የመዲናዋን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል አዲስ ስትራቴጂክ ጅማሮ

የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ሕይወቱን ለመምራት ሲል ከባህላዊ ትራስፖርት እስከ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ይጠቀማል፡፡ ዛሬ ላይ በባህላዊ ትራንስፖርት ከመጓዝ ባሻገር በአውሮፕላንና መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የረቀቀ የትራንስፖርት መጓጓዣ ሥርዓት ላይ ተደርሷል፡፡ ‹‹ትራንስፖርት›› የሚለው ቃል የእግሊዝኛ ቃል ሲሆን የአማርኛ ትርጉሙ መጓጓዣ የሚል አቻ ትርጉም አለው፡፡

ለዚህም ነው ትራንስፖርት የሀገር የምጣኔ ሀብትና ዕድገት መሠረት ነው የሚባለው፡፡ አንዳንዶች ትራንስፖርትን የአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብት የደም ሥር ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡ የጤና፣ ትምህርት፤ ግብርና፣ የኢንዱስትሪው ሥራ በተገቢው መንገድ የሚሳለጠው፤ የሚሰምረውና የሚሳካው የትራንስፖርት አቅርቦቱ ሲሟላ ነው፡፡ ታዲያ ትራንስፖርት በተለይ በአንድ የዘመናዊ ከተማ ላይ የሚጫወተው ሚና ሲገለጽ የከተማን ሕይወት ይዘውራል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

አንድ ከተማ የከተማነት ለዛና መአዛ የሚኖረው በውስጡ ዘመናዊ የሆኑ የትራንስፖርት አይነቶች የሆኑት መኪና ሲርመሰመስበትና የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ሲኖረው ነው፡፡ መኪና ሰውንም ሆነ ቁሳቁስን ከቦታ ቦታ ያዘዋውራሉ፣ ሆቴልም ይሁን ሆስፒታል፣ ፖሊስ ጣቢያ፤ ጤና ጣቢያ፣ ቀብር ቤትም ሆነ ሠርግ ቤት ለመሄድ ባለንበት የሠለጠነው ዓለም የመኪና ትራንስፖርት አስፈላጊ ነው፡፡

በከተማ ውስጥ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ ሲኖር ትራንስፖርቱ የተቀላጠፈ፤ ለሕዝብ ተደራሽ የሆነ፤ ክፍያውም ተመጣጣኝ ሲሆን ንግዱ፤ ማህበራዊ መስተጋብሩ ይቀላጠፋል፡፡ የገበያ የግብይት ሥርዓቱ፤ መሸጥ መለወጡ፤ ማውረድ መጫኑ ይሟሟቃል፡፡ ይህ ሲሆን የከተማ ምጣኔ ሀብት ያድጋል፤ የዜጎች ሠርቶ የመለወጥ ተስፋ ይለመልማል፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብርንም ያጠናክራል፡፡ ጠቅለል ሲል አገልግሎቱ ያማረ፤ የሰመረ ይሆናል፡፡

እንደሚታወቀው ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ያለው የትራንስፖርት አቅርቦት ከከተማዋ እድገት ጋር የተመጣጠነ አልነበረም፡፡ ይህን ተከትሎም በመዲናዋ የሚታየው የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ሁልጊዜም የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ነው። ችግሩን ለማቃለልም መንግሥት በየጊዜው የተለያዩ የመፍትሄ ርምጃዎችን እየወሰደ ነው።

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ብሎም የበርካታ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መቀመጫ እደመሆኗ መጠን ስሟን የሚመጥን ዝና ተላብሳ እንድትቀጥል የሚደርጋት አንዱ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ነው፡፡ የተጀመረው የኮሪዶር ልማት የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ያለመ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ ለዚህም ዘመናዊ የአውቶብስ ተርሚናሎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በመዲናዋ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ተግባራት መካከል የግል ዘርፉ ተሳትፎን ማሳደግ ነው፡፡ በቅርቡ የከተማዋ መስተዳድር ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር በተወሰነ መልኩ መቀነስ የሚያስችሉ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ 100 ተሽከርካሪዎች ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡ ተሽከርካሪዎች በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መሆናቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው በእጅጉ ታምኖባቸዋል።

ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ መኪኖች ሰሞኑን ወደ ሥራ በገቡበት ወቅት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ በከተማዋ በተለይም በሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓት ላይ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

የመዲናዋ ከንቲባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ ወደ አገልግሎት የገቡት 100 ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ጠዋትና ማታ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ያለውን የትራንስፖርት ሰልፍ እና የሕዝብ እንግልት የሚቀንሱ እንደሆኑ አመልክተዋል።

መንግሥት ያወጣውን የአየር ብክለት የመከላከል ፖሊሲን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር ብሎም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገባውን ነዳጅ እና የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ የሚረዱ መሆናቸውንም ከንቲባዋ አስታውቀዋል፡፡ ጅማሮው የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያበረታ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ዲጂታል ትኬቲንግ ሥርዓትን ተግባራዊ የሚያደርጉ፣ ዲጂታል ባስ ካርድ ሥርዓት (Bus Card System) እውን የሚያደርጉ፣ በካሜራ እና ጂፒኤስ ድጋፍ እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው እንዲሁም ሀገር ውስጥ የበለፀገ ሲስተም የተገጠመላቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎትን በማሳለጥ ጥራት ያለው ፈጣን አገልግሎት ለሕዝብ ለመስጠት ከለውጥ በፊት የነበረው የአውቶብስ ቁጥር በእጥፍ መጨመሩ፣ ከለውጡ በፊት ከ 20 በመቶ በታች የነበረውን የመንገድ ሽፋን በ10 በመቶ ከፍ ማድረግ ፤ ተርሚናሎችን እና የመኪና ማቆሚያዎችን በአስር እጥፍ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል። ይህም መጋቢት 24 የተጀመረው ለውጥ ያመጣው መሠረታዊ ውጤት እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

የመሠረተ ልማቱ ማደግና መዘመን የትራንስፖርት አገልግሎት ከማቀላጠፍ ባሻገር ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዲሠሩ ዕድል የሚሰጥ ነው። በተለይም ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ መነቃቃት የሚፈጥር ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሀገራዊ ተሞክሮ ባለሀብቶቻችን በሀገር አቋራጭ የሕዝብ አውቶብሶች እንጂ በከተማ የሕዝብ አውቶብሶች ሥራ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ምንም የሚባል ነው። ይህ ደግሞ በዘርፉ ባለሀብቶቻችን በስፋት እንዳይሳተፉ ብቻ ሳይሆን እንዳይደፋፈሩም ያደረገ ነው።

የከተማዋ መስተዳድር በመዲናዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን ወደ ዘርፉ ለመሳብ ያደረገው ጥረት እና በተጨባጭ ያገኘው ውጤት የሚበረታታ ነው። ይህ አይነቱ ጥረት ሀገር እና ሕዝብን፤ ባለሀብቱንም ጭምር በሚጠቅም መንገድ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ይህ አይነቱ ጅማሮ በቀጣይ የውጪ ባለሀብቶችን ወደ ዘርፉ ለመሳብ እንደመልካም አጋጣሚ የሚታይ፤ በዘርፉ የውጪ ባለሀብቶች ፤ በተለይም የከተማ አውቶብስ አምራች ኩባንያዎች ሊሳተፉ የሚችሉበትን የፖሊሲ አግባቦችን ማየት እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው።

አስተዳደሩ በመዲናዋ ያለውን የሕዝብ ትራንስፖርት ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት የጀመራቸው ዘርፈ ብዙ የመፍትሄ አማራጮች ሀገር እና ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ፤ የሚበረታቱ ፤ ተገቢው እውቅና ሊቸራቸው የሚገቡ ፤ የአዲስ ስትራቴጂክ እይታ የጅማሮ ስኬት ናቸው።

ኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመ ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You