
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የትንሳኤ በዓል ነው። በዓሉ ካለው መንፈሳዊ ፋይዳ በተጨማሪ ከአርባ እና ሃምሳ የጾም እና የጸሎት ቀናት በኋላ የሚከበር መሆኑ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው። የበዓሉ ገበያም ሰፊና ደማቅ ነው።
በዓሉ ከበዓልነቱ ባለፈ የጾም መፍቻ በዓል መሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ያላቸውን ቋጥረው ወደ ገበያ በስፋት የሚንቀሳቀሱበት ነው። የበዓሉ ገበያም ዶሮን ጨምሮ የእርድ እንስሳት በስፋት የሚስተናገድበት፣ የቅቤ ፣ የሽንኩርት የእንቁላል .. ወዘተ ገበያም ከወትሮ የተለየ የሚሆንበት፣ ሁሉም እንደየአቅሙ በዓሉን በዓል ለማስመሰል ወደ ገበያ የሚተምበት ነው።
የበዓል ገበያው ከሁሉም በላይ፤ በአንድም ይሁን በሌላ የማኅበረሰቡን የመግዛት አቅም ታሳቢ ያደረገ እና የበዓሉን መንፈስ የሚሸከም እንዲሆን የሁሉም ምኞት ነው። ይህንን እውን በማድረግ ሂደት ነጋዴው ፣የሚመለከተው የመንግሥት አካል እና ሸማቹ ማኅበረሰብ የየራሳቸው ኃላፊነት እና የቤት ሥራ አለባቸው። የበዓል ገበያው ድምቀትም የሚወሰነው ሁሉም ኃላፊነታቸውን በተወጡበት ልክ ነው።
ነጋዴው ፣ሸማቹ ለበዓሉ የሚፈልጉትን ሸቀጦች የመግዛት አቅሙን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በበቂ መጠን በማቅረብ በዓሉ በዓል እንዲመስል ትልቅ ኃላፊነት አለበት። ነግዶ ከማትረፍ ባለፈም እንደ አንድ የማኅበረሰቡ አካል የበዓሉ ገበያ ፍትሐዊ እና ሁሉንም አካታች እንዲሆን የማድረግ የሞራል ኃላፊነት አለበት።
በተለይም የትንሳኤ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለብዙዎች የመስቀል ሞት የሞተበት፣ የመስዋዕትነት በዓል መሆኑ፤ የበዓሉ ገበያ ቢያንስ ቢያንስ የተጋነነ እና የእምነቱን ተከታዮች ያልተገባ ዋጋ የሚጠይቅ፤ በተጋነነ ትርፍ የበዓሉን መንፈስ የሚያደበዝዝ እንዳይሆን የማድረግ ኃላፊነት አለበት። የበዓል ገበያው “የአቅሜ ይበቃኛል” በሚል የኃላፊነት መንፈስ የተገራ እንዲሆን ማድረግ አለባቸው።
የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት፣ በበዓል ገበያው የሸቀጦች እጥረት እንዳይፈጠር ገበያውን የማረጋጋት ሥራ መሥራት አለባቸው። ይህ ቀደም ብሎ በዕቅድ የሚከናወን ቢሆንም፤ በቀጣይ ቀናት ሁኔታዎች በታቀደው መሠረት እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ጠንካራ የቁጥጥር እና የክትትል ሥርዓት አበጅተው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።
ገበያው በታሰበው መንገድ የተረጋጋ መሆኑን ፣ ሰው ሰራሽ የሸቀጦች እጥረት ገበያው ላይ አለመከሰቱን ፣ ከሁሉም በላይ በተለያዩ አማራጮች ወደ ገበያው የገቡ ሸቀጦች በተቀመጠላቸው የዋጋ ተመን እየተሸጡ ስለመሆኑ በአግባቡ መከታተል፣ችግር ሲያጋጥም ፈጣን የእርምት ርምጃ መውሰድ የሚያስችል ዝግጁነት መፍጠር ይኖርባቸዋል።
ከእዚህም ባለፈ በበዓል ገበያዎች የሚያጋጥሙ ሕገወጥ የግብይት ሥርዓቶችን እና ማጭበርበሮችን ከሚመለከታቸው ተቋማት እና ከሕዝቡ ጋር በመሆን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራዎችን ሊያከናውን ይገባል። ለጤና ጠንቅ የሆኑ ሸቀጦች ገበያውን እንዳይቀላቀሉ ከማድረግ ጀምሮ ገበያው የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ሰለባ እንዳይሆን መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
ሸማቹም ማኅበረሰብም አቅምን መሠረት ያደረገ የተገራ ፍላጎት ይዞ የበዓል ገበያውን መቀላቀል ይጠበቅበታል። በበዓል ገበያ ወቅት ከሚያጋጥሙ ጥድፊያዎች እና አላስፈላጊ የግብይት ሥርዓቶች መውጣት፤ ከበዓል ማግስት ያሉ ቀናቶችን ታሳቢ ያደረገ ግብይት ማድረግ፤ ከበዓል ሞቅታ ወጥቶ አቅምን ታሳቢ ባደረገ ገበያ ውስጥ መገኘት ይኖርበታል!
ይህን ማድረግ መቻል በዓሉ በሁሉም ዘንድ የደመቀ እንዲሆን፤ ከበዓል ማግስት ከሚፈጠር ጸጸት ራስን ቀድሞ መታደግ የሚያስችል ነው። በነጋዴው ፣ በመንግሥት እና በሸማቹ ማኅበረሰብ መካከል ዘላቂ መተሳሰብ እና መተማመንን የሚፈጥር ነው!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም