
የሾላ ገበያ መግቢያው እንደ ወትሮው የበዓል ገበያ አይነት ስሜት ይታይበታል። ለትንሳኤ በዓል ጥቂት ቀናቶች ይቀራሉና ገበያው ሙሉም ቢሆን ሸማቹ ግን አነስተኛ ነው። ነጋዴዎቹም የበዓል ገበያ ነውና ለበዓሉ የሚሆነውን ሁሉ አቅርበው ሸማቹን ይጠባበቃሉ። ምን ሊገዛ እንደመጣ ባልተረዱበት ሁኔታም ግባ (ግቢ) እያሉ ይጣራሉ። በመደብራቸው የያዙትን እየጠቆሙም ገዢዎቻቸውን ለመማረክ ይሞክራሉ። የአንዳንዶቹ ሁኔታ ደግሞ ያስገርማል። አቀራረባቸው በልምምጥ ነው። አላፊ አግዳሚውም ቀልቡ ባረፈበትና ሊገዛ የሚፈልገውን ባየበት ጎራ ይላል። በዋጋም በአይነትም የሚመጥነውን ሲያገኝ ይሸምታል።
በአንዳንዶቹ ገበያ ሸማቹን ለመሳብ የሚጠቀሙበት አቀራረብ ለየት ያለ ነው። በሁኔታቸው ስቆ የሚያልፍ አልያም በጥሪያቸው ተስቦ የመጣበትን ዓላማ ስቶ ሌላ የሚሸምት አይጠፋም። እኛም ይህንን አስገራሚ ንግግር እየሰማንና እየሳቅን ወደ ገበያው መሀል ዘለቅን። አካባቢውን በተለያየ መዓዛ ያወደው ኑ ወደህ የሚለው የእጣን መንደር ደረስን። ግራ ቀኝ ተጉዘን የእጣኑ ዋና ድምቀት የሆነውን የቡና ገበያን ተቀላቀልን። ከዚያ አለፍ ብለን ቅቤ ተራ ገባን። በዓልም አይደል ይህ አይነቱ ሽታ የግድ እንደሆነ አምነንና በተለያየ ጣዕም ባለው ሽታ ታውደን ወደ ቀጣዩ የበዓል ገበያ አመራን። ቅቤውን ተከትሎ ያለው ቅመማቅመሙ ነውና ዓይናችን እርሱ ላይ አረፈ። አፍንጫችንም የቅመማቅመሙን መዓዛ ተረከበ። እግራችንም ተገታ።
ወይዘሮ የሺወርቅ አየለም ለበዓሉ ገበያ የሚሆን ቅመም ይዘው ቁጭ ያሉ እናት ናቸው። የበዓል ገበያው ምን እንደሚመስል ጠየቅናቸው። እንዲህ ሲሉ አጫወቱን።
‹‹የዘንድሮ ገበያ በብዙ መልኩ ቀዝቅዟል። ይህን ጊዜ የሾላ ገበያን በዚህ መልኩ አታገኘውም ነበር። ትርምሱ ጠጠር አያስጥልም። በተለይ ይህ ወቅት የሰርግ ጊዜ ስለሆነ የቅመማቅመም ሽያጩ ቀላል አይደለም። በዓል ካለፈ ለድግስ የሚሆን ቅመማቅመም የሚሸምት ሰው ብዙ ነበር። ይህን ወቅትም የዓመት ገቢያችንን የምንሰበስብበት ያህል እንደሆነ አምነን ነው ለገበያ የምንቀመጠው። ነገር ግን አሁን ደንበኞቻችን ብቻ ናቸው መጥተው የሚገዙቱ። አለፍ ካለ አንዳንድ ተላላፊ ሰው ሊጎበኝሽ ይችላል እንጂ ገበያው ቀንሷል።
ሰው የኑሮ ውድነት ይዞት ሊሆን ይችላል የሚገዛን በጣም ጥቂት ሰው ነው። የቅመማ ቅመም ዋጋ ከወትሮ በጣም ጨምሯል። ይሄም ሌላው ምክንያት ሊሆን ይችላል። ገበያው እንደከዚህ ቀደሙ የበዓል ገበያ አይመስልም። ምናልባት ወደትንሳኤ ቀኑ ጠጋ ሲል ዓርብ ቅዳሜ ገዢ በብዛት ይመጣ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።» ይላሉ፡፡
በቅመማቅመም ንግዱ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩትና ዋናው የገቢ ምንጫቸው እንደሆነ ያጫወቱን ወይዘሮ የሺወርቅ፤ በዚህ ሥራቸው ያለ አባት ስድስት ልጆችን አስተምረዋል። ለወግ ማዕረግም ያበቋቸው አሉ። አሁን ግን ገበያው እየተቀዛቀዘ በመሆኑ ቤተሰቡን ለመምራት የሚቸገሩበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ያስባሉ። በዘያው ልክም ተስፋ የማያደርጉት ጊዜ አለ። ይህም ከሰኞ እስከ ዓርብ ያለው የገበያ ወቅት ነው።
ወይዘሮ የሺወርቅ ከቅመሙ ሽያጭ ባለፈ ለበዓል ወቅት የሚሆኑ ጭሳጭሶችንም ያቀርባሉ። በባሕላዊ ስፌት የተሰሩ ክዳኖችን ከእነ ምግብ ማቅረቢያቸው በሸክላ ሰርተው በገበያው ለመሸጥም ይታትራሉ። ምክንያቱም ጊዜው በአንድ ሥራ ብቻ የሙጥኝ የሚባልበት እንዳልሆነ ያምናሉና። ለሁሉም ገበያው ቀዝቃዛ ነው ብለው ልጆቻቸውን ጦም ማሳደር ስለማይሹ ገበያውን እያዩ የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑም አጫውተውናል። እናትነት ለልጆች ራስን አሳልፎ መስጠት ነው። በዚህም ገበያው ሞቀም ቀዘቀዘም ለልጆቼ ቁርስ የሚሆን ይዤ ለመግባት ስል የማልሰራው ሥራ የለም ይላሉ።
ሌላኛዋ ያነጋገርናቸው ሴት የእቃ ሽቦ ሲሸጡ ያገኘናቸው እናት ናቸው። ሦስት ልጆች አላቸው። እንደ ወይዘሮ የሺወርቅ ሁሉ ልጆቻቸውን ብቻቸውን ያሳድጋሉ። አሁን ለበዓል በሚል ለተለያየ አገልግሎት የሚውል የእቃ ማጠቢያዎችን ይዘው ቀርበዋል። እስፖንጅ፤ የእቃ ማጠቢያ ሽቦ ካቀረቧቸው መካከል ናቸው።
ለገበያ ያቀረቡዋቸውን እቃዎች ስናይ ምንም ገበያ ያላቸው አይመስሉም። ገቢውም እምብዛም መሆኑን መገመት ይቻላል። ወይዘሮዋ ጉልት በሚመስል መልኩ ምንም መጠለያ ሳይኖራቸው በፀሐይ እየተቃጠሉ ሸማቹን መጠበቅ ግድ ይላቸዋል። በአጋጣሚ ጠጋ ብሎ ላወጋቸው ግን ፈገግታቸው ብቻውን ለገበያ ይማርካል። ምስጋናቸው ደግሞ ማንም በዝምታ እንዲያልፍ አያደርግም። እኛም አልፈናቸው መሄድን አልቻልንምና የፍላጎታችንን ሸምተን የበዓል ገበያ እንዴት ነው ስንል ጠየቅናቸው፡፡
እርሳቸውም ፈገግታቸውን እየመገቡን ‹‹ተመስገን ነው። እግዚአብሔር ከዚህ በላይ አያሳጣን። ቢያንስ የልጆቼን ጉሮሮ ደፍኜ አድራለሁና ደስተኛ ነኝ›› አሉን። አዎ! ምስጋናቸው ልክ ነው። ባላቸው ላይ ይጨመርላቸዋል። ፈገግታቸው እርሳቸውንም ቤተሰቡንም እየመገበ እንደሆነ ተመልክተናል። እዚያው ቆመን ሳይቀር ስማቸውን እየጠሩ ያቀረቡትን እየወሰዱ የሚሸጡላቸው ብዙዎች ናቸው።
ገበያ በፈገግታ የሚደምቅ፤ በምስጋና የሚጠራ ሥራ እንደሆነም ከእርሳቸው ተማርን። ገበያ ደራም ቀዘቀዘም ሽያጩ ይወስነዋልን ያየነው እርሳቸው ዘንድ ነው። እናም በዚህ አጋጣሚ ነጋዴዎች ፈገግታችሁ ለሁሉም ይጋባ፣ የዛኔ ትርፋችሁን ታገኙታላችሁ ለማለት እንወዳለን።
ቀጣዩ ሴቶችና የበዓል ገበያ የመለው ጉዟችን ያደረሰን የበዓል ድምቀት በሆነው የሀበሻ ልብስ ሽያጭ ውስጥ ነው። ወይዘሮ ሙሉ ታምራት ደግሞ የሀበሻ ልብሶችን በተለያየ ቀለምና አሰራር፤ ለእናቶች፤ ለወጣቶች፤ ለሕጻናት ሳይቀር የሚያቀርቡ ነጋዴ ናቸው። የሚያቀርቧቸው አልባሳት ለቤተክርስቲያን፤ ለአዘቦት ቀን፤ ለሰርግ፤ ለብርድ ጊዜ አንገት ላይ ጣል ለማድረግና መሰል አገልግሎቶች የሚውሉ እንደሆኑ ይናገራሉ።
ፋሲካ የምግብ በዓል በመሆኑም የሰርግም ወቅት ነውና የሀበሻ ልብሶች በእጅጉ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ገበያው እንደዚህ ቀደም ሞቅ ደመቅ ያለ አይደለም። እንደበፊቱ በትዕዛዝ ጭምር አሰርቶ ለመልበስ የሚፈልግ እምብዛም ነው። በዚህም ይህ ጊዜ ለእርሳቸው የተለየ የገቢ ምንጫቸውን የሚጠብቁበት ቢሆንም የሚፈልጉትን ያህል አልሆነላቸውም።
በዓሉ ከአለፈ በኋላ ትዕዛዞች ሊመጡ ይችላሉ እንጂ እስካሁን ምንም አይነት ‹‹እዚህ ግባ›› የሚባል ገበያ የለም ይላሉ። በእርግጥ ሸማቹም አይፈረድበትም። አንድ ሀበሻ ልብስ ላሰፋ ቢል ገበያው በየግዜው ያሻቅባል። ለምሳሌ ከአስራ አምስት ቀናት በፊት በ80 ብር ይገዛ የነበረው ‹‹መነን›› የሚባለው የአገር ባሕል ጨርቅ አሁን ላይ 150 ብር ገብቷል። እንዲህ መሆኑ ብቻ በአንድ የሐበሻ ልብስ ላይ በትንሹ 500 ብር እንዲጨምር ያደርጋል። ይህ ደግሞ ከኑሮ ጫና ጋር ተዳምሮ እጅጉን ይከብዳል። እናም ሌሎች አማራጮችን እንደሚፈልግ ያስገድደዋል ሲሉ የገበያውን ዋጋ አይቀመሴነት ያነሳሉ።
ወይዘሮ ሙሉ የገበያ ጫናው ሸማቹ ላይ ብቻ እንዳያርፍና እኛም ገበያችንን እንዳናጣ ለማድረግ የእኛን ልፋት እየተውን ጭምር ገበያውን እያንቀሳቀስነው ነው ብለው የገበያው መቀዛቀዝ በእርሳቸው ላይ ብቻ የመጣ ስላልሆነ እርሱ የፈቀደው ይሆናል ብለን ነገን እያለምን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን ብለውናል።
ሌላዋ ያነጋገርናት ወይዘሮ የናኒ ሽፎን ባለቤት ናኒ ወንድማገኝ ናት። የሽፎን ገበያን የጀመረችው ብትን ጨርቅ በመሸጥ ነበር። ገበያው በጣም እየደራ ሲሄድና ደንበኞቿ እየበዙ ሲመጡ ለምን ሁሉንም አገልግሎት መስጠት አልጀምርም በሚል ከጓደኛዋ ተምራ ስፌቱን አከለችበት። እንዳሰበችውም ገበያዋ ሞቅ ደመቅ አለ። ደንበኞቿም ከወትሮው በዙ። ስፌቷንም ብዙዎች ወደዱላት።
አንዱ በአንዱ እየተጠራራ ዛሬ ላይ በዓልን ጠብቃ ብቻ ሳይሆን ዘወትር ሰራተኛ አድርጓታል። በተለይ ጥምቀት መፈናፈኛ እንዳልነበራት ታነሳለች። አንዳንዴ የምትቀበለው ትዕዛዝ በግዜው ላይደርስላት ይችላል። እንዲህ በሆነ ግዜ ደንበኞቿን ላለማስቀየም እውነቱን ነግራቸው ለምታምናቸው ባለሙዎች እየሰጠች እንዲሰፉላት ታደርጋለች። በዚህም በሽፎን ገበያ ሁሌ በዓል ነው ትላለች።
ሽፎኖች በበዓላት ወቅት ብቻ ተለይተው ለገበያ የሚቀርቡ አይደሉም። ሰው ሁሉ የሚወደው ጥራት ያለው ምርት ማቅረብ፤ ዋጋን ተመጣጣኝ ማድረግና ጥርት ያለ ሥራ መሥራት ከተቻለ የበዓል ገበያውን ወደ ዘወትር ገበያው ማዘዋወር የሚቻልበት እንደሆነ ናኒ ትናገራለች። ከዚያ ባሻገር በእምነትና በሀቅ የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት ነው። እነዚህ ሁሉ ተግባራትን ማከናወን ከተቻለ ገበያው ሁሌም በዓል ይሆናል፤ ደንበኞችም ፈልገውና መርጠውን ይጎርፋሉ ስትል ታስረዳለች።
ናኒ የሽፎን ገበያ እንደ ሀበሻ ልብሱ አሁን ላይ የበዓል ብቻ እንዳልሆነ ታነሳለች። ምክንያቱም ሽፎን ከበዓላት ውጪም የሚለበስ ነው። ማንኛውም ፕሮግራም ሲኖር በግሩፕ አልያም ደግሞ በግል ወይም በቤተሰብ በጋራ ደምቀው የሚታዩበት ነው። በግል ለመዋብም ይህ ልብስ ብዙዎች በተለያየ ዲዛይን ያሰፉታል። በዚህም ተመራጭና ተወዳጅ እንደሆነ ቀጥሏል።
ሽፎን አንዲት ሴት በአለባበሷ ክብሯን ጠብቃ እንድትታይ ያደርጋል። ነጻነትን የሚሰጣት፣ ውበቷም እንዲጎላ ጭምር ተጽዕኖ ይፈጥራል። በዚህ ልብስ ‹‹ቦርጬ ወጣ፤ ነፍሰጡር ነኝ፤ እግሬ አያምርም›› ይሉት ስጋት አይሰራም። ሁሉም በአቅም. በፍላጎቱ የሚደምቅበትም ነው። ከፊታችን ውጪ ያለውን የሰውነት ክፍል በመሸፈን አሸብር ቀን እንድንወጣ ያደርጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በዋጋ ብዛት ከሌሎች እንዳናንስ እድል ይሰጠናል። ስለዚህም ሽፎንን የሴቶች የበዓላት መድመቂያ ብንለው አያንስበትም ትላለችም። ከገበያ አንጻርም እሰየው የሚያስብል ገቢን የሚያጎናጽፍ እንደሆነ ታስረዳለች።
ሴቶችና የበዓል ገበያ ሲነሳ ናኒ አንድ ነገር አጥብቃ ታነሳለች። ይህም የእናትነትን ልዩ ዋጋ ከፋይነትን ነው። ገበያ ተለዋዋጭ ነው፤ የገንዘብ አቅምንም ይጠይቃል። ለአንዱ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል። አንዳንዱን ደግሞ ዘወትር በፀሐይ እየተቃጠለ እንዲኖርና የእለት ገቢውን እንዲያገኝ ይፈርድበታል። ጥናቶችን ባላደርግም አብዛኞቹ እናቶች የንግድ ሥራን ሲሰሩ ብዙን ጊዜ በጉልት መልክ ተቀምጠው ነው። ይህ ደግሞ ከባድ ችግርን መጋፈጥን ይጠይቃል።
ነገን እያሰቡ መሥራትንም ይፈልጋል። ስለሆነም ለልጆቻቸው ነገ ዛሬ ላይ ይጠቁራሉ፤ ብርዱና ፀሐዩም ይፈራረቅባቸዋል። በበዓላት ወቅት ምንም ሳያምራቸው ለልጆቻቸው መድመቅ ይጨነቃሉም። ምንም ባኖራቸው እንኳን ተበድረው ልጆቻቸው ከማንም እንዳያንሱ ያደርጓቸዋል። በአጠቃላይ የበዓል ገበያና ሴቶች እንዲህ አይነት መልክ አለውም ስትል አጫውታናለች።
አበበች ሙላቱን የቀጣይ ባለቤቷን እዮብን ያገኘናቸው በሾላ ገበያ ውስጥ ለቀጣይ ኑሯቸው ማድመቂያ የሚሆነውን ብረት ድስት እየመረጡ ሳለ ነው። ፋሲካ ላይ ተጋብተው አንድ ላይ ለመኖር እንዳቀዱና አሁን ለዚያ ኑሯቸው የመሆን የቤት እቃዎች ከወዲሁ ለመግዛት እየተጣደፉ እንደሆነም አውግተውናል። እኛም ገበያውን እንዴት እንዳገኙት ጠየቅናቸው፡፡
አበበችም ዋና ዋና እቃዎች የምንላቸውን የምንገዛው ከባዛሮች ነው። ምከንያቱም በዓሉን ተከትሎ ብዙ ቅናሾች ይደረጋሉ። ስለዚህም ይህንን አማራጭ ከወዲሁ መጠቀሙ ለእኛ ገና አዲስ ለሆንን ጎጆ ወጪዎች እጅጉን ይጠቅመናል። በዘያ ላይ በአቅማችን የምንገዛቸውን አማራጭ እቃዎች እንድናገኝ እድሉን የሚሰጠን ነው ትላለች።
ባለታሪኮቻችን እንደነገሩን ከሆነ የበዓል ገበያ ለሴቶች የተለየ ትርጉም አለው። ቤተሰቦቻቸውን ከበያው ሲሳይ ባገኙት ገንዘብ ደስተኛ አድርገው የሚያውሉበት ልዩ ቀን ነው። ራሳቸውም ቢሆኑ የፈለጋቸውን ሸምተው ነጻነታቸውን የሚያውጁበት ልዩ ዕለት ነው። ደምቀው ለሌሎች ብርሃንን የሚፈነጥቁበትና ነጋቸውን የሚያመቻቹበትም ነው። ስለሆነም መልካም የመድመቂያ በዓል በማለት ለዛሬ የያዝነውን ቋጨን።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም