸው እዚሁ አዲስ አበባ በመቅረት ለአርበኛ ልጆች የሚሰጠውን የትምህርት እድል ለመሞከር ደጅ ጠኑ፤ ይሁን እንጂ እንዳለሙት ሳይሆን ቀርቶ “ምስክር አምጣ” ተብለው የሚያውቋቸው ሰዎች እንዳሉ ፍለጋ ሲኳትኑ ፋሺስቱን ጣሊያንን ለመዋጋት በአርበኝነት ከአባታቸው ጋር የተዋደቁትንና ምድር ጦር የነበሩትን ጀኔራል ተድላ መኮንን አገኝዋቸው። ስለሁኔታው ቢያዋይዋቸው ሊቀርቡላቸው አልቻሉምና “ሕይወታችሁን ያተረፋችሁበት ነፍሳችሁን ያቆያችሁበት የአባቴ ሞሰብ ተዘንግቷችሁ ነው እንደማያውቀኝ ሁሉ እንቢ የሚሉኝ?” አሉና እሳቸውን የሚያውቅ እማኝ በመጥፋቱ የትምህርታቸውን እድል ውሃ ሲበላው እያዩ ሆድ ብሷቸው በምትኩ አርሲ ክፍለ ሀገር ሊሰጣቸው የነበረውን የእርሻ መሬት ገፍተው እንባቸውን እያዘሩ ወደቀያቸው ተመለሱ።
“ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ነውና ከጊዜ በኋላ በእንባ የተለዩትን የአዲስ አበባን ምድር በሳቅ ረገጡት፤ ህልም የተዳፈነ ቢመስልም አንድ ቀን የብርሃን ጮራ መፈንጠቁ አይቀርምና መላ ሀገሪቱን ያዳረሰው የክቡር ዘበኛና የኮሪያ ዘማቾች ወሬ ልባቸውን አሸፍቶት በ18 ዓመታቸው ክቡር ዘበኛ ተቀጠሩና የአራተኛ ቃኘው ሻለቃ አባል እንዲሁም ምክትል አስር አለቃ በመሆን የኮሪያ ዘማቾችን ተቀላቀሉና የወታደርነትን ሕይወት አሀዱ አሉ። ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ማለትም 1947 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የነፍስ አባታቸው ሚስት ለምነው አታሞ አጮሁባቸውና ሦስት ወንዶች ሁለት ሴት ልጆች ለማፍራት በቁ፤ በሥራቸው ተመስግነው ሹመታቸው ቢዳብርም የመጀመሪያ ልጃቸውን በወለዱበት ዓመት ከማዕረግ የሚያጎድል ችግር ተከሰተ። ወርሃ ታኅሣሥ 11 ቀን1953 ዓ.ም ወንድማማቾቹ ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይና ሻለቃ ግርማሜ ነዋይ በፈጠሩት መፈንቅለ መንግሥት ሁሉም ሠራዊት አለበት ተብሎ ስለታሰበ ከሃምሳ አለቅነታቸው ሁለት ማዕረግ ተቀንሶ ወደ ሐረር ሦስተኛው የአንበሳ ክፍለ ጦር ተዛወሩ። በሂሳብ ክፍል ውስጥ እየሠሩ እንዳሉ የመኮንንነት ትምህርት አጋጠማቸውና ወለታ ገነት የጦር ትምህርት ቤትን ተቀላቀሉ። በጥሩ ውጤት ከተመረቁ በኋላ በእዚሁ ክፍለ ጦር ውስጥ የተወዳጇቸውን መንግሥቱ ኃይለማርያምን ተሰናብተው ተሰኔ ተዛወሩ፤ ስፍራው የሱዳን ጠረፍ በመሆኑ ጀምረውት የነበረውን የማታ ትምህርት ከስምንተኛ ክፍል ለማቋረጥ ቢገደዱም በወታደርነት ሕይወታቸው ግን ሻለቃ መድረስ ችለዋል። ከምንም በላይ ታሪክ የማይዘነጋቸው የዚያድባሬን ጦር ለመመከት ከኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ጋር ሆነው ታጠቅ የጦር ሰፈርን ማደራጀታቸውን ያስታውሳሉ።
በአሁኑ ሰዓት የጡረታ እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ልምዳቸውን ለማካፈል የኮሪያ ዘማቾች ማህበር ውስጥ የቦርድ አባል ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
ሃብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም