
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የነበረውን የወንጀል ምጣኔ በዘንድሮ በጀት ዓመት በ42 በመቶ መቀነስ መቻሉን የአዲስ አበባ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።
የአዲስ አበባ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚደቅሳ ከበደ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በከተማው የነበረውን የወንጀል ምጣኔ በጥምር የጸጥታ ኃይሉ በሠራው ሥራም በባለፈው በጀት ዓመት 32 በመቶ በዘንድሮ ዓመት ደግሞ በ42 በመቶ ምጣኔውን መቀነስ ተችሏል።
እንደ ቢሮ ኃላፊ ገለጻ ፤ ሰላምን የማስጠበቅ ሥራም በርካታ ተዋንያን የሚሳተፉበት ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን፤ የሰላም ሠራዊትን ፣ የፌደራል ፖሊስ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የሪፐብሊካን ጋርድ በጋራ በመሆን የሚሳተፉበት በአንድ ጥምር ግብረ ኃይል የሚሠራ ነው። በከተማው ውስጥ የሚታየው አስተማማኝ ሰላም የጋራ ጥምር ግብረኃይሉ ውጤት ነውም ብለዋል።
42 በመቶ የወንጀል ምጣኔውን ለመቀነስ ትልቅ አቅም የፈጠሩት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በሚሠሩ ሥራዎች መሆናቸውን አመልክተው፤ ቢሮውም የሕዝብን አቅም በመጠቀም ረገድ ጥሩ ሥራ ሠርቷል። የጋራ ጥምር ኃይሉ በጋራ እንዲያቅድ፣ በጋራ እንዲፈጽም እና በጋራ ሥራዎችን እንዲገመግም ቢሮው በኃላፊነት እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከተማዋም 7/24 በጥምር ኃይሉ እንደምትጠበቅ የገለጹት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሚደቅሳ፤ በሰላም ሠራዊቶች የሚያዙ ወንጀለኞችን ለፖሊስ በመስጠት ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ሥራ ይሠራልም ብለዋል።
ኃላፊው የሰላም ሠራዊቶች ከሕዝቡ የወጡ በጎ ፈቃደኛ የሕዝብ አገልጋይ መሆናቸውን ገልጸው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች በመሆናቸው በከተማዋ የሚ ደረጉ የትኛዎቹም እንቅስቃሴዎች ከሰ ላም ሠራዊቶች የተደበቁ አይደሉም። በዚህም በተደራጁባቸው ብሎኮች ውስጥ ወንጀለኞችን የመያዝ አቅማ ቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት ቅድመ የመከላከል ሥራ ላይ ትኩረት በማድረግ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ እና ወንጀልን የመከላከል ሥራ እንደሚሠራም ተቁመዋል። ለወንጀለኞች ሽፋን ሲሰጡ በተገኙ አባላት ላይ ርምጃ የመውሰድ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም