ለምረቃ የበቃችው ናኦታ የሕጻናት መጽሔት፡-

  • አንባቢ ትውልድ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የምታግዝ ናት
  • ትውልዱ የሀገር ፍቅር እንዲኖረው ታደርጋለች

አዳማ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአፋን ኦሮሞ ያስመረቃት “ናኦታ” የተሰኘች የሕጻናትና የልጆች መጽሔት አንባቢ ትውልድ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የምታግዝና ትውልዱ የሀገር ፍቅር እንዲኖረው የምታደርግ በመሆኗ ተደራሽነቷ ላይ ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው ናኦታ መጽሔት ከመማሪያ መጽሐፍት በተጨማሪ ልጆች የንባብ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት እና ክህሎታቸውን የሚያጎለብቱበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

መጽሔቷ ትናንት በአዳማ ኃይሌ ሪዞርት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራ እንደሞንና በዕለቱ በተገኙ

እንግዶች በታደሙበት በተመረቀበችበት ወቅት ቢቂላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን ማዳን ከተፈለገ ትውልድ ላይ መሥራት የግድ የሚል ነው፡፡ ትውልድን መገንባት ደግሞ ሀገርን እንደመገንባት የሚቆጠር ነው። ናኦታ የልጆች መጽሔትም ትውልድን ለማዳንና አንባቢ ትውልድ ለማፍራት የሚደረገውን የሀገር ጥረት የምታግዝ ናት፡፡

የኢትዮጵያ ትንሳኤ እውን እንዲሆን ከተፈለገ የነገውን ትውልድ በመልካም ሥነ ምግባር እና በእውቀት ማነጽ ተገቢ ነው ያሉት ቢቂላ (ዶ/ር)፣ መጪው ትውልድ ከእጃችን እንዳይወጣ ሕጻናት ላይ መሥራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

በትውልድ ግንባታ ላይ አተኩሮ እየሠራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሊመሰገን የሚገባው ከመሆኑም በተጨማሪ ያስመረቀው መጽሔት ወደ ልጆቹ ተደራሽ እንዲሆን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ማዕከላቸው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

የናኦታ መጽሔት ተደራሲያን የኢትዮጵያ ልጆች እንኳን ደስ ያላችሁ ሲሉ ንግግራቸው የጀመሩት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው፤ ልጆች በዕድላቸው ያድጋሉ ሲባል የመጣው አባባል አሁን ያለውን ሀገራዊ ስብራት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ ከዚያ ይልቅ ልጆችን በመልካም ሥነ ምግባር እና በእውቀት ኮትኩቶ ማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል፡፡

አቶ መሳፍንት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባለፈው ሐምሌ ወር የብላቴናት የልጆች መጽሔትን አስመርቆ ለንባብ አብቅቷል፡፡ ትናንት ደግሞ ናኦታን አስመርቋል፡፡ ድርጅቱ በዚህ ብቻ የሚያቆም ሳይሆን በቀጣይም ልጆች አፋቸውን በሚፈቱበት በሌሎች ቋንቋዎች የሕጻናት መጽሔትን ለሕትመት ለማብቃት የሚሠራ ይሆናል፡፡ ድርጅቱ፣ ላለፉት 84 ዓመታት ጋዜጦችን እና መጽሔቶችን አዘጋጅቶ እያሳተመ በመንግሥትና በሕዝብ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ እዚህ ደርሷል።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር)፤ መንግሥታችን በለውጡ ከሚሠራቸውና ተቀዳሚ አጀንዳዎች አንዱና ዋነኛው የትውልድ ግንባታ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በትውልድ ላይ መሥራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ትውልዱ የሀገር ፍቅርና አብሮነትን እንዲያዳብር እየሠራ ያለ ሥራ የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል፡፡ እንደ ኦሮሚያ ክልል ብቻ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ያሉት የተማሪዎች ቁጥር ሰባት ሚሊዮን ሲሆን፣ በተደራሽነቱ ላይ ከድርጅቱ ጋር በጋራ የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከወራት በፊት ያስመረቀው “ብላቴናት” የሕጻናት መጽሔትን ጨምሮ ትናንት ደግሞ አዳማ በነበረው የምረቃ መርሐ ግብር በአፋን ኦሮሞ በየወሩ ታትማ ለንባብ የምትበቃውን “ናኦታ” መጽሔትን አሳትሟል፡፡ አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በተለያዩ ቋንቋዎች አዲስ ዘመን፣ ዘ-ኢትዮጵያን ሔራልድ፣ በሪሳ፣ ዓል ዓለም፣ በካልቾ፣ ወጋህታ እንዲሁም ደግሞ ከቅርብ ወራት በፊት ትኩረቷን ኢኮኖሚ ላይ ያደረገች ዘመን ኢኮኖሚን እያሳተመ ለኅትመት እያበቃ ያለ የኅትመት ሚዲያው ፈር ቀዳጅ የሚዲያ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጋዜጦቹ ዕለታዊ እና ሳምንታዊ ሲሆኑ፣ በትናንትናው ዕለት ለምረቃ የበቃችው ናኦታ መጽሔትን በየወሩ እየታተመች ለንባብ የምትበቃ መሆኑ ታውቋል፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You