
የፋሲካ በዓል በመስዋዕትነት ላይ የተመሠረተ የእርቅ እና የመታዘዝ በዓል ነው። የክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ እንደሚያመለክተው ፤የሰው ልጅ የፈጣሪውን ትዕዛዝ በመተላለፍ ከገባበት ኃጢያት እና የኃጢያት ፍርድ ነጻ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ እየሱስ /የእግዚአብሔር ልጅ በመስቀል ላይ በከፈለው ዋጋ የኃጢያት ሥርየት የተገኘበት፤ ዳግም ከአምላኩ ጋር ኅብረት ማድረግ የሚችልበትን የልጅነት መብት/ሥልጣን የተጎናጸፈበት ነው።
ይቅር ባይነት፣ ትሁትነት ፣ ሰላማዊነት ፣ ታማኝነት ፣ ለሌሎች መኖር …ወዘተ፣ የክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ መሠረት መሆናቸውን የእምነቱ አባቶች ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ የሃይማኖቱ እሴቶች ከክርስቶስ ኢየሱስ የሕይወት ባህሪ የተቀዱ ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ላይ ሞት በተከናወነ የኃጢያት ስርየት ከእግዚአብሔር ጋር ያስታረቀ አምላክ ተገላጭ ባህሪያት ናቸው።
ቀደም ባለው ዘመን የሰው ልጅ ከነበረበት የኃጢያት ሕይወት የተነሳ ለይቅርታ ልቡ የደነደነ ፣ ትህትና የጎደለው አመጸኛ ማንነት ባርያ የነበረ ፣ለመታመን የሚሆን የሕይወት ልምምድ ያልነበረው ፣ ራስ ወዳድ እና ራሱን አምላኪ ፣ ከቃኤል ጀምሮ በወንድሙ ላይ በቅናት አድብቶ የወንድሙን ደም ያፈሰሰ እና በእዚህም ሰላም እና እረፍት የሌለው ነበር።
ካለመታዘዝ እርግማን የተነሳም ፣ ለበጎ ሥራ ራሱን ያልገራ ፣ ከጥፋት ጋር ኅብረት ለማድረግ የፈጠነ ፣ በእዚህም የራሱን ዕጣ ፈንታ ከፈጣሪው በጎነት ተናጥቆ በጨለማ ውስጥ ብዙ ዋጋ ለመክፈል የተገደደ ፣ በእያንዳንዱ የጥፋት እንቅስቃሴው ቀጣይ ትውልድን ባለዕዳ አድርጎ ባልተከፈለ የዕዳ ግዞት ውስጥ ለመኖር የተገደደ እና ይህም እጣ ፈንታው የሆነ ነበር።
የክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ምድር መምጣት፤ የእርቅ ፣ የመመለስ እና የሕይወት ወንጌልን መስበክ ሆነ፤ በብዙ ጣር የመስቀል ላይ ሞትን መሞት፤ የሰው ልጅ አምላኩን /ፈጣሪውን ባለመታዘዙ የተነሳ የተበላሸውን ፍጥረታዊ ማንነቱን/ በሽታውን በመፈወስ ለተፈጠረበት ዓላማ ይኖር ዘንድ የተሰጠው ተጨማሪ ዕድል ነው።
ኢትዮጵያውያን ክርስትና ሃይማኖትን ቀድመው ከተቀበሉ ሀገራት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ከመሆን ባለፈ ፤ በክርስትና ሃይማኖት አስተምሮ ውስጥ ዘመናትን ያስቆጠሩ ሕዝቦች ሀገር ናት። የእምነቱ ተከታዮችም በየዓመቱ ፋሲካ በዓልን ሲያከብሩ ብቻ ሳይሆን የዕለት ተዕለት መንፈሳዊ አስተምህሮዎቻቸው ከክርስቶስ ኢየሱስ የምድር ላይ ሕይወት እና አስ ተምህሮ የተቀዳ ነው።
ብዙዎቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች በየትኛውም አስተምህሮ መከፋፈሎች ውስጥ ቢሆኑም፤ እሴቶቻቸው፣ የእምነታቸው ጀማሪ እና ፈጻሚ ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከከፈለው የሕይወት ዋጋ የሚቀዳ ነው። አስተምህሮዎቻቸውም ይቅር ባይነት ፣ ትሁትነት ፣ ሰላማዊነት ፣ ታማኝነት ፣ ለሌሎች መኖር … ወዘተ መሠረት ያደረጉ ናቸው።
የእምነቱ ተከታዮች እነዚህን የሃይማኖቱን እሴቶች ከልጅነት ጀምሮ አሁን እስካለበት እድሜ እና የመንፈሳዊነት ደረጃ አንድ ሺ አንድ ጊዜ ያልሰማ ፣ ለእነዚህ መንፈሳዊ እሴቶቹ ባዕድ የሚሆን የለም። እንደ ማኅበረሰብ ያሉን ባህላዊ እሴቶችም እነዚህን እሴቶች የሚያጎለብቱ እንጂ የሚቃረኑ አይደሉም። ዘመናዊነትም ቢሆን በመርህ ደረጃ እነዚህን እሴቶች ተቀብሎ የሚያስተናግድ ነው።
ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው፤ ክርስትናን የሕይወት መርህ አድርገን በተቀበልንባቸው ረጅም ዘመናት ያሳለፍነው ማኅበረሰባዊ ሕይወታችን ምን ይመስላል የሚለው ነው። ትናንት ብቻ ሳይሆን ዛሬም እየኖርነው ያለነው ሕይወት የቱን ያህል በክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮዎች የተገሩ ናቸው። የዕለት ተዕለት ሕይወታችንም ሆነ ከሕይወታችን የሚቀዳው ባህሪያችን፤ ለዘመናት በሃይማኖቱ አስተምህሮ ውስጥ ያለፈን ማኅበረሰብ የሚመስል ነው ወይ የሚለው ነው።
ዘመናት ባስቆጠረው የሀገረ መንግሥት ትርክታችን ውስጥ ያሳለፍናቸው የእርስ በርስ ጦርነቶች እና ግጭቶች ከእዚህ እንዳንወጣ እየፈተነን ያለው ለእርቅ እና ለይቅርታ የደነደነ ልብ ፣ ቅናት እና ራስ ወዳድነት ፣ ዳተኝነት እና ሰላም ጠልነት ከየት ያመጣናቸው ናቸው ።
በተለይ አሁናዊ በሆነው ሀገራዊ እውነት የሚስተዋለው ለበጎ ሥራ ራስን ከመግራት ይልቅ ፣ ከጥፋት ጋር ኅብረት ለማድረግ መፍጠን ፣ ውሸት እና ሀሜተኝነት ፣ ወንድምን ከመደገፍ ይልቅ በወንድም ውድቀት መደሰት እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ ዕጣ ፈንታችንን የጋራ አድርጎ ከመቆም ይልቅ በራስ ወዳድነት ፣ በልበ ደንዳናነት እና በደንታ ቢስነት ለራስ ከንቱ ፈቃድ አልፎ መቆምን ከየትኛው የክርስትና አስተምሮ ተቀዱ የሚለው መታየት አለበት፡፡
ከፊታችን ያሉትን የስቅለት እና የትንሳኤ በዓል ስናስብ፤ ይህንን አሁናዊ እውነታ በአግባቡ እያስተዋልን፤ ለተቀበልናቸው መንፈሳዊ እሴቶች ያለንን ተገዥነት በእውነት እና በመንፈስ አድሰን እንደገና ከራሳችን እና ከአምላካችን ጋር እርቅ ለማድረግ ወስነን ሊሆን ይገባል። ይህን ስናደርግ በእያንዳንዱ ያለመታዘዝ ጥፋታችን ከገባንበት ግዞት ወጥተን በነጻነት መቆም እንችላለን። እውነተኛ ዕጣ ፈንታችንም የሚቀዳው ከእዚሁ የመመለስ መንገዳችን ይሆናል!
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም