ኮምቦልቻ – አረንጓዴዋ ከተማ

ዜና ሀተታ

በምግብ ራስን የመቻል ንቅናቄ እንደሀገር ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ከግብርና ሥራ ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ መርሃ-ግብሮች ተግባራዊ በመደረግ ላይ ናቸው ፤ ከእነዚህም አንዱ የከተማ ግብርና ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች የከተማ ግብርና የጓሮ መሬትን ከማልማትም ባለፈ በከተማዋ የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን ሁሉ ጥቅም ላይ እያዋለ፤ ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር ተዳምሮ አረንጓዴ ከተሞች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን የምትገኘው ኮምቦልቻ ከተማ የዚህ አንዷ ማሳያ ነች። የከርሰ ምድር ውሃ በቅርብ ርቀት የሚገኝባት ኮምቦልቻ ይህን ለዘመናት የያዘችውን እምቅ ጸጋ ጥቅም ላይ እንድታውል የከተማ ግብርና መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላት የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። ኮምቦልቻ በተለይም የከተማ ግብርና በስፋት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ከዳር እስከዳር በአትክልትና ፍራፍሬ እየተሸፈነች መምጣቷን ያስረዳሉ።

ኢብራሂም አሊ በከተማዋ እምብርት ልዩ ስሙ መልካ ራፉ በሚባል ቦታ ካሮት ተክሎ ሲንከባከብ ያገኘነው ነዋሪ ነው። መሬቱ ከተሰጠው ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን ሲያለማ እንደቆየ ገልጾልናል። ‹‹እንደምታዩት የማለማው መሬት ትንሽ ነው፤ አንድ ሄክታር እንኳን አይሞላም ፤ እዚህ አካባቢ የውሃ ችግር የለም፤ መሬት ቆፍረን በቀላሉ ማግኘት እንችላለን፤ በግብርና ሙያተኞች ድጋፍና ክትትል እየተደረገልን በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ እናመርታለን›› ይላል።

በአንድ ጊዜ ከ20 ኩንታል የሚበልጥ ምርት በተለያዩ ጊዜዎች እንደሚያመርትም ይገልጿል። ምርቱን ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ነጋዴዎች ቦታው ድረስ እየመጡ እንደሚገዙትም ያስረዳል። በከተማ ግብርና አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት ከጀመረ ወዲህ ኑሮው እየተሻሻለ መምጣቱን የተናገረው ኢብራሂም፤ የከተማው ነዋሪ የግብርና ሥራዎችን ጎን ለጎን በመሥራቱ ከራሱም አልፎ ሌሎችን ተጠቃሚ እያደረገ ስለመሆኑ ጠቅሷል።

የኮምቦልቻ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የእርሻና መሬት ኃላፊ ጀማል ጃቢር (ዶ/ር) እንደሚያስረዳው፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ተግባራዊ ካደረጋቸው 28 ኢኒሼቲቮች አብዛኛዎቹ በወረዳው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ስምንት የሚሆኑት ከአግሮ ኢኮሎጂ ጋር የተያያዙ ናቸው የሚለው ጀማል፤ በወረዳው ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ በመስኖ ለማልማት ታስቦ በአሁኑ ጊዜ ከ7 ሺህ 400 በላይ ማልማት እንደተቻለ ጠቅሷል።

‹‹እንደምታዩት በከተማዋ የሚገኙ ክፍት ቦታዎች ሁሉ በአትክልትና ፍራፍሬ የተሸፈኑ ናቸው። ለበጋ ግብርና የሚውለው ውሃ ከከርሰ ምድር የሚገኝ በመሆኑ፤ ሰዎች በኤሌክትሪክ ኃይል ታግዘው ውሃውን እንዲስቡ እስከ እርሻ መዳረሻዎቻቸው ድረስ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ተደርጓል። የግብርና ባለሙያዎችም ቀን ከሌት ድጋፍና ክትትል በማድረግ ሙያዊ እገዛ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል›› ብለዋል።

ወረዳው በሌማት ትሩፋት እና በመስኖ ልማት ምርታማነቱ እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ጀማል (ዶ/ር) የገበያ ትስስር በመፍጠር የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከነጋዴዎች ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማዋና በአካባቢው የሚመረቱት የካሮት፣ የድንች፣ የቀይ ስር፣ የፍራፍሬና የእንቁላል ምርቶች እስከ ሀረርና ጂግጂጋ ከተሞች እየሄዱ የሚሸጡ እንደሆነና ወደ ሶማሌላንድም ኤክስፖርት እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። በገጠርም በከተማም ተግባራዊ እየተደረጉ ባሉ ኢኒሼቲቮች የአካባቢው ነዋሪዎች ተጠቃሚ እየሆኑና መልክዓ ምድሮችም ገጽታቸው እየተቀየረ መምጣቱን ጀማል (ዶ/ር) አስረድተዋል። አካባቢውን በማየት፣ የእያንዳንዱን ሰው የአኗኗር ዘይቤ እና የቁጠባ ደብተር በመመልከት እውነታውን መረዳት እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

ወይዘሮ ሚስኪ መሃመድ የምስራቅ ሀረርጌ ዞን አስተዳዳሪ በበኩላቸው እንዳስረዱት፤ ምስራቅ ሀረርጌ ዞን ውስን የእርሻ መሬት ያለውና እና የዝናብ እጥረት ያለበት አካባቢ ነው፤ ሕዝቡ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ ያለውን ውስን የመሬት ሀብት ከከርሰ ምድር ውሃ ጋር እያጣጣመ እንዲጠቀም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። በዚህም ውጤት ተገኝቷል፤ በተለይም የሌማት ትሩፋት ለአካባቢው በጣም አስፈላጊና የሕዝብን ኑሮ ይለውጣል ተብሎ የተያዘ ፕሮግራም ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

በክልሉ የተሠሩት የተፋሰስ ሥራዎች የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጨመር አድርገዋል ያሉት ወይዘሮ ሚስኪ፤ ይህም በየአካባቢው አትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲተከሉ አስችሏል ብለዋል። በቀጣይም የተፋሰስ ልማቱን አጠናክሮ በመቀጠል በዞኑ ያሉ የገጠርና የከተማ ክፍት ቦታዎችን ሙሉ ለሙሉ በአትክልትና ፍራፍሬ ለመሸፈን ጥረት ይደረጋል ሲሉ ወይዘሮ ሚስኪ አስረድተዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You