
አዲስ አበባ፦ የአዲስ አበባ እድገትና ፈጣን ለውጥ ለአፍሪካ የእድገትና የተስፋ ምልክት ሆኗል ሲሉ የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ ገለጹ።
በ5ኛው የኢትዮ-አልጄሪያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ፤ አዲስ አበባን በተለያዩ ጊዜያት የመመልከትና የመጎብኘት እድል እንደገጠማቸው በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመት የተለያዩ የከተማዋን አካባቢዎች እንደጎበኙ ተናግረዋል።
ወደ ከተማዋ በመጡ ቁጥር ከተማዋ በፈጣን እድገትና ለውጥ ላይ እንደሚያገኟት እና ይህም እንደሚያስገርማቸው የገለጹት አሕመድ አታፍ፤ ከተማዋ ውብና ማራኪ እንድትሆን ቀን ከለሊት ለሚሠሩት አመራሮች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስ በሠራችሁት ሥራ ልትኮሩ ይገባል ነው ያሉት።
በቀጣይ የሚሠሩ ሥራዎችም አዲስ አበባ ላይ የበለጠ ውበት የሚጨምሩ መሆናቸውን ተናግረው፤ አምስተኛውን የሁለቱን ሀገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ የአልጄሪያና የኢትዮጵያ ግንኙነት እንደ አዲስ አበባ በተመሳሳይ መልኩ በማላቅ በአፍሪካ እና በሌሎችም ላሉ ሀገራት መነሳሳትን መፍጠር አለብን ነው ያሉት።
የአልጄሪያና የኢትዮጵያ ግንኙነት የሁለቱን ወገኖች ብቻ ሳይሆን የመላው አህጉር ርካታን የሚፈጥር ጠንካራ እና አርአያነት የሚሆን ወዳጅነት እንደሚሆን ገልጸው፤ በአዲስ አበባ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን ለማስተዋወቅ እና የጋራ ግቦቻችንን ለማሳካት ከፓን አፍሪካውያን እሴቶች፣ መርሆች እና ፅንሰ-ሃሳቦች ጋር በሚጣጣም መልኩ እየሠራን ነው ያሉት አሕመድ አታፍ፤ በጋራ በመሆን የአፍሪካን ፖለቲካዊ አንድነት እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት በመደገፍና ኃላፊነቶችን በመውሰድ አስደናቂ ግቦችን ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ረጅም ዓመት ያስቆጠረ መሆኑን ገልጸው፤ ሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ባደረገ መንገድ ያላቸው ትብብር በአፍሪካ የፖለቲካ አንድነት እና የኢኮኖሚ ውሕደት እንዲጠናከር በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
ኢትዮጵያና አልጄሪያ መደበኛ የፖለቲካ ምክክር እና በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ጉብኝት ማድረግ የስትራቴጂክ አጋርነት አንዱ አካል መሆን እንዳለበት ተስማምተዋል።
አምስተኛው የኢትዮጵያ እና የአልጄሪያ የሚኒስ ትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በግብርና፣ በሥራ ፈጠራ እና ኢኖቬሽን፣ በስፔስ ሳይንስ፣ በመድኃኒት እና ቁሳቁስ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፣ በስፖርት እና ባህል ፣ ኢንቨስትመንት በማስተዋወቅ፣ በትምህርት እና ሳይንሳዊ ምርምሮች እንዲሁም የጋራ የንግድ ምክር ቤት መመሥረት የሚያስችሉ የመግባቢያ ስምምነቶች በመፈራረም ተጠናቋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም