
መንግሥት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በያዘው ቁርጥ አቋም በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ንቅናቄ በማድረግ የሀገሪቱን ምርታማነት በማሳደግ ላይ ይገኛል፡፡ የበጋ ስንዴና ፣ የከተማ ግብርና፣ የሌማት ትሩፋትንና መሰል መርሃ ግብሮች በአራቱም የሀገሪቱ ኮሪዶሮች እና በመሃል ከተሞች ጭምር እስከ ዛሬ የት ነበርን የሚያስብሉ ተስፋ ሰጪ የግብርና ውጤቶች እንዲመዘገቡ እያደረገ ነው፡፡
ከሰሞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሰባተኛው የመስክ ምልከታ መርሃ-ግብሩ ከግብርና ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በምስራቅ ሀረርጌ እና በሐረሪ ክልል የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ለጋዜጠኞች አስጎብኝቷል፡፡ በጉብኝቱም በተፋሰስ ልማት ወደ ምርታማነት የተመለሱ መልክዓ-ምድሮችን፣ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር ብቻ ሳይሆን ከምግብ ዋስትናም ጋር ተያይዞ የለማ አረንጓዴ ዐሻራን፣ በመኖሪያ ግቢያቸው ዓሳን እያረቡ የሚመገቡ አርሶ አደሮችን፤ የዶሮ፣ የንብ ፣ የወተት ላም መንደሮችን፣ የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን እና ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን እንዲሁም ሌሎች በርካታ የልማት ሥራዎችን ተመልክተናል።
አርሶ አደር በከሪ አብዱርአማን በሐረሪ ክልል ድሬ ጢያራ ወረዳ አቦከርሙጢ ገበሬ መንደር ነዋሪ ነው። በከሪ ጫት ከማምረት ወደ ጓሮ አትክልት ማምረት የተሸጋገረበትን ሁኔታ እንዲህ ያስረዳል። ‹‹በምታዩት መሬት ላይ ከዚህ በፊት ተተክሎ የነበረው ጫት ነው። የጫት ተክል ምርት የሚሰጠው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ የእኔም ገቢ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሰብስቤ በምሸጠው ጫት ላይ የተመሠረተ ነበር›› ሲል ይገልጻል።
ጫትን ትቼ አትክልቶችን ባመርት ውጤታማ መሆን እንደምችል በግብርና ባለሙያዎች ምክር ሲሰጠኝ አምና ለሙከራ ብዬ በተወሰነች ቦታ ላይ የጓሮ አትክልት ተከልኩኝ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከልኩት የአበባ ጎመን ነበር ፤ 75 ኩንታል አገኘሁ፤ አንዱን ኪሎ በ150 ብር ሂሳብ በመሸጥ በአንድ ጊዜ ምርት ብቻ ወደ 800 ሺህ ብር አገኘሁ፤ በሙሉ ማሳዬ ላይ የጓሮ አትክልት ብተክልና በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ባመርት ሊያዋጣኝ እንደሚችል ስረዳ ማሳው ላይ የነበረውን ጫት ሙሉ ለሙሉ ነቅዬ በጓሮ አትክልቶች ተካሁት ይላል።
ከዚህ በፊት ለጫቱ የምጠቀመውን ውሃ ለመስኖ ልማቱ በማዋል ወደ ሥራ ገባሁ። ዘንድሮ ከአምናው አንጻር ሲታይ ሶስትና አራት እጥፍ የሚበልጥ የጓሮ አትክልት ተክያለሁ፤ ስለዚህ የተሻለ ውጤት እጠብቃለሁ ነው ያለው።
“እንደምታዩት ዘንድሮ የተከልኩት ቃሪያ ነው፤ በጣም ጥሩ ሆኗል፤ ጥሩ ገቢ አገኝበታለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በአትክልትና በጫት ገቢ መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ፤ ከጓሮ አትክልት በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ ማምረት ይቻላል፤ ጫት ግን አንዴ ከተተከለ በኋላ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጠውን ምርት እየጠበቁ መቀመጥ ነው። አሁን እኔ ኑሮዬን እየቀየረ ወደሚገኝ ጥሩ የግብርና ሥራ ገብቻለሁ። በሂደትም የበለጠ እየተሻሻልኩኝ እንደምሄድ ይታየኛል›› ሲል ይገልጻል።
የግብርና ባለሙያዎች አርሶ አደሩ ገቢው እንዲያድግና ምርታማቱ እንዲጨምር አዳዲስ የሥራ ባህሎችን ማስተዋወቃቸው ጠቅሞናል የሚለው በከሪ፤ የሚያደርጉልንን ድጋፍና ክትትልም አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ይላል።
በዚሁ ወረዳ ሌላው ጫትን በመተው የጓሮ አትክልቶችን ሲያለማ ያገኘነው አርሶ አደር አብዱርጀባር ሳሊ ነው። እርሱም ልክ እንደ አርሶ አደር በከሪ ለመስኖ ሥራ እንግዳ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ ቲማቲም እያመረተ አግኝተነዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ የበሰለውን የምስራች ፍሬውን ለቅሞ 30ሺ ብር ሸጧል፤ የተቀረውም ጊዜውን ጠብቆ ሲደርስ ቢያንስ እስከ ሁለት ጊዜ ተመሳሳይ ገቢ እንደሚያገኝ ይጠቅሳል። ገና ውጤቱን በደንብ ማጣጣም ላይ እንዳልደረሰ የተናገረው አብዱልጀባር ፤ ከጅምሩ ያየው ውጤት ግን ተስፋ ሰጪ እንደሆነ አስረድቷል።
የሐረሪ ክልል ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ዑመር እንደሚገልጹት፤ ክልሉ የቆዳ ስፋቱ አነስተኛ እንደመሆኑ በዚያው መጠን የያዘው ለእርሻ የሚሆን ለም መሬትም አነስተኛ ነው። እንደ እርሳቸው አባባል የክልሉን ምርታማነት ለማሳደግ በውስን መሬት ላይ በዓመት ሶስት ጊዜ የማምረት እቅድ ተይዟል፤ ለዚህም ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ማዕከል ጋር በጋራ በመሥራት ለአካባቢው የሚሆኑና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ምርቶችን በመለየት ወደ ሥራ ተገብቷል።
በድሬ ጢያራ አካባቢ በስፋት የሚታወቀው የጫት ምርት ነው ያሉት ወይዘሮ ሮዛ ፤ አርሶ አደሩን በዓመት አንድ ጊዜ ምርት ከሚሰጥ የጫት ተክል ቀስ በቀስ ውጤታማ ወደሚያደርጉ ሌሎች የግብርና ሥራዎች የማለማመድ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የጫት ዋጋ በሀገር ውስጥ ገበያ አይወሰንም ያሉት ምክትል አስተዳዳሪዋ በተለይም ወደ ጂቡቲና ሶማሊላንድ የሚላከው ጫት በተለያዩ ምክንያቶች ፈላጊ ካላገኘ እና ዋጋው ከወረደ አርሶ አደሩ ተጎጂ እንደሚሆን ጠቅሰዋል። በዘንድሮው ዓመትም እንዲህ አይነት ችግር አጋጥሞ እንደነበር አስታውሰዋል።
አርሶ አደሩ ከጫት አምራችነት ወደ ሌላ ለመሸጋገር ፍርሃት አድሮበት እንደነበር ተናግረው፤ በጫት ማሳዎቹ ውስጥ ከጎን አትክልቶችን እንዲተክል በማድረግ አዋጭነቱን እንዲያጤነው ተደርጓል ብለዋል። በዚህም የተሻሉ ውጤቶች በመገኘታቸው አንዳንድ አርሶ አደሮች ጫቱን እየነቀሉ አትክልቶችን የመትከል ልምምድ ላይ ናቸው ብለዋል። ይህም በአካባቢው ግብርና ምርታማነት ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ እና በምግብ ራስን የመቻል ዋስትናን የሚሰጥ አዲስ ተሞክሮ እንደሆነ ወይዘሮ ሮዛ ገልጸዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም