
“ፖሊሲ” በአጭሩ አንድን ግብ ለማሳካት መደረግ ያለባቸውንና የሌለባቸውን ተግባራት የሚያመላከት መርህ፣ መመሪያና ደንብ የያዘ የዕቅድ ሰነድ ነው ማለት ይቻላል። ፖሊሲ ሀብትን ለመደልደልና አደጋዎችን አበክሮ ለመከላከልም የማይተካ ሚና አለው። የትምህርትና የጤና ፖሊሲዎችን እዚህ ላይ ልብ ይሏል። የንግድ ፖሊሲው ዘመኑንና ትውልዱን የዋጀ ወይም ዘመነኛ የንግድ ሥርዓትን ለመተግበር ምን ምን መሠራት አለበት፤ ምን ምን መሠራትስ የለበትም የሚለውን የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ ነው። እንዴት ይፈጸማል የሚለው ደግሞ በንግድ ስትራቴጂው ላይ የሚመላከት ይሆናል።
ሰሞኑን በሀገሪቱ የንግድ ፖሊሲ ረቂቅ ላይ የመጨረሻ ምክክር ተደርጓል። ረቂቅ የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ እና የባለድርሻ አካላት የውይይትና የግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሂዷል። የውይይትና የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) መንግሥት የንግድ ዘርፉን ግልፅ፣ ፍትሃዊ፣ ተወዳዳሪና ተገማች የሆነ የገበያ ሥርዓትን ለመፍጠር እንዲሁም ጥራትን ለማረጋገጥ ሰፋፊ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን፤ ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎም በንግዱ ዘርፍ ርካታ ውጤቶች የተገኙ መሆኑን፤ የንግድ ከባቢን ውጤታማና ምቹ ለማድረግ የንግድ ሥራ ለመጀመር የሚወስደውን 32 ቀናት ወደ 7 ቀናት ማውረድ እንደተቻለ በተጨማሪም ብቃት የሚጠይቁ ዘርፎችን በመቀነስ እና የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓትን በመዘርጋት በ2017ዓ.ም 2.5 አገልግሎቶች መሰጠቱን አንስተዋል።
ለሸማቹ ማህበረሰብ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብም 1,300 በላይ የቅዳሜና እሁድ የግብይት ማዕከላት በሀገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን፤ በተመሳሳይ በወጪ ንግድ ዘርፍ ከፍተኛ ስኬት የተገኘ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) የሀገራችን ወጪ ንግድ በ2010ዓ.ም ከተገኘው የ2.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በ2017ዓ.ም ባለፋት 8 ወራት ወደ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማሳደግ እንደተቻለ ጠቅሰዋል። ይህም የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ስኬት ነው ሲሉ ገልፀው፤ በንግዱ ዘርፍ ጥራት ለማረጋገጥም በ8.2 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ዘመናዊ የጥራት መንደር የተገነባ መሆኑን በመግለፅ የአህጉራዊና የዓለም አቀፍ የንግድ ትስስሮችን ለማጠናከር እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2026 የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየተሠራ መሆኑን፤ ሀገራዊ የንግድ ዘርፍ ረቂቅ ፖሊሲው በሁሉም የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት እየዳበረ እንደሚገኝ በወቅቱ መግለጻቸው አይዘነጋም።
ባለፉት ዓመታት ሚኒስቴር መ/ቤቱ በስኬት ካከናወናቸው ሥራዎች ዋና ዋናዎቹ የንግድ ሴክተር ተቋማዊ ግንባታ ሂደት ውስጥ በዋናነት ከሚጠቀሱት ተግባራት መካከል የንግድ ሕግን ከ62 ዓመት በኋላ ሀገራዊ የንግድ ሥርዓትን ለመምራት ካለው ፍላጎትና ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም ዓለምአቀፍ የንግድ ተሞክሮ አኳያ ማሻሻል መቻሉን፤ በተመሳሳይ ንግድን የሚመለከቱ አሠራሮች በተበታተነ እና ትስስር በሌለው ሁኔታ ይመራ ከነበረበት በማውጣት በአዲስ አደረጃጀት የንግድ አሠራርን የማዘመን፣ ግልጽ ተደራሽና ፍትሃዊ ውድድር የሰፈነበት እንዲሆን የማድረግ፣ ቀጣናዊ ትስስርን የማጠናከር፣ የወጪ ንግድን በማስፋፋትና በማሳደግ፣ የዕቃዎችንና የአገልግሎቶችን የጥራት ደረጃ የማዘጋጀትና ተግባራዊነቱን የመቆጣጠር፤ የሽማቹን፣ የንግዱን ማህበረሰብና የሀገርን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የንግድ ሥርዓት የመገንባት ተልዕኮ ተሠጥቶት ተቋቁሟል።
የንግድ ሴክተር አደረጃጀትን ተከትሎ ሥራውን በሕግና ሥርዓት ለመምራት የሚያስችል ከ25 በላይ የሚሆኑ የሕግ ማእቀፎች (አዋጅ፣ ደንብ እና አሠራር መመሪያዎች) በአዲስ ተዘጋጅተው ወደሥራ እንዲገቡ መድረጉን፤ ዘርፉ በውድድር እንዲመራ በማድረግ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን በተሻለ መልኩ ማሳደግ የሚያስችል ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው የቆዩት የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላ እና የችርቻሮ ንግድ ክፍት እንዲሆን ተደርጓል። በተቋማዊ ግንባታ እና የሕግ ሥርዓቶች ማሻሻያዎች በተጨማሪ በቁልፍ ዘርፎች ላይ የሪፎርም ሥራዎችን በመተግበር በርካታ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉ ተመልክቷል።
በላይሰንሲንግና ሪጉላቶሪ ዘርፍ የኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በማዘመን እና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የንግዱን ማህበረሰብ የጊዜና ሀብት ብክነት እና የተገልጋዮች እንግልት በማስቀረት በኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በ2017 ዓ.ም በ8 ወር ውስጥ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ተችሏል። መሠረታዊ የሆኑ የግብርና ምርቶች ሊከሰት የሚችለውን የዋጋ ንረት ለመታደግ የገበያ ማዕከላትን በማስፋት ሸማቹ ህብረተሰብ በአቅራቢያው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችሉ ሸማቹን እና አምራቹን በቀጥታ የሚያገናኙ 1,417 የቅዳሜና እሁድ ግብይት ማእከላት መቋቋማቸው፤ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ማሻሻያን ተከትሎ ይፈጠራል ተብሎ የተሰጋውን የዋጋ ጭማሬ እና የገበያ አቅርቦት ክፍተት ለመከላከል ለአራት ወራት በየቀኑ ያልተቋረጠ ተከታታይና የተቀናጀ የቁጥጥር ሥራ በመሥራት እና ሕገወጦችን በማረም ስጋቱን መከላከል መቻሉ በስኬት የተከናወኑ ሥራዎች ናቸው።
ከወጪ ምርቶች ገቢ በሀገር ደረጃ ከስድስት ዓመት በፊት ከ2.7 ቢሊዮን ዶላር በታች የነበረው አፈጻጸም በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 4.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። በዓመቱ ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት እየተሠራ ይገኛል። ሀገራችን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2019 የፈረመችውን የአፍሪካ አህጉር ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት በርካታ ድርድሮችን በማካሄድ የሙከራ ንግድ ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል። እንዲሁም ሀገራችን ለዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ጥያቄ ካቀረበች ከ20 ዓመት በላይ የቆየች ቢሆንም ለዓመታት ያልፈታነውን የአባልነት ድርድር ከተቋረጠበት እንደገና በማስጀመር በዚህ ዓመት ውስጥ በርካታ የድርድር ሰነዶችን በማዘጋጀትና ድርድሮችን በማካሄድ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአባልነት ጥያቄያችን የሚመለስበት ደረጃ ደርሷል፡፡
ጥራት መሠረተ ልማት ዘርፍ በሀገራችን ንግድና ኢንቨስትመንትን በማሳለጥ ሀገራዊ እድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የጥራት መንደር ለመገንባት በተደረገው ከፍተኛ የመንግሥት ቁርጠኝነትና ርብርብ በአፍሪካ በአይነቱና በሚሰጠው አገልግሎት ልዩ የሆነ በውስጡ አራት የጥራት መሠረተ ልማት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አንድ የቴክኖሎጂ ተቆጣጣሪ ተቋም አካቶ የያዘ ብሔራዊ የጥራት መንደር በ8.2 ቢሊዮን ብር በላይ ተገንብቶ ወደ ሥራ ገብቷል።
እንደሚታወቀው የንግድ ሥራ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቀደምት እና የኢኮኖሚ ማዕከል ሆኖ የቆየ ቢሆንም እስከ አሁን የሀገሪቱን የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ንግድ ሥርዓትን ለመምራት የሚችል ወጥ የሆነ የንግድ ፖሊሲ አልነበረም። ይልቁንም የሀገሪቱ ንግድ ሥራ በ1952 ዓ.ም በወጣው የንግድ ሕግ እና በየጊዜው በሚወጡ አዋጆችና ደንቦች ሲመራ ቆይቷል። በመሆኑ በንግድ ዘርፉ ላይ ያሉ የንግድ እድሎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች እና ስታንዳርዶች በተመለከተ የአሠራር ወጥነት ችግሮች ይስተዋላል። በዚህ ምክንያት የሚፈፀሙ ሕገ-ወጥ የንግድ ተግባራት፣ የተለያዩ የንግድ ዘርፎችን የሚመሩ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ የሚደረጉ ያልተጠበቁ ተደጋጋሚ ለውጦች መኖር በንግድ ከባቢው እና በኢንቨስትመንት ልማት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
በንግድ ዘርፍ ከዚህ የላቀ ውጤት ለማምጣትና ሀገራዊ የብልፅግና ራዕይያችንን ለማሳካት በዘርፉ የሚታዩ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታትና ዘርፉን ለማዘመንና ተወዳዳሪ ለማድረግ የንግድ ፖሊሲ ወሳኝ በመሆኑ ሀገራዊ ግብን፥ ነባራዊ ሁኔታን እና ዓለምአቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን መሠረት በማድረግ ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነ ረቂቅ የንግድ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል።
የፖሊሲ ዝግጅቱ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያላቸው ባለሙያዎች የተሳተፉበት፤ አጠቃላይ ሀገራዊ የንግድ ሥርዓትን የሚዳስስ ዝርዝር የጥናት ሰነድ ተዘጋጅቶ እሱን መሠረት በማድረግ የንግድን ሁሉ አቀፍ ሴክተራል ባህሪ በመረዳት የፖሊሲ ቅንጅትና ወጥነትን ለማረጋገጥ ከሌሎች ሀገራዊና የዘርፍ ፖሊሲዎች ጋር እንዲተሳሰር ተደርጎ የፕላንና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ያዘጋጀውን የፖሊሲ ዝግጅት ማሕቀፍን መሠረት ተደርጎ የተሰናዳ ነው።
ረቂቅ የፖሊሲ ሰነዱ ላይ በተለያዩ ጊዜያት በግሉ ዘርፍ፥ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤቶች፣ የተለያዩ የልማት አጋሮች፣ በክልልና በፌዴራል የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች እንዲወያዩና እንዲያዳብሩት ተደርጓል። ፖሊሲው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመፅደቅ ከመቅረቡ በፊት ማጠቃለያ አስተያየት እንዲሰጥበት መድረኩ መመቻቸቱም ተመልክቷል።
ባለፉት አስር ዓመታት በሀገራችን ለተመዘገበው ፈጣንና ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ ዕደገት የንግዱ ዘርፍ የተጫወተው ሚና እና ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። የንግዱ ዘርፍ በአንድ በኩል በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዕድገትና ልማት የላቀ ድርሻ የሚያበረክትና የዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ ይታወቃል። በሌላ በኩል ስር የሰደዱ ችግሮች በተለይም ዘርፉ የሚመራበት ራሱን የቻለ ፖሊሲ ባለመኖሩ የገቢ ንግድ ወጥ በሆነ እሳቤ እና አደረጃጀት የሚመራ አለመሆኑ ፤ የወጪ ንግድም ቢሆን በበርካታ ተቋማት የሚመራ እና ቅንጅትና መናበብ የሚጎለው ሆኖ ቆይቷል።
በዚህ ምክንያት የንግድ ሥርዓታችን ፍትሃዊ ውድድር የሚጎለው፤ የተለያዩ ሕገ-ወጥነትና ብልሹ አሠራሮች የበዛበት፤ ሸማቾችን ያማረሩ የግብይት ሁኔታዎች የሚስተዋልበትና በዓለም አቀፍ ገበያም ተወዳዳሪነትን ያላረጋገጠ ዘርፍ ነው። ንግዱን የሚመለከቱ የፖሊሲ ጉዳዮች በሌሎች ሴክተር ፖሊሲዎችና በተለያዩ ጊዜ በሚወጡ አዋጆችና ደንቦች ውስጥ በተበታተነ ሁኔታ መገኘታቸው ዘርፉን በተሟላ ሁኔታ ለመምራትና ተፈላጊውን ውጤት ለማምጣት አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል።
ይህንኑ ክፍተት በመገንዘብ ባለፉት ዓመታት ዘርፉን ውጤታማና ተወዳዳሪ ለማድረግ ሲከናወኑ ከቆዩት የንግድ ሪፎርም አጀንዳዎች መካከል በዘርፉ የሚታዩ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ብሔራዊ ፖሊሲ እንዲኖረው ማስቻል ትኩረት ተሠጥቶት ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል። በዚሁ መሠረት የንግዱ ፖሊሲ ሀገራዊ የብልፅግና ራዕይ ለማሳካት ጉልህ ሚና ያለውን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የአስር ዓመቱን የልማት ዕቅድ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃዎች መነሻ በማድረግ ተዘጋጅቷል።
ፖሊሲው መንግሥት በሀገር ውስጥና በውጭ ንግድ መስኮች የሚተገብራቸው አጀንዳዎች እና የሚወስዳቸው ርምጃዎች ግልፅ አቅጣጫዎችን የሚያመለክት ነው። የዘርፉ ቁልፍ ተዋናይ የሆነው የግል ዘርፍም ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም አቀፍ የንግድ ምህዳር ውስጥ ወጥነት የጎደለውና ተገማች በሆነ የፖሊሲ ከባቢያዊ ሁኔታ ውስጥ ሥራውን መምራትና ማስተዳደር እንዲችል ጭምር በፖሊሲው ትኩረት ተሠጥቶታል፡፡
በሌላ በኩል ሀገራዊ የንግድ ፖሊሲው የተቀረፀው በሀገራችን እየተገነባ ባለው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ማሕቀፍ ውስጥ ሲሆን የግሉ ዘርፍ ዋነኛ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር አድርጎ በመውሰዱና መንግሥት በግሉ ዘርፍ ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር የንግድ ፖሊሲው ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን የማሳደግ፣ ወጪ ንግዱን የማስፋፋት፣ የወጪ ምርቶችን በዓይነት፣ በመጠን፣ በመዳረሻ ገበያ የማስፋት፣ ፈጠራንና ግልፅነትን የማበረታታት፣ የንግድ እድሎችን ለማስፋት እንዲሁም በሀገር ውስጥ ንግድና በጠረፍ ንግድ እና በመዳረሻ ገበያዎች ያሉትን መሰናክሎች በማስወገድ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
ፖሊሲው የሠራተኛው እውቀትና ክህሎት ለማሻሻል እና የተቀመጡ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ግቦችን እንዲሁም የሴቶችና ወጣቶች የሥራ እድሎች ፈጠራ ላይ ያለመ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ያግዛል። በተመሳሳይ ሀገራችን የንግድ ግንኙነቷን ለማስፋት ከበርካታ መንግሥታት የሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ስምምነቶችን ታደርጋለች። በተለይም ሀገራችን የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድሆን ሰፋፊ ሥራዎች ይሠራሉ። ዓለም አቀፍ የንግድ እድሎች ያላቸውን ጠቀሜታ መረዳት ላይ ያለው እሳቤ አናሳ እንደሆነና ሀገራችን በሚገባት ልክ ቀጣናዊና ዓለምአፋዊ ንግድ ውስጥ ዋና ተዋናይ እንድትሆን ፖሊሲው የማይተካ ሚና ይኖረዋል፡፡
የንግድ ፖሊሲው የሀገሪቱን የንግድ ዘርፍ አሠራር ድርድሮችን፣ ስምምነቶችን እንዲሁም ውይይትን ወጥ በሆነ እሳቤ ለመምራት የሚያስችል ነው። በአጠቃላይ ይህ የንግድ ፖሊሲ የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት የሚመራ፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የኢኮኖሚውን ሂደት መልከብዙ በማድረግ አስተማማኝ እና ተጨባጭ የሆነ ልማትና ዕድገት ለማምጣት የሚያገለግል ዋነኛ የሕግ ማሕቀፍ ነው፡፡
የንግድ ፖሊሲው በሀገራችን እየተስተዋሉ ያሉትን የንግድ ዘርፍ ጉድለቶችን ለመሙላት አበርክቶው ከፍ ያለ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በዋነኛነት ወጥነት ያለው እና የተቀናጀ የንግድ ሥርዓት አመራር አደረጃጀት ለመዘርጋት፣ ፍትሐዊ የሆነ የንግድ ውድድር አውድ ለመፍጠር፣ ለሀገራችን ምርቶች ሰፊና ተገማች የገበያ ዕድል ለማመቻቸት፣ የግብይት መሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት፣ የሎጅስቲክስና ገበያ ትስስር ችግሮች እና በዓለም አቀፍ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ ለማድረግ፤ በተመረጡና በጥናት ላይ በተመሠረተ የገበያ ጉድለት ባለባቸው ዘርፎች የመንግሥት ጣልቃ የመግባት ጠቀሜታን ግምት ውስጥ በማስገባት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ነው። በሌላ በኩል የሀገራችን የወጪ ንግድ በግብርና ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት በማላቀቅ የወጪ ምርትና አገልግሎት ብዝሃነት እና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችል መሠረታዊ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው፡፡
ፖሊሲው የተመረኮዛቸውን መርሆዎች እንመልከት፦
- ጥራት ተኮር፡- በገበያው የሚቀርቡ ምርቶችና አገልግሎቶች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ እና ጥራት ያለው የንግድ አገልግሎቶችን መስጠት።
- አቅርቦት መር፡- የምርትና አገልግሎቶች ግብይት ሥርዓቱ በዋናነት አቅርቦትን በሚያሳድግ አግባብ መምራት።
- ነፃ ገበያ፡- በሁለም ደረጃ የሚካሄድ የንግድ አሠራሮች የነፃ ገበያ መርህን የተከተሉ ናቸው።
- አካታችነት፡- በሀገር ውስጥም ሆነ በወጪ ንግድ ሥራ ፍትሃዊ የሆነ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እንዲሁም የተለየ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አካላት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ።
- ተወዳዳሪነት፡- የሀገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶች ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እና የአምራቾች ምርታማነት እንዲሻሻል በትኩረት መሥራት።
- ግልጽነትና ተጠያቂነት፡- የንግድ ሕጎችና አሠራሮች ለሁለም የንግድ ተዋንያን ግልፅ የሚሆኑበት እና የንግድ ሕጎችና አሠራሮችን በሚጥሱት ላይ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ።
- ተገማችነት፡- የንግድ ሕጎችና አሠራሮች ለሁለም የንግድ ተዋንያን ተገማች መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው።
- ዓለምአቀፋዊነት፡- የንግድ ሥርዓቱ ዓለምአቀፍ ሕጎችና ድንጋጌዎችን ባከበረ አግባብ መተግበር፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ፖሊሲ አጠቃላይ ዓላማ ግልፅነት ያለው፣ አካታች እና በፍትሐዊ ውድድር ላይ የተመሠረተ የሀገር ውስጥ ንግድ እና ተወዳዳሪ የወጪ ንግድ በመገንባት ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ዘላቂ ልማትና ሀገራዊ ብልፅግና ማረጋገጥ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከትና ከዓለም አቀፍ ንግድ ተገቢውን ድርሻ ማግኘት ነው።
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም