በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር መድረክ በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ

 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ክልልን አጀንዳ ተረከበ

አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ገለጹ። በክልሉ ለምክክሩ የተሰበሰበው አጃንዳ ርክክብ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በመርሐ-ግብሩ ላይ እንደገለጹት፣ በክልሉ የተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ስኬታማ ሆኖ ተጠናቋል፡፡ በክልሉ የሕዝብ ወኪሎች የተሰበሰቡት አጀንዳዎችም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ላጋጠሙ ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህም ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመነጋገር እና በመወያየት እንዲሁም በመተማመን መሥራት ባህል እንዲሆን ጭምር ያገዘ እንደሆነም ተናግረው፤ የቀረቡ አጀንዳዎች ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ ሰላም እና አብሮነት መጠናከር የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው ጠቅሰዋል። ለዚህ ስኬታማነትም ሕዝቡ በሂደቱ በንቃት እንደተሳተፈው ሁሉ እስከ መጨረሻው ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።

እንደ ኮሚሽነር መላኩ ወልደ ማርያም ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ እያካሄደ ያለው የምክክር ሂደት በሺህ ዓመታት የሀገራችን የምሥረታ ዘመን በኋላ አሁን ላይ መደረጉ ታሪካዊ ክስተት ነው። ከመጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በነበረው የምክክር ሂደት ከተሳታፊዎች በርካታ ቁም ነገሮችን አግኝተናል፣ ትምህርትም ቀስመንበታል። ያስረከባችሁንን አጀንዳዎች ወደ ኮሚሽኑ ምክር ቤት በማቅረብ ከሌሎች ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ አጀንዳዎች ጋር ተጣምረው እንዲቀርቡ አደራውን ተረክበናል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ምክክርን ባሕል በማድረግ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየሠራ ባለው ሥራ ሕዝባችን ከኮሚሽኑ ጎን ሆኖ ያደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት መሠረት የቀረቡ አጀንዳዎች ተፈጽመው ሕዝባችን የራቀው አንድነት፣ ሰላም እና አብሮነት እውን ይሁን ዘንድ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ያካሄደውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ በስኬት እንዲያጠናቅቅ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። ከመጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ሲካሄድ የሰነበተው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ በስኬት መጠናቀቁንም አስታውቀዋል። ለቀናት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የተሳተፉ ተወካዮችም አጀንዳቸውን ለምክክር ኮሚሽኑ አስረክበዋል። በማጠቃለያ ዝግጅቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች እና በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሂደት የተሳተፉ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You