
የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄን ዳር እስከ ዳር ለማቀጣጠል ግልጽ፣ስሜት ኮርኳሪና አሳማኝ የሆነ ራእይን የሰነቀ መልዕክትን በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ራስን በመቻል ወይም በself reliance እና በብሔራዊ ኩራት ዙሪያ ቀርጾ መሥራት ይጠይቃል። አዎ ንቅናቄውንም እንደ የሕዝብ ግንዛቤ ወይም ማኸዘብ ወይም popularise፣የፖሊሲ ቅስቀሳ ወይም policy advocacy፣ የወጣቶች እና የሠራተኞች ተሳትፎ፣ የንግድ አጋርነት እና የጠንካራ የሚዲያ ተሳትፎ ንቅናቄ ባሉ ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ መታነጽ ይጠይቃል። ከዚህ ጎን ለጎን የንቅናቄውን ተጽዕኖን ለማሳየት በአንድ ክልል ወይም የከተማ አስተዳደር የንቅናቄውን ምልክቶች፣መፈክሮች እና ታሪኮችን በማጉላት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤታማ መሆኑን የሚያሳይ ሙከራ ወይም pilot ማስጀመር ያሻል።
ከመንግሥት፣ ከመገናኛ ብዙሃን፣ ከኢንዱስትሪ እና ከሲቪል ማሕበረሰብ ጋር ስትራቴጂካዊ ቅንጅቶችን መፍጠር፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ዲያስፖራዎች ማሳተፍ፤ ስኬቶችን እየተከታተሉ እውቅና መስጠት፤ በአንድ ኢንዱስትሪ ወይም ፋብሪካ የተገኘን አርዓያነት ያለው ተሞክሮ ቀምሮ ሀገር አቀፋዊ ማድረግ እና ማስፋት ይፈልጋል። የ”ኢትዮጵያ ታምርት”ንቅናቄን ከእነዚህ የንቅናቄ አላባውያን ወይም መሠረታውያን አልያም elements ጋር ስገመግመው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ሆነ የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ይበል የሚያሰኝ እና ለሌላ ንቅናቄ አርዓያ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ለዚህም በልካቸው ከመቀመጫዬ ብድግ ብዬ ባርኔጣዬን አንስቼ እውቅና መስጠት እወዳለሁ።
የንቅናቄው ውጤታማነት ማሳያዎች ማነቋቸው ተፈቶ ወደ ሥራ የገቡ ኢንዱስትሪዎች ብዛት፤ የፈጠሩት ሰፊና አስተማማኝ የሥራ ዕድል፤ ዜጋው በሀገሩ ምርት ለመኩራት እያሳየው ያለው ተስፋ፤ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በመግባታቸው ያስገኙት የውጭ ምንዛሬ፤ለሀገራዊ ጥቅል ምርቱ ያበረከቱት አስተዋፅኦ፣ ወዘተረፈ ናቸው። ከፍ ሲል ባነሳኋቸው የንቅናቄ ማቀጣጠያ ማንጸሪያነት የ“ኢትዮጵያ ታምርት”ታላቁ ሩጫን እና ኤክስፖ እንድትመለከቷቸው እንደሚከተለው አቀረብኩላችሁ።
በመጪው እሁድ ሚያዝያ 19 ለ3ኛ ጊዜ ከመስቀል አደባባይ ተጀምሮ መስቀል አደባባይ የሚያልቅ ኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ይካሄዳል፤ በዚህ ሩጫ 1ኛ ለሚወጡ በሁለቱም ፆታዎች 300,000 ብር 2ኛ ለሚወጡ በሁለቱም ፆታዎች 200,000 ብር፤3ኛ ለሚወጡ በሁለቱም ፆታዎች 100,000 ብር፤ ሽልማቱ በሁለቱም ፆታዎች እስከ 10ኛ ድረስ ይቀጥላል፤ እንዲሁም አንደኛ የሚወጡ ክለቦች በሁለቱም ፆታዎች 100,000 ብር ይሸለማሉ፤ በርካታ ታዋቂ አትሌቶች የሚሳተፉበት የ10 ኪ.ሜ ሩጫ ላይ ይሳተፉ፤ ለመመዝገብ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይምጡ የሚለውን ማስታወቂያ ሰማሁ።
ወዲህ ቀለስ ስል ደግሞ፤ ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ብልህ አምራች ምርቱን አምርቶ ወደ ገበያ ለማስገባት ሌት ከቀን ሳይታክት በጥራት ይሰራል፤ ምርቱን በቴክኖሎጂ ያዘምናል በገበያውም ብቁ ተወዳዳሪ ይሆናል፤ ዛሬ ያመረቱትን ምርት የት ልሽጥ ብለው አይጨነቁ ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ አለልዎት፤ ኢትዮጵያ እጇን ታጥባ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥራት ያመረተቻቸውን ምርቶች በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ትሸጣለች፤ አምራች የኢንደስትሪ ባለቤቶች በኢትዮጵያ ታምርት ላይ በመሳተፍ በቀጥታ ከገዢ ጋር ይገናኙ ይላል።
ኢንዱስትሪዎቹስ ምን ያመርታሉ? ፈርኒቸር፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የኮንስትራክሽን ግብአቶች፣ ማሽነሪ እና ተሽከርካሪ፣ ኬሚካልና የንፅህና መጠበቂያዎች፣ ምግብና መጠጥ፣ ፋርማሲዩቲካል፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳ፣ አልባሳት፣ ኮስሞቲክስ፤ ወ.ዘ.ተ፤ ሁሉንም ምርቶች በሚያገኙበት በኢትዮጵያ ግዙፉ ኤክስፖ ላይ ይሳተፉ! ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከሚያዝያ 25 እስከ 29 በአዲስ ኢንተርናሸናል ኮንቬንሽን ሴንተር ይካሄዳል። መመዝገቢያ ቦታ አራት ኪሎ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚል ሌላ ቀልብ ያዥ ማስታወቂያ ሰማሁና ሁለቱም ሁነቶች ተመጋጋቢና ተያያዥ መሆናቸውን ታዘብኩ።
በንቅናቄው የተገኙ ስኬቶችንና ውጤቶችን በወፍ በረር ስንመለከት፤ከወጪ ንግድ ከ140 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን፤ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ከ27 ቢሊዮን በላይ ብር ብድር መቅረቡን፤ ከ390 ኢንዱስትሪዎች በላይ ዳግም ወደ ሥራ መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል። በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አያና ዘውዴ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በዚያ ሰሞን እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ቅንጅታዊ አሠራር በተደረገው የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ የተገኙ ውጤቶች በርካታ ናቸው። በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሰባት ወራት የአምራች ኢንዱስትሪዎች ወጪ ምርት መጠንና ገቢን ለመጨመር በተደረገው ጥረትም 74 ሺህ 955 ቶን ምርት ወደ ውጪ እንዲላክ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ 140 ሚሊዮን 313 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማስገኘት ተችሏል።
ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የብድር አቅርቦትን ለማሳደግ በተደረገው የተቀናጀ ክትትልና ድጋፍ 23 ቢሊዮን 71 ሚሊዮን ብር ብድር ማቅረብ ተችሏል ያሉት አያና (ዶ/ር) ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ሦስት ቢሊዮን 44 ሚሊዮን ብር የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ ተችሏል ሲሉ ጠቅሰዋል። ከዚህ ውስጥ የሊዝ ፋይናንስ ሁለት ቢሊዮን 52 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የሥራ ማስኬጃ አንድ ቢሊዮን 384 ሚሊዮን ብር ብድር ማቅረብ መቻሉን አብራርተዋል።
አያና ዘውዴ (ዶ/ር) 129 የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና 292 የሀገር ውስጥ ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ አንድ ሺህ 493 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙ መደረጉን ገልጸው፤ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተውና ማምረት አቁመው ከነበሩ 460 ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 390 ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። በተጨማሪም በትግራይ ክልል ብቻ 217 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ተደርጓል። በዚህም ለ120 ሺህ 667 ዜጎች ቋሚ ሥራ እድል መፍጠር ተችሏል።
ኢትዮጵያን በተሻለ ፍጥነት ማሳደግ ካስፈለገ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የግድ መጠቀም አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ዓመት በሚሊኒየም አዳራሽ የተሰናዳውን የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ከከፈቱ በኋላ፤ ጥራትና ውበት ያላቸውን የሀገር ውስጥ ምርቶችን በሰፊው በመጠቀም በጋራ ማደግ ይገባል። ልብስ አዘጋጅተንም መጀመሪያ የሀገሬውን ሰው ማልበስ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ አምርታ ከምትልከው ይልቅ ከውጭ የምታስገባው ምርት ተመን በቢሊዮን ዶላሮች እንደሚልቅ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አልባሳትን ለአብነት በማንሳት በሀገር ውስጥ ጥራትና ውበት ያላቸው ምርቶች በመኖራቸው እኔም እየተጠቀምኩ ነው ብለዋል። ስለዚህ በሀገር ውስጥ ያለን ምርት መጠቀምን መለማመድ ይኖርብናል ማለታቸው አይዘነጋም።
“ኢትዮጵያ ታምርት !” የሚለው መሪ ቃል ወይም ሞቶ አስኳል ወይም ሞተር ኢንዱስትሪው ነው። በአንድ ኢኮኖሚ ውስጥ ምርትን አገልግሎትን የማምረት ሂደት ኢንዱስትሪ ይሰኛል። በውስጡ ሰፊ ዘርፎችን ያካትታል። ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ግብርና፣ የማዕድን ፍለጋና ልማት፣ መጓጓዣና መሠረታዊ አገልግሎቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ። ለአንድ ሀገር ልማትና ዕድገት ኢንዱስትሪ ወሳኝ ዘርፍ ነው። ለዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ለሀገር ሀብት ያካብታል። በአጠቃላይ ለሁለተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ለዚህ ነው የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በቅርበት ለመፍታት እና የዘርፉን ምርትና የማምረት አቅም ለማሳደግ ዓላማ አድርጎ “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚል ሀገራዊ የንቅናቄ የተጀመረው፡፡
ባለፉት ዓመታት የአመራረት ዘዴና የምርት ውጤቱ በአዳዲስ ቴክኖሎጂና በሸማቾች ተለዋዋጭ ባህሪና ፍላጎት የተነሳ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ላይ ይገኛል። የአውቶሜሽንና የዲጂታላይዜሽን መስፋፋት የኢንዱስትሪዎችን የማምረት ብቃትና ምርታማነትን በእጅጉ አሳድጎታል። በአናቱ የበይነ መረብ ንግድ ወይም የe-commerce መስፋፋት የችርቻሮ ኢንዱስትሪውን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋገረው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የ4ኛው ኢንዱስትሪ አብዮት ወይም የ “industry 4.0” አልያም የሰው ሰራሽ አስተውሎትና የሮቦቴክስ ወደ ኢንዱስትሪው መቀላቀል የዘርፉን መልከዓ እንደ አዲስ እየበየነው ይገኛል።
ዘርፉ በአሕጉራችንም ሆነ በሀገራችን ኋላ ቀርና ዘመኑን የማይዋጅ ነው። እንደ ነዳጅ ፣ ጋዝ፣ ማዕድንና የግብርና ውጤት ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምር ወደ ውጭ በመላክ ላይ የተንጠለጠለ ነበር ማለት ይቻላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን እሴት የተጨመረባቸውን በርካታ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ወደ ውጭ መላክ ተጀምሯል። በአህጉሩ ኢንዱስትሪ በተወሰኑ ዘርፎች ተስፋ የሚጣልባቸው ውጤቶች በመመዝገብ ላይ ቢሆንም ገና ያልተሻገራቸው በርካታ ተግዳሮቶች እንደ ሰሜን ተራሮች ጀብራ ከፊቱ እንደተገተሩ አሉ።
የመሠረተ ልማት ዕጥረት፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል ዕጥረት ፣ ሙስና፣ የተንዛዛ ቢሮክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር ችግርና ሌሎች። እነዚህ ተግዳሮቶች የአፍሪካንም ሆነ የሀገራችንን ኢንዱስትሪ ከምዕራባውያንና በመልማት ላይ ካሉ ሀገራት ጋር ተፎካካሪና ተወዳዳሪ እንዳይሆን ቀይደው ይዘውታል። እነዚህን ማነቆዎች ለመፍታት የፖሊሲ ማሻሻያና የመርሀ ግብር ለውጥ እያደረጉ ነው። የሀገራችንን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያንና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በአብነት ማንሳት ይቻላል።
ከዚህ ጎን ለጎን መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ኢንቨስት ማድረግ ፤ ለውጭ ባለሀብቶች ማበረታቻዎችን ማቅረብ፤ የትምህርት ጥራትን ማሻሻልና ኢንዱስትሪው በተከፈተበት አካባቢ ያለን አምራች ኃይል ማሰልጠን ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። የታዳሽ ኃይል መስፋፋት ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ መነቃቃትና የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ዕድገት ተስፋ የሚጣልባቸው ስኬቶች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ። እነዚህ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ ምርታማነትን የማሳደግና በአህጉሩ የኢኮኖሚ ዕድገትን የማሳለጥ ሚና እንዳላቸውም ይታመናል።
በተለይ ወደ ሀገራችን ስንመጣ በዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ እያመጣ ባይሆንም ላለፉት በርካታ ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እየተመዘገበ መሆኑ አይካድም ጥያቄው ዕድገቱ ፍትሐዊና አካታች ነው፤ በዜጎች ገበታ ላይም ሆነ አኗኗሪ ላይ ለውጥ አምጥቷል ወይ የሚለው ነው። የሀገሪቱ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርትም ሆነ የነፍስ ወከፍ ገቢው ቢያድግም፤ ኢኮኖሚው ላይ የገነገነው መዋቅራዊና ተቋማዊ ትብታብ ትሩፋቱ ለዜጎች እንዳይተርፍ አድርጓታል። የዋጋ ግሽበቱን ተከትሎ የተከሰተው የኑሮ ውድነት እና የተንሰራፋው ሥራ አጥነት ጥላ እንደጣለበት ይገኛል። ሀገራችን ግዙፍና የተለያየ የግብርና ዘርፍ ቢኖራትም፤ የውጭ ንግድ መር ማኑፋክቸሪንግ ላይም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።
በነገራችን ላይ ካለው እምቅ አቅም የተነሳ ቀደም ባሉት ዓመታት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ የተሠራው ሥራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። አሁንም ሀገሪቱ ካላት የሰው ኃይል ፣ ግብዓትና ገበያ አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ ነው። መንግሥት ይሄን በመረዳት ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች የታክስ እፎይታ በመስጠት፣ መሠረተ ልማት በማሟላት፣ ሙስናን ለማስወገድ ፣ ማነቆዎችን በመፍታትና ቀልጣፋ የፋይናንስ አቅርቦትን በማመቻቸት ለውጥ ለማምጣት ጥረት እያደረገ ነው። የጨርቃጨርቅ ፣ የልብስ ፣ የሌዘር ፣ የቆዳ ውጤቶች፣ ሲሚንቶና ሌሎች የግንባታ ቁሳቁሶች ከሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ዋና ዋናዎች ናቸው። ሌላው ትኩረት እያገኘ ያለው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ቴክኖሎጂ ነው። መንግሥት የቴክኖሎጂ መንደርና መናኸሪያ ያቋቋመ ሲሆን ፣ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን በፋይናንስ እየደገፈና እያበረታታ ይገኛል። በዘርፉ የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ችግሮችና ዓለም አቀፍ ጫናዎች የሚቋቋም ኢንዱስትሪ እስከ መፍጠር እንደሚዘልቅ ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ጫናዎች እየተፈተነ ያለውን ኢንዱስትሪ መታደግ የሚያስፈልግበት ነባራዊ ሁኔታ መፈጠሩን ያመላክታል። በጦርነትና በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ሥራቸውን አቁመው ቆይተዋል። ቀሪዎቹም ማምረት ከሚገባቸው ከ50 በመቶ በታች እያመረቱ ነበር ። በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚደረጉ ግጭቶች ወደ ውጭ በሚላኩና ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጫና በማሳደሩ ኢትዮጵያንና መሰል በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው እንደሆነ እንደ ማሳያ ሊወሰድ ይችላል።
ኢትዮጵያ በእነዚህና በሌሎች የተለያዩ ችግሮች ሳቢያ የተጎዳውን ኢንዱስትሪ በዘላቂነት ለማቋቋም “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚል ንቅናቄ መጀመሯ ውጤት ማሳየት ጀምሯል። “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚለው ንቅናቄ በዓለም ላይ በሚያጋጥም ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችና ማዕቀቦች የሚረበሸውን ኢንዱስትሪ ለመታደግና ዘላቂ እድገት እንዲኖረው ያግዛል። ኢትዮጵያ ጠንካራና ተወዳዳሪ ሀገር ሆና ውጫዊ ጫናዎችን ለመቋቋም ያላትን አቅም አሟጣ መጠቀምና ማምረት ያለባት ጊዜው አሁን ነው። ራስን መቻል የሉዓላዊነትና የክብር ጉዳይ ነው። በእጃችን ላይ ያለውን ሀብት ተጠቅመን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የምንቀይርበትን ንቅናቄ ጀምረናል። ንቅናቄው በ2022 ዓ.ም እንደ ሀገር የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ለመተግበር ሰፊ እድል ይኖረዋልም።
ኢትዮጵያ በርካታ ጸጋ እና ሰፊ የሰው ኃይል እንዲሁም የተመቻቸ ፖሊሲ ቢኖራትም ይህንን ወደ ሀብት የመቀየርም ሥራ ይቀራታል። የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ላይ የሚያጋጥሙ የአጭር ጊዜ ችግሮችን መፍታት ብቻ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የሚያጋጥሙ ስጋቶችን መፍትሔ እንዲሆን እየተሠራ ነው። ኢትዮጵያ ያላትን ጸጋዎች በመጠቀም በቀጣይ አስር ዓመታት ኢንዱስትሪው ሀገራዊ የምርት ድርሻው ከ6.9 በመቶ ወደ 17.2 በመቶ ለማሳደግ ግብ ተጥሏል። ሀገሪቱ በ2022 ዓ.ም ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በዓመት ወደ ውጪ ከሚላክ ምርት አሁን ከሚገኘው 4 መቶ ሚሊዮን ዶላር ወደ 9 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ ዋነኛ ዓላማው ነው። በተጨማሪም የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የማምረት አቅም ወደ 85 በመቶ ማሳደግ እንዲሁም ከ5 ሚሊዮን ለሚልቁ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው።
ከተጀመረ ሶስት ዓመት ያለፈው የ’ኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ፤ ባለድርሻ አካላትም ተቀራርበው መሥራት እንዲችሉ አግዟል። የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችን፣ ባለድርሻ አካላት፣ ሚዲያዎችና ሌሎችም ጉዳዩን ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ አድርገው በመንቀሳቀሳቸው በዘርፉ ትልቅ መነቃቃት ተፈጥሯል። የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለመጨመር የኃይል አቅርቦት፣ የመሬት፣ የሥልጠና፣ የብድር አቅርቦትና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተሠራ ይገኛል።
የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በቅርበት ለመፍታት እና የዘርፉን ምርትና የማምረት አቅም ለማሳደግ ዓላማ አድርጎ ኢትዮጵያ ታምርት በሚል የተዘጋጀ ሀገራዊ የንቅናቄ የተጀመረው ከዓመት በፊት ሲሆን፤ የሀገራዊ ንቅናቄው ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል፣ በዘርፉ ያለውን የሥራ ባሕል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ የሚሉ ናቸው፡፡
እንደ ሀገር ያሉን ያልተነኩ ጸጋዎች (የግብርና፣ የማዕድን፣ የቱሪዝም ሀብቶች) እና ከገበያ፣ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች ባለቤቶች ሆነን እንዴት በምንጠላው የድህነት አዙሪት ውስጥ እንኖራለን በሚል ጥያቄ፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች በገጠማቸው ዘርፈ ብዙ ችግር ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ የማምረት አቅም አጠቃቀማቸው መውረድ እና በ2022 ኢትዮጵያ ልታሳካ የያዘችው ትልልቅ ሀገራዊ የብልጽግና ግቦች ግፊት ለንቅናቄ መርሃ ግብሩ ዋና መነሻዎች ናቸው።
የግብዓትና አቅርቦት ችግር፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ እጥረት፤ የቅንጅታዊ አሠራር፣ የክትትል እና ድጋፍ ሥርዓት ደካማ መሆን እንዲሁም ከመፈጸምና ማስፈጸም አቅም ግንባታ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራርና የአመራር ቁርጠኝነት ይጠይቃል። በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችና መፍትሔዎች ላይ መግባባት መፍጠር፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ እና ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር፤ የውጪ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጪ ምንዛሬን ማዳን ለ10 ተከታታይ ዓመታት ከሚቆየው የንቅናቄ መርሃ ግብር የሚጠበቁ ውጤቶች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በሚቀጥሉት 10 ዓመታትም ተጠናክሮ የሚቀጥልና ራሱን የቻለ ፕሮጀክት ቢሮ ተቋቁሞለት በጥብቅ ዲስፕሊን እየተመራ እንደሚገኝ ፤ በማምረቻ ኢንዱስትሪ ላይ ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት በሀገር ምርትና ምርታማነት ላይ በማተኮር የሀገር ሉዓላዊነት አጀንዳም ጭምር መሆኑን ልብ ይሏል። እንደሀገር ለኢትዮጵያ የማምረት ጉዳይ የሕልውና ጉዳይ ነው፤
የምንፈልጋት ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር ለማድረግ ሁሉም ዘርፎች ማምረት አለባቸው። ለዚህ ምቹ መደላድል ለመፍጠር የኢንዱስትሪ ፖሊሲውን የማሻሻል፣ ልዩ ልዩ የአምራች ዘርፍ የማበረታቻ መመሪያዎች በመዘጋጀት ላይ ሲሆኑ ቅንጅታዊ አሠራሩን ለማዘመን የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸው፤ የአምራች ዘርፉን የሀገር ውስጥ ገበያ ድርሻ ከ30 በመቶ ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ በተያዘው እቅድ መነሻነትም በቅርቡ የሀገር ውስጥ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶችን (ፈርኒቸሮችን) በሀገር ውስጥ ገበያ ለመተካት የሚያስችል የገበያ ከለላ ማበረታቻ መደረጉ አይዘነጋም።
ሻሎም። አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም