
አቶ ሽመልስ ታምራት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በከተማ ውስጥ ያለውን የቤት አቅርቦት ችግር እንዲቀርፍ ታስቦ በከተማ አስተዳደሩ የተቋቋመ ነው። ባለፉት ዓመታት የተለያየ አደረጃጀት የነበረው ሲሆን፤ በኋላም ኮርፖሬሽን ተብሎ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ሊቋቋም በቅቷል። ወደተግባር የገባው ቀደም ሲል የነበረውን 20/80 ቤቶች ግንባታ፣ የ40/60 ኢንተርፕራይዝ እና የቤት አስተዳደር ኤጀንሲን በጋራ አጣምሮ ነው። አጠቃላይ የተጣለበትን ተልዕኮ ለመወጣት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። በተለያዩ መርሃ ግብሮችም የ20/80 እና የ40/60 ቤት ሲገነባ ቆይቷል። ቀደም ሲል የ10/90 ቤት ሲገነባ እንደነበረም የሚታወስ ሲሆን፤ ጎን ለጎንም የከተማ አስተዳደሩ በካፒታል ፕሮጀክት የሚገነባቸውን ለኪራይ የሚሆኑ ቤቶችንም በተመሳሳይ መልኩ ለሚመለከተው አካል ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡
እስካሁን ድረስ ባለው መርሃ ግብር ከ320 ሺ ቤት በላይ በነባሩ መርሃ ግብር ተላልፏል። ሌሎች ለኪራይ የገነባቸው ቤቶች አሉ። በተመሳሳይ መልኩ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍል የግል ባለሀብቱና መንግሥት በጋራ የገነቧቸውንም ለማኅበረሰቡ በማስረከብ ላይ ነው። አሁን ደግሞ በነባሩ ሞዳሊቲዎች ብቻ ሳይሆን ጨመር አድርጎ የ70/30 እንዲሁም የማኅበር ቤት ጨምሮ ወደ ሥራ ገብቷል። ይሁንና የጋራ መኖሪያ ቤት እድለኞች ዛሬም ቅሬታ አላቸው። መሠረተ ልማት አለመሟላቱን፣ ሊፍት አለመገጠሙን እና መሰል ቅሬታዎችን ሲያነሱ፤ ተመዝግበው ቤት ያልደረሳቸው ደግሞ ዕጣ ፈንታችን ምንድን ነው? ይላሉ። አዲስ ዘመንም እነዚህን ቅሬታዎች ይዞ የኮርፖሬሽኑን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራትን አነጋግሮ ተከታዩን ይዞ ቀርቧል።
አዲስ ዘመን፡- የ14ኛ ዙር የቤት እድለኞች መካከል በመሠረተ ልማት አለመሟላት ምክንያት ያልገቡ ያሉ ሲሆን፤ የገቡትም በፈተና ውስጥ መኖራቸውን ይናገራሉ። በዚህ ጉዳይ ምን መፍትሔ አምጥታችኋል?
አቶ ሽመልስ፡– እንደተባለው በመሠረተ ልማት በኩል አንዳንድ ቦታዎች ችግሮች ነበሩ። ነገር ግን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በተቻለ መጠን የመሠረተ ልማት አቅራቢው ተቋምና የእኛ ተቋም በጋራ ሆነው ሰፊ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ ሲሆን፤ ችግሮችም እየተቀረፉ ይገኛሉ። ይህን ለማረጋገጥ ተንቀሳቅሶ ማየት ይቻላል።
እርግጥ ችግሩ ነበር፤ ነገር ግን ተቋማቱ በመቀናጀታቸው ምክንያት በተለይ ዕጣ ደርሷቸው ቤታቸው ገብተው እየኖሩ ላሉ የከተማ አስተዳደሩ ቅድሚያ እንዲሰጥ በማድረጉ በተለይ በዚህ ዓመት የተደረገው ሰፊ እንቅስቃሴ ነው።
እንደተባለው ዕጣ የደረሳቸው፤ በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ በኮሪደር ምክንያት ተነሺ ሆነው ወደጋራ መኖሪያ ቤቶች የሔዱ ነዋሪዎች አሉ። እነዚህ ወዲያውኑ አገልግሎቱን ማግኘት ስላለባቸው የመብራትና የውሃ አቅርቦቱን በቅንጅት ለመሥራት ጥረት ተደርጓል። በዚህም የተነሳ ብዙ ቦታ የነበረው ችግር ተፈትቷል። አሁን ደግሞ የሚቀሩ አካባቢዎች አሉ። ለምሳሌ ከመብራት ጋር ተያይዞ ትራንስፎርመር ተዘርግቶ ኃይል ያልተገኘበት፣ አንዳንድ ቦታ ደግሞ ትራንስፎርመር የጎደለበት ቦታ አሉ። ነገር ግን በየደረጃው ለመመለስ እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ በመንገድ በኩል ችግር መኖሩን ነዋሪዎች ይጠቁማሉና ከዚህስ አኳያ ምን ሊደረግ ታስቧል?
አቶ ሽመልስ፡- መንገድን በተመለከተ በተቻለ መጠን ነዋሪው ገብቶ ሊወጣበት የሚችልበት፤ ከተቻለ ደግሞ ሙሉውን መንገድ በዲዛይኑ መሠረት መሠራት አለበት። ካልሆነ ግን ቢያንስ ሊያስወጣው የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ መኖር አለበት በሚል በአብዛኛው ቦታ እንዲኖር ተደርጓል። በዲዛይኑ በተያዘው መሠረት መንገዶችን የመሥራት ሥራ ጎን ለጎን ጥረት ተደርጓል።
ለምሳሌ አንዳንድ ቦታ ላይ ኮንትራክተሮች ተሰጥቷቸው ሳይሠሩት የቆዩበት ሁኔታ ነበር። ይህ ወዲያኑ ተቋርጦ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በራሱ ገብቶ እየሠራ ይገኛል። እየሠራ ካለባቸው አካባቢዎች አራብሳንና ሐያትን መውሰድ ይቻላል። በዚህ ጉዳዩ የከተማ አመራሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶት የተረባረበበት ዓመት ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህ ቀደም ሲል ኮንትራክተሮቹ ይዘውት፤ ነገር ግን ሳይሠሩት ለዓመታት በመቆየታቸው ተነጥቀው በኃይል የተገባበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ በመጀመሪያ ቅድሚያ ለማኅበረሰቡ በሚል የተደረገ ርምጃ ነው። የሚቀር ቦታ አለ ከተባለ አዎ አለ፤ በቀጣይ ደግሞ ከስር ከስር እየታየ የሚሠራ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከመብራት ጋር ተያይዞም በርካታ ችግር እንዳለ ይታወቃል፤ ብዙዎች ከዚህ የተነሳ ለተለያዩ ወጪዎች ተዳርገዋልና ይህ ጉዳይ በአፋጣኝ መስተካከል ያልቻለው ለምንድን ነው?
አቶ ሽመልስ፡- ከመብራት ጋር ተያይዞ ያለው ሁኔታ እንደተባለው ብዙ ቦታዎች ላይ ችግር አለ። ነገር ግን ነዋሪዎች ሲገቡ በመጀመሪያ ሳይቱ ላይ ያለውን መብራት ለመስጠት ይሞከራል። ነዋሪው የሚያበራው ነገር እንዳያጣ በሚል ለግንባታ ያስገባነውን መብራት እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራ ይሠራል። ጎን ለጎን መብራት እየገባ ሲሔድ ከመብራት ኃይል ጋር እየተዋዋለ ትራንስፎርመር እንዲገባና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች እንዲሟሉ ተደርጎ ሰው መብራት እንዲያገኝ በመሠራት ላይ ነው።
በዚህ ዓመት በተደረገው የጋራ ቅንጅት አብዛኞቹ ቦታዎች ላይ ትራንስፎርመር ገብቷል። ብዙ ቦታዎችም ኃይል እንዲተላለፍ ተደርጓል። አንዳንድ ቦታዎች ግን ትራንስፎርመርም ገብቶ ኃይል ያልተለቀቀባቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ትራንስፎርመር፣ ተሟልቶ ያልገባባቸው ቦታዎች አሉ። ነገር ግን ስምምነታችን በፍጥነትና በተቻለ መጠን ከውጭ የሚመጡ ትራንስፎርመሮች ቅድሚያ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች በተለይም ነዋሪዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በሚል ከፍተኛ ጥረትና ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ እየተደረገ ነው። ከዚህ የተነሳ በየቀኑ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመሆናቸው መናገር ይቻላል። ይህንን በአካልም ጭምር ተገኝተን እያረጋገጥን ስለሆነ በዚህ መንገድ እየፈታን የምንሔድ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የጋራ መኖሪያ ቤቶች ችግር መንገድና መብራት ብቻ ሳይሆን የውሃም ጭምር ነው፤ ይህ መፍትሔ የሚያገኘው መቼ ነው?
አቶ ሽመልስ፡– ከውሃ አንጻር ብዙ ችግር አለ ብዬ አልወስድም። ምክንያቱም በጣም ብዙ ችግር ካለ እንኳ በአካባቢያቸው ውሃ እንዲኖር ታስቦ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋልና ነው። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ቀርቦ ፓምፕ ባለመገጠሙ ምክንያት ብቻ የማይወጣበት ሁኔታ አለ። ለእነዚህ በከፍተኛ ርብርብ ፓምፕ የማቅረብ ሥራ እየሠራን ነው። እንደሚታወቀው ፓምፕም ኢምፖርት የሚደረግ እንደመሆኑ ችግሩ እንዳለ የሚታወቅ ነው። ከዚህም የተነሳ በጨረታው እና በመሰል ነገሮች ብዙ መደነቃቀፎች አሉ። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት ውሳኔ ተወስኗል። በቀጥታም ግዥ ጭምር እንቅስቃሴ እየተካሔደ በአሁኑ ጊዜ አራብሳ ላይ አብዛኛው ፓምፕ እየገባ ነው።
ጥቂት አቅራቢዎቹ አካባቢ የሚቀሩ ነገሮች አሉ፤ እሱን በማሻሻል ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለመሔድ ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው። ምክንያቱም በተለይ ጂ-7 ላይ ውሃው አይወጣምና ነው። ከዚህ የተነሳ አንዳንድ ቦታ ላይ ውሃ ቀርቦ ወደውጪ የማይወጣባቸው ሁኔታዎች ስላሉ እሱን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው። በአቅርቦት ደረጃ ግን ብዙ ችግር የለም። ቢያንስ የጋራ ውሃ እንዲኖራቸው ይደረጋል።
ሌላው የፍሳሽ ሁኔታ ሲሆን፤ ከዚያ ጋር የተያያዘ በጣም ከፍተኛ ተቃውሞ የነበረበት እሱ ነው። ከእሱ ጋር ተያይዞ ለምሳሌ በጣም ሰፊ እና በርከት ያሉ ቤቶች ያሉት አራብሳ ነው። ሳይቶቹም የተለያዩ ሲሆኑ፤ አራብሳ ሦስት፣ አራብሳ ስድስት እንዲሁም አራብሳ ሃምሳ አምስት በመባልም ይታወቃሉ። ከዚህ የተነሳ በጣም ሰፊ ነው። አብዛኛው በአሁኑ ጊዜ እየተነሳ ያለው የልማት ተነሺ ዕጣ ደርሶት አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል እየገባ ያለው ወደዚያ ነው። መንገድም ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ያለነው ወደዚያ ነው፡፡
ከዚህ በመነሳት ፍሳሽ ላይ ያደረግነው ነገር ቢኖር በመጀመሪያ ጊዜያዊ መፍትሔ እንስጥ የሚል ነው። ጊዜያዊ ሴፍቲ ታንክ በመቆፈር ነው፤ ይህ በእርግጥ በጣም ውድ ነው። ነገር ግን በመጀመሪያ ሰው አገልግሎት ማግኘት ስላለበት በሴፍቲ ታንክ እንዲገለገል ለማድረግ ተሞክሯል። አሁን ግን እንደሚታወቀው በቦሌ አራብሳ ሳይት ላይ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ለማቅረብ የተሠራው ‘ትሪትመንት ፕላንት’ ትልቅ ፕሮጀክት ነው። እሱ ስለተጠናቀቀ አራብሳ ላይ ያለው አጠቃላይ የፍሳሽ ችግር ይፈታል። የቀሩት የዝርጋታና መሰል ጉዳዮች ናቸው፤ ከእነርሱ ጎን ለጎን እየተሠሩ ነው። ስለሆነም በዚህ መንገድ ለመፍታት ጥረት እያደረግን እንገኛለን። ስለዚህም ዋናው ጉዳይ የመሠረተ ልማት ችግሩ አለ ወይ? ለተባለው አዎ አለ፤ ነገር ግን ተቀናጅቶ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ግን አዎንታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡- ነዋሪዎች አሁንም ድረስ አንድ ጀሪካን ውሃ እስከ 70 ብር ድረስ በመግዛት እየተጠቀሙ ነው፤ ከዚህ የተነሳ ለመጸዳጃ ቤትም ፈተና ነው፤ ይህ ችግር የሚያቆመው መቼ ነው? ከመብራት ጋር ተያይዞም ችግሩ የሚፈታው መቼ ነው? ይህ ነው የተባለ የጊዜ ገደብ ሊቀመጥለት አይችልም?
አቶ ሽመልስ፡- የውሃውን ነገር እኔ እስካለኝ መረጃ ድረስ በአብዛኛው ቦታ ላይ ተጠናቋል፤ ከንጹህ መጠጥ ውሃ አኳያም በጣም በከፍተኛ ፍጥነት የተሠራ እና የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ተቋምም ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ ነው። ከዚህ የተነሳ ብዙ ችግር አለ ብዬ አልወስድም። እንዳልኩሽ ግን ከፓምፕ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከውሃ አኳያ ብዙ ችግር ይኖራል ብለን አናስብም፡፡…
አዲስ ዘመን፡- … በዚህ ዓመት መጠናቀቅ ይችላል?
አቶ ሽመልስ፡-…በአሁኑ ጊዜ ወደመጠናቀቁ ተቃርቧል ብዬ አስባለሁ። የተወሰነ ቦታ የተንጠባጠበ ነገር ከመኖሩ በስተቀር በውሃ ላይ ብዙ ችግር አለ ብዬ አልወስድም። ምክንያቱም በውሃ ጉዳይ እየተደረገ ያለው ርብርብ ከፍተኛ ነው። እንዳልኩሽ ከቢሮክራሲያዊ አካሔድ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ካላነቀው በስተቀር ማለት ነው። ፓምፑን ወደየአካባቢዎቹ እያቀረብን ሲሆን፤ አሁንም የቀሩትን ፓምፖች በቅርብ ቀን እናስገባለን። ከዚህ የተነሳ ይህ ዓመት ሳይጠናቀቅ ከወዲህ ችግሩ ሊፈታ ይችላል። በቀጣዮቹ ወራት አጠናቅቀን እናስገባለን የሚል እምነት አለ። የቢሮክራሲው ሒደት ስለሚይዘን እንጂ በአንድም በሁለትም ቀን የሚቻል ጉዳይ ነው። ዋናው ነገር ፓምፑ እዚህ ሀገር ውስጥ ስለመኖሩና ትክክለኛው ፓምፕ ስለመሆኑ ከማጣራት ውጪ በጊዜው እንዲጠናቀቅ ይደረጋል፤ ካልሆነም ደግሞ በቀጥታ ግዥ የሚከናወን በመሆኑ በተቻለ መጠን ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ተቀናጅተን እየሠራን እንገኛለን፡፡
መብራቱም ቢሆን ዋናው የትራንስፎርመር ጉዳይ ነው። ትራንስፎርመር ወደሀገር ውስጥ ሲገባ መብራት ኃይል ቅድሚያ እየሰጠ ያለው ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ነው። ይህ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ያስቀመጠው አቅጣጫም ነው። ምክንያቱም ነዋሪው እየኖረ ያለበት አካባቢ ቅድሚያ መሰጠት አለበት በሚል ከፌዴራል ጀምሮ በቅንጅት እየተሠራበት ነው። ነገር ግን ትራንስፎርመሩ በመጀመሪያ መቅረብ ስላለበት አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚጎድሉ አሉ። ነገር ግን በተሠራው ሥራ አብዛኛው ቦታ ትራንስፎርመር ለማቅረብ ተሞክሯል። ይህ የሚበረታታ ነው፤ በዚህ አጋጣሚ ተቋሙን በዚህ ማመስገን እንፈልጋለን። የሚቀሩ ግን አሉ።
አዲስ ዘመን፡- የጋራ መኖሪያ ቤቶች እስካሁን አሳንሰር ያልተገጠመላቸው አሉ፤ አቅም ያጡና ነፍሰ ጡሮችም ልጆቻቸውን ተሸክሞ ደረጃውን ለሚወጣ ግለሰብ በመክፈል ላይ እንዳሉ ይነገራል። ከዚህ በተጨማሪም አሳንሰሩ ባለመገጠሙ ምክንያት ለአደጋም ጭምር ስጋት በመሆኑ ነዋሪው በቆርቆሮ እስከመዝጋት ደርሷልና በቅርቡ መፍትሔ ይኖረው ይሆን?
አቶ ሽመልስ፡– የሊፍት አቅራቢዎች ባለፉት ዓመታት በጨረታ አሸንፈው ወደ ሥራ ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው። እኛ በደረስንበት ጊዜ በተለያዩ ሎቶች ወደ አራትና አምስት የሚሆኑ አቅራቢዎች ነበሩ። እነዚህ አቅራቢዎች በኋላ ላይ ከኤልሲ እና ከሌላም ጉዳይ ጋር ተያይዞ በርካታ ነገሮችን ያነሱ ነበር።
ችግሮቹን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። አስተዳደሩም በጣም ትልልቅ ውሳኔዎችንም ወስኖ ጭምር ሊፍቶቹ ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ጥረት አድርጓል። አቅራቢዎቹ ዘንድ ከኤልሲ አከፋፈት፣ በኋላ ላይ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የዋጋ መዋዠቅ አንጻር ራሳቸው የጠየቁት ጥያቄ አለ፤ እነዚህ እነዚህን ሁሉ ለመፍታት ጥረት ለማድረግ ሞክረናል።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ 338 ሊፍቶች ለ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቀርቧል። የቀረው መግጠም ብቻ ነው። ለ20/80 የተወሰኑ ቦታዎች ቀርቧል። ነገር ግን ገና የሚቀሩና ወደብ ላይ የደረሱ አሉ፤ ይህን ታሳቢ በማድረግ አንዳንዶቹን አቅራቢዎች አይተን ውላቸው እንዲያበቃ ያደረግንበት ሁኔታ አለ። የሚያቀርቡት መረጃ በሚቀርብ ጊዜ የሚገባ እና አጠቃላይ ሒደቱን ተከትሎ ሕጋዊ ርምጃ የወሰድንባቸው አሉ። ሌላ ተጨማሪ ጨረታ የወጣባቸው ሁኔታዎችም አሉ፡፡
ከዋጋ መዋዠቅና ከመሰል ችግሮች ጋር ተያይዞ የሚገጥሙን ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል። ይህ ደግሞ በበጀቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ያሳድራል። የጋራ መኖሪያ ቤቶች የተገነቡበትና የሚተላለፉበት መንገድ የሚታወቅ ነው። ስለዚህ ሸክሙን የተሸከመው የከተማ አስተዳደሩ ነው። እንዲያም ሆኖ ችግሩ መፈታት አለበት የሚል አቋም ግን አለ። አሁን በሒደት እየፈታን እንሔዳለን። በ20/80ም አሁን ያቀረቡት እንዲገጥሙ፤ ወደብ ላይ ያለውም ቶሎ መጥቶ ችግሩ እንዲፈታ የማድረግ ክትትል እያደረግንበት ነው። ያላቀረቡት ደግሞ ተጨማሪ ጨረታ ወጥቶ ቶሎ የሚገባበት ሁኔታ ይፈጠራል። የ40/60 ግን እንደገለጽኩት ሲሆን፤ በሻሌ ላይ ያለውን ግን እንዲያቆም ስላደረግን እሱን የመተካት ሥራ ይሠራል እንጂ ችግሩ እንዳለ ግን እናውቃለን።
አዲስ ዘመን፡- ከዛሬ ስድስት ወራት በፊትም ጨረታ ወጥቶ ግዥ በመፈጸም ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ነው የሚል ምላሽ ተሰጥቶበት እንደነበር ይታወቃልና ከዚህስ በኋላ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? ቁርጥ ያለ ጊዜ ቢገለጽ?
አቶ ሽመልስ፡- የራሳቸው የጊዜ ሰሌዳ ከግዥ ኤጀንሲ አገልግሎት ጋር የገቡት ውል አላቸው። በዚያን ጊዜ ማቅረብ አለባቸው። ካላቀረቡ ደግሞ ሕጋዊ ርምጃ ይወሰድባቸዋል። ዋናው ነገር ግን በመንግሥት አጠቃላይ ወጪ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ የሚገኝ ስለሆነ ጥረት እያደረግን ያለነው በጥንቃቄ ለመሄድ ነው። በፊት የገባበት ዋጋ አለ፤ የተወሰነ ደግሞ ለማሻሻል ተሞክሯል። እቃው ታዝዞ በስማችን እስከመጣ ድረስ እሱ ገብቶ የሚገጠምበትን ሁኔታ መፍጠር ነው።
እንደተባለው ሕጋዊ አሠራሩ ተጠብቆ የማያቀርቡ ከሆነ እነርሱም ይቀጣሉ፤ ጉዳዩ እንዲቆም ይደረግና ተጨማሪ ጨረታ ይወጣል። ተጨማሪ ጨረታ ሲወጣ ደግሞ ከዚህ ከፍ ያለ ጭማሪ ያለው ዋጋ ሊወጣ ይችላል። በእሱ በኩል ለመሔድ እየሞከርን ያለነው በጥንቃቄ ለመሄድ ነው። ምክንያቱም እንደሚታወቀው ነዋሪው ላይ የምንጨምረው ዋጋ አይኖርም።
አሁን 40/60 ላይ እየተገጠሙ ያሉት በዚህ ዓመት ይጠናቀቃሉ። 20/80 ላይም እየተገጠሙ ያሉ አሉ። አሁን ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ያሉ ሊፍቶች በምንፈልገው ፍጥነት ከገቡ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ አብዛኞቹ ይጠናቀቃሉ ብለን እናስባለን።
የሚያሳስበው ከዚህ በኋላ የሚወጡ ጨረታዎች መኖራቸው ነው። በዚህ በኩል እነርሱን ተጫራቹን አግኝቶ በፍጥነት ወደዚያ ማስገባት ነው። ከዚህ ጎን ለጎን በፍጥነት እንዴት ማከናወን እንደምንችል የሚያስችሉ ሌሎች አማራጮች እያየን ነው። ይህ የጨረታ ሒደቱ ረዥም ርቀት ሔዶ፤ ከዚያ በኋላ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉ ረዥም ወራት የሚወስድ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ብዙ አቅራቢዎች ራሳቸው መጥተው እየጠየቁን ይገኛሉ። እነዚህን የፋይናንስ አሠራሩን ጠብቆ ጋብዞ በተለይ ሀገር ውስጥ የገቡ ሊፍቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሁኔታ ቢፈጠር ጥሩ ነው፤ እንዲህ ሲባል ሀገር ውስጥ አስገብቻለሁ የሚል የሊፍት አቅራቢ እድል የሚሰጥበት ሁኔታ ለመፍጠር አንዳንድ ሥራዎችን እየሠራን ነው። ለሚመለከተው አካል አቅርበን ካስወሰንን በኋላ ለማፍጠን ጥረት እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- የልማት ተነሺዎችን በተመለከተ በተለይ ከቀበሌ ቤት የተነሱ ወደተዘጋጀላቸው ቦታ ሲሄዱ አንደኛ እና ሁለተኛ ወለል ላይ ለመሆን ሲሉ ክፍያ የሚፈጽሙ አሉ ይባላል፤ በእናንተ በኩል የልማት ተነሺዎቹ ወደተዘጋጀላቸው ቦታ ሲሄዱ የሚያረካክቡ ባለሙያዎች ወይም ፈጻሚ አካላትን የምትቆጣጠሩበት ሥርዓት ምን ይመስላል? ገንዘቤን ተበላሁ የሚሉ ቅሬታዎች እናንተ ዘንድስ ይመጣሉ?
አቶ ሽመልስ፡– በጣም የሚገርመው ከልማት ተነሺዎች ጋር በተያያዘ እንዲህ አይነት ነገር ዛሬ መስማቴ ነው። በጣም በርካታ የልማት ተነሺዎችን አስተናግደናል። አጠቃላይ በኮሪደር ልማቱ የልማት ተነሺዎችንና ኪራይ ቤቶችን ጨምሮ ወደ 11 ሺ አባወራ አስተናግደናል። አጠቃላይ የኪራይ ቤቶችን ጨምሮ ወደ 11 ሺ አባወራ አስተናግደናል። ይህ በመጀመሪያው የኮሪደር ልማትና በሁለተኛው የኮሪደር ልማት በጣም በርካታ ሰው ወደ ምትክ ቤት እንዲገባ ተደርጓል።
ሒደቱ አሠራርን የተከተለ ነው። በተለይ ወደእኛ ከመጣ በኋላ ከወረዳና ከክፍለ ከተማ የቤተሰቡ ብዛት ታውቆ ምን ያህል ቤት እንደሚያስፈልግ ከተወሰነ በኋላ በተመሳሳይ መልኩ አድልዎ ሳይደረግ የተሠራ ሥራ ነው።
ለልማት ተነሺ ቤት የሚሰጥበት የራሱ መመሪያ አለው። ግን ደግሞ እንደነበራቸው የቤት አይነት ይሆናል። በዚያ መንገድ በሚዛናዊነት ለማስተናገድ ጥረት አድርገናል። የኮሪደር ልማት ተነሺዎችም የተሰጣቸው በዕጣ ነው። ምክንያቱም የቤት አይነትም፣ ሳይትም ሆነ ወለል የሚሰጣቸው በዕጣ ነው። ዕጣውን ያወጣው ግለሰብ ስድስተኛ አሊያም ሰባተኛ ወይም አንደኛ ወለል ላይ ሊደርሰው ይችላል። ስለዚህ ያስተናገድነው በደረሰው ዕጣ አማካይነት ነው።
ዕጣ ካወጡ በኋላ ቅሬታ ያቀርባሉ። ትልቁ ፈተና እንዲያውም እሱ ነው። ቅሬታ የሚያቀርቡበትን ሥርዓት ዘርግተን ቅሬታው ሲቀርብ መጨረሻ ላይ የሚወስነው አመራሩ ነው። በዚህ መንገድ ብዙ ሰዎች ተስተናግደዋል። በዚህ መንገድ ቅሬታ አቅርበው የተስተናገዱ አካላት የስም ዝርዝራቸውን ማየት ይቻላል። ቅሬታቸው ስለተፈታ እጅግ በጣም ደስተኞች እንደሆኑም ገልጸዋል።
ካልተቸገርን በስተቀር በብዛት የተጠየቅነውን ለመመለስ ጥረት እናደርጋለን። ለምሳሌ ጎሮ ስላሴ የደረሰው ግለሰብ “እኔ የሚጦረኝ ሰው አራብሳ ስላለ እዚያ ይሻለኛል” ካለ አራብሳ እንቀይረዋለን። ይህን ማረጋገጥ ይቻላል። ከቤት አይነቱ ጋር ተያይዞ በሚያቀርበው ጥያቄ ላይ ተመስርተን እና መነሻውን አጣርተን ለጥያቄው ምላሽ እንሰጣለን።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንዳሉት በዚህ ረገድ ኮርፖሬሽኑ ዘንድ ችግር ባይኖርም፤ ነገር ግን ጉዳዩን በሚፈጽሙ ባለሙያዎች ዘንድ አይኖርም ብለው ያስባሉ?
አቶ ሽመልስ፡- ፈጻሚውም ቢሆን እንደዚያ የሚያደርግበት እድል የለውም፤ ምክንያቱም ውል ስላለ የሚስተናገደው በዚያ ውል አማካይነት ነው። ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ የለም ማለት አይደለም። እየተንጠባጠበ የሚመጣ ጉዳይ አለ፤ ‹‹ በደላላ እንዲህ እና እንዲያ ሆንኩ›› የሚል አለ። ይሁንና ባገኘነው አጋጣሚ ግን ይጠየቁበታል፤ የተጠየቁም የተከሰሱም እንዲሁም የታሰሩም ሰዎች አሉ። ብዙ ጊዜም ለማስጠንቀቅ ሞክረናል። የተጠየቁና የተከሰሱም ስላሉ ሌሎቹ ከዚያ እንዲማሩ አድርገናል፡፡
እንዳልኩት በተቻለ መጠን ቅሬታቸውን ለመፍታት እንጥራለን፤ የማይፈታ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ የማይፈታበት ምክንያት አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ተብሎ ለግለሰቡ ይነገረዋል። ለመሄድ የተሞከረው በዚህ መንገድ ነው። ስለዚህ ችግር እንዳይፈጠር በጥንቃቄ ስለሄድንበት ቅሬታ የፈታንበትንም መንገድ ሰፋ በማድረግ ያከናወንነው ስለሆነ መፍትሔ ለመስጠት ችለናል። አንድ መጥቀስ የምፈልገው ነገር፤ ቤት የደረሰው ሁሉ ቅሬታ አቅርቧል ማለት ያስደፍራል። ለሁሉም እንደየሁኔታው ምላሽ ሊሰጥ ተሞክሯል። ከውጭ ግን በድለላ እንዲህ እና እንዲያ እናደርጋለን የሚሉ አሉ። ማኅበረሰቡ ግን በዚህ ደረጃ መታለል የለበትም። የማኅበረሰቡ መረጃ ውሉ ናት። የእሱ ውል ባለአንድ ቤት ሆኖ ወደሳይት ሲሔድ ባለሁለት መኝታ ከገባ፣ ነገ ይወጣል፤ ምክንያቱም የእሱን ቤት አልያዘምና።
አዲስ ዘመን፡- የ2005 ዓ.ም የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች ዕጣ ፈንታቸው ምንድን ነው? ተብሎ በተደጋጋሚ ተጠይቋል፤ ይሁንና ቁርጥ ያለ ምላሽ ባይኖርም እስካሁን ብዙዎቹ በተስፋ እየቆጠቡ ነው፤ በዚህ ጉዳይ የሚሉት ምንድን ነው?
አቶ ሽመልስ፡– ጥሩ ጥያቄ ነው፤ የአዲስ አበባ ቤት አቅርቦትን በተመለከተ በጣም ሰፊ ሥራ መሠራት አለበት። ካሉን የልማት እቅዶች ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል በሚል የከተማ አስተዳደሩ ጠንካራ አቋም ይዟል። ምክንያቱም እንደተባለው ከነባር ተመዝጋቢዎች የሚቆጥቡ አሁንም ያልደረሳቸው አሉ፤ እስካሁን ተስፋ ባለመቁረጥ ቆጥበዋል። ከእነርሱ በተጨማሪ ደግሞ አዳዲስ ፍላጎቶች አሉ።
ስለዚህ ይህን የሚመጥን የቤት አቅርቦት ሊኖር ይገባል የሚል ፍላጎትና አቋም አለ። ይህን ታሳቢ አድርጎ በነባሩ አካሔድ መሔድ በመንግሥት አስተባባሪነት ብቻ ቤት በማቅረብ ችግሩን መፍታት አይቻልም። በተቻለ መጠን ሁሉንም አማራጮች መጠቀምና የግል አልሚውንም ማበረታታት ያስፈልጋል። በተመሳሳይ ሌሎች አማራጮችንም አጥንተን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል። የመንግሥትና የግል አጋርነት በሚባለው 70/30 አካሄድ ተግባራዊ ለማድረግ አብዛኛው ባለሀብት በሚባለው ደረጃ ፍላጎት አሳይቶ በአሁኑ ጊዜ ወደተግባር እየተገባ ነው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ በጣም በተሻለ ፍላጎት መስፈርቱን ያሟሉና አቅም ያላቸው ሁሉ ወደተግባር ለማስገባት እየሞከርን ነው። አልሚዎች ወደ ሥራ ገብተዋል፤ ወደ 120 ሺ የሚሆኑ ቤቶች የተጀመሩበት ሒደት አለ፤ 120 አልሚዎች አካባቢ ወደሥራ የገቡበት አካሔድ አለ። ይህ በተቻለ መጠን የቤት አቅርቦቱ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ብለን እናምናለን። ይህ ሥራ የተለያየ ቦታ ሲሆን ለምሳሌ ለገሃር፣ ተክለሃይማኖት፣ ገላን ጉራ፣ ደግሞ ኦቪድ የሚገነባው አለ። እስካሁን ያሉ ጅምሮች ጥሩ ናቸው።
ይህ አሠራር እየጨመረ ሲሆን፤ በቅርብ ጊዜ ተዋውለን ወደተግባር ያስገባናቸውን አልደመርንም። ስለዚህ ይህ ችግሩን በሁለት መንገድ ይቀርፋል ብለን እናስባለን። አንደኛው 30 በመቶ ድርሻ የመንግሥት አለ። በቀጣይ በሚያወጣው አሠራር መሠረት ይተላለፋል። ሁለተኛው ደግሞ 70 በመቶው አልሚው እንዲሁ በቤት አቅርቦቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ይሆናል። የቤት አቅርቦቱ በሰፋ መጠን የቤት ዋጋ እየቀነሰ ማኅበረሰቡም በሚመጥነው መንገድ ቤት እያገኘ እንዲሔድ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል። አንዳንድ ለተመዝጋቢው እድል የምንሰጣቸው ርቀቶች አሉ። እነሱ በቀጣይ የሚገለጹ ይሆናሉ። ይህ ማለት ለተመዝጋቢው ቅድሚያ ሰጥቶ ለመሄድ የሚደረግ ጥረት አለ።
ሌላው የማኅበር ቤት ነው። እንደሚታወቀው በመጀመሪያ ቅድሚያ የተሰጠው ለቆጣቢው ነው። በዚህ መልክ ወደ 54 የሚሆኑ ማኅበራት ተደራጅተው ቦታ ተረክበዋል። በአሁኑ ጊዜ ወደ ሥራ እየገቡ ነው። በእርግጥ የተለያዩ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያያዥ ችግሮች ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ በመፈታታቸው ወደሥራ በመግባት ላይ ናቸው። ከሦስት ሺ 500 በላይ ሰው የያዘ በመሆኑ ቀላል የሚባል አይደለም።
በሌሎች ሞዳሊቲዎች እንዲሁ ቅድሚያ ለመስጠት ጥረት እያደረግን ነው። ዋናው ነገር ቀደም ሲል ኮርፖሬሽኑ ቤት ይገነባ የነበረው ከባንክ በሚያገኘው ብድር ነው። በርካታ እዳ የነበረበት ሲሆን፤ ከለውጡ ወዲህ ግን ብዙ ዕዳ ለማቃለል ተሞክሯል፤ ዕዳው አሁንም አለ። ይህ ስለሆነ ብድር በፈለግነው መንገድ ለማግኘት እየተቸገርን ነው። ስለዚህ ሞዳሊቲዎቹን እያሰፋ የቤት አቅርቦቱ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል።
ሌላው የኪራይ ቤት አቅርቦትም ነው። ከተማ አስተዳደሩ በራሱ ካፒታል ፕሮጀክት መድቦ የሚያሠራቸው የራሱ ኪራይ ቤቶች አሉ። እነዚህም ዝቅተኛ ገቢ ላለው ማኅበረሰብ መፍትሔ እየሰጡ ነው። የተለያየ ቦታ ገንብተን ያስተላለፍናቸው ቤቶች አሉ። አሁንም በመገንባት ላይ ያሉ አሉ፡፡
ሌላኛው የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች የሚሳተፉበት የበጎ አድራጎት ቤት አቅርቦት አለ። በጎ ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች እና መንግሥት በጋራ ሆነው ሠርተው ከመንግሥት ካዝና ብዙ ገንዘብ ሳይወጣ፤ ነገር ግን አንዳንድ አስተዋጽኦ አድርገው በጋራ ሆነው የተሠሩ ቤቶችን በጣም የደሃ ድሃ ለሚባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የምናስረክባቸው ቤቶች አሉ። ይህ መርሃ ግብር እየቀጠለ ነው። ስለዚህ አቅርቦቱ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ካልሆነ በስተቀር ነባሩ ሞዳሊቲ ላይ ብቻ ተጣብቀን ከቀረን አንችለውም። አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር የግንባታ ወጪው የሚታወቅ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የ120 ሺ ቤት ግንባታ በ70/30 ውስጥ የሚሔድ ነው፤ ተመዝጋቢ ቤት ፈላጊዎች ደግሞ እየጠበቁ ያለው በ40/60/ እና 20/80 አካሔድ ነው፤ ለምሳሌ የ20/80 ቤት ፈላጊዎች 70/30 ላይ የአቅማቸው ሁኔታ ሊፈትናቸው ይችላልና መላው ምንድን ነው?
አቶ ሽመልስ፡- አሁን የ40/60 እና የ20/80 ቤት አቅርቦትን በተመለከተ አስቀድሜ እንደገለጽኩልሽ ከፋይናንስ አቅርቦቱ አንጻር ብዙ እየሔድንበት አይደለም። እንዲህ ሲባል ተዘግቷል ማለት አይደለም። ጎን ለጎን ግን አማራጮችን ማቅረብ መቻል አለብን። በተቻለ መጠን የ70/30 መርሃ ግብርም ቢሆን ለምሳሌ ከ70 በመቶ ድርሻ ባለሀብቱ ለተመዝጋቢዎች ቅድሚያ መስጠት የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት የሚደረግበት አግባብ አለ። ነገር ግን ዋጋው ሚዛናዊ እንዲሆን ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ በተቻለ መጠን እየተነጋገርንበት እንሔድበታለን።
በዚያ መንገድ አንዳንድ ቦታ ብዙዎቹ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት እየተፈጠረ ነው። በቀጣይ ይፋ የምናደርጋቸው አንዳንድ መርሃ ግብሮች አሉ። በመርሃ ግብሮች ላይ በተለይ 70/30 መርሃ ግብሩ ላይ ከ70 በመቶ ስንት በመቶ ድርሻ ለሚለው ነገር ግን መንግሥት ደግሞ አስታራቂ ሃሳብ እያቀረበ ለተመዝጋቢው ማለትም የቤት ቆጣቢውን ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ እየተዘጋጀ ያለ መርሃ ግብር አለ። ይህ ማለት ቅድሚያ ለተጠቃሚ ተሰጥቶ የሚጠቀምበት መንገድ ማለት ነው። በቀጣይ ይፋ አድርገናቸው ቆጣቢውን የምናወያይበት ሥርዓት እየጠበቅን ሲሆን፤ በቅርቡ ተግባራዊ እናደርጋለን ብለን እናስባለን። በጥቅሉ ግን የተሻለ የሚሆነው አማራጮቹን ማቅረቡ ነው።
በመጨረሻም ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት፤ የጋራ መኖሪያ ቤት በዕጣ ደርሶትም ሆነ በልማት ተነሺ ሆኖ ቤቱ የገባ በመሠረተ ልማት አቅርቦትና አንዳንድ ባልተጠናቀቁ ጉዳዮች ላይ እጅግ በጣም ታግሶናል። በዚህ በጣም ለማመስገን እንፈልጋለን። በጋራ በመሆን አንዳንድ ጉዳዮችን እየፈታን እንሔዳለን፡፡
ሌላው ኮርፖሬሽኑ በሚፈልገው መጠን እንዳይንቀሳቀስ አስሮ የያዘው ፋይናንስ ነው። በአሁኑ ወቅት ቤት የመሥራትም ሆነ በአጭር ጊዜ የመገንባት ልምዱ ዳብሯል፤ በየጊዜው በሚደረገው እንቅስቃሴ አቅም ያላቸውን ተቋማት መፍጠር ችለናል። ከስር እየመጡ ያሉ ማኅበራት ጭምር ብቃት እያሳዩ ነው። ችግሩና ተግዳሮቱ ግን ፋይናንስ ነው። ይሁንና ይህ ችግር ዘላቂ ላይሆን ይችላል። በተለያየ መንገድ የተለያዩ አማራጮችን እያሰብን ነው። ስለዚህ ታግሰው እየቆጠቡ ያሉ የከተማችን ነዋሪዎች በሚፈጠሩ አማራጮች የሚመጥናቸውን እያዩ እንዲገቡበት፤ በቀጣይ ደግሞ ችግሮች እየተፈቱ ሲሄዱ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚፈጠር በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እወዳለሁ። እስካሁን ለነበራቸው ትዕግስትም በመንግሥት ስም በከተማ አስተዳደሩና በኮርፖሬሽኑ ስም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ ላመሰግንዎ እወዳለሁ፡፡
አቶ ሽመልስ፡- አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም