ሰላም የሁሉንም ወገን ቀና ትብብር ይፈልጋል !

ሰላም፣ ፀጥታና ደኅንነት ከፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ፖለቲካዊ ብስለት፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ማኅበራዊ መረጋጋት፣ የአንድን ሀገር የሰላም፣ የፀጥታ እና የደኅንነት ሁኔታዎች ይወስናሉ፡፡ ይህ እውን እንዲሆን በመንግሥት ደረጃ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል፤ በመሥራት ላይም ናቸው።

የሀገራችንን ልማት ወደፊት የሚያስፈነጥሩ፤ ኢኮኖሚው ላይ የራሳቸውን ዐሻራ የሚያኖሩ የፕሮጀክት ዕቅዶችም አሉ። የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች ግንባታም በስፋት ቀጥሏል። በማኅበራዊ ጉዳዮችም የኅብረተሰቡን ጤና፣ ትምህርት፣ የመኖሪያ ቤት እና የመሳሰሉትም ትኩረት የተሰጣቸው ማኅበረ- ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ናቸው።

በሀገሪቱ በተለይም ባለፉት ሰባት ዓመታት የተሠሩ ሥራዎችንና የተገኘውን ውጤት ለማበላሸት፤ የሀገራችንን መልካም ስም ለማጉደፍ በግራና በቀኝ፣ በውጪና በውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሠላም ኃይሎች የኅብረተሰቡን ሰላም ለማደፍረስ ያለ መታከት ሲሠሩ ቆይተዋል።

ሩቅ ሳንሄድ፣ በትግራይ ክልል የነበረው የሰላም መደፍረስ ሀገርና ሕዝብን ከፍተኛ ዋጋ በማስከፈል መጥፎ የታሪክ ጠባሳን ጥሎ ማለፉ የሚዘነጋ አይደለም። ድርጊቱ ክልሉ ሌሎች አቻ ክልሎች በለሙት ልክ የልማት ትሩፋትን እንዳያገኝ እንቅፋት የነበረ መሆኑም ግልጽ ነው። ይህ ሁሉ ሳያንስ፣ አሁን ደግሞ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታየው ግጭት የየክልሎቹን ልማት ወደ ኋላ የሚመልስ፣ ተማሪውን ከትምህርት ገበታ ውጪ እያደረገ፤ ልማትን ከማደናቀፍም ባለፈ ሕዝብን ከሰላማዊ ኑሮው እያፈናቀለ ያለ እኩይ ተግባር ነው።

የሚታየው ይህ የሰላም መደፍረስ በአንጻራዊ ሁኔታ መሻሻል የታየበት ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ የሰላምና የፀጥታን ሁኔታ ለማረጋገጥ አሁንም ቀሪ ሥራዎችን ይጠይቃል። በተለይ ሰላም እንዲሰፍን በመንግሥት ሆደ ሰፊነት የሚሠራውን ሥራ በማገዝ በኩል ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለበት፤ ይጠበቅበታልም።

በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት የተጀመረው እንቅስቃሴ ፍሬው መታየት ጀምሯል፡፡ ይህን ሥራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ማኅበረ-ባሕላዊ መንገዶችን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ሰላማዊ መንገዶች መጠቀም ይገባል፡፡ የሰላም መንገድን መርጠው ለሚመጡ አካላት ተገቢውን ክብካቤ ማድረግ እና ሠልጥነው ወደ ሕዝቡ እንዲቀላቀሉ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሰላም አማራጮችን አንቀበልም ብለው ፍላጎታቸውን በኃይል ለማስፈጸም በሚንቀሳቀሱት ላይ የተጀመረውን ሕግ የማስከበር ተግባር አጠናክሮ መቀጠል የግድ ይሆናል፡፡

ከኢትዮጵያ ጠላቶች ተልዕኮ እየተቀበሉ በሀገር ውስጥ ችግር ለመፍጠር የሚጥሩ ኃይሎች ከዕለት ወደ ዕለት አቅማቸው እየተዳከመ፣ ተቀባይነታቸውም እየከሰመ መጥቷል፡፡ የገንዘብና የሰው ኃይል ምንጫቸውም እየነጠፈ ነው፡፡ ነገር ግን እስከ ወዲያኛው እስኪጠፉ ድረስ ሕግ የማስከበር፣ የሰላም አማራጮችን አሟጦ የመጠቀም እና ሕዝብን የማንቃት ሥራዎች ያለ ማቋረጥ ሊሠሩ ይገባል፡፡

ሕዝቡም ሰላሙን በመጠበቅና በማስከበር የጀመረውን አኩሪ ተግባር አጠናክሮ መቀጠል አለበት። ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚመጡ ታጣቂዎች ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ እነዚህን ታጣቂዎች ተቀብሎ ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። በመሆኑም የዚህ ሥራ ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀናጅተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ሰላም እንዲሰፍን በመምከር፣ ከዚያም አለፍ ብሎ በመገሰጽ ጭምር በየቦታው የሚታየው የፀጥታ ችግር እንዲቆም መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

በኃይል እና በአመጽ ፍላጎትን የማስፈጸም መንገድ ዘላቂ ውጤት እንደማያመጣም በተግባር ታይቷል፡፡ ይህንን መንገድ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተቀላቀሉ ወገኖች ወደ ሰላማዊ የሃሳብ መድረክ እንዲመጡ መንግሥት በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቧል። አሁንም ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ሲባል ለሰላማዊ ውይይት ዛሬም ዝግጁ መሆኑን እያረጋገጠ ይገኛል።

የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት የሀገርን ሠላምና ደኅንነት ለመጠበቅ እየከፈሉት ያለው መስዋዕትነት የሚደነቅ ሲሆን፤ የሀገራችን ሁለንተናዊ ብልፅግና እስኪረጋገጥ ድረስ ይህንንኑ ሀገራዊና ሕገ መንግሥታዊ አደራችሁን እንዲወጡ መንግሥት ከአደራ ጭምር አሳስቧል።

የሀገራችን ሰላም የሚረጋገጠው በራሳችን ስለሆነ ሁሉም ዜጋ ለሰላም መክፈል ያለበትን መስዋዕትነት መክፈል ይጠበቅበታል። መንግሥት ለሰላም እጁን ዘርግቶ እየጠበቀና ተደጋጋሚ ጥሪ እያቀረበ በመሆኑ ለጥሪው አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይገባል። ከመንግሥት ጋር መተባበርና የሀገራችንን ሠላም ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ ይገባል !

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You