
እንደ ሀገር ከለውጥ ማግስት በተወሰዱ ዘርፈ ብዙ ርምጃዎችና ማሻሻያዎች በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል። በዚህ በኩል ከሚጠቀሱት ደግሞ ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ከፍ ወዳለ ደረጃ ከማድረስ እና ሁለንተናዊ ብልፅግናን እውን ከማድረግ አኳያ የተከናወነው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ/ሪፎርም አንዱ ነው፡፡
ይሄ ሪፎርም እንደ ሀገር ያሉ አቅሞችን ከመለየት፤ ከማልማት እና ጠብቆ ከመጠቀም አኳያ ትልቅ ውጤት የታየበት፤ ኢትዮጵያም በፈተና ውስጥም ሆና የማይበገር ኢኮኖሚን ወደመገንባት እንድትሸጋገር እድል የፈጠረላት ነው። ይሄን ውጤታማ ሪፎርም ተከትሎም፤ ከፍ ያሉ ሀገራዊ ፍላጎቶችንና ጥያቄዎችን ከመመለስ አኳያ የተወሰደው እና ትልቅም እምርታ እየተገኘበት ያለው ደግሞ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ ነው፡፡
መንግሥት እንደ ሀገር ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ ሲገባ በርካታ ጉዳዮችን ታሳቢም፣ ታላሚም አድርጎ ነበር። በተለይ ከገንዘብ ፖሊሲ ጋር በተያያዘ ፋይናንሱ በገበያ እንዲመራ በማድረግ በኩል የተወሰደው ርምጃ ዛሬ ላይ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተገኙ ላሉ ውጤቶች ጎልቶ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡
ለምሳሌ፣ ይሄ ርምጃ ከተወሰደ ወዲህ፣ እንደ ሀገር የውጪ ምንዛሬ ክምችትን ማሳደግ፤ የመጠባበቂያ ገንዘብን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ማድረስ ተችሏል። የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ፤ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከፍ ማድረግ፤ የማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶችን፣ እንዲሁም የገቢ አቅምን ማሳደግን የመሳሰሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎችም በአንድ በኩል ተኪ ምርቶችን ወደማምረትና የውጪ ምንዛሬ ማዳን፤ በሌላ በኩል የወጪ ምርቶችን በማምረት የውጪ ምንዛሬ ማስገኘት ችለዋል። ለዚህ ደግሞ የነበሩትን በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ የሚያስችል የአቅም ማሳደግ ተግባር ተሠርቷል፤ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችም ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
የወጪና ገቢ ምርቶችንም ከስትራቴጂክ ፋይዳቸው አኳያ እየታየ የተሠራባቸው ሲሆን፤ ገቢ ምርቶች እንደ ሀገር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ምርትና አገልግሎቶች ቅድሚያ ተሰጥቷል። በወጪ ምርቶች በኩልም በጥራትም፣ በመጠንም፣ በዓይነትም ከፍ የማድረግ፤ ብሎም እሴት ጨምሮ ወደመላክ መሸጋገር ተችሏል። ለዚህ አንድ አብነት የሚሆነው ቡና ሲሆን፤ ቡና በጥራትም በመጠንም ከፍ እንዲል ተደርጓል፤ በጥሬው ብቻም ሳይሆን፣ እሴት ተጨምሮ ለውጪ ገበያ የሚቀርብበት አሠራር ተጀምሯል፡፡
በኢንዱስትሪውም፣ በወጪና ገቢ ዘርፉም እንደታያው ሁሉ፤ በግብርናው ዘርፍም ከፍ ያለ እምርታ ተመዝግቧል። ይሄ ደግሞ እንደ ሀገር የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር፤ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለው አበርክቶ አሁንም ጉልህ መሆኑን አሳይቷል፡፡
የአገልግሎት እና ቱሪዝም ዘርፉም ቢሆን፣ ከተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራው በኋላ ትልቅ መነቃቃት የታየበት ነው። ምክንያቱም፣ አገልግሎቱ በዓይነትም፣ በጥራትም፣ በቴክኖሎጂም ከፍ እያለ መጥቷል። ለዚህ አብነት የሚሆነው ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ያለው ዘርፈ ብዙ ልህቀት ሲሆን፤ ይሄን መሰሉ የአገልግሎት ጥራት ማደግ በቱሪዝም ዘርፉ እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት ጋር ሲደመር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ አበርክቶውን እየተወጣ ይገኛል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያን የመገንባት ሂደቱም፣ ከተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራው በኋላ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ትልቅ እምርታ የታየበት ነው። ይሄም በኢትዮ-ቴሌኮም እና በባንኮች የቴክኖሎጂ ተደራሽነት እንዲጎለብት በማድረግ የፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮችን በማቃለል የተሳለጠ የኢኮኖሚ ጉዞ እውን እንዲሆን አስችሏል። ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለሰው ኃይል አቅም ግንባታ እና ለአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና ሂደቶችም የማይተካ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል፡፡
እነዚህ እና ሌሎችም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ ሂደቱን ተከትሎ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራት እና የተገኙ ውጤቶች ደግሞ፤ እንደ ሀገር በዓመቱ የስምንት ነጥብ ሦስት በመቶ እድገት እንደሚመዘገብ የቅድመ ትንበያ እንዲያዝ አድርገዋል። ይሄ ብቻም አይደለም፤ እንደ ሀገር በቀጣይ ለሚሠሩ ሥራዎች እርሾ ሆነው የሁለንተናዊ ብልጽግና ሂደቱ እውን እንዲሆን የሚያፋጥኑ አቅሞች ናቸው።
ምክንያቱም፣ ሂደቱ የሰው ኃይሉን ከማብቃት፣ ቴክኖሎጂውን ከማጎልበት፣ የኢንዱስትሪው አቅም የሚሆኑ ግብዓቶችንም ሆነ የኃይል አቅርቦቶች በመሙላት እንዲገኙ መደላድል የፈጠረ፤ እንደ ዓባይ ግድብ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ከፍጻሚ እንዲደርሱ ያስቻለ፤ ግብርናው፣ ቱሪዝሙ፣ አገልግሎቱ፣ ማዕድንና ኢንቨስትመንቱ ሁሉ ላይቀዛቀዝ ወደፊት እንዲያስፈነጥር የሚያደርጉ ናቸው። ለአመራሩም የሞራል ስንቅ በመሆን መነሳሳትን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም