
በሀገርኛ ወግና ባህል ‹‹ባይበላስ ቢቀር!›› የሚባልባቸውን አጋጣሚዎች አውቃለሁ።ለምሳሌ፤ አንድ ሰው ሰርቆ ተይዞ ሲዋረድ፤ ታዛቢዎች ‹‹ባይበላስ ቢቀር!›› ይላሉ።እንዲህ ከመዋረድ በረሃብ መሞት ይሻላል እንደማለት ነው።ይህን የሚሉ ሰዎች የህሊና እና የሞራል ከፍታ አለን የሚሉ ሰዎች መሆናቸው ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ አንድ ሰው እጅግ አድካሚ የሆነ ሥራ ሲሠራ፣ አንዲት ትንሽ ነገር ለማግኘት ከፍተኛ ድካም ሲደክም ሲያዩት ‹‹ባይበላስ ቢቀር!›› ይላሉ።ይሄኛውን እንኳን ስንፍና ብሎ መግለጽ ሳይሻል አይቀርም።ላለመድከም ብሎ ከመቸገር፤ ከፍተኛ ድካም ደክሞ ትንሽዬ ነገርም ቢሆን ማግኘት ይሻላል።ለትንሽ ነገር ብዙ የሚደክሙት የሥራ አመራጭ ያጡ እና የተቸገሩት ሊሆኑ ይችላሉ።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ‹‹ባይበላስ ቢቀር!›› የሚባለው ሌሎችን ሰዎች የሚረብሽ ነገር ሲደረግ ነው።ለምሳሌ፤ አንድ ሰው የሚበላው ነገር በዙሪያው ያሉትን ሰዎች የሚረብሽ ከሆነ(ድምጽ የሚፈጥር፣ ሽታ ያለው…) እንዲህ እየተሳቀቁ ከመብላት ባይበላስ ቢቀር! ሊባል ይችላል።ይህን የሚያደርጉ ሰዎች(እየረበሹ የሚበሉ ማለት ነው) ረሃብ አስገድዷቸው ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የግለዴሽነት እና የምን አገባኝነት ስሜት ያላቸው ናቸው።በዛሬው ትዝብቴ ‹‹ባይበላስ ቢቀር!›› ያልኩበት ምክንያት ከእዚህኛው ጋር ሳይቀራረብ አይቀርም! ምክንያቴ ደግሞ የሰሞኑ የበዓል ሁኔታ ነው፡፡
ከእዚህ በፊት በነበሩ በዓላት ይህን ትዝብት መግለጻችን ይታወሳል።ዳሩ ግን ችግሩ ስላልተቀረፈ አሁንም ጉዳይ እናደርገዋለን።
በዓል በመጣ ቁጥር የሚያበሳጨኝ ነገር፤ ከበዓሉ በኋላ በየመንገዱ የሚጣለው የእንስሳት ተረፈ አካል ነው።አዲስ አበባን የሚያህል ትልቅ ዓለም አቀፍ ከተማ ውስጥ እርድ የሚከናወነው በዘፈቀደ ነው።በተለይም እንደ ዳርቻ ባሉ አካባቢዎች ደግሞ ይብስበታል።በተለይም እንደ ገና እና ፋሲካ ያሉ በዓላት ደግሞ የቅርጫ ሥጋ ስለሚከናወንባቸው ከብት በብዛት ይታረዳል።የከብት ተረፈ አካል ደግሞ ብዙ ነው።ያ ሁሉ ተረፈ አካል በዘፈቀደ በየመንገዱ ይጣላል።ከቆዳ ጀምሮ ለብዙ የፋብሪካ ውጤቶች ያገለግላሉ የሚባሉት የእንስሳት አካላት መንገድ ላይ ይጣላሉ፤ የሚፈለገው የሚበላው ክፍል ብቻ ነው።ይህ የሚያሳየን ከሥልጣኔ ያለንን ርቀት ነው።እንደ ቆዳ ያሉ የእንስሳት ተረፈ አካልን የፋብሪካ ውጤት ማድረግ የሚያስችል የኢንዱስትሪ አቅም ባይኖረን እንኳን፤ ቢያንስ ሰዎችን እንዳይረብሽ ማድረግ አልቻልንም።እዚያው ይበላል፤ እዚያው ይጣላል!
‹‹ባይበላስ ቢቀር!›› የሚያሰኝ ሃሳብ የሚመጣብኝ እዚህ ላይ ነው።ግቢ ውስጥ ወይም በር ላይ ከብት ወይም በግ ወይም ፍየል ይታረዳል።ግቢው ደም በደም ይሆናል።ምናልባት ትንሽ የተሻሉ ሆኑ ከተባለም ከውጭ በኩል በር ላይ ያረዱ ካሉም በሩ ደም በደም ይሆናል፤ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ ይረብሻል።ቆዳውን ጨምሮ ከእያንዳንዱ የሥጋ ብልት ላይ የሚጣለው ተረፈ ሥጋ በዘፈቀደ በየሜዳው ይጣላል።ደሙ እና የተጣለው ተረፈ ሥጋ ዝናብ ወይም ፀሐይ ሲነካው አደገኛ ሽታ ይፈጥራል።የሚበላው ሥጋ ደግሞ በሚፈለገው አይነት እየተዘጋጀ የቅመም ዝርያ ሁሉ እየገባበት ይሠራል።ከእዚያም ይበላል ማለት ነው።
የሙያ ውድድር የተደረገበት እና የቅመም ዝርያ ሁሉ ተደርጎበት የተዘጋጀው ምግብ የሚበላው በሩ አካባቢ ጭንቅላት የሚበትን ሽታ ባለበት ነው።ምናልባት ሽታው ቤት ውስጥ ባይገባ እንኳን፤ እንግዳ ለመቀበል ወጣ ባሉ ቁጥር የተጣለውን ተረፈ ሥጋ ሽታ ተቋቁመው ነው።ወደእዚህ ቤት ተጠርቶ ሊበላ የሚመጣ ሰው ያ ሽታ ሲሸተው ‹‹ባይበላስ ቢቀር!›› አይልም? ከበላሁ በኋላ ከታመምኩ ምን ያደርግልኛል? በበዓላት ለምግብ የተጋነነ ትኩረት እንሰጣለን።አምናለሁ(አውቃለሁ) የሠለጠኑ ሀገራት ዜጎች ለምግብ ከፍተኛ ቦታ ይሰጣሉ። እንዲያውም እኛ ሐበሾች ለምግብ ብዙም ትኩረት አንሰጥም።እንዲያውም በሐበሻ ሥነ ልቦና ለምግብ ትኩረት የሚሰጥ ሰው እንደ ሆዳም እና ሰነፍ ነው የሚታየው።ነጮች ለምግብ ትልቅ ዋጋ ይሰጣሉ።ልዩነቱ ግን እነርሱ ትኩረት የሚያደርጉበትና እኛ ሐበሾች ትኩረት የምናደርግበት መንገድ የተለያየ ነው።እነርሱ ጤናቸውን ለመጠበቅ ነው፤ እኛ ሐበሾች ደግሞ ጭራሽ ጤና የሚጎዳ ነው፡፡
ምግብ አለመመገብ ጤናን ይጎዳል፤ በተመሳሳይ ምግብ ከመጠን በላይ መብላትም ጤናን ይጎዳል።እኛ ጋ ሁለቱም ችግር አለ፤ በጣም መራብ እና በጣም መጥገብ የብዙ ሰዎች ባህሪ ነው።በተለይ ለበዓል ሲሆን ደግሞ ከልክ በላይ መጥገብ የበዓሉ መገለጫ እየመሰለ ነው።
በሌላ በኩል የበዓል ዋናው ዓላማ ምግብ አስመስለነዋል።ይህ ልማዳችን ዝርክርክ እና ኋላቀር እንድንሆን ሳያደርገን አይቀርም።ብዙ ነገሮች እንዲበለሻሹ እያደረገ ነው።ቀላል ምሳሌ ልግለጽ፡፡
ባለፈው ቅዳሜ(የትንሳኤ ዋዜማ) ዕለት እንዲህ ሆነ።ይህ በዓይኔ ያየሁት ገጠመኝ ነው።የሕግ ታራሚዎች ለመጠየቅ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሄድኩ።ሁለታችንም አካባቢውን ከእዚህ በፊት ስለማናውቀው በሌላ ሰፈር ያሉ የትራንስፖርት አማራጮችን አናውቃቸውም።ከመገናኛ ቃሊቲ ሄደን ከቃሊቲ ቀጥታ ወደ ቂሊንጦ ሄድን፤ ጠዋት ስለነበር መንገዱ ክፍት ነው።
ታራሚዎችን ጠይቀን ስንመለስ፤ ወደ ቃሊቲ የሚወስድ ታክሲ የለም።ትንሽ እንቆምን ‹‹መንገድ እኮ ዝግ ነው!›› ተባልን።ቅርብ መስሎን በእግራችን ጀመርነው።ትንሽ እንደሄድን መንገዱ ሁሉ ከብት በከብት ሆኗል፤ መንገዱ የተዘጋው ቃሊቲ የከብት ገበያ ስላለ ነው።አይተነው ስለማናውቅ በዚህ አጋጣሚ እንጎብኘው ብለን እየተቀላለድን የእግር ጉዞውን ጀመርነው።ችግሩ ግን ወደ ገበያ ቦታው እየተቃረብን ስንሄድ በእግር ለመሄድ እንኳን የማይቻል ሆነ።ሰው ከከብት ጋር እየተጋፋ ይሄዳል።
አንዳንድ ቦታ ላይ በሬ ያመልጣል፤ ሰው ሁሉ ይደነብራል።ልጆች፣ ሴቶች እና በዕድሜ የገፉ እናቶችና አባቶች እየወደቁ እየተነሱ ይሄዳሉ።በሬ አመለጠ በተባለ ቁጥር በሽሽት ሰው በሰው ላይ እየተደራረበ ትርምስ ይሆናል።ክስተቱ ለወጣት ወንዶች እንደ መዝናኛ ጭምር ይታያል።እኛም በክስተቶች አልፎ አልፎ ዘና ብንልም፤ እናቶችና አባቶች ሲወድቁ ማየት ግን ያሳቅቃል።በሬ ባለመጠ ቁጥር ሰዎች ከፊታቸው ካለ ነገር ጋር ሁሉ ሲጋጩ ያሳዝናሉ።በእዚያን ዕለት ባያጋጥመኝም በእንዲህ አይነት ሁኔታ ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ በተደጋጋሚ አይተናል።በእዚህ አጋጣሚ አሠራሩ ሊታሰብበት ይገባል።
ይህ ብቻ አልነበረም ችግሩ! እኛ ካየንበት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጀምሮ እስከ ቃሊቲ ድረስ መንገዱ ሁሉ በከብቶች ጽዳጅ በረት ይመስል ነበር።በእዚያ ሰሞን በእዚያ አካባቢ የሚያልፍ ሁሉ ለጉንፋን እና አስም ሕመም ይዳረጋል ማለት ነው።በዓሉ ካለፈ በኋላ እንኳን በሥነ ሥርዓት አይጸዳም።ይህ በየዓመቱ ስናየው የነበረ ልማዳችን ነው።ከበዓል በኋላ በጉንፋን መያዝ ልማድ አድርገነዋል።
ወደ ቃሊቲ እየተጠጋን ስንሄድ በግ፣ ፍየል እና ዶሮ የሚሸጥባቸው ቦታዎች ላይ ደረስን።የመጥፎ ሽታው ነገር በጣም ብሶበታል።ሞተው የተጣሉ ዶሮዎች ሁሉ ይታያሉ፤ የሚጣሉትም በዘፈቀደ መንገድ ላይ ነው።ተላላፊውም ምንም ሳይመስለው እንደዋዛ እያየው ያልፋል፤ ምክንያቱም እንደ ችግር አይታይም ማለት ነው።
የበዓል ውበቱ ይህ አይነቱ ግርግሩ ጭምር መሆኑን አምናለሁ።ዳሩ ግን በሰለጠነ መንገድ ማድረግ ይቻል ነበር።መታመም እና መረበሽ የበዓል ግዴታ አይደለም።በየቦታው የእንስሳት ተረፈ አካል መጣል የበዓል ግዴታ እና ውበት አይደለም።ስለዚህ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚደረግ የከብት ሽያጭ እና የእርድ ሥነ ሥርዓት ሊዘምን እና ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል።
በዓል ውበቱን ጠብቆ፣ አክባሪውም ጤናውን ጠብቆ ይጠናቀቅ ዘንድ የባሕል አብዮት ያስፈልገናል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም