እሴት በተጨመረበት ቡና እንዴት ውጤታማ መሆን ይቻላል?

በምርት መጠን፣ በጥራትና በገቢ ታሪካዊ ስኬት እያስመዘገበ የመጣው የኢትዮጵያ ቡና በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቷል። የሀገሪቱን የወጪ ንግድ እያነቃቃው ይገኛል። በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተወዳዳሪነትና ተፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን ላይ በከፍተኛ መጠን አድጓል።

በቡናው ዘርፍ ለመጣው ከፍተኛ ለውጥ በዘርፉ የተካሄደው ሪፎርም ከፍተኛ ደርሻ አለው። ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በቡናው ዘርፍ የተካሄደው ይህ የሪፎርም ሥራ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። በዋናነት ከሚጠቀሱ የዘርፉ ስኬቶች መካከልም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አንዱ ነው፤ ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረው 833 ሺ ቶን ቡና የማምረት አቅም በአሁኑ ወቅት አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ቶን ቡና የማምረት አቅም መፍጠር እንደተቻለ የኢትጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን መረጃ ያመላክታል።

ከቡና ወጪ ንግድ ገቢ አንጻርም እንዲሁ ከ700 እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር ሲገኝ የነበረው፤ ከለውጡ ወዲህ በተሠራው የሪፎርም ሥራ ይህ አሀዝ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከፍ ያለበት ታሪካዊ ስኬት ተመዝግቧል። ይህ አሀዝ ዘንድሮ ደግሞ ሁለት ቢሊየን እንደሚደርስ ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅትም ይህን ገቢ በእጥፍ በማሳደግ በቀጣዮቹ ዓመታት ከጥሬ ቡና ወጪ ንግድ ብቻ ከሁለት እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዓመት ከሶስት መቶ ሺ ቶን በታች ይላክ ከነበረበት ሁኔታ በመውጣትም ባለፉት ዓመታት ከሶስት መቶ ሺ ቶን በላይ ቡና ተልኳል፤ ዘንድሮ ይህን አሀዝ ከ450 እስከ 500 ሺ ቶን ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ያም ሆኖ ግን ቡናን ለዓለም ያስተዋወቀችው ኢትዮጵያ ከዘርፉ እያገኘች ያለችው ጥቅም የሚገባትን ያህል እንዳልሆነ ሁሌም ይገለጻል። ለዚህ አንዱ ምክንያት ሀገሪቱ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ቡና በጥሬው ብቻ ሆኖ መቆየቱ በምክንያትነት ይነሳል። ቡና ገዢ ሀገራት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከኢትዮጵያ የሚገዙት ጥሬ ቡና ነው።

የኢትጵያን ቡና የሚገዙ በርካታ ሀገራት ቡናውን እንደ ማጣፈጫ ቅመም በመጠቀም ከሌሎች ቡናዎች ጋር ቀላቅለው ለገበያ በማቅረብ ቡናን ለዓለም ካቀረበችው አምራች ሀገር የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

መንግሥት ሀገሪቱ ከዚህም ገበያ ተጠቃሚ እንድትሆን ሁሌም ያሳስባል፤ ይህን ተከትሎም አንዳንድ ጥረቶች ሲደረጉ ይታያሉ። በተለይ በቡና ቆልቶ ላኪዎች ማሕበር በኩል የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ይህን ተከትሎም እሴት የተጨመረበት ቡና ከቀደመው አኳያ ሲታይ ለውጥ ያሳየበት ሁኔታ መፈጠሩም ይገለጻል። ይሁንና መንግሥት ከሰጠው ትኩረት አኳያ ሲታይ ብዙ ርቀት አልሄደም። ኢትዮጵያ አሁን ከምትልከው አጠቃላይ ቡና ውስጥ እሴት የተጨመረበት ቡና አንድ በመቶም አልደረሰም።

ሀገሪቱ ቡናን በጥሬው ለዓለም ገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት ጨምራ በመላክ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን ያልቻለችው ለምንድን ነው? በዚህ በኩል በመንግሥት በኩል የተጀማመሩ ሥራዎች ምን ላይ ናቸው? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ገለታ እንዳሉት፤ ቡና ላይ እሴት ጨምሮ ወይም ቆልቶና ፈጭቶ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በርካታ ማነቆዎች ይገጥማሉ። እነዚህን ማነቆዎች ለመሻገርም ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።

‹‹ለእዚህም የጥሬ ቡናውን ጥራት ማስጠበቅ ይቀድማል›› ያሉት አቶ ካሳሁን፤ ለአብነትም ለዓለም ገበያ የሚቀርበው ቡና ጥራቱ የተጠበቀ እንዲሆን ሪፎርም መካሄዱንም ገልጸዋል፤ ላኪዎች ጥራት ያለው ቡና አዘጋጅተው ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚችሉበት ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

በእሴት ጭመራውም እንዲሁ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ለአብነትም የሕግ ማሕቀፎችን ምቹ የማድረግ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል። ብዙ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ እንግዶችና ልዑካን ስለ ሀገሪቱ ቡና በማስተዋወቅ እሴት ጨምረው ለገበያ ማቅረብ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ እንዳለ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተሰርቷል ይላሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ እየተከናወነ ያለው ተግባር የተለያዩ ፓኬጆችን በማዘጋጀት እሴት የተጨመረበት የተቆላ አልያም ተቆልቶ የተፈጨ ቡናን በስጦታ መልክ ለእንግዶች በማቅረብ ትክክለኛውን የኢትዮጵያን ቡና ጣዕም እንዲያውቁ የማድረግ ሥራም እየተሰራ ይገኛል። ይህ አንዱ የማስተዋወቂያ መንገድ በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ እንግዶች የኢትዮጵያን የቡና ጣዕም በቀላሉ መለየት የሚችሉበትን ሁኔታ በመፍጠር እሴት ጨምሮ ማዘጋጀት እንደሚቻል ማሳየት ተችሏል። በዚህም ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን እሴት ጨምሮ ማዘጋጀት የሚቻልባት ልትሆን እንደምትችል መልዕክት ማስተላለፍ ተችሏል።

እንዲህ አይነቱ የማስተዋወቅ ሥራ የውጭ ባለሃብቶችን የሚያበረታታና የቡና መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ቡና ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ዕድል ይፈጥራል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በአሁኑ ወቅት መንግሥት ባለሃብቶች ጥሬ ቡና ኢትዮጵያ ውስጥ አልምተው ለውጭ ገበያ መላክ እንዲችሉ በር ከፍቷል። ይህም በእሴት ጭመራ ላይ እየተከናወነ ያለውን ተግባር ያበረታታል።

መንግሥት የውጭ ባለሃብቶች በቡና ልማት መሳተፍ እንዲችሉ መፍቀዱን የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት 10 ሚሊዮንና ከዛ በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ የውጭ ባለሃብቶች ቡና ላይ ተሰማርተው ከልማቱ እስከ ግብይቱ መሥራት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ቡናን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ምርት በጥሬው ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ መላክ የበለጠ አዋጭ እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ቡናን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ደግሞ የበለጠ አዋጭና ተመራጭ በመሆኑ ከዚህ አንጻር በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው።

እስካሁን አበረታች ሥራዎች ቢከናወኑም በርካታ ተግዳሮቶች እየገጠሙ ናቸው ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ቡና ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ የሚያስገኘው ውጤት በግልጽ ቢታወቅም ያደጉትን አገሮች መወዳደር ፈተና እንደሆነ ጠቁመዋል። ሀገሮቹ የኢትዮጵያን ቡና በጥሬው የሚያውቁ በመሆናቸው ጥሬ ቡና ብቻ መግዛት ይፈልጋሉ። በመሆኑም ዓለም አቀፉ ገበያ ትልቁ ማነቆ ሆኗል ሲሉ አመልክተዋል።

የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ቡና ላይ እሴት ጨምረው ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ከዓለም አቀፉ ገበያ በተጨማሪ የአገር ውስጥ ቢሮክራሲዎች ችግር እንደሆኑባቸው ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን የሀገር ውስጡን ቢሮክራሲ መፈታት እንደቻለ ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የኢትዮጵያን ቡና በጥሬው የሚገዙ የውጭ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ጥሬ ቡና ገዝቶ እሴት በመጨመር እንዲሁም ከሌሎች ቡናዎች ጋር በመደባለቅ ወደ ሌሎች ሀገራት ኤክስፖርት በማድረግ የበለጠ ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው። ስለዚህ ይህ ጥቅም እንዲቀርባቸው አይፈልጉም፤ እሴት የተጨመረበትን የኢትዮጵያ ቡና የመግዛት ፍላጎት የላቸውም።

እሳቸው እንዳሉት፤ ቡና ላይ እሴት ጨምሮ ለመላክ ትልቁ ችግር ዓለም አቀፉ ገበያ ቢሆንም፣ በሂደት ውጤት እንደሚገኝ በማመን ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ከሚደረጉ ጥረቶች መካከልም አዳዲስ ገበያዎችን ማፈላለግ አንዱ ሲሆን፤ ለአብነትም እንደ ቻይና ላሉ አዲስ የገበያ መዳረሻዎችን በመጠቀም እንዲሁም ለሌሎች አገራት ጭምር በማስተዋወቅ ገበያ ውስጥ ለመግባት እየተሰራ ነው።

በአሁኑ ወቅትም 100 የሚደርሱ ቡና ላይ እሴት ጨምረው የሚልኩ ቡና ላኪዎች አሉ፤ እነዚህ ላኪዎች ይብዛም ይነስም በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፉ ገበያ እሴት የተጨመረበትን ቡና ለማቅረብ እየተጉ ነው። ነገር ግን ትላልቅ ኩባንያዎች በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ቀድመው ስለገቡ፣ ስለታወቁና ብራንዳቸው ስለሚፈለግ ገበያውን ሰብሮ ለመግባት ያስቸግራል። ችግሩ ሰፊና ዓለም አቀፍ ቢሆንም በብዙ ጥረት ማሳከት እንደሚቻል በማመን ጥረቶች ቀጥለዋል።

በተለያየ መንገድ የሚደረጉ ጥረቶች አበረታች እንደሆኑና በቀጣይም ጥረቱ መቀጠል እንዳለበት የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፤ በተለይ መንግሥት በዚህ ላይ እጁን ማስገባት እንዳለበት አመላክተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በየሀገሩ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንጽላዎች ከጥሬ ቡና ባለፈ እሴት የተጨመረበትን የኢትዮጵያን ቡና በያሉበት የማስተዋወቅ ሥራ እየሰሩ ነው። የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም እንዲሁ ወደ ውጭ አገራት ሲሄዱ እሴት የተጨመረበትን የኢትዮጵያን ቡና ለትላልቅ የሥራ ኃላፊዎች በስጦታ መልክ በማቅረብ የማስተዋወቅ ሥራ እየሰሩ ሲሆን፤ እንዲህ አይነት ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

በእሴት ጭመራ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚገባ የሚያምኑት አቶ ካሳሁን፤ በ2016 ዓ.ም 500 ቶን የሚደርስ እሴት የተጨመረበት ቡና ወደ ውጭ መላክ እንደተቻለ ጠቅሰው፣ በዚህም አራት ነጥብ ሁለት የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል። ይህም በጥሬው ከተላከው የቡና መጠን ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ጅማሬው የሚበረታታ ነው። ጅማሬው ቀጣይነት እንዲኖረውም ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ያስፈልጋል።

እሴት የተጨመረበት ቡናን ዓለም አቀፉ ገበያ በሚፈልገው መንገድ በጥራት ማዘጋጀት ከተቻለ ገበያውን ማግኘት ቀላል ነው ያሉት አቶ ካሳሁን፤ ከፓኬጂ ጀምሮ በጥራት በማዘጋጀት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻልም ጠቁመዋል። ለዚህም የተለያዩ ድጋፎችና ማበረታቻዎችን ማድረግ አስፈላጊና ተገቢነት እንዳለው አመላክተው፣ በእሴት ጭመራ ላይ ለተሰማሩ ላኪዎች ማበረታቻና ድጋፎች እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አቶ ካሳሁን እንዳስታወቁት፤ ከድጋፎቹ መካከልም ቡና ላይ እሴት ጨምረው ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ የተዘጋጁ ላኪዎች የብቃት ማረጋገጫ በፍጥነት እንዲያገኙ የሚደረግበት ሁኔታ ይጠቀሳል። ከባለሙያዎች ጋር በሚደረግ የዕለት ተዕለት ግንኙነትም በኤክስፖርት ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን በመከታተል ለመፍታት ይሰራል። ይሁንና የኢትጵያን ቡና በጥሬው መግዛት የለመደው ዓለም አቀፉ ገበያ ኢትዮጵያ ውስጥ እሴት የተጨመረበትን ቡና የመግዛት ፍላጎት የለውም። ያም ቢሆን የተጀማመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ወደፊት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ታምኖበት እየተሰራ ነው።

በዓለም አቀፍ ገበያ ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት ጥሬ ቡና ባለፈ እሴት በተጨመረበት ቡና ለመታወቅ ተወዳዳሪ መሆን የግድ ነው ያሉት አቶ ካሳሁን፤ ለዚህም የተጀማመሩት ሥራዎች አበረታች እንደሆኑ ገልጸዋል።

አሁን በዓለም አቀፍ የገበያ ሁኔታ እሴት የተጨመረበትን ቡና ግብይት በሚፈለገው መልኩ ሰብሮ መግባት አዳጋች ቢሆንም፣ ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት እንደ ቻይና ያሉ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ሰብሮ በመግባት እሴት የተጨመረበትን ቡና ማስተዋወቅ ይቻላል።

እሴት የተጨመረበትን ቡና ከኮሎምቢያ፣ ከብራዚልና ከሌሎች ዓለም ሀገራት እያስገቡ በሚጠቀሙ የአፍሪካ ሀገራት ዘንድ ተደራሽ በመሆን ገበያውን መቆጣጠር ይቻላል። ይህን ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ኢትዮጵያ ከጥሬ ቡና እያገኘች ካለችው ገቢ የተሻለ ገቢ በማምጣት ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ማሳደር ይቻላል ብለዋል።

በቡናው ዘርፍ በተከናወኑ ሥራዎች ወደ ውጪ በሚላክ ቡና መጠን፣ ስፔሻሊቲ ቡና በብዛት በመላክ፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝትና በመሳሰሉት ተጠቃሽ ለውጦች መጥተዋል። በዚህ የመንግሥትም የግሉ ዘርፍም ጽኑ ፍላጎት በሆነው እሴት የተጨመረበት ቡናን ለውጭ ገበያ በሚፈለገው መልኩ የማቅረብ ሥራ በሰፊው ተሰማርቶ ለውጥ ማስመዝገብ ያስፈልጋል። ከፍተኛ ገቢ በማስገኘት በሚታወቀው እሴት የተጨመረበት ቡና ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ በሀገር ውስጥ የሚስተዋሉ የዘርፉን ተግዳሮቶች እየተከታተሉ መፍታት፣ ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትም በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል። ሌሎች የዘርፉን ችግሮች በመፍታት ውጤት ማምጣት እንደተቻለ ሁሉ በእዚህም ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You