
ኢትዮጵያ በአትክልትና ፍራፍሬ / ሆርቲካልቸር ልማት ከቀዳሚ ሀገራት ተርታ ሊያሰልፋት የሚያስ ችል እምቅ አቅም መኖሩ በተደጋገሚ ሲነገር እንሰማለን። ይህንን አቅም ወደ ተግባር በመለወጥ የሀገርን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የትምህርት ተቋማት ፤ አምራች ኃይሉና በመንግሥት መካከል ያለው ጥምረት ጠንካራና ዘላቂነት ያለው እንዲሆን ይጠበቃል።
በተለይም በዘርፉ በትምህርትና የልማት ሥራዎች ከተሠማሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብዙ የሚጠበቅ ይሆናል። በቅርቡ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር “ሆርቲካልቸር ለዘላቂ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው ለሶስት ተከታተይ ቀናት የቆየ የሆልቲ ፍሎራ ኤክስፖ ተካሂዷል።
ተሳታፊ የነበሩ ባለሙያዎች እስካሁን የተሠሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት የተመዘገበባቸው ቢሆንም እንደ ሀገር ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ይናገራሉ። በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ የሆርቲካልቸርና የእጽዋት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ፍቃዱ (ዶ/ር) የሆርቲካልቸር ትምህርትና ልማት በዩኒቨርሲቲው ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚሠሩ ጕዳዮች መካከል ነው ይላሉ።
የምንሠራቸው ምርምሮች መለያ ቀዳሚ መስፈርት ምን ያህል አካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል ነው። «እኛ ሕዝብ ውስጥ ነን» በሚል መሪ ቃል ሁሉንም ባይሆንም ለአካባቢው ማህበረሰብ ጠቃሚ የሆኑትን ግኝቶቻችንን በመለየት በየወቅቱ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እናደርጋለን። በዚህም በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እያከናወንን እንገኛለን። በቅርቡ ይፋ ካደረግናቸው መካከል ከአጥንት የተፈጥሮ ማዳበሪያ መሥራት አንዱ ነው ብለዋል።
ይህም ከተለያዩ ማዳበሪያዎች ጋር ተቀላቅሎ አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚችልና ለአሲዳማ አፈር ተመራጭ እንደሆነ ተረጋግጦ በአሁኑ ወቅት በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል የሚሉት ኃላፊው ፤ ከዚህ በተጨማሪም አዳዲስ የተዳቀሉ የቡናና የሙዝ ዝርያዎችን በማውጣት ለተጠቃሚ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ይናገራሉ።
አላጌ ግብርና ኮሌጅ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንተርፕራይዝ ዲቨሎፕመንት ምክትል ዲን አዲሱ አባተ በበኩላቸው፤ አላጌ በቂ የከርሰ ምድር ውሃ ያለውና አፈሩም ጥሩ በመሆኑ ለአትክልትና ፍራፍራ ልማት ተመራጭ ሲሆን ከማስተማር በተጨማሪ ሰፊ የአትክልትና ፍሬፍሬ እንዲሁም የሰብል ማሳዎች አሉት። እስከ ቅርብ ጊዜ ልማቱ ያለ ቢሆንም ዋና ሥራው ማስተማር ነው።
በአሁኑ ወቅት ግን በስፋት እንደ በቆሎና በሎቄ ባሉ ጥራጥሬዎች ላይ ይሰጥ የነበረውን ትኩረት በማዛወር በፍራፍሬና በሽንኩርት ላይ እየሠራ ይገኛል። በዚሀም ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት የኮሌጁን ገቢ ለማሳደግ በተሠራው ሥራ በአካባቢው ያሉ የተደራጁና ግለሰብ አርሶ አደሮችንም ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በተጨማሪ በቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት ክፍል በምርምር የሚገኙ ውጤቶችንና ቴክኖሎጂዎች ለአካባቢው ማህበረሰብ ተደራሽ እየተደረጉ ይገኛል። ለአካባቢው ነዋሪ ለልጆች፤ እንዲሁም ለራሱ ለአርሶና አደሩ ከአጫጭር ሥልጠና እስከ ከፍተኛ ትምህርቶች የሚሰጥ ሲሆን ባለሙያዎች በገበሬ ማሠልጠኛ ተቋማት እየሄዱ ሥልጠናና ምክር እንደሚሰጡ አመልክተዋል።
በተመሳሳይ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ተስፋሁን በላይ፤ በየኒቨርሲቲው በአትክልት ፍራፍሬ አበባ ልማትና አጠቃላይ ድህረ ምርት አያያዝ ረገድ ምርምሮች እየተካሄዱ ናቸው የሚሉት አቶ ተስፋሁን፤ ለዚህም በቆጋ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት አስራሁለት ሄክታር መሬት ላይ የሠርቶ ማሳያ ቦታዎች ተዘጋጀተው እየተሠራባቸው ይገኛል።
በተለይ በድህረ ምርት አያያዝ ረገድ ለሽንኩርና ለአበባ ምርት ከዩኒቨርሲቲው የወጡት ግኝቶች ብዙዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው። በሽንኩርት ምርት ድህረ ምርት አያያዝ ረገድ በአሁኑ ወቅት ወደ ማህበረሰቡ እየተባዛ ያለው ግኝት ሽንኩርትን እስከ ስድስት ወር ሳይበቅል ሊያቆይ የሚችል ነው። እንደአጠቃላይ በምርምር የተገኙ ውጤቶች ወደ ተግባር እንዲቀርቡ ከአርሶ አደሩ ጋር በጥምረት እየሠራን የምንገኝ ሲሆን አዳዲስ ግኝቶች ባይኖሩም አርሶ አደሩ በሠርቶ ማሳያው እንዲገኝ በማድረግ የሃሳብ፤ የእውቀትና የልምድ ልውውጥ ይደረጋል ብለዋል።
በኤክስፖው የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል። የአትክልትና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር) ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በርካታ ቁጥር ያላቸው በሆርቲካልቸር ዘርፍ የተሠማሩ አነስተኛ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ይህንን ጅምር ለማስቀጠልና የሀገርንና የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በዘርፉ የተሠማሩ የትምህርት ተቋማት ሚና ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።
መንግሥት ዘርፉን ለማሻሻል ትልቅ ትኩ ረት በመስጠት አነስተኛ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንተፕራይዞችን ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል። ያሉት ሚኒስትሩ ዘርፉ ጥሪት ለማፍራትና በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ለሚመጣው የሥራ ፈላጊ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሲሆን እስካሁን በሥራ እድል ፈጠራው ተጠቃሚ ከሚሆኑት መካከል 80 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የሆርቲካልቸር ልማት እያደገ መምጣት የወጪ ንግድን በማሳደግ በቂ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚያስችል ሲሆን ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ከ366 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘት ችሏል። ይህንን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ውጤት ለማስቀጠል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዘርፉ ውስጥ የሚኖራቸውን ድርሻ ማሳደግ እንደሚገባም አስታውቀዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም