የትልቅ ራዕይ ትልቅ ውጤት

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖችን፣ ጉባኤዎችንና ሌሎች ኹነቶችን ማስተናገድ የሚያስችል ግዙፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ማዕከል ለከተማዋም ለሀገሪቱም አበርክቷል። ግዙፍ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን፣ ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት እየታወቀች የመጣችው ኢትዮጵያ በዚህ ማዕከል ደግሞ ሌላ ከፍታን ትጎናጸፋለች። ታላላቅ ኤግዚቢሽኖችንና ጉባኤዎችን በማስተናገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ሀገሮችን ጎራ እንድትቀላቀል ትልቅ አቅም በመሆን ሊያገለግል ይችላል።

ይህ አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን በመባል የሚጠራው ማዕከል በርካታ ዘመኑን የዋጁ መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት ስለመሆኑ መረጃዎች አመላክተውናል። እነዚህ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች በራሳቸው የማዕከሉን ግዝፈት ያሳያሉ።

ይህ በተለምዶ ሲኤምሲ ተብሎ በሚጠራው አደባባይ አጠገብ በተንጣለለ ስፍራ ላይ ያረፈ ማዕከል ያካተታቸው መሠረተ ልማቶች፣ የተገነባበት መንገድ ከተማዋም ሀገሪቱም ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖችን፣ ጉባኤዎችን ወዘተ. ደረጃቸውን በጠበቀ ማዕከል እንዲያስተናግዱ የሚያስችል ብቻም አይደለም። ለአዲስ አበባ ከተማም ልዩ ውበትና ገጽታን አጎናጽፏታል። የከተማዋን ውብትም ለውጭው ዓለም ለማሳየት የሚያስችል ትልቅ አቅም የተፈጠረበትም ነው።

ማዕከሉ በከተማ አስተዳደሩ ቢገነባም፣ ከከተማ አስተዳደሩም ባሻገር የሀገርም ግዙፍ ሀብት ነው። ሀገሪቱን ተመሳሳይ ማዕከላት ካላቸው ሀገሮች ተርታ በብዙ መልኩ ማሰለፍ የሚያስችል አቅም ይዞ የመጣ ነው።

በከተማ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው፤ በ40 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ይሄ ዓለም አቀፍ የኮንቬንሽን ማዕከል፣ ከሦስት ሺ እስከ አራት ሺ የሚደርሱ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችሉ ሁለት ግዙፍ አዳራሾች፣ እንዲሁም አስር ሺህ ተሳታፊዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ሌሎች ስምንት ዘመናዊ አዳራሾች አሉት። ወደ አስራ አምስት ሺህ ካሬ የሚጠጋ የውጪ ኹነት ማስተናገጃ ቦታ ስፍራም ተገንብቶለታል።

በአጠቃላይ ወደ አንድ ሺ የሚደርሱ መኝታ ክፍሎች ያሏቸው ሁለት ባለ አምስት ኮከብ ዘመናዊ ሆቴሎች የሚኖሩት ሲሆን፣ ሬስቶራንቶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የጤና፣ የመዝናኛ እንዲሁም እንደ ሱቆችና ባንኮች ላሉ ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫዎች የተመቻቸ ተደርጎ የተገነባ ነው።

በአንድ ጊዜ እስከ ሁለት ሺህ ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚያስችል የመኪና ማቆሚያ ስፍራም /ፓርኪንግ/ ያለው ሲሆን፣ ይህም ትላልቅ ኹነቶችን ሲያስተናገድ ሊገጥም የሚችለውን የፓርኪንግ እጥረት እንደሚያስቀር ታምኖበታል። የማዕከሉን መሠረተ ልማቶች በጥቂቱ ነው የጠቀስኩት።

በማዕከሉ የሚዘጋጁ ኹነቶችን ከውጭ የሚመጡ ተሳታፊዎች ወይም የኹነት አዘጋጆች በቀላሉ መታደም የሚያስችላቸው ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በጎሮ አርጎ በቀጥታ የሚያገናኝ መንገድ እየተገነባለት ይገኛል።

ከተለያዩ የከተማዋ አቅጣጫዎች ወደ ስፍራው መሄድ ለሚፈልጉም ሆነ ከማዕከሉ ወደመጡበት ለሚመለሱ የባቡር ትራንስፖርትን ጨምሮ ምቹ የመንገድ መሠረተ ልማት ባለው ስፍራ ላይ መገኘቱም በራሱ ሌላው ተመራጭ የሚያደርገው ማዕከል ነው። መንገዶች ሁሉ ወደ ማዕከሉ ይወስዳሉ ሊባልለት የሚገባ ነው።

እነዚህን መረጃዎች በመገናኛ ብዙኃን እናውቃቸዋለን፤ እነሱን ይዘን ማዕከሉን ስንጎበኝ በስፍራው የምንመለከተው ደግሞ ከመረጃዎቹም በተጨማሪ ግዙፍነቱንና ውበቱን እንድንመሰክር ያስገድደናል።

በቴሌቪዥን በመመልከት፣ ከተለያዩ የኅትመት ውጤቶች በማንበብ ስለማዕከሉ በቂ መረጃዎችን አሉኝ። የማዕከሉን ፕሮጀክት ከሥራ ጋር በተያያዘ አስቀድሜም አውቀዋለሁ። ስፍራውን በግንባታ ወቅት ላይ እያለም በርቀትም ቢሆን ተመልክቼዋለሁ።

ማዕከሉ ግንባታው ሊጠናቀቅ አካባቢ እንዲሁም ሲመረቅና ከተመረቀ በኋላ ብዙ መረጃዎች በመውጣታቸውም ማዕከሉ ምን እንደሚመስል ተጨማሪ ግንዛቤ ተፈጥሮልኛል። እናም ስለማዕከሉ የማውቀው አለኝ ብዬ አስባለሁ።

በስፋራው ተገኝቶ ማዕከሉን መመልከት ደግሞ የራሱ ፋይዳ አለው፣ ለእዚህም ብዬ፣ ሥራም ተፈጥሮ በአንድ ድንጋይ….እንዲሉ ሥራዬን እየሠራሁ ማዕከሉን በወፍ በረር አየሁት።

በተለያዩ መረጃዎች የተመለከትኳቸውን የማዕከሉን መረጃዎች መሬት ላይ ካሉት ጋር እያገናዘብኩ ጎበኘሁት። የጎበኘሁት ደግሞ ምድረ ግቢውንና ሁለት አዳራሾቹን ብቻ ነው። የምሽቱን ትዕይንት አላየሁም፤ ወደ ወለሎችም አልወጣሁም። ሌሎች አገልግሎት መስጫዎችንም አልጎበኘሁም።

ያየሁት ብቻ ከሰማሁት መረጃ ጋር ተዳምሮ ማዕከሉ በእጅጉ ግዙፍና ውብ መሆኑን አረጋግጦልኛል። ከግቢም ሆኜም ግቢው ውስጥ ሆኜ ምድረ ግቢውን ቃኝቻለሁ። ያምራል የሚለው ብቻ አይገልጸውም። ምድረ ግቢው የተገነባበት መንገድ ሣሩ፣ በሰፊ ቦታ ላይ መልማቱ ስፍራው በእጅጉ ማራኪ እንዲሆን አድርገውታል።

የተገነባለት የአረንጓዴ ስፍራ ሌላው የማዕከሉ ውበት ነው። በሰፊው የተንጣለለ ምድረ ግቢ ላይ የለማው አረንጓዴ ስፍራ ግቢውን ስጋጃ የተነጠፈበት አስመስሎታል። ግቢው በአጥር ያልተከለለና ሰፊ በመሆኑም አረንጓዴ ስፍራው የግቢው ብቻም ሳይሆን የአካባቢውም ድምቀት ሆኗል።

ነፋሻ አየሩ ሕይወትን ያድሳል፤ ነፋሱ በስፍራው ከፍ ተደርገው የተሰቀሉትን የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገሮች ሰንደቅ ዓላማዎች ፋታ እያሳጣ እንዲውልበለቡ እያደረጋቸው ያለበት ሁኔታም ለእኔ የማዕከሉ ውበት ነው።

በእጅጉ በለማው የከተማዋ አካባቢ መገንባቱም አካባቢውም ሌላ ተጨማሪ ግዙፍና ውብ መሠረተ ልማት እንዲያገኝ አድርጎታል። በውበት ላይ ውበት አሳድርቦታል።

የሰማሁት የተመለከትኩት አንድ ነገር መለስ ብዬ እንዳስታውስ አረጉኝ። ግዙፍ የኤግዚቢሽን ማካሄጃ ለመገንባት ታስቦ ሥራው ተጀምሮ ዓመታትን ማስቆጠሩም ታወሰኝ። ያኔም ግዙፍ ማዕከል ለመገንባት ራዕይ ተሰንቆ የተጀመረ ነው። ግን ዘግይቷል።

አሁን የተመለከትኩት ሁኔታ ያ ግንባታ እንኳንም ቆየ እንኳን ዘገየ አሰኝቶኛል፤ በአጀማመሩ ልክ ተገንብቶ ቢሆን ዛሬ ማዕከሉ ያካተታቸውን ግዙፍ ተቋማትና ምድረ ግቢ ሊይዝ አይችልም ነበር። አንዳንድ ነገር ለደግ ይጓተታል፤ ይቀራል፤ የዚህ ግንባታ መቆየት ለደግ ነው እላለሁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሮጀክቱን ከታሰበው በላይ አስፍቶ ሠርቶታል። በአካባቢው ያሉ ሕንፃዎችን የማዕከሉ አካል እንዲሆኑ አድርጓል። ተጨማሪ ቦታ እንዲኖረው በማሰብ ከአካባቢው ነዋሪዎችንና ተቋማትን የማንሳት ሥራ መካሄዱንም ሰምቻለሁ። በእርግጥም ከተማ አስተዳደሩ ብዙ ደክሞበታል። በምረቃው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም ፕሮጀክቱን የጀመሩት ሌሎች ናቸው። መንግሥት ደግሞ ብዙ ነገሮች እንዲካተቱበት አድርጎ ጨርሶታል።

ከተማ አስተዳደሩ ለአዲስ አበባ ከተማና ሕዝብ በአዲሱና በዘመነው የከተማዋ ክፍል ገንብቶ ያበረከተው ትልቅ ስጦታ ነው፤ ይህ ብቻም አይደለም። ኢትዮጵያም ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኹነቶችን እንድታስተናግድበት የተገነባ ነውና ለሀገር የተበረከተ ስጦታም ነው። ሰፊ ሀሳብ ተፀንሶ የተወለደበት ፕሮጀክት ሊባል ይችላል።

ሀገሪቱ እንደ ሆቴል ያሉ መሠረተ ልማቶችን ጭምር ባሟላው በዚህ ግዙፍ ማዕከል ዘና ብላ ዓለም አቀፍ ኹነቶችን ማስተናገድ የምትችልበት ትልቅ አዲስ አቅም ተፈጥሮለታል።

እንዲህ ዓይነት ማዕከላት በኮንፈረንስ ቱሪዝም በሚታወቁት እንደ ጀርመን አሜሪካ ባሉት ሀገሮች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። አንድ ማዕከል ኮንቬንሽን ማዕከል ለመባል የራሱ መስፈርት አለው። ይህ ማዕከል እነዚያን መስፈርቶች አሟልቶ ይዟል። ለእዚያም ብዙ የተደከመበት።

የተገነባበት ስፍራ ነፋሻማ መሆን፣ የአረንጓዴ ስፍራው በሚገባ መልማት፣ ከአዳራሽ ውጪ ለሚደረጉ ኹነቶች የሚሆን የተንጣለለ ግንባታ የተካተተበት መሆኑ ማዕከሉ ለሁሉም ከፍ ያሉ አገልግሎቶች ዝግጁ እንዲሆን ያደርጉታል።

ማዕከሉ ገና ከአሁኑ ተፈላጊ ሆኗል። እንደተመረቀ አካባቢ ከአስር በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ወረፋ ይዘው እንደነበር መረጃዎች አመላክተዋል። እስከ አሁን ወደ ሦስት የሚደርሱ ኹነቶች ተስተናግደውበታል።

ከምረቃው ጋር ተያይዞ ይመስለኛል አንድ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ተካሂዶበታል። ከዚያም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች የኪነጥበብ ፌስቲቫልም ለቀናት ተካሂዶበታል። ሰሞኑን ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄን አካሂዶበታል።

ታላላቅ ኤግዚቢሽኖቿን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ በሚሊኒየም አዳራሽ እና በመሳሰሉት ስታደርግ ለቆየችው ሀገር የዚህ ማዕከል የኤግዚቢሽን ማሳያ አዳራሾች ስፋት፣ አዳራሾቹ ከኤግዚቢሽን በዘለለም እንደ ሰርከስ ትርዒት ያሉትን በብቃት ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ የተገነባበት ሁኔታ፣ የተገነቡበት መንገድ፣ ለተለያዩ የውጪ ኹነቶች የተዘጋጀው ስፍራ ብቻ ሲታሰብ በአዲስ አበባ ብቻም ሳይሆን እንደ ሀገር በኤግዚቢሽን ማሳያ ስፍራ ትልቅ አብዮት ተደርጓል ማለት ያስችላል። የትልቅ ራዕይ ትልቅ ውጤት ነው።

ወደ ስፍራው ያመጣኝ አንዱ ምክንያት ሰሞኑን በማዕከሉ ተከፍቶ የነበረውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ኤግዚቢሽን ነው። ኤግዚቢሽኑ ወደ ተዘጋጀባቸው አዳራሾች ዘለቅሁ። አዳራሾቹን፣ መግቢያ መውጪያቸውን ቃኘሁ።

በሁለት ትላልቅ አዳራሾች የከተማ አስተዳደሩ በእቅፌ ውስጥ አቆይቼ ለባለ ኢንዱስትሪነት አብቅቼያቸዋለሁ ያላቸውን እንዲሁም ለኤግዚቢሽኑ ይጠቅማሉ ብሎ ያስገነባቸውን ሌሎች ትላልቅ ባለኢንዱስትሪዎች በአጠቃላይ ከ250 በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ይዘው ቀርበው አስተዋውቀዋል፤ ሸጠዋል፤ ትስስር ፈጥረዋል።

ጋርመንቶች፣ ቡና ላይ እሴት የሚጨምሩ፣ የእንጨት ሥራ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤት አምራቾች፣ ተኪ ምርት ላይ የተሠማሩ ኢንዱስትሪዎች፣ ማርና ወተት አቀነባባሪዎች፣ የብረታ ብረት ውጤት አምራቾች፣ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪዎች፣ ወዘተ. በአዳራሾቹና ከአዳራሾቹ ውጪ በተዘጋጁ ስፍራዎች በብዛት ቀርበዋል። ማዕከሉ በሁለት ግዙፍ አዳራሾቹ እነዚህን ሁሉ አስተናግዶም አየሁ ያለ አይመስልም።

የካፌና መሰል አገልግሎቶቹ፣ ሙዚቃው፣ ወዘተ. ደግሞ ሌሎች ጎብኚዎች ተረጋግተው ማዕከሉን እንዲመለከቱ የሚያስችሉ አገልግሎቶች ናቸው። ማዕከሉ ዛሬም ድረስ ከተለያዩ ተቋማት በመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተጎበኘ ነው። የኤግዚቢሽኑ ጎብኚዎችም ሌሎች የማዕከሉ እንግዶች ናቸው።

በስፍራው የተገኘሁት ኤግዚቢሽኑ በተከፈተ በሦስተኛ ቀን፣ ሊዘጋ በዋዜማ ላይ እያለ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ከእነግለቱ ነው የሚያሰኝ ግብይት፣ ጉብኝትና ትውውቅ አይቼበታለሁ። ኤግዚቢሽኑ የተከፈተ እለት እና በመዝጊያው እለት ሊኖር የሚችለውን መጨናነቅ ደግሞ መገመት ይቻላል።

ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳል ነውናም ማዕከሉ እጅግ ግዙፍ ማዕከል ነው። ከሚነገርለትም በላይ ግዙፍ ነው። ለታሰበለት ዓላማ የደረሰ የከተማዋም የሀገርም ኩራት ሊባል ይችላል።

አካባቢውንም በብዙ መልኩ ሊቀየር የሚችል ማዕከል ነው። ዝግጅቶችን ለመታደም ስፍራውን ለመጎብኘት ሆቴሎቹን ለመገልገል ወዘተ በቀጣይ በርካቶች አካባቢውን እንደሚረግጡ ይጠበቃል። እነዚህን ሁሉ ታሳቢ ያደረጉ አገልግሎቶች እንደሚኖሩ ቢጠበቅም የአካባቢው የንግድ ተቋማትና የመሳሰሉት በእጅጉ እንደሚነቃቁ መገመት ይቻላል።

ማዕከሉ የተገነባው በዋናነት ዓለም አቀፍ ኹነቶችን ታሳቢ ተደርጎ እንደመሆኑ እነዚህን ኹነቶች መሳብ ቀጣዩ ትልቅ ሥራ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። እርግጥ ሀገሪቱ እስከ አሁንም ዓለም አቀፍ ኹነቶችን በመሳብ በኩል ጥሩ እየሠራች ትገኛለች። ለእዚህም ባለፉት ወራት ከ80 በላይ ዓለም አቀፍ ኹነቶችን ያስተናገደችበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል።

በማዕከሉ መሥራት የሚፈለገው ከዚህ በእጅጉ የሚልቁ ኹነቶችን ማስተናገድ እንደሆነ ይታመናል። ለብልህ አይነግሩም ለአንበሳ አይመትሩም እንደሚባለው የሚመለከታቸው አካላት በዚህ በኩል በትኩረት እንደሚሠሩ ቢታወቅም፣ ማዕከሉን በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በሰፊው ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። የቱሪዝም ዘርፉ ባለሙያዎችም ይህን ይመክራሉ።

በእዚህ ማዕከል ዓለም አቀፍ መድረኮች የሚካሄዱ እንደመሆናቸው እነሱን ማግኘት የሚቻለው ከዓለም አቀፍ ገበያው እንደመሆኑ በእዚህ ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል።

በተለያዩ ሀገሮች የኮንቬንሽን ማዕከል በሚዘጋጁ ሁነቶች ላይም በመገኘት ተሞክሮ መጋራት ልምድ መለዋወጥ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ አስባለሁ። ይህ እየተደረገ ሊሆን ቢችልም አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ይህን ጥረት ከእጥፍም በላይ ማሳደግን የግድ ይላል።

በማዕከሉ ለመስተናገድ የሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ቁጥር ገና እንደሚጨምር ይጠበቃል። ማዕከሉ በስፋት እንዲተዋወቅ ሲደረግ የሚያመጣቸው ጉባኤዎችና ኤግዚቢሽኖች ይበረክታሉ።

ይህ አንድ ነገር ሆኖ ግን ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን መሳብ ቀጣዩ ትልቅ ሥራ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፤ ይህም በቴክኖሎጂ ሊደረግ ቢችልም፣ ከዚያም በዘለለ በኮንቬንሽን ማዕከላቸው የሚታወቁ ሀገሮችን ተሞክሮ በየጊዜው እየተገኙ መቅሰምም ያስፈልጋል።

ማዕከሉን ለማፍራት ትልቅ ሥራ ተሠርቷል፤ የጀመሩትም የጨረሱትም ትልቅ ዓለም አቀፍ ኹነት ማዘጋጃ ማዕከል እውን በማድረግ ራዕያቸውን ተሳክቷል። ይህ ራዕያቸው የበለጠ የሚሳካው ደግሞ ማዕከሉ የሚጠበቅበትን ኹነት ከዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳድሮ ማምጣት ሲችል ነው፤ ውድድር መጪው ትልቅ ሥራ ይሆናል።

በተለይ ዓለም አቀፍ ኹነት የሚካሄድበት እንደመሆኑ እነዚህ ኹነቶች ደግሞ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ትልቅ ፋይዳ ያላቸው እንደመሆናቸው በኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ ለመሆን እየተደረገ ያለው ጥረት በእዚህ ማዕከል በሚገባ መታየት ይኖርበታል።

የኮንቬንሽን ማዕከል አስፈላጊነትን በማመን ግንባታው መካሄዱ አንድ ነገር ሆኖ ሀገሪቱ የኮንፈረስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት በቱሪዝም ሚኒስቴር ስር ኮንቬንሽን ቢሮም ከፍታለች። ይህ ቢሮ አሁን ሰፋፊ ሥራዎች ይጠብቁታል። ማዕከሉ ገበያ በማፈላለግ የሚሠራ የራሱ አደረጃጀት ሊኖረው ይችላል ተብሎ ይታሰባል፤ ያ እንዳለ ሆኖ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በመጠቀም፣ የዓለም አቀፍ መድረክ ተሳታፊዎችን እንደ አንድ አስተዋዋቂ ለመጠቀም አጥብቆ መሥራት ያስፈልጋል።

ኃይሉ ሣሕለድንግል

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You