‹‹ለዘመናት በደምና በአጥንት ለተሳሰረው አብሮነታችንና አንድነታችን ከምንም በላይ ክብር ይኑረን›› ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወይም የአንድ ሌላ ታዋቂ ፖለቲከኛ ንግግር እንዳይመስላችሁ። በርግጥ ይህ አስደናቂ መልዕክት የተላለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠሩት ‹‹መቶ ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀምበር›› አገራዊ አረንጓዴ አሻራን የማሳረፍ ቀን ከተገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ችግኝ ተካዮች መካከል ከአንደኛው ነው።
ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው አረንጓዴ አሻራን የማሳረፍ ብሔራዊ የችግኝ ተከላ ቀን እኛም የራሳችንን አሻራ ለማሳረፍ በተመደብንበት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ስሙ ኃይሌ ጋርመንት በሚባል ቦታ ተገኝተናል። እኛ ችግኞችን የምንተክለው በብዕራችን አማካኝነት ሁነቱን ለብዙሐኑ በማዳረስ ነውና በሚያስቀና አንድነት በህብረት ሆነው ከሰማይ የሚወርደው ካፊያና የምድሩ ጭቃ ሳይበግራቸው በሰፊው ሜዳ ላይ ከወዲያና ወዲህ እየተሯሯጡ በትጋት ችግኞችን እየተከሉ የነበሩ ሰዎችን እየተዟዟርን ቃለ መጠይቅ እያደረግን አብረናቸው አረፈድን። ከረፋዱ አምስት ሰዓት ተኩል አካባቢ ግን አንድ ለየት ያለ ትዕይንት ዓይኔ ውስጥ ገባ።
ከዚያ ሁሉ ሰው መሐል መካከለኛ ቁመትና ደንደን ያለ ቁመና ያለው ጥቁር ቲሸርት የለበሰ አንድ ጎልማሳ ችግኝ ሲተክል ቆይቶ ቀና ሲል ትልቅ ባነር ደረቱ ላይ አንጠልጥሎ ተመለከትኩ። ይኼ ነገር ምን ይሆን? ከችግኝ ተከላው ጋርስ ምን አገናኘው? ብዬ ቀርቤ ሳይ ጎልማሳው ደረት ላይ የተንጠለጠለው ባነር ‹‹ለዘመናት በደምና በአጥንት ለተሳሰረው አብሮነታችንና አንድነታችን ከምንም በላይ ክብር ይኑረን›› የሚል ጽሑፍ በደማቁ ሰፍሮበታል። የበለጠ ትኩረቴን ስለሳበው አነጋገርኩት።
‹‹ሳሙኤል በቀለ እባላለሁ፤ እዚሁ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ሃና ጽዮን ክሊኒክ ነው ሰፈሬ››። ሲል የመጣበትን ቦታ ገለፀልኝ። በደረቱ ላይ ስላለው መልዕክት ጠየኩት። ‹‹ሁላችንም አረንጓዴ አሻራችንን በሀገራችን ላይ ለማሳረፍ በሀገር ደረጃ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን በተላለፈው መልዕክት ተነሳስቼ ችግኝ በመትከሌ በጣም ደስ ብሎኛል። ነገር ግን ይህ መልካም ሆኖ እያለ ሌላም የሚያሳስቡ ችግሮች አሉብን። በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ዘረኝነት፣ ብሔርተኝነት፣ መለያየት በጣም እየተስፋፋ መጥቷል። ይህም ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድም አሳሳቢ ችግር የሚሆን ይመስለኛል። እናም ችግኞችን እየተከልን አስጊውን የአየር ንብረት መዛባት ችግር ለመፍታት ጉዞ እንደጀመርነው ሁሉ ዘረኝነት፣ ብሔርተኝነት፣ ጎጠኝነት፣ መለያየትና መጠላላትን ልናስቀር ይገባል።›› ብሏል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 23/2011
ይበል ካሳ