
ሀገራችን ብዙ የዜማ እና የዝማሬ ፤ የደስታ እና የእልልታ፤ የስኬት እና የከፍታ ዘመናት እንዳሳለፋችሁ ሁሉ ለቅሶ እና ዋይታ ፤ ኀዘን እና ምሬት፤ ጦርነት እና እልቂት ፤ ስደት እና መፈናቀል የበዙባቸው ዘመናትን አሳልፋለች። የዘመናት የሀገርነት ትርክቶቻችንም ለዚህ እውነታ የተገዙ ናቸው። ትናንቶቻችን የዚህ እውነት ጥላ እንደሆኑ ሁሉ ዛሬዎቻችንም ከዚህ ያመለጡ አይደሉም ።
ለዚህም ደግሞ ከሁሉም በላይ ኃይልን አምላኪ የሆነው ፤ ለዘመናት በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ዜማ እና ግጥም የተቃኘው ፤ የብዙ ትውልዶችን ተስፋ የሚናጠቀው ፤ ዛሬ እና ነገን በትናንት መነጽር እያየ ትውልዶችን ትናንት ላይ አቁሞ የተስፋቸው ባለዕዳ ያደረጋቸው ፤ ለሰላማዊ የፖለቲካ አመራጮች እና ለሃሳብ ልእልና ባእድ የሆነው የፖለቲካ ባህላችን ተጠያቂ ነው።
ጊዜ እና ሁኔታዎችን በመገምገም ከዛሬ የተሻለ አማራጭ የለም በሚል የአስተሳሰብ ስንኩልነት የሚገዛው ይህ የፖለቲካ ባህል፤ በየዘመኑ እንደ ሕዝብ የተፈጠሩ የለውጥ መነሳሳቶችን ጠልፎ በመውሰድ ፤ ትውልድ ስለ ለውጥ መሻታቸው ያልተገባ ዋጋ አብዝተው እንዲከፍሉ ፤ስለ ተስፋቸውም አቅመ ቢስ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ከዛሬ ሁለት መቶ እና ሶስት መቶ ዓመት በፊት የነበሩ ፤ በዘመናቸውም ሀገር እና ሕዝብን ለከፋ ውድቀት እና የኋልዮሽ ጉዞ የዳረጉ ፤ ምድሪቱን የደም ፤ ሀገሪቱን የጉስቁልና ምድር ያደረጉ እነዚህ አስተሳሰቦች ፤ ዛሬም ለአስተሳሰቡ ታማኝ ባሪያ በሆኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች ትንሳኤ አግኝተው በተመሳሳይ መንገድ ሀገርን እና ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ እያስከፈሉ ነው።
እነዚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች እንደቀደሙት ዘመናት ባልተገባ ስሌት፤ ዙሪያ ገባው እና ወቅቱን አንብበው ለግለሰባዊ እና ቡድናዊ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ አቅም ይሆናል ብለው ባሰቡ እና ባመኑ ቁጥር ፤ ከሁሉም በላይ በነሱ ምክንያት ተስፋውን ተነጥቆ ተስፋ ቢስ የሆነውን ትውልድ የፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ እቃ ፤ ለሚፈልጉት የፖለቲካ ቁማር የመቆመሪያ ካርድ አድርገው የሚወስዱ ናቸው። ይህንን ላለማድረግ የሚፈትናቸው ምንም አይነት ሠብዓዊነት የሌላቸው ናቸው።
ለፍላጎታቸው ስኬት የተሻለ ዕድል ነው ብለው ባሰቡበት ወቅት ሁሉ ፤ በዙሪያቸው ያለውን ፤ ከተስፋው ጋር ተፋትቶ ፤ በገዛ ቀኑ ላይ የቆዘመውን ሕዝብ አሰልፈው ወደ ተገማች ጥፋት ለመግባት ፤ የንጹሃንን ደም ተረማምደው የፍቃዳቸውን ሃሳብ ለመውረስ ሁሌም ዝግጁ ናቸው።
ሕዝብ የራሱ ፍላጎት እና ፈቃድ ያለው የማይመስላቸው ፤ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ አስተሳሰቦችን የሕዝብ የህልውና መሠረት አድርገው የሚወስዱ ፤ ሕዝብ እንደ ሕዝብ እነሱ የፈጠሩት፤ ህልውናውም ከእነርሱ ዕጣ ፈንታ ጋር የተሳሰረ ርካሽ የፖለቲካ ሸቀጥ አድርገው የሚወስዱ ፤ ለዚህም የትኛውንም አይነት የጥፋት መንገድ ላይ ለመራመድ የቀና ማንነት ያላቸው ናቸው፡፡
ራሱን መሆን ከተጨባጭ እውነታዎች ጋር መታረቅ ፤ ዘመኑን መስሎ ከዘመኑ ጋር ታርቆ ለመሄድ የሚፈልግ ፤ ለዚህ የሚሆን ማንነት የገነባን ግለሰብ ሆነ ቡድን ከመፈረጅ እና ከማሸማቀቅ ባለፈ ፤ ለማጥፋት የሚተጉ ፤ ይህንንም እንደ አንድ የፖለቲካ ስኬት አድርገው የሚወስዱ እና በዚህም የሚኮፈሱ ናቸው።
ከዛሬ ይልቅ ከትናንት ጋር ተጣብቀው ፤ ሕዝብን ከዛሬ ጋር አጣልተው ከነገ ተስፋው ጋር አራርቀው ትናንትን አምላኪ የሚያደርጉ ፤ ዛሬን እና ነገን በሚያስረሳ ትርክት የሕዝብን ዛሬ እና ነገን የሚናጠቁ፤ ትናንትን እና ራሳቸውን ጣኦት አድርገው የሚመለከቱ፤ ራሳቸውን አምልከው መመልከት የሚፈልጉ፤ ለዚህ የሚሆን የገድል ታሪክ ሲጽፉ እና ሲያጽፉ የሚኖሩ ናቸው።
በተበላሸ አስተሳሰባቸው ከዘመን ጋር ተጣልው ትውልድን ከዘመኑ ጋር የሚያጣሉ ፤ የትውልድን ትርጉም ያለው በተስፋ የተሞላ ሕይወት የእነርሱ የትናንት ዕዳ ማወራረጃ አድርገው የሚወስዱ ፤የሕይወት ዘመን ስኬታቸውን በዚህ ነውር የሚያሰሉ ናቸው። ማር እና ወተት ስለሚፈስባት ምድር እየሰበኩ ፤ ብዙውን በምድረ በዳ ያስቀሩ፤ ቀሪውንም በምድረ በዳ ሕይወት ያ ልተገባ ዋጋ የሚያስከፍሉ ፤ አንገተ ደንዳኖች ናቸው።
እነዚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች ዛሬም ሕዝባችን እንደ ሕዝብ የጀመረውን የለውጥ መነቃቃት ፤ ከዘመን ጋር የመታረቅ አዲስ የለውጥ ጉዞ በብዙ መልኩ እየተፈታተኑት ነው ። ተስፋ ካደረጋቸው የዜማ እና የዝማሬ፤ የደስታ እና የእልልታ፤ የስኬት እና የከፍታ ዘመናት ሊያደናቅፉት ሌት ተቀን እየተጉ ነው። የተስፋ ትርክቱን ሊናጠቁት የሚይዙት የሚጥሉትን አጥተዋል።
እነዚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች እንደ ሕዝብ ካስከፈሉን እና እያስከፈሉን ካለው ያልተገባ ዋጋ፤ ከዚያም ባለፈ ከደገሱልን የለቅሶ እና ዋይታ፤ የኀዘን እና ምሬት፤ የጦርነት እና እልቂት፤ የስደት እና መፈናቀል የጥፋት ተልዕኮ አኳያ ፈጥነን ልናስቆማቸው ፤ በቃችሁ ብለን ልንታገላቸው ይገባል። ይህን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው እንደትውልድ የተስፋችን ባለቤት የምንሆነው !
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም