
በመጪው ክረምት ሀገራችን የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ መጠናቀቅን የሚያበስረውን ሪቫን ከመቁረጥ ባሻገር፤ ክረምት በመጣ ቁጥር የሚከናወነውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከቀደሙት ወቅቶች በተሻለ እና በተነቃቃ መንገድ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቶችን እየጨረሰች ነው::
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተራቆቱ መሬቶችን በደን ከመሸፈን ባለፈ ለኑሮ የተመቻች ሀገር ለመጪዎቹ ትውልዶች ለማስረከብ የሚያስችል እንደሆነ በብዙ ተነግሯል:: አፈርን ከመከላት፤ ወንዞች እና ሐይቆች በደለል ከመሞላት እንዲሁም አፈርን ከመሸርሸር ለመጠበቅ እንደሚረዳ እንዲሁ::
መርሐ ግብሩ ለዱር አራዊቶች እና ለአእዋፎች ዘላቂ የተሻለ የተፈጥሮ አካባቢ ለመፍጠር ይረዳል፤ ለዜጎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ከመሆን ባለፈም በምግብ እህል እራሳችንን ለመቻል ለምናደርገው ሀገራዊ ጥረት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው።
በቀጣዩ ክረምት ሰባተኛ ዓመቱን የሚያከብረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሀገርን እንደ አትሌቶቻችን በዓለም መድረክ በክብር እያስጠራ ያለ ታሪክ ተሻጋሪ ሥራ ነው:: በደን ጨፍጫፊነት ትታወቅ የነበረችውን ሀገራችን ደን በመትከል ተጠቃሽ እንድትሆን አድርጓታል:: በድርቅና በረሃብ ይጠራ የነበረውን የሀገራችንን ስም በበጎ የቀየረ አመርቂ ሥራ ነው::
ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሲጀመር 23 ሚሊዮን ሕዝብ ባደረገው ተሳትፎ 353 ሚሊዮን 533 ሺህ 666 ችግኞች በአንድ ቀን መትከል እንደተቻለ ይታወሳል:: አኃዙ ለመትከል ከታቀደው በ200 ሚሊዮን ወይም 75 በመቶ ብልጫ ያለው ነበር:: ይህም 60 ሚሊዮን ችግኞች በአንድ ቀን በመትከል በጊነስ ወርልድ ቡክ ሪከርድ ያስመዘገበችውን ሕንድ ያስከነዳ ብልጫ እና ሪከርዱን በኢትዮጵያ እንዲያዝ ያደረገ ነው::
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። እንደ ሀገር የተተከሉ ችግኞች መጠነ ፅድቀታቸው ከ85 በመቶ በላይ ነው:: የተተከሉ ችግኞች የተራቆተ መሬት በመጠበቅ፣ የውሃ ሀብትን በማሳደግ፣ የደን ምርትና ምርታማነትን በመጨመርና የፍራፍሬ ልማት ሥራዎችን በማስፋፋት እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ርብርብ ዓይነተኛ ሚና እየተወጡ ይገኛሉ።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ አንስቶ ባለፉት ስድስት ዓመታት የችግኝ ጣቢያዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ አድገዋል። ለመጪው ክረምት አረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም ከ120 ሺህ በሚልቁ የመንግሥት፣ የግል፣ የማኅበራት፣ የግብረ ሠናይ ድርጅቶችና የፕሮጀክቶች ችግኝ ጣቢያዎች፤ ችግኞች እየፈሉ ይገኛሉ።
በያዝነው ዓመት/ በ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል። የታቀደውን ግብ ለማሳካት በዋናነት የደን ዛፍ፣ የቀርከሐ፣ የጥምር ግብርና/ዘርፈ ብዙ (የፍራፍሬ፣ የመኖ እና ሌሎች) … ወዘተ የሚባሉ የችግኝ ዘር ዓይነቶች ተመርጠው የማፍላት ሥራው እየተከናወነ ነው።
ከኢትዮጵያ ደን ልማት የተገኘ መረጃ እንደሚያ መለክተው፤ በተያዘው በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 2ሺህ 247 ኩንታል የችግኝ ዘሮች (የደን ዛፍ፣ የቀርከሐ እና የጥምር ግብርና/ዘርፈ ብዙ አግሮ ፎረስተሪ) ተሰብስበው በችግኝ ጣቢያዎች የችግኝ ማፍላት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። እስካሁንም 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞችን ማፍላት ወይም ማዘጋጀት ተችሏል:: ለ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት 441 ሺህ ሄክታር መሬት የተከላ ቦታ ተለይቷል። ከእዚህ ውስጥ 50 በመቶው ወይም 220 ሺህ ሄክታር የተከላ ቦታ ካርታ ተዘጋጅቶለታል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በ2011 ዓ.ም ከተጀመረ ጀምሮ የዘንድሮን ሳይጨምር ባለፉት ስድስት ዓመታት (በችግኝ ማፍላት፣ ችግኝ አፍልቶ በመሸጥ፣ ዘር ሰብስቦ በመሸጥ፣ ችግኞችን በመንከባከብ፣ በለሙ ተፋሰሶች ላይ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በመሥራት ለአብነት ንብ በማነብ፣ በከብት ማድለብ … ወዘተ) 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ በ11 ክልሎች በተሰበሰበ መረጃ መሠረት 132 ሺህ 800 ለሚጠጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል::
ኢትዮጵያ ካላት መሬት ውስጥ 26 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በደን እንደተሸፈነ መረጃዎች ያሳያሉ:: ይህም የሚያሳየው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የደን ሽፋኑ እየጨመረ መምጣቱን ነው። የደን ሽፋኑ ለመጨመሩ በዋነኝነት ተጠቃሽ የሆነው ደግሞ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ነው።
በዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት ጥናት እንደሚያመላክተው፤ እንደ ሀገር ከ2000 እስከ 2013 ዓ.ም በዓመት ከ92 ሺህ ሄክታር በላይ ደን ይጨፈጨፍ ነበር፤ ይህ አኃዝ አሁን ላይ ወደ 27 ሺህ ሄክታር ዝቅ ብሏል። በንጉሡ ዘመነ መንግሥት እስከ 1960ዎቹ መጨረሻ ድረስ አኃዙ እስከ 800 ሺህ ሄክታር ደርሶ ነበር፤ በደርግ ዘመነ መንግሥት ይኸው አኃዝ በዓመት 275 ሺህ ሄክታር ደን ዝቅ ብሏል::
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ባለው አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የኅብረተሰቡ አስተሳሰብ በመቀየሩና ማኅበረሰቡ የደን ፍጆታውን በቀየው በማግኘቱ እንደ ሀገር የደን ጭፍጨፋ ከ92 ሺህ ሄክታር ወደ 27 ሺህ ሄክታር ዝቅ ብሏል። ይህ አሁን ላለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለመጪ ትውልዶች የተሻለ የመኖሪያ እና የተፈጥሮ አካባቢ ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ሀገራዊ ጥረት ተስፋ ሰጭ እንደሆነ በተጨባጭ የሚያመላክት ነው።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም