በቱሪስት ፍሰትም፣ በገቢም እምርታ የታየበት አፈጻጸም

ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የአንበሳውን ድርሻ ከሚያበርክቱ ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፍ አንዱ ነው:: ዘርፉ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር በእጅጉ ይጠቀሳል::

ኢትዮጵያም በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብት፣ እንዲሁም ዘርፉ ለምጣኔ ሀብቷ ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶ ተብለው ከተያዙት አምስት ዘርፎች አንዱ አርጋ እየሠራች ትገኛለች::

በዚህም የሀገሪቱ የቱሪዝም መስህቦች እንዲጎበኙ የሚያስችሉ እንደ መናፈሻ ፓርኮችና ሪዞርቶች ያሉ መሠረተ ልማቶችን በአዲስ አበባ ከተማና በክልሎች በመገንባት ወደ ሥራ አስገብታለች፤ ሌሎች በርካታ መሠረተ ልማቶችንም መገንባቷን ቀጥላለች::

ይህ ልማቷ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተከናወኑ ሥራዎች በዘርፉ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት እንዲታይ እያደረገ ይገኛል:: ይህ መነቃቃት እየታየ ካለባቸው መካከልም አዲስ አበባ ትጠቀሳለች::

በከተማዋ በርካታ የቱሪስት መስህቦች እንዳሉ ይታወቃል:: በዚህ ላይ ደግሞ መንግሥት የአንድነት፣ የእንጦጦ እንዲሁም የወዳጅነት ፓርኮች ገንብቶ ወደ ሥራ አስገብቷል::

ከተማ አስተዳደሩም በሥሩ የሚገኙ መናፈሻዎችን በማልማት፣ የኮንፈረንስ ማዕከላትን በመገንባት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንዲገነቡ በማድረግ፣ ወዘተ እየሠራ ይገኛል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ሌላው ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ታምኖበታል::

እነዚህ በዘርፉ የተከናወኑ ተግባሮች የቱሪስቶች ፍሰት እንዲጨምር፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ እንዲያድግ፣ የከተማዋና የሀገሪቱ ገጽታ እንዲገነባ እያደረጉ ናቸው::

የአዲስ አበባ ከተማ ባሕል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁንዴ ከበደ የቢሮውን የ2017 በጀት ዓመት ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም አስመልክተው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ ወደ ከተማ የሚመጣው የቱሪስት ፍሰት እየጨመረ ይገኛል:: ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተሠራ ከፍተኛ ሥራ ከዘርፉ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ መሆን ተችሏል::

እምብዛም ትርጉም የሌለው በሚመስለው የሀገር ውስጥ የቱሪስት ፍሰት በቁጥርም በግንዛቤም እምርታ እየታየ መሆኑን አቶ ሁንዴ ጠቁመዋል::

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 743 ሺ 264 / ሰባት መቶ አርባ ሶስት ሺ ሁለት መቶ ስልሳ አራት/ የውጪ ቱሪስቶች መስተናገዳቸውን አስታውቀዋል:: በእነዚህ ወራት ለማስተናገድ የታቀደው 773 ሺ 243 /ሰባት መቶ ሰባ ሶስት ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሶስት/ የውጭ ቱሪስቶችን እንደነበር ጠቅሰው፣ የእቅዱን 96.1 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል::

እኚህ ጎብኚዎች በጉባዔዎች እንዲሁም በተለያዩ ሁነቶች ላይ ተሳታፊ የነበሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል:: ከውጭ ጎብኚዎች በእቅድ ደረጃ 99 ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እንደነበር ጠቅሰው፣ አፈጻጸሙ ግን 100ነጥብ ሶስት ቢሊየን ብር መሆኑን ገልጸዋል:: ገቢው ቀጥታ ከቱሪስቶች የተሰበሰበ እንዳልሆነም ምክትል የቢሮ ኃላፊው ገልጸው፤ ቱሪስቱ ከተማ ሲመጣ በተለያየ መንገድ ያወጣው ከግምት ውስጥ ገብቶ የተሰላ እንደሆነ ጠቅሰዋል::

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት አንድ ቱሪስት በሀገሪቱ ሲቆይ በቀን ሁለት መቶ ሰላሳ አራት ዶላር ገደማ ያወጣል:: የዘጠኝ ወር የገቢ ስሌት በዚህ መሠረት የተሠራ ነው::

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ስድስት ነጥብ ስምንት (6.8) ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችን ለማስተናገድ ታቅዶ እንደነበር ጠቅሰው፣ በአፈጻጸሙ ከእቅዱም የላቀ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚደርሱ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች መስተናገዳቸውን አመልክተዋል::

እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ ለዚህ አፈጻጸም ከፍተኛ መሆን እንደ ዋነኛ ምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ በሀገሪቱ የሚደረጉ ትላልቅ ሕዝባዊ በዓላት የላቀ ሚና አላቸው:: በተለይ የአዲስ ዓመትን መግባት ተከትሎ በወርሀ መስከረም የሚከበሩ እንደ ኤሬቻ፣ መስቀልና የመሳሰሉት በርካታ ሚሊዮን ሕዝብ የሚያከብራቸው በዓላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል:: ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት ለሀገር ውስጥ የቱሪስት ፍሰት መጨመር ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል::

በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት መስፈርት መሠረት አንድ ቱሪስት ቱሪስት ለመባል ከቤቱ ወጥቶ ሃያ አራት ሰዓታት ቆይታ ማድረግ ይኖርበታል፤ አንድ ግለሰብ በሄደበት አካባቢ ከአንድ ዓመት በታች መቆየት ከቻለም እንዲሁ ቱሪስት ሊባል ይችላል፤ በዚህ ምክንያት ከተለያየ የሀገራችን ክፍሎች ወደ ከተማዋ ለንግድና በመሳሰሉት፣ ለዘመድ ጥየቃ፣ ለመዝናናት እና ለመሰል ጉዳዮች የሚመጡ ሁሉ በዚህ ደረጃ ይታያሉ::

በገቢ ደረጃም በእቅድ ደረጃ ከሀገር ውስጥ ቱሪስቶች 40.9 ቢሊየን ብር ይገኛል ተብሎ ታቅዶ እንደነበር ጠቅሰው፣ ይሄም ወደ ከተማዋ ኢኮኖሚ ይገባል ተብሎ ከሚጠበቀው 55.8 ቢሊየን አካባቢ እንደሚሸፍን ገልጸዋል:: ኃላፊነት እንዳለበት መሥሪያ ቤት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሀገሪቱ ጥሩ በሚባል የቱሪስት ፍሰት ላይ ትገኛለች ሲሉም ጠቁመዋል::

አዲስ አበባ ከአፍሪካ መዲናነት ባለፈ በርካታ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በማስተናገድም ትታወቃለች:: በውስጧም ነባር እና አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ቢገኙም ከዘርፉ ግን በሚገባው ልክ ተጠቃሚ ስትሆን ኖራለች::

ከተማዋ ከቱሪስት መስህቦቿና መዳረሻዎቿ ተጠቃሚ እንድትሆን ምን እየተሠራ እንደሆነ የጠየቅናቸው ምክትል የቢሮ ኃላፊው አቶ ሁንዴ ከበደ ሲያብራሩ እንደገለጹት፤ የቱሪዝም ዘርፉ በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያቀፈ ነው፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለብዙዎች ጥቅም የሚሰጥ ዘርፍም ነው::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ መንግሥት ዘርፉ ላይ ኢንቨስት እያደረገ ያለበት ሁኔታ ዘርፉ የተሻለ እምርታ እንዲያሳይ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ምክትል የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል:: ዘርፉ በተስፋ ሰጪ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል::

አቶ ሁንዴ እንዳብራሩት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት መዝናኛው ላይ መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ፓርኮች፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣ ትላልቅ መሠረተ ልማቶች፣ ከተማችን ላይ መገንባታቸው በቱሪዝም ዘርፉ እየታየ ላለው ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል::

መሠረተ ልማቶቹ የሥራ እድሎችን በመፍጠር፣ ለተዝናኖት እንዲሁም የተለያየ አገልግሎት ሰጪነት በመዋል ከቱሪስት ከሚገኘው ገቢ ባለፈ ማኅበረሰቡን እየጠቀሙ ይገኛሉ:: በከተማዋ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መኖራቸው ዘርፉ ላይ ያለውን ተግዳሮት በማስቀረት ቱሪስቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል::

ከዘርፉ እየተገኘ ያለው ገቢ እንደ ሀገር ካለው እምቅ ሀብት አኳያ በቂ ነው ተብሎ ሊወሰድ እንደማይችል ተናግረው፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግን የተሻለ እምርታ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል::

አቶ ሁንዴ እንዳሉት፤ አዲስ አበባ እያካሄደች ካለችው የኮሪደር ልማት እንዲሁም እንደ ሀገር እየተሠራ ባለው የውበት እና የአረንጓዴ አካባቢ ንቅናቄ ጋር በተያያዘ የከተማዋ ስም በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር በአዎንታዊ መልኩ እየተነሳ ይገኛል::

ከአዲስ አበባ ወቅታዊ ለውጥ እና የኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን እየሰጡ ያለበት ሁኔታም ሌላው የለውጡ አንድ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል:: የሚዲያው ዘርፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ወደ ከተማዋ ሲመጡ ያለውን ለውጥ በማሳየት፣ እንደ አፍሪካ ህብረት ያሉ ግዙፍ ዝግጅቶችን በመጠቀም ብሎም እንግዶችን ወደ ከተማዋ ከመጥራት ጀምሮ መሠራቱ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን ገልጸዋል::

በቀጣይም በዘርፉ ላይ የተሻሉ ማስታወቂያዎችን እንዲሁም በገጽታ ግንባታ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን በመሥራት የበለጠ ተጠቃሚነትን መፍጠር እንደሚቻል አመልክተዋል:: በመዲናዋ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ተከትሎ የሚመጡ እንግዶችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ባለድርሻ አካላትን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከማስተዋወቅ አኳያ እንደሚሠራ ጠቁመዋል::

የቱሪዝም እንቅስቃሴው፣ እንዲሁም አጠቃላይ የልማት ንቅናቄው ሽፋን እንዲያገኝ ለማድረግ ፓኬጅ በማዘጋጀት ጭምር እንግዶችን ወደ ቱሪስት መዳረሻዎች በመውሰድ፣ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል የቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል::

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ግለሰቦች ስለከተማዋ ሲናገሩ በተደጋጋሚ ሰምተናል ሲሉም ተናግረው፣ በቀጣይም ራሳችንን በይበልጥ በማስተዋወቅ ተሽለን የምንገኝበትን እድል መፍጠር ይገባናል ሲሉ አስገንዝበዋል::

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የቱሪዝሙ ዘርፍ የራሱ ዓለም አቀፍ ሕግጋት አሉት:: በተለይ ቱሪስቶች ለጉብኝት ወደ አንድ ሀገር ሲሄዱ ወጪ ያደርጋሉ:: በወጪያቸው ልክ አገልግሎት እንዲያገኙ ደግሞ ዘርፉ ከአስጎብኚ ጀምሮ ባለው ሂደት የተደራጀ መሆን ይገባዋል:: ከዚህ ጋር በተያያዘ የቱሪዝም ዘርፉ በምን አቋም ላይ እንደሚገኝ አቶ ሁንዴ አብራርተዋል::

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ዘርፉ እንደ አስጎብኚ ድርጅቶች ያሉ በርካታ ባለድርሻ አካላት አሉት፤ በማህበር ደረጃ የተዋቀሩ የአዲስ አበባ የአስጎብኚ ማህበራት እቅድ ከማውጣት ጀምሮ ከቢሮው ጋር በቅርበት እየሠሩ ይገኛሉ:: አፈጻጸምን ጭምር በጋራ በመገምገም በእያንዳንዱ ሂደት ላይ ተናቦ የመሥራት ሁኔታ ይስተዋላል:: ቢሮው ከአቅም ግንባታ አኳያም ለአባሎቻቸው ግንዛቤ የሚፈጥሩ ሥልጠናዎችን እስከ መስጠት የደረሰ ትስስር አለው::

ማህበራቱ የሀገር ገጽታን በመገንባት ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የጠቀሱት አቶ ሁንዴ፣ ከዚህ አኳያ ቱሪስቶችን በሚመለከት ብቁ አገልግሎት ከመስጠት አኳያም ተናቦ የመሥራቱ ነገር ወሳኝ ነው ብለዋል::

ከአስጎብኚ ማህበራት ባለፈ እንደ ሆቴል ባለንብረቶች ያሉ በርካታ ባለድርሻ አካላት፣ እንዳሉ ጠቅሰው፣ ከሁሉም ጋር በቅንጅት በመሥራት ሥራዎች እየተገመገሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል::

እንደ ምክትል የቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በዲፕሎማሲው ዘርፍ ሀገሪቱ ባላት ዓለም አቀፍ ስም በሀገር ውስጥ የሚገኙ የውጭ ሀገር ዲፕሎማትን በመጋበዝ መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ፣ የኮሪደር ልማቱን እንዲመለከቱ በማድረግ በኩል ብዙ ርቀት በመሄድ ተሠርቷል:: በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመጡ እንግዶች ፓኬጅ በማዘጋጀት በገጽታ ግንባታ ላይ ተሠርቷል:: የዓለም የቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ ለሚመጡ እንግዶችም ሆነ በሀገሪቱ ላሉ እንግዶች መዳረሻዎችን በማዘጋጀት እንዲጎበኙ ማድረግ ላይም እንዲሁ የተለያዩ ተግባሮች ተከናውነዋል::

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የትራንዚት ተጓዦች ከተማዋን መጎብኘት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ አየር መንገዱ ኢሚግሬሽን እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውሰን፣ ቢሮው ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን እየሠራ እንደሚገኝም ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹በዘርፉ ላይ እንደ መቆየቴ ስምምነቱን ታሪካዊ ስምምነት እንደሆነ አድርጌ ነው የምመለከተው›› ሲሉ ተናግረዋል::

በዚህ በኩል ሀገሪቱ ትልቅ ሀብት እንዳላት ጠቅሰው፣ ይህን ሀብቷን በአግባቡ ያልተጠቀመች ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ስምምነቱ ብዙ ጥያቄዎችን እንደሚመልስም ገልጸዋል:: ‹‹ያልተጠቀምንውን የቱሪዝም እድል እንድንጠቀም ከማድረግ አኳያ በትልቁ የሚታይ ነው›› ብለዋል::

ከአየር መንገዱ ግዙፍነት እና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ጋር ተያይዞ ትራንዚት መንገዶኞች ከተማዋን/ሀገሪቱን/ እንዲጎበኙ ስምምነት መፈረሙ በተለይ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት መልካም እና አዲስ ክስተት መሆኑን አስታውቀዋል::

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጓዦች አንድ ቦታ ላይ ተቀምጦው ለረጅም ጊዜ የሚያሳልፉበትን አጋጣሚ ወደ እድል ቀይሮ ለሀገር ኢኮኖሚ ማዋል ደስ የሚያሰኝ ተግባር ነው ሲሉ ያብራሩት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፣ ‹‹ተጓዦች ሶስት፣ አምስት አሊያም አስር ሰዓት ሊኖራቸው ይችላል፤ ይህን ያህል ሰዓት አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ከሚቀመጡ ከተማዋን እንዲጎበኙ መደረጉ ለዘርፉ ትልቅ ለውጥ ይዞ ይመጣል ብለዋል::

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ስምምነቱን የፈረሙት ሶስት ወሳኝ የሆኑ መሥሪያ ቤቶች ናቸው:: በተለይ ከኢሚግሬሽን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙ ከሆነ በቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ እምርታ እንደሚመጣ ይጠበቃል::

ለተግባራዊነቱም እንደ ከተማ መስተዳድር ቴክኒካል ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል ሲሉ ጠቅሰው፣ ከኮሚቴዎቹ ውስጥ እሳቸው የሚመሩት ባሕል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ መሆኑን ገልጸዋል:: ቴክኒካል ቡድኑ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመው፣ በቀጣይ እንደ ሀገር ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበትን ሁኔታ የመፈጠር እድሉ ሰፊ መሆኑን አንስተዋል::

ሀገራችን በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ሀብቶቿ የበለጸገች ሆና ሳለ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ሳታገኝ መኖሯ በእጅጉ ያስቆጫል፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የተወሰዱ ርምጃዎች ይሄን ቁጭት ወደ ዕድል በመቀየር ሀገሪቱ በሚገባት ልክ ባይሆንም ተስፋ ሰጪ ለውጦችን እንድታይ አድርገዋታል:: በሁሉም አካባቢ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች የተሻለ እምርታን በመፍጠር ቱሪዝሙ እንዲመነደግ የሚያደርጉ መሆናቸውን እኛም ለማወቅ ችለናል::

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You