የፋሽን ኢንዱስትሪው አንጋፋ ተዋናይ

የዛሬዋ የስኬት እንግዳችን በፋሽን ኢንዱስትሪው ስማቸው ጎልቶ ከሚነሳ ኢትዮጵያውያን አንዷ ናቸው፤ ወይዘሮ እጅጋየሁ ኃይለጊዮርጊስ ይባላሉ። የእጅግ ዲዛይን መሥራችና ባለቤት ናቸው፡፡

በሙያው ከ30 ዓመት በላይ ዘልቀዋል፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጆችን ጨምሮ በኢትዮጵያ በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድሮች አልባሳትን በማዘጋጀት ከፍተኛ እውቅና ማግኘት ችለዋል።

እንግዳችን የተወለዱት አዲስ አበባ ቢሆንም ያደጉትና ትምህርታቸውን የተማሩት በምሥራቋ የፍቅር ከተማ ሐረር ነው። ሐረር ከተማ ባለው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴና መድኃኒዓለም ትምህርት ቤቶች በመግባት የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልጅ ዶክተር የመሆን ፍላጎት ነበራቸው፤ ይሁንና እድሜያቸው እየጨመረ ሲመጣ የእጅ ሥራ መሥራትና ያገኙትን ልብስ እየቀደዱ መስፋት ማዘውተር ጀመሩ። ይህ ልምድ እየጎለበተ መጥቶም አሁን ለደረሱበት ዓለምአቀፍ የዲዛይነርነት ሙያ መሠረት እንደጣለላቸው ይገልጻሉ። ለልብሳቸውና ፋሽን ልዩ ትኩረት ይሰጡም ነበር። ‹‹በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ሳለሁ ያለፈውን ዓመት ዩኒፎርሜን በትኜና በምፈልገው ዲዛይን ቀድጄ እሰፋውና በወታደሩ አባቴ ካውያ ተኩሼ አዲስ ልብስ አደርገው ነበር›› በማለት ያስታውሳሉ።

ይህንን በሚያደርጉበት ጊዜ ግን ስለፋሽንም ሆነ ዲዛይን እውቀቱ ኖሯቸው ሳይሆን ስሜታቸውን በመከተል ብቻ እንደሆነ ያስረዳሉ። ‹‹ከራሴ አልፌ የእናቴን የፅዋ ልብስ ከመሶብ ላይ አንስቼ እቀድ ነበር›› የሚሉት ወይዘሮ እጅጋየሁ፣ በሁኔታቸው የተሰላቹት እናታቸው አንዳንድ ልብሶችን ታበላሽብኛለች በሚል ስጋት ይደበቁባቸው እንደነበረም ይገልጻሉ፡፡

ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ኪሮሻቸውን እያነሱ ዳንቴልና ሌሎች አልባሳትን አዳዲስ ፈጠራ በማከል ጭምር መሥራት የዘወትር ተግባራቸው እንደነበር ይገልፃሉ። ገና በልጅነታቸው ወላጆቻቸው በሚያሰፉላቸው ልብስ ላይም የራሳቸውን ዲዛይን ይጨምሩበት እንደነበር ያስታውሳሉ።

ገና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ትዳር መያዛቸውን የሚናገሩት ዲዛይነሯ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁትም በትዳር ውስጥ ሳሉ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናውን በጥሩ ውጤት አልፈው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርት ስኩል የመግባት ዕድሉ አጋጥሟቸው የነበረ ቢሆንም፣ በትዳር አጋራቸው የሥራ ባሕሪ ምክንያት ወደ ግሪክ በመሄዳቸው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሳይከታተሉ ቀሩ።

እናም በግሪኳ አቴንስ ከተማ ኑሯቸውን ካደረጉ በኋላ ግን ከቀለም ትምህርቱ ይልቅ ወደ ሙያው ልባቸው አዘነበለና በዚያው ግሪክ በሚገኝ የአሜሪካ የሴቶች ዲዛይን ትምህርት ቤት ገብተው ተማሩና ዲፕሎማቸውን ያዙ፡፡

በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ የመሳተፍ ዕድሉን ያገኙት እንግዳችን፣ ባሕር ማዶ ያዩዋቸውን አዳዲስና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን አልባሳት ለመሥራት አልመው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። ‹‹ወደሀገሬ ስመጣ እዛ ያየሁትን ሁሉ ለመሥራትና ፋሽን ሾው ለማዘጋጀት አስቤ ስለነበር በሻንጣዬ ይዤ የመጣሁት ልሠራባቸው የምችልባቸውን መሣሪያዎች ብቻ ነው›› በማለት በወቅቱ የነበራቸውን ጉጉት ያስረዳሉ።

እንደመጡም ለአይቤክስ ሆቴል ኃላፊዎች ሃሳባቸውን አጫወቷቸው፤ በአጋጣሚ አርቲስት ቻቺ ታደሰንም አግኝተዋት ስለነበር አብረው ለመሥራት ተስማሙ። በተለይም አርቲስት ቻቺ ሞዴሎችን የመመልመሉን ኃላፊነት እንድትሠራ በማድረግና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አዳዲስ አልባሳትን በመሥራት የመጀመሪያውን የፋሽን ትርዒታቸውን አቀረቡ፡፡

‹‹የመጀመሪያው የፋሽን ትርዒታችን ብዙ ሰው የተመለከተውና ውጤታማ የሚባል ቢሆንም እንደጠበኩት በዚያ ሁኔታ ሊቀጥል አልቻለም›› ሲሉ ያነሳሉ። በወቅቱ በርካታ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች እየተዘጋጁ የተለያዩ የፋሽን ትርዒቶች ቢካሄዱም የሚቀርቡት አልባሳት ደረጃቸውን ያልጠበቁና ከሱቅ ጭምር ተገዝተው ምንም ዓይነት የፈጠራ ሥራ የማይታይባቸው በመሆኑ ከዓላማቸው አንፃር እሳቸውን የሚመጥን ሆኖ አላገኙትም። ፋሽን ራሱን የቻለ ኢንዱስትሪ ነው የሚሉት ወይዘሮ እጅጋየሁ፣ ይህንን ያገናዘበ ነባራዊ ሁኔታ በወቅቱ ስላልነበር፤ ሙያውን እየወደዱት በተለመደው ደንበኛ ተኮር ልብስ ስፌት ሥራ ውስጥ ለመግባት መገደዳቸውን ያስረዳሉ፡፡

ይሁንና በ2003 ዓ.ም ላይ ‘’ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ’’ ውድድር በአዲስ አበባ ሲዘጋጅ እሳቸውም የሥራቸውን ውጤቶች የማቅረብ ዕድል ስላጋጠማቸው ዳግም ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪው ገቡ። ለ26ቱም የውድድሩ ተሳታፊዎች የሚሆኑ አልባሳትን በሙሉ በመሥራት ውጤታማ መሆን ቻሉ። በተለይ ሞዴል ሃያት መሐመድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወዳደረችባቸውን አልባሳት መሥራታቸው ከፍተኛ ደስታ ይፈጥርላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

እንግዳችን በወቅቱ የእርሳቸው የእጅ ሥራ ውጤት አልባሳት መታየታቸው እንጂ ስለስማቸውም ሆነ ስለእውቅና ትኩረት እንዳልሰጡ ይገልፃሉ። ‹‹ይህም አንድም ካለማወቅ፤ ሁለትም ለሥራው ከነበረኝ ጉጉት የመነጨ ነበር›› ይላሉ።

በሁለተኛው ውድድር ግን አዘጋጆችን የፋሽን አልባሳቱ ዲዛይነር እርሳቸው መሆናቸው በመድረኩ እንዲገለፅ አልያም ደግሞ ለእያንዳንዱ ልብስ እንዲከፈላቸው መጠየቃቸውን ይናገራሉ። በዚህም ከአሜሪካው የውድድሩ አዘጋጅ ጋር በክፍያው ተስማምተው 13 አልባሳት በተናጠል እንዲከፈላቸው የተደረገ ስለመሆኑና ከሠሯቸው አልባሳት መካከልም በወቅቱ አንደኛ ሆና ያሸነፈችው አርቲስት ሳያት ደምሴ ለብሳ የተወዳደረችበት እንደነበር ይገልፃሉ።

ከፋሽን ውድድሩ ጎን ለጎን የተለያዩ አልባሳትን በትዕዛዝ መሥራት መቀጠላቸውን የሚናገሩት ዲዛይነር እጅጋየሁ፤ በሂደትም ሜዳ በሚባል ድርጅት አማካኝነት ከሌሎች 11 ዲዛይነሮች በመገናኘትና በመመካከር የኢትዮጵያ ፋሽንና ዲዛይነሮች ማኅበር መሠረቱ። አሁን ላይ ዘጠኝ ዓመት በሆነው ማኅበራቸው ምክንያት በርካታ የፋሽን ትዕይንቶችንና ክዋኔዎችን በማዘጋጀት የፈጠራ ሥራቸውን በስፋት ማቅረብ ቻሉ።

‹‹የኢትዮጵያ ፋሽን በሚል ስያሜ ሀገር አቀፍ የፋሽን ትርዒቶችን በማዘጋጀት ዘርፍ ከፍተኛ እውቅና እንዲኖረው ባለሙያዎችም የልፋታቸው ውጤት ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ የበኩላችንን ጥረት አድርገናል›› ይላሉ። ወይዘሮ እጅጋየሁ ማኅበሩን ለሰባት ዓመታት ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል። አሁን የቦርድ አባል በመሆን ለዘርፉ እድገት ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዕደ ጥበባት ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ ናቸው።

አሁን ላይ በሀገር ባሕል አልባሳት ፋሽን ዲዛይነርነት ስማቸው ጎልቶ ከሚነሳ ኢትዮጵያውያን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠሩት የዛሬዋ ባለስኬት እንግዳችን፣ ወደ ባሕል አልባሳት ሥራ የገቡት በተለይም የመጀመሪያው ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ ላይ በተሳተፉበት ጊዜ ለ26ቱም ተወዳዳሪዎች አንድ አይነት የባሕል ልብስ ማግኘት ባለመቻላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በወቅቱ ያጋጠማቸውን ተግዳሮት በሸማኔዎች ካሠሩ በኋላ ግን ራሳቸው በሚፈልጉት ዲዛይን፣ ጥራት ደረጃ ራሳቸው መኖሪያ ጊቢያቸው ውስጥ ቤት ሠርተው ሁለት ሸማኔዎችን ቀጥረው ማሠራት ጀመሩ።

ዲዛይነሯ እንግዳችን በተለየ መንገድ የሚሠሯቸው የባሕል አልባሳት ከፍተኛ ተቀባይነት እያደገ መጣ። በተለይም የባሕል አልባሳት በአዘቦት ቀናትም ጭምር መልበስ በሚያስችልና ወጣቱንም ትውልድ በሚስብ መልኩ ዲዛይን አድርገው የሚሠሩ መሆኑ የምርቶቻቸው ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ ስለመምጣቱ ይናገራሉ።

ይህንን ተከትሎም በኢንዱስትሪ ደረጃ በስፋት ወደ ማምረት መግባት እንዳለባቸው ወሰኑና ጉዳዩን አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ያሉ ኃላፊዎች አማከሩ፤ ለተከታታይ አራት ዓመታት ያለመታከት ወደ ተቋሙ በመመላለስ የቦታ ማምረቻ ጥያቄ አቀረቡ።

ከአራት ዓመታት በኋላ ግን የዲዛይነሯን ጥረትና እየሠሩት ያሉባት የቀበሌ ቤት ቦታው ድረስ በመሄድ ያዩት ኮሚቴዎች ለሀገር ከሚያበረክቱት አስተዋፅዖና ከሥራው ስፋት አንፃር ፈፅሞ የማይመጥን መሆኑን በመገንዘባቸው ቀጨኔ በሚገኘው የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ማምረቻ ማዕከል ውስጥ የማምረቻ ሼድ እንዲሰጣቸው አደረጉ። ከልማት ባንክ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብድር በመውሰድ 44 የስፌት ማሽኖች አስገቡ። በተጨማሪም ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ገንዘብ ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ብር ከእናት ባንክ ወስደው በስፋት ማምረት ጀመሩ።

በተጨማሪም አርባ ምንጭ ድረስ በመሄድ ሸማኔዎችን በአንድ አካባቢ በማደራጀትና አምስት ሴቶችን በፈታይነት በመቅጠር አስፈላጊውን ግብዓት ሁሉ በማሟላት ጭምር የተለያዩ የሽመና ውጤት የሆኑና ከዘመነኛ ዲዛይኖች ጋር በማጣመር ለትውልዱ የሚመጥኑ የዘወትርና የበዓላት አልባሳትን በስፋት ማምረት ያዙ።

በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ መንግሥታዊና የግል ድርጅቶች ሳይቀሩ የባሕል አልባሳትን በመሥራት ዝናቸው መጨመሩን ይገልፃሉ። በቱርክ ኢዝሚር፣ ሕንድና በኒውዮርክ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ላይ የኢትዮጵያን ባሕላዊ አልባሳት በማቅረብም የሀገራቸውን ምርቶች አስተዋውቀዋል፤ ከራሳቸው አልፈው ለሀገርም ጭምር ገቢ በማስገባት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ አበርክተዋል።

‹‹በተለይም ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጆች የሚለብሱትን የባሕል ልብስ በማዘጋጀቴ ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል›› ይላሉ። ለአየር መንገዱ በየወሩ 350 የባሕል አልባሳትን እያመረቱ የሚያስረክቡ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት 28 ቋሚና ከ50 የሚልቁ ጊዜያዊ ሠራተኞችን ቀጥረው እያሠሩ ይገኛሉ። በተጨማሪም የሙለጌ ቡና ላኪዎች ማኅበር ሠራተኞችን የሥራ አልባሳት በሙሉ በጨረታ አሸንፈው በቋሚነት እያመረቱ ናቸው። ሆስፒታሎች፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ሆቴሎችም የእጅግ ዲዛይንን ምርቶችን ከሚጠቀሙ ድርጅቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ሥራ በጀመሩበት በቅሎ ቤት አካባቢ ካለው ሱቃቸው ባሻገር በአሁኑ ወቅት ስካይላይት ሆቴል ውስጥ የባሕል አልባሳት ሱቅ በመክፈት ለዓለም አቀፍ ጐብኚዎች ሽያጭ የሚከናወንበት ተጨማሪ ሱቅ ከፍተው እየሠሩ ነው ያሉት። ከዚህም ባሻገር ወቅቱ የዲጂታላይዜሽን እንደመሆኑ ባለሙያዎችን በመቅጠር ኢ-ኮሜርስ (የኤሌክትሮኒክስ መንገድ ግብይት) ሥርዓት በመፍጠር በመረጃ መረብ፣ ኢንስታግራም፣ ሊንክዲንና ሌሎችም ማኅበራዊ ገፆችን በመጠቀም የሽያጭና የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራሉ፡፡

በአነስተኛ የልብስ ስፌት ማሽን የፋሽን ኢንዱስትሪውን የተቀላቀሉት የዛሬዋ የስኬት ዓምድ እንግዳችን አሁን ላይ ከበርካታ ዘመናዊ ማሽኖቻቸው በተጨማሪ ከ10 ሚሊዮን ብር የማያንስ ካፒታል ማፍራት ችለዋል። ‹‹ይህንን ኩባንያ ወደፊት በልጆቼ አማካኝነት እንደብራንድ ማስቀጠል እፈልጋለሁ›› የሚሉት ወይዘሮ እጅጋየሁ፤ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ወደ ትልቅ ኢንቨስትመንት ሥራ ለመግባት እየሠሩ መሆኑንም ገልፀውልናል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያን በአግባቡ የሚያስ ተዋውቁና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አልባሳትን በማዘጋጀት ወደ ውጭ ለመላክ እየተዘጋጁ ናቸው። ለዚህም ደግሞ ባለፈው ዓመት ድርጅታቸው ያገኘው አይሶ 1590 የተሰኘው የጥራት ደረጃ ሰርተፍኬት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።

እንግዳችን የንግድ ትርዒት በተሳተፉባቸው ሀገራት የተመለከቷቸውን የሽመና ቴክሎጂዎች ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣትና የሽመና ዘርፍን ለማዘመን ከፍተኛ መሻት እንዳላቸውና በጉዳዩ ዙሪያም ከሚመለከታቸው የመንግሥት አመራሮችና ከኤምባሲዎች ጋር መነጋገራቸውን ይገልጻሉ። ‹‹እነዚህ ማሽኖች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው የሸማኔዎቻችንን ጉልበትና ጊዜ በመታደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል፤ ዘርፉን በማዘመንና ጥራትን በማስጠበቅ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታችንን ማሳደግ ያስችለናል›› ሲሉም ያብራራሉ።

‹‹አሁን ላይ ባለው ሁኔታ ግን ሥራው አድካሚ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሸማኔዎች ከዘርፉ እየወጡ በመሆናቸው ወደፊት ዘርፉን የሚረከብ ትውልድ እንዳናጣ እፈራለሁ፤ ለዚህም ነው ማሽኖቹ ወደ ሀገር እንዲገቡ ስል የበኩሌን ጥረት እያደረኩኝ ያለሁት›› ሲሉ ያስገነዝባሉ። ይህ ጥረታቸው ከተሳካና ኢንቨስትመንቱን እውን ማድረግ ከቻሉ ለሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገባ ትልቅ ኢንዱስትሪ ለመፍጠር ሃሳብ አላቸው። በአሁኑ ወቅት በተጓዳኝ ወደ ጫማ ሥራ እየገቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ሥራ ራሱን ችሎ እንዲቆም እየሠሩ ናቸው።

ወይዘሮ እጅጋየሁ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት አስተዋፅዖ እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ። ድጋፍ ካደረጉላቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከልም ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ለአካል ጉዳተኞች ለሦስት ዓመታት የሰጡት ሥልጠና እና ድጋፍ እንደሚጠቀስ ተናግረዋል። በተጨማሪም የእድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ላላቸው 12 እናቶች ቤታቸው ሆነው ልጆቻቸውን እየጠበቁ የፈትል ሥራ በመሥራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረጉ ነው ያሉት።

የሀገር ባሕልና የዕደ-ጥበብ ሥራዎችን በማስተዋወቅ ረገድም ለሀገር ባበረከቷቸው አስተዋፅዖዎች ‹‹ኢትዮጵያ ጥበብን ትሸልማለች›› በሚል ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው መርሐ ግብር የእውቅና ሰርተፍኬትና ዋንጫ ማግኘት ችለዋል።

በፋሽንና ዲዛይን ሥራ ከ30 ዓመታት በላይ ሲዘልቁ ነገሮች አልጋ ባልጋ ሆነውላቸው አይደለም፤ ሥራቸውን ለማቆም የሚያስገድዱ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመዋቸው እንደነበር አስታውሰዋል። በተለይም በቀበሌ ቤታቸው ውስጥ ሆነው በሚሠሩበት ጊዜ በአንድ ምሽት ማንነታቸው እስከአሁን ባልታወቀ ሰዎች በትዕዛዝ የሠሩት የሙሽራ ልብስን ጨምሮ በርካታ ማሽኖችን የተዘረፉበትን አሳዛኝ ሁኔታ ጨርሶ አይዘነጉትም።

ከሁሉም የከበደው ደግሞ ባለቤታቸው ያለጥፋታቸው ታስረው ለስምንት ዓመታት በቆዩባቸው ጊዜያት ሥራውን ሳያቋርጡ ልጆቻቸውን ብቻቸውን ለማሳደግ የከፈሉት ዋጋ ከባድ ነበር።

ይሁንና ላጋጠሟቸው ችግሮች እጅ አልሰጡም፤ ሥራቸውን በፅናት በመቀጠላቸው አሁን ላይ ለስኬት መብቃት መቻላቸውንም ያስረዳሉ። አሁን ላይ ያለው ወጣት ከእሳቸው ሕይወት እንዲማር ይሻሉ። በተለይ በአቋራጭ ከመክበር ይልቅ በሐቅና በትክክለኛው መንገድ ሠርተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲያሳድጉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You