በሀገር በቀል እውቀትና ክህሎት ውጤታማ የሆነው የእንጨት ባለሙያ

ከተፈጣሪ የሚሰጥ መክሊትንም ሆነ የነፍስ ጥሪን አስቀድሞ አውቆ መሰማራት ውጤታማ ካደረጋቸው ሰዎች መካከል ናቸው፤ የዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችን አቶ ሰለሞን ጌታሁን። የተወለዱትም ሆነ ያደጉት እዚሁ አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ቄራ ቡልጋሪያ አካባቢ ነው። ወንድማማችና ቅዱስ ያሬድ እንዲሁም ንፋስ ስልክ አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

እንግዳችን አናፂና የእንጨት ሥራ ባለሙያ አባታቸውን የሥራ ውጤቶች እያዩና አብረው እየሰሩ ማደጋቸው፤ ለእንጨት ሥራ የተለየ ፍቅር እንዲያድርባቸው ያደረጋቸው መሆኑን ያስረዳሉ። ገና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳሉም አንድ ወንበር በመስራት የአባታቸውን ፈለግ ተከታይ መሆናቸውን አስመስክረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በልምድ ያገኙትን እውቀት በቀጥታ አሴር ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅና በአዲስ ተግባረዕድ የእንጨት ሥራ ቴክኖሎጂ ዲፕሎማዎችን አግኝቷል።

በተለምዶ ጥይት ፋብሪካ በሚባለውም ለሶስት ዓመት ያህል በእንጨትና ብረታብረት ሰራተኝነት፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኮምፖልሳቶ ድርጅት ውስጥ ከአናፂ ክፍል ኃላፊነት እስከ ምርት ክፍል ማናጀር ሆነው ለአምስት ዓመታት ሰርተዋል። አሁን ላሉበት ደረጃ በዚህ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው በሚሰሩበት ጊዜ ያገኙት ተሞክሮ መሰረት የጣለላቸው መሆኑን አይሸሽጉም። በተለይ ደግሞ ስለሀገር በቀል ዛፎች ባህሪና ምርቶቻችው ጥልቅ እውቀት ማግኘታቸውን ይገልፃሉ።

በኢትዮጵያ ኮምፖልሳቶ ፋብሪካ ተቀጥረው በሚሰሩበት ጊዜም፣ የተፈጥሮ እንጨቶችን በመጠቀም ባሕላዊና ዘመናዊ ቁሳቁሶችን በተለየ ጥበብ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን በመስራት፤ ቴክሎጂዎችን ቶሎ በመቀበልና አሻሻሎ በመስራት በተቋሞቻቸቸው አመራሮች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ አድርጓቸውም ነበር።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በእንጨት ሥራ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰሩ ሥራዎችን በማየትና ጥናት በማድረግም የነበራቸውን እውቀት ለማሳደግ ጥረት ያደርጉ እንደነበርም ያነሳሉ። በዋናነትም በዓለም የሰፋሪ ሥራ የሚባለውና ተፈጥረዊ ይዘቱን የጠበቀ የእንጨት ሥራ ቴክኖሎጂም በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲስፋፋም ሰፊ ምርምር አድርገዋል። በተጓዳኝም ከአባታቸው ጋር በመሆን አዳዲስ የእንጨት ፈጠራ ሥራ ውጤቶችን ይሰሩ ስለነበርና ሥራዎቻቸው በበርካታ ሰዎች ተቀባይነት በማግኘታቸው ሙሉ ለሙሉ በግል ቢሰሩ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማመን የራሳቸውን ድርጅት ለመክፈት ወሰኑ።

‹‹እንደመንግሥት ሰራተኝነቴ ምንም እንኳን ያጠራቀምኩት ገንዘብ ባይኖረኝም ከአባቴ ያገኘሁት የዓመታት ልምድና በትምህርት የዳበረ እውቀቴ እንዲሁም አንዳንድ መሳሪያዎች ስለነበሩኝ ብዙ አልተቸገርኩም›› ሲሉም፤ ከዛሬ 16 ዓመት በፊት የራሳቸውን ሥራ የጀመሩበትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ።

በነበረቻቸው 1ሺ 500 ብር የተለያዩ ግብዓቶችን በመግዛትና በ250 ብር አነስተኛ ቤት በመከራየት የእንጨት ሥራቸውን መጀመራቸውን የሚነገሩት አቶ ሰለሞን፤ አስቀድመው ከሰዎች ትዕዛዝ ተቀብለው ስለነበርም በቀጥታ ወደ ምርት ሂደት መግባታቸውን ይገልፃሉ። እንደዋንዛ ያሉ ሀገር በቀል እንጨቶችን ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን፤ ቅርጻቸውንና መልካቻንም ጭምር እንደያዙ የተለያዩ የእንጨት ምርቶች በማምረት ማስተዋወቅ ያዙ።

የሥራቸውን ውጤት ያዩ የአካባቢው ማሕበረሰቦችም የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶችን እንዲሰሩላቸው ወደ አቶ ሰለሞን አነስተኛ ሱቅ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። ሥራው እየሰፋ መጣ፤ ይህን ጊዜ ታዲያ እጃቸው ላይ ከነበረው መሳሪያ በተጨማሪ መከራየትና ረዳቶችን መቅጠር የግድ አላቸው። በተለይም ደግሞ ከተለመደው የእንጨት ሥራ ውጪ ተፈጥሯዊ ይዘቱን በጠበቀና በጥራት የሚሰሯቸው የእንጨት ውጤቶች የብዙዎችን ቀልብ መያዝ ቻለ። እናም የአቶ ሰለሞንን የሳፋሪ እንጨትን ምርቶችን ለመጠቀም ከመኖሪያ ቤች ባሻገር ትልልቅ የመንግሥትና የግል ድርጅቶችም ሳይቀሩ ፍላጎት አሳዩ።

የአቶ ሰለሞን ጥረት የተገነዘበው የቀበሌው አስተዳደርም በአካባቢያቸው የሚገኝ የሕብረት ሥራ ሼድ ውስጥ እንዲሰሩ እድሉን ፈጠረላቸው። ከቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች በተጨማሪ የቡና ቤት ባንኮኒዎች፣ የመሬት ወለል (ፐርኬ) እና መሰል ምርቶችን በስፋት በማምረት ለትልልቅ ድርጅቶች ወደ ማስረከብ ገቡ። ምርቶቻቸው ባሕላዊና ተፈጥራዊ ይዘት ስላላቸውም፣ የተለያዩ ሬስቶራንቶችና ሎጆችም ሳይቀር ትኩረት ሳቡ።

የሰራተኞቻቸቸው ቁጥርንም ሆነ የመስራት አቅማቸውን እያሳደጉ ባለበት ወቅት ግን የዓለም ሕዝብ የጤና እና የኢኮኖሚ ቀውስ ያስከተለው የኮረና ቫይረስ መጣና ሥራቸው የመቀዛቀዝ አደጋ አጋጠመው። ሆኖም የተፈጠረውን ችግር በፀጋ በመቀበል የሳፋሪ ሥራዎቻቸቸውን በማስተዋወቅ የድርጅታቸውን ሕልውና ለማስቀጠል ታገሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ በገበያው ከውጭ በሚመጣው የእሽግ እንጨት (የኤምዲኤፍ) ቴክኖሎጂ ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ የሳፋሪ ሥራቸውን በተወሰነ መልኩ ተገዳድሮት እንደነበር አይሸሽጉም። ሆኖም ላጋጠማቸው ችግር እጅ ሳይሰጡ፤ በተለየና አዳዲስ የፈጠራ ሥራ ብቅ በማለት፤ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ጥምረት በመፍጠርና ሰብ ኮንትራት ጭምር በመያዝ ገበያውን ዳግሞ ለመቆጣጠር መቻላቸውን ያስረዳሉ። በተለይም በጊዮን ሆቴል ጊቢ ውስጥ የነበረውን የግሮቭ ጋርደንና ሬስቶራንት የመናፈሻ ወንበሮች፣ ጠረጴዛ፣ የእንጨት ባለአንድ ወለል ፎቅ ቤትና አጠቃላይ የእንጨት ሥራዎችን በመስራት እውቅናቸውን አሳደጉ።

‹‹ይህም ሥራዬን የመንግሥትን ቀልብ በመሳቡ የእንጦጦ ፓርክ ላይ አንዳንድ የሳፋሪ እንጨት ሥራ ውጤቶችን በሰብ ኮንትራት ለመስራት እድል ፈጠረልኝ›› ሲሉ ያስታውሳሉ። በተመሳሳይ በሰቃ ሎጅ ላይም ለበርሃ ስፍራ የሚያገለግሉና በዲዛይናቸው ለየት ያሉ የተለያዩ የእንጨት ጥላዎችንና ሌሎች ባሕላዊ የሆቴል ቤት ቁሳቁሶችን ሰርተዋል። እንዲሁም ጨበራ ጩርጩራ ላይ ፓርክ ሲሰራ ለነበረ አንድ ፕሮጀክት የተለያዩ ባሕል ነክ ቁሳቁሶችን በናሙና መልክ ሰርተው እንደነበር፤ ሆኖም ፕሮጀክቱ በመቋረጡ ምክንያት ምርቶችን በስፋት ማቅረብ እንዳልቻሉ ያመለክታሉ።

ከዚህም ባሻገር የአቶ ሰለሞን የእንጨት ሥራዎች ተጠቃሚ ከሆኑ የግል ድርጅቶች መካከልም ዮድ አቢሲኒያ የባሕል አዳራሽና ዱከም ላይ የሚገኘው ወሊማ ሪዞርት ተጠቃሽ ሲሆን፤ በእነዚህም ተቋማት የኢትዮጵያን ገፅታና ባሕል የሚያንፀባርቁ የእንጨት ስነ-ጥበብን ማሳየት ችለዋል።

ለተፈጥሮና ለባሕል የተለየ ፍቅር ያላቸው እንግዳችን ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡትን የእንጨትና ብረታ ብረት ውጤቶችን በሀገር በቀል ዛፎችና በሀገር ባሕል ምርቶች የመተካት ራዕይ አላቸው። በተለይም ከውጭ የሚመጡት እሽግ እንጨቶችና የእንጨት ውጤቶችን ውሃ ሲነካቸው በቀላሉ የሚበላሹ እንደመሆናቸው በተቃራኒው ደግሞ የሳፋሪ እንጨቶች በጥንካሬም በውበትም የተሻሉ መሆናቸውን ለማሕበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠርና የሀገር በቀል ሥራዎች በገበያው ተቀባይነት እንዲኖራቸው ትኩረት አድርገው እየሰሩ ይገኛሉ። ይህንን ራዕያቸውን እውን ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ያጠኑ ሲሆን ለዚህም ሰፊ ቦታ በጀት የሚያሻቸው በመሆኑ አጋር አካላትን እያነጋገሩ መሆኑን ነው ያጫወቱን።

በሌላ በኩል ይህ አይነቱ ሀገር በቀል የአመራረት ሂደትና ክህሎት ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዲሻገር ትልቅ መሻት ያላቸው መሆኑን ይናገራሉ። በቅርቡም ከቂርቆስ ማኑፋክቸሪንግ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት የፈጠሩ ሲሆን፤ የማኑፋቸሪንግን ሰራተኞች በማሰልጠን የእውቀትና ክህሎት ሽግግር ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ። በተጓዳኝም የእርሳቸውን ምርቶች የገበያ መዳረሻዎች ለማስፋት በጋራ ለመስራት መስማማታቸውንም ያመለክታሉ።

በአሁኑ ወቅት ካፒታላቸውን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ማሳደግ የቻሉት አቶ ሰለሞን፤ ለ11 ሰዎች ቋሚ የሥራ እድልም ፈጥረዋል። እንደየሥራ ሁኔታም እስከ 20 የሚደርሱ ሰራተኞችን በጊዜያዊነት ቀጥረው እያሰሩ ይገኛሉ።

የእንጨት ባለሙያው አቶ ሰለሞን ወደፊት ሀገር በቀልና አዳዲስ ፈጠራ ሥራቸውን ወደ ኢንዱስትሪ ከፍ ለማድረግ እቅድ ይዘዋል። ለዚህም የሚሆናቸውን መሬት ለማግኘት ፕሮፖዛል አዘጋጅተው ለክፍለ ከተማው ያቀረቡ ሲሆን፤ ይህም እውን መሆን ከቻለ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር በተለይ ከውጭ የሚመጣውን የእንጨት ሥራ (ፈርኒቸር) የሚተኩ ሥራዎችን በስፋት በመስራት ለሀገር አወንታዊ ሚና ለመጫወት የሚያስችላቸው መሆኑን ነው ያስረዱት።

የዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችን ሁሉም ያለውን ነገር ተካፍሎ መብላት ሀገር እንደሚያፀና ያምናሉ። ዛሬን ጥሩ በመስራት ነገን ማሳመር የሕይታቸው መርሆ ነው። ለዚህም ነው ይጠቅማል ባሉትና በተጠየቁት ሥፍራ ሁሉ ገንዘብና እውቀታቸውን ለማካፈል ወደኋላ የማይሉት። በተለይም ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር መሳካት ድጋፍ ያደርጋሉ፤ ይተክላሉ፤ የተተከሉትንም የመንከባከብ ሥራ ይሰራሉ።

ወደ ኢንዱስትሪ የመሸጋገር ትልማቸው እውን ከሆነ መሬት ማግኘት ከቻሉም ጎን ለጎንም በዘላቂነት ሀገር በቀል ዛፎችን በማልማት ለኢንዱስትሪያቸው ግብዓት እንዲሁም ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራው የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት አስበዋል። ይህንንም የሚያደርጉት ለሚሰሩት ሥራም ሆነ ለሀገር ልማት ወሳኝ ሚና እንዳለው ስለሚያምኑ እንደሆነ ነግረውናል።

በተጨማሪም ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶችን ያለምንም ክፍያ እሳቸው ጋር መጥተው እንዲሰለጥኑ በማድረግ ራዕይ ያለው ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲፈጠር የበኩላቸውን ሚና እየተወጡም ነው። ከዚህም ባሻገር ከቀበሌ ጀምሮ ባሉ የመንግሥት መዋቅር አማካኝነት በሚከናወኑ ማሕበረሰብ አቀፍ ሥራዎች ላይ በመሳተፍም በግንባር ቀደምትነት የሚነሱ ሰው ናቸው። ከእነዚህም መካከል የአቅመ ደካሞችን ቤት ለማደስ በሚደረጉ እንቅሰቃሴዎችና በምገባ ስርዓት ላይ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።

አቶ ሰለሞን፣ አሁን ላይ በተለይም ከለውጡ ወዲህ ለተፈጥሮ ሃብቶችና ሀገር በቀል እውቀቶች እንደመንግሥት የተሰጠው ቦታ እንደእርሳቸው አይነት ባለሙያዎችን ያበረታታል ብለው ያምናሉ። ይሁንና ከዓመታት በፊት ለሀገር ውስጥ ምርት የነበረው አመላከከት ዝቅ ያለ ስለነበር፤ ብዙ የለፉበት ሥራ ዋጋ የማያገኝበትና ተጠቃሚ የማያደርግ ስለነበር ብዙዎች ከዘርፉ ተስፋ ቆርጠው የሚወጡበት ሁኔታ እንደነበር ያነሳሉ።

በሌላ በኩል ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በዘርፉ የካባተ እውቀትና ልምድ ያለውን ሰው ያለማሳተፍ ችግር እንደነበር አስታውሰው፤ ይህም ዘርፍ እንዳያድግና ባለሙያውም ተገቢውን ስፍራ እንዳያገኝ ያደረገው መሆኑን ያመለክታሉ። በመሆኑም አሁን ላይ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረትና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You