
አዲስ አበባ፦ በሲዳማ ክልል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቡናና የአቮካዶ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ መምህሩ ሞኬ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ክልሉ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሚታወቅበትን የቡና እና የአቮካዶ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየሠራ ነው። ለዚህ የሚሆን የመሬት አጠቃቀም አዋጅ አውጥቷል፡፡
በተያዘው ዓመት ወደ ማዕከላዊ ገበያ 40 ሺህ ቶን ቡና ለማቅረብ አቅዶ እስካሁን 37 ሺህ ቶን ቡና መሰብሰብ ማቻሉን ያመለከቱት አቶ መምህሩ ፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ምርት ዕድገት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በምርታማነት ረገድ ቀደም ሲል ቡና በሄክታር ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ኩንታል ይመረት እንደነበር አመልክተው ፤ አሁን ላይ አኀዙን በሄክታር ወደ 11 ኩንታል ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።
በክልሉ አሁን ላይ የቡና ማደስ እና የመትከል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው ፤ በማይገባ ቦታ የተተከሉ ባህር ዛፎችንና ያረጁ የቡና ዛፎችን በመንቀል ከ6 ሺህ 500 ሄክታር በላይ ተጨማሪ መሬት ማግኘት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
የቡና ምርትን ለማሳደግ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል ችግኞችን ማፍላት አንዱ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ 132 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ለማፍላት ታቅዶ ፤አሁን ላይ 130 ሚሊዮን ችግኞች ማፍላት መቻሉን አስታውቀዋል። ከሚያዝያ ወር ጀምሮ የመትከል ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡
ከቡና ምርት ቀጥሎ በሲዳማ ክልል የአቮካዶ ምርት በስፋት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መምህሩ ፤ እስካሁን ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ ነባር የአቮካዶ ዛፍ መኖሩን ፤ ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ አዳዲስ ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በአብዛኛው በክልሉ የቡና ምርትም ሆነ አቮካዶን ለማምረት ምቹ የሆኑ ሥፍራዎች ቢኖሩም አሁን ላይ ተጨማሪ ነጻ መሬት በስፋት አለመኖሩን አስታውቀው ፤ ቢሮው ችግሩን ለመቅረፍ ምርታማነት ለማስፋት በዋናነት በተለያዩ ተቋማት የሚገኙ ነጻ ቦታዎችን እየተጠቀመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቢሮው ለምርት የሚሆኑ ቦታዎች ላይ የበቀሉ የባህር ዛፎችን የመንቀል ሥራዎችን ከመሥራት ባለፈ የመሬት አጠቃቀም አዋጅን በማውጣት እየሠራ እንደሚገኝ ፤ ከእዚህም አንጻር በዚህ ዓመት 15 ሺህ ሄክታር መሬት በመለየት 12 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ ባህርዛፍ የመንቀል ሥራ መሠራቱን አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ የፍራፍሬ ምርት አፕልና አናናስ ሌላኛው በትኩረት የሚሠራበት እንደሆነ ፤ በተያዘው ዓመት ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የአፕል ችግኝ የማባዛት ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል ፡፡ የፍራፍሬ ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ከበሽታ ጋር ተያይዞ እየተፈተነበት ያለበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል
ቢሮው አሁን ላይ ችግኞችን የማፍላት ፣ የማባዛት እና በሽታዎች እንዳይከሰቱ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየሠራ መሆኑን ያስታወቁት አቶ መምህሩ ፤ከበሽታ ጋር በተያያዘ በ11 ወረዳዎች ልዩ ትኩረት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም