‹‹ማዕከሉን ለችግኝ መትከያ የመረጥነው በግቢው በዘለቄታ ህይወታቸውን የሚመሩ አረጋውያን የሚኖሩበትና በተለያየ ጊዜ ገብተው አገግመው የሚወጡ ጎዳና ተዳዳሪዎች ያሉበት ማዕከል ስለሆነ ነው›› የሚሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛ ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ትናንት በቃሊቲ አረጋውያን ክብካቤ ማዕከል ችግኞችን ተክለዋል፡፡
ከአረጋውያን ማኅበር ከአካል ጉዳተኞች እና የእድር ማኅበራት ሥራና ሠራተኛ ኤጀንሲ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ችግኞቹን የተከሉት ወይዘሮ አለምፀሐይ፣ ማዕከሉ ለችግኝ መትከያ የተመረጠው ለአረጋውያን እና ለጎዳና ተዳዳሪዎች ቀጣይነት ያለው ክብካቤ የሚደረግበት ስፍራ ስለሆነ እና ሁልጊዜ ስለምንጎበኘውም ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
ችግኞቹ እንደሚፀድቁና ለቁም ነገር እንደሚበቁ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ተናግረው፣ከተተከሉት ችግኞች አብዛኞቹ ማንጎ፣ አቦካዶ፣ ፓፓያ፣ አፕልና የመሳሰሉ የፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡ ፡ችግኞቹ ሲደርሱ በማዕከሉ የሚገኙ ዜጎችን ጤና ለመጠበቅ፣ የአየር ብክለትን ለመከላከልና ለምግብነት እንደሚያገለግሉ ያብራራሉ፡፡
አረጋውያኑ በችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ቁፋሮና ተከላ መሳተፋቸውን ጠቅሰው፣ “ዜጋው አረጋውያንን እየተንከባከበ አረጋውያን ደግሞ ችግኞቹን ለመንከባከብ መዘጋጀታቸውንም ይናገራሉ።
‹‹አንድ ጊዜ ተክሎ ዞር ማለት ሳይሆን ሁሉም ድርጅቶች ከተማችንን አረንጓዴ ለማድረግ በሚደረገው ዘመቻ በመሳተፍ ችግኞችን በመንከባከብ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል። ቀደም ሲልም ቢሮው በሚያስተዳድራቸው አራት ተቋማት 1ሺ ችግኞች ተክሏል››ያሉት ወ̸ሮ ዓለምፀሐይ፣”ተክለን አናቆምም፤ መንከባከቡም ይቀጥላል” ሲሉም አስታውቀዋል።
ከልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 እድሮች ምክር ቤት አቶ ነስሩ በማዕከሉ ችግኞችን ተክለዋል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊትም 14 ሺ የዛፍ ችግኝ በጉራጌ ልማት ማኅበር ተሰባስበው ወደ ጉራጌ ዞን ሄደው መትከላቸውንም ይጠቅሳሉ።
መንግሥት ባደረገው ጥሪና ታሪካዊ በሆነ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ተሳታፊ መሆናቸው እርካታ እንደሚሰማቸው ተናግረው፣የችግኝ ተከላው ለመጪው ትውልድ ቅርስ መሆኑንም ያመለክታሉ።
የቀድሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በፍቃዱ ቶላ እንዳሉት፤ እሳቸው በሚሠሩበት ድርጅት ኢትዮ የግል ጥበቃና ሴኩሪቲ አገልግሎት በኩል ለማዕከሉ 1ሺ 400 ብር በማውጣት ለችግኝ ተከላው አስተዋጽኦ ተደርጓል፡፡ 1ሺ600 አባሎቻቸው ችግኝ መትክላቸውንና ይህም ለትውልድ አንድ አስተዋጽኦ የተበረከተ መሆኑን ይገልፃሉ።
ረዱ ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የኦፕሬሽን ኃላፊ ዋና ሳጅን ካሳሁን ሶሪ ትናንት ችግኝ በመትከል አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ጠቅሰው፣ በሴኩሪቲ ኩባንያቸው በኩል ለማዕከሉ 1ሺ 400 ችግኞች መበርከታቸውን ያብራራሉ።
ከአዋጭ የብድርና ቁጠባ ማኅበር የተወከሉት ወይዘሮ ይታይሽ ታምሬ ‹‹ልጆቻችን ጤናማ አየር እንዲያገኙ ለማድረግ ችግኝ መትከል ያስፈልጋል›› ብለው በማዕከሉ ግቢ የፍራፍሬ ጽድና የዘንባባ ችግኞችን መትከላቸውን ተናግረዋል።
የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ሸለማ በበኩላቸው ‹‹በችግኝ ተከላው የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት በራሳችን ፍላጎት ደስ ብሎን ተገኝተናል። ችግኝ የተከልነው በህይወት ጉዳይ ነው።››ይላሉ፡፡ ‹‹ወደ 20 ሺ ብር አውጥተን ለችግኝ ተከላው ድጋፍ አድርገናል›› የሚሉት አቶ ዘሪሁን የተከሉትን ችግኝ በመንከባከብ ለቁም ነገር ለማብቃት እንደሚሠሩ ይናገራሉ፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ፍቃዱ ከበደ ለሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ በተደረገልን ጥሪ መሠረት በአቅማችን ችግኝ ተክለናል ይላሉ። አካል ጉዳተኞች ባላቸው አቅም አሻራቸውን እንዲያስቀምጡ መደረጉን ይጠቁማሉ፡፡”ችግኝ ልክ እንደ ህፃናት እንክብካቤ ይፈልጋል፤እዛው ተክለን መሄድ የለብንም” ሲሉም ተናግረዋል።
የቃሊቲ አረጋውያን ክብካቤ ተቋም ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ከበደ እንደሚሉት፤የግቢው አጠቃላይ ይዞታ ወደ 54 ሺ ካሬ ሜትር ነው። የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይና በዘርፉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትና የህዝብ ክንፎች በአጠቃላይ በተዘጋጀው ጉድጓድ ከ2 ሺ 600 በላይ ችግኞችን ተክለዋል።
ችግኞቹ በግቢው መተከላቸው ለመጽደቅና እንክብካቤ ለማግኘት ትልቅ ዋስትና መሆኑን ይናገራሉ፡፡አረጋውያኑ እንደ ጊዜ ማሳለፊያ በመቁጠር ችግኞቹን በየጊዜው ሊንከባከቡም እንደሚችሉ ያብራራሉ። ችግኞቹ መቶ በመቶ ይፀድቃሉ፤ለቁም ነገር ይበቃሉ ብለን እናስባለን የሚሉት ሃላፊው፣ቀደም ሲል የተተከሉትን አረጋውያኑ ተንከባክበው እንዳሳደጓቸው ይጠቅሳሉ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 23/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ