
ባለፈው አርብ ዶናልድ ትራምፕ ቻይና የሚመረቱ የተወሰኑ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ከታሪፍ ነጻ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አሳውቀዋል። ነገር ግን የአሜሪካው የንግድ ሚኒስትር ሐዋርድ ሉትኒክ ባለፈው እሁድ እንዳሉት እንደዚህ ዓይነቶቹ ውሳኔዎች ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ ናቸው። በእነዚህ ምርቶች ላይ በተለየ ሁኔታ የታሪፍ ጭማሪ የሚደረግ ሲሆን፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጭማሪው ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
“እነዚህ ምርቶች በአሜሪካ እንዲሠሩ እንፈልጋለን” ሲሉ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ በጻፉት መረጃ በእነዚህ ምርቶች ላይ የሚደረገው የታሪፍ ጭማሪ ቀርቷል መባሉ “ሐሰት” ነው ብለዋል። በአንጻሩ የተለየ የታሪፍ ሥርዓት እንደሚበጅላቸው ተናግረዋል።
ትራምፕ አክለውም “ሁሉንም የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች እና ሰማይኮንዳክተር የአቅርቦት ሰንሰለትን በቀጣይ በሚደረገው የብሔራዊ የጸጥታ ታሪፍ ጥናት ላይ እንመለከታቸዋለን” ብለዋል። ይህ ንግግራቸውም እንደ ስልክ፣ ኮምፒውተር እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ምርት አቅራቢዎች ላይ ስጋትን ፈጥሯል። የቻይናው ንግድ ሚኒስቴር በኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ላይ የተጣለው የታሪፍ ጭማሪ በአሜሪካ የተደረገ “ውስን ርምጃ ነው” ያሉት ሲሆን፣ ርምጃው የሚኖረውን ተጽእኖም ቤጂንግ እየገመገመች መሆኑን ገልጿል።
ነገር ግን የትራምፕ አስተዳደር በእነዚህ ምርቶች ላይም ቢሆን በቀጣይ ታሪፍ ለመጨመር ማቀዱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ጦርነት የበለጠ ያጋግለዋል ተብሎ ይታሰባል። በሚያዚያ ወር መጀመሪያ ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ የ54% የታሪፍ ጭማሪ አድርገው ነበር። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ይህ የታሪፍ ጭማሪ ወደ 145 በመቶ አድጓል።
ቻይናም የአሜሪካን ርምጃ በመከተል በአሜሪካ ምርቶች ላይ የ34 በመቶ ታሪፍ ጭማሪ አድርጋ ነበር። አሜሪካ ጭማሪ ስታደርግ ቻይናም በአሜሪካ ላይ የምትጥለውን የታሪፍ ጭማሪ ወደ 84 በመቶ ያሳደገች ሲሆን አሁን ላይ 125 በመቶ አድርሳዋለች። በቅርቡ የተደረገውን ጭማሪ ተከትሎ የተጀመረውን የንግድ ጦርነት አሜሪካ የምትቀጥልበት ከሆነ ቻይና እስከመጨረሻው ለመፋለም መዘጋጀቷንም አስታውቃለች።
የታሪፍ ጭማሪ በማይደረግባቸው ምርቶች ላይ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን እንደሚሰጡ ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል። ዋይት ሐውስ አሜሪካ የታሪፍ ጭማሪ የምታደርገው ከሀገራት ጋር በመደራደር የተሻለ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት በማሰብ መሆኑን ገልጿል።
ዶናልድ ትራምፕ በዓለም ላይ ያለውን ‘የተዛባ’ ያሉትን የንግድ ሥርዓት ማስተካከል፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር እና ፋብሪካዎችን ወደ አሜሪካ መመለስ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን እንደሚተገብሩ አስታውቀዋል። ነገር ግን ይህ ጣልቃ ገብነት በስቶክ ማርኬት ላይ ከፍተኛ ግሽበት ያስከተለ ሲሆን፣ የዓለም ንግድን በመቀነስ በሥራ እና በግለሰቦች ኢኮኖሚ ላይ መቀዛቀዝን ያስከትላል የሚል ስጋትንም ፈጥሯል ሲል ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም