አዲስ ዘመን ድሮ

ፈገግታና አግራሞትን የሚያጭሩ፣ ትውስትና ትዝታን የሚጥሉ የዘመን አጋጣሚና ሁኔታዎችን በአዲስ ዘመን ድሮ ቅኝቶቻችን፣ ጊዜን ወደኋላ ስበን ሁሉንም የዛሬን ያህል እንጋራቸዋለን። በመከተል ተያዙ ስለተባሉ 50 ወንበዴዎች፣ ጓደኛውን ገድሎ ለጅብ የሰጠው ሰውዬ ድርጊት፤ እንዲሁም ጠንቋዩና 32 አስጠንቋዮቹ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል። ከጳውሎስ ኞኞ አምዶች መካከል “ለወይዛዝርት ገጽ” ከተላኩ ደብዳቤዎች አንደኛው ለቅምሻ ይሁነን፡፡

ከመተከል 50 ወንበዴዎች በአዳኝ

ቡድን ተያዙ

ደብረ ማርቆስ(ኢ.ዜ.አ)- በመከተል ወረዳ አውራጃ አስተዳደር በሠፊው ሕዝብ ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ሲያደርሱ የቆዩት 50 ወንበዴዎች ሰሞኑን ውንብድና ለማጥፋት በተሠማራው አዳኝ ቡድን ተይዘዋል፡፡

በሻለቃ አበበ ደስታ ተሰማ የጓንጉ ወረዳ አስተዳዳሪና በግራዝማች ተደስ ጀምበሬ የሚመራው ይኸው የአዳኝ ቡድን ወንበዴዎቹን የያዘው ከሰኔ 15 ቀን እስከ 26 ቀን 1967 ዓ.ም ድረስ ባደረገው አደን መሆኑን በአውራጃው በተቆጣጣሪነት የተመደቡት የአሥር አለቃ ያለው ሺበሺ ገልጠዋል፡፡

የተያዙትም ወንበዴዎች በፖሊስ ጣቢያና በወህኒ ቤት የሚገኙ ሲሆን፤ የወንበዴዎቹ አዳኝ ቡድን አሁንም የማደን ተግባር እንደቀጠለ መሆኑን የአውራጃው አስተዳዳሪ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

(አዲስ ዘመን ሐምሌ 1 ቀን 1967 ዓ.ም)

ጓደኛውን ገድሎ ለጅብ ሰጥቷል የተባለ እጁን ለፖሊስ ሰጠ

አዲስ አበባ ውስጥ በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቦሌ ኮተቤ እየተባለ በሚጠራው ገጠራማ አካባቢ ጓደኛውን ገድሎ ለጅብ ሰጥቷል የተባለ ተጠርጣሪ ግለሰብ በቅርቡ እጁን ለፖሊስ ሰጠ፡፡

የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን አስተዳደር ከትናንት በስቲያ እንደገለጸው ግለሰቡ ደቡ ዳቢ የተባለውን ጓደኛውን በጩቤ ወግቶ የገደለው፤ አምጣልኝ ሳልለው ከሴት ጓደኛዬ 50 ብር ተቀብሎ ለግል ጥቅሙ አውሏል በሚል ነው፡፡

ግለሰቡ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ከለሊቱ ሰባት ሰዓት የካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመድረስ እጁን መስጠቱን ገልጿል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባሎች ወደ ሥፍራው ባመሩበት ወቅት የሟች አስክሬን በጅብ መንጋ እየተበላ እንዳለ ማግኘታቸውንና ጅቦቹን በማባረር ጥቂት የሟች የሰውነት ክፍሎች ለማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 20 ቀን 1997 ዓ.ም)

ጠንቋይና 32 አስጠንቋዮች በቀበሌ

ማኅበር ተያዙ

በቦሌ ወረዳ በ03-በ04-31 ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆነች ወ/ሮ ዘሐራ ፋንታ የተባለች ሴት ሕዝቡን ሥራ በማስፈታት ሕገ ወጥ የሆነ የጥንቆላ ተግባር ስትፈጽም ተገኝታ ለማስጠንቆል ከሔዱት ሰላሳ ሁለት ሰዎች ጋር ተይዛ ፖሊስ ጣቢያ ትገኛለች፡፡

በአንደኛዋ ተከሳሽ ቤት ይህንኑ አስነዋሪ የሆነ የማስጠንቆል ተግባር ሲፈጽሙ ከተገኙት 32 ሰዎች መካከል 22 ሴቶችና 10 ወንዶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ ሁለት ወታደሮች እንደሚገኙ ምርመራውን የያዘው ወታደር ኪሮስ ሞልቶት አስረድቶቷል፡፡

(አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 1979 ዓ.ም)

የዓይን ጠብታ ወይንስ ቡና?

ስለ እራስ ወዳድ ነጋዴዎች ያልተባለና ያልተጻፈ ነገር የለም። ለሚሰጣቸው ገንዘብ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ብዙ ተመክሯል። ይሁን እንጂ በግል ጥቅም ታውረው ነውሩን እንደጌጥ በማየት ከብዝበዛ ሥራቸው ያልታቀቡ ጥቂት አይደሉም፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት 2 እና 25 ሳንቲም የነበረው አንድ ፍንጃል ሲኒ ቡና ዛሬ 50 እና 55 ከዚያ በላይ አድርገውታል። ይግረማቸሁ ብለው ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አካባቢ ያሉት መደዳ ቡና ቤቶች የዓይን ጠብታ ይመስል ከፍንጃሉ ግማሽ የወረደ ከጉሮሮ የማይደርስ ቡና ጠብ እያደረጉ ማቅረብ ጀምረዋል። ድርጊቱ በተለይ የቡና ሱስ ያለብንን ሰዎች ቅሬታ አሳድሮብናል ሲሆን ራሳቸው አገልግሎታቸውን ያስተካክሉ። አሻፈረን የሚሉ ከሆነ ጉዳዩ በቸልታ መታለፍ ስለሌለበት የሚመለከተው ያስብበት፡፡

(አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 1976 ዓ.ም)

ለወይዛዝርት ገጽ አዘጋጅ

-አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ

*አንዳንድ ሴቶች ጥፋታቸው ሳይታያቸው እየቀረ ሞራላችን የተበላሸው በወንዶች ነው ሲሉ እሰማለሁ። ተሳስተዋል። አንዳችን በአንዳችን ላይ ልናመሃኝ አንችልም። ሁላችንም ተበላሽተናል። የብልሽቱ መሠረት በሊቃውንት ተመርምሮ መታወቅ አለበት። ሴቱም ወንዱም ሰካራምና ዝሙተኛ ሆነ። የመጥፊያው ምንጭ አልታወቀም። እንዲያው ሴቶች በድፍረትና በይሉኝታ ማጣት ከወንዱ ብሰዋል። ባይን፣ ባፍንጫና በግንባር ልዩ የመነጋገሪያ ቋንቋ ከፈጠሩ ጊዜው አጭር አይደለም። በትምህርት ቤትም ቢሆን ቦታ ሲያጣብቡ የሚገኙት እስከ 6ኛ ክፍል ነው። ሕግ አውቀው ዳኝነት አይረዱም። አስተዳደር ተምረው አገር ገዢ አልሆኑም። በወታደርነትም ሙያ ቢሆን በወህኒ ቤት ዘበኝነት የተቀጠሩትን ብቻ እናያለን። የባልትና ሙያ ኖሯቸው ያሳዩት ግልጋሎት የለም። በዲሞክራሲ ሕግ መሠረት ከእኛ ጋር እኩል ሁኑ ብለን መብት ብንሰጣቸው ለሥራ የኛን አርአያ በመከተል ፋንታ በየክርታሱ እየተወሸቁ ተበላሽተው እኛንም በከፊል አጠፉን። ለሀገር ልማትና ለወሰን ጥበቃ በየበረሃው ስንከራተት እነሱ ሊያበረታቱን ሲገባ ፍቅርህ ገሎኝ ሞቼ ተቀብሬያለሁና በቶሎ ድረስልኝ እያሉ በማባበል ያሸንፉናል። ከሴት ተለይቶ ለመኖር ተፈጥሮን መግታት አስቸጋሪ ሆነ። የሴቶቹ ጉድ ብዙ ቢሆንም፤ በጠቅላላው የማኅበሩ ጠላቶች እነርሱ ናቸው ለማለት ብደፍርም፤ እነርሱን ለዚህ ያበቃቸውና እኛንም ለውድቀቱ ያንበረከከን፤ መንፈሳችንን ያላላው የተዳፈነው ነገር ይታወቅ እላለሁ። በእኛም በነሱም አይፈረድም። አቶ ጳውሎስ ምን ይላሉ?

ሽመልስ አስፋው(ከገሙ ጎፋ)

-እኔስ የምለው በጥቂቱ ነው፤ ሴቶቹ አይብዙ እንጂ በሁሉም ሥራ ቦታ አሉ። በእኛም በእነሱም ካልተፈረደ በማን ይፈረድ? በእግዜር ነው? ብቻ ብቻ በአዳምና ሐሄዋን ጊዜ የተጀመረ ሰበብ እስካሁንም አለ፤”ጌታዬ ሔዋን ናት” “የለም ጌታዬ! እባቢቱ ናት አኮ”፡፡

(አዲስ ዘመን መጋቢት 16 ቀን 1969 ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You