
ፖለቲከኛው አቶ አንዱዓለም አራጌ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሰሞን በአንድ መጽሔት ላይ ጽፎት ያነበብኩት ገጠመኙ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው:-
አቶ አንዱዓለም አራጌ ፕሮፌሰር መስፍንን ለመጠየቅ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ሆነው ወደ ፕሮፌሰር ቤት ይሄዳሉ። ከጥየቃ በኋላ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ናቸውና ጨዋታቸው በሀገራቸው ወቅታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሆነ። ልዩነታቸው ምን እንደሆነ ባይገልጽም፤ ፍፁም ተቃራኒ በሆነ ሃሳብ ሲከራከሩ ይቆያሉ። በተለይም አንዱዓለም እና ፕሮፌሰር መስፍን በተለምዶ ‹‹ዱላ ቀረሽ›› የሚባለውን ዓይነት ክርክር ሲከራከሩ ቆዩ።
በመጨረሻ ተሰነባብተው ሊሄዱ ሲሉ ፕሮፌሰር መስፍን አንዱዓለምን እጁን ጨብጠው በከፍተኛ አድናቆት አመሰገኑት። ፕሮፌሰር መስፍን ማስመሰል የማይወዱ፣ ሀቀኛ እና ደፋር መሆናቸውን የሚያውቀው አንዱዓለም ምስጋናቸው ልባዊ መሆኑን ስላወቀ እየገረመው ‹‹እንዴ! ምኑን ነው የሚያደንቁኝ? ከጀመርን ጀምሮ እኮ በአንድ ጉዳይ ላይ እንኳን አልተስማማንም! ስንጨቃጨቅ ነው የቆየን!›› ሲላቸው፤ ፕሮፌሰሩም ጭንቅላታቸውን በአድናቆት እየነቀነቁ ‹‹እኔም የወደድኩልህ ይሄንን ነው!›› አሉት።
ምሁር እና አዋቂ እንዲህ ነው፤ ማግኘት የሚፈልገው ከእርሱ ተቃራኒ የሆነውን ነገር ነው። ከራሱ ውስጥ ያለውን ነገር የሚደግምለት ሳይሆን ከራሱ ውስጥ የሌለውን ነገር የሚናገርለት ነው። አዲስ ነገር የምናገኘው ከተቃራኒ ነገር ነው፤ የራሳችን ሃሳብማ ራሳችን ውስጥ ያለ ነው።
በማህበራዊ ገጾች ላይ ብዙ ሰዎችን እታዘባለሁ። የሚፈልጉት የራሳቸው እምነት የሆነውን ብቻ የሚነግራቸውን ነው። ከእነርሱ ተቃራኒ የሆነ አተያይ አይወዱም። ‹‹ብሎክ›› ያደርጋሉ፤ ወይም የተሰጠውን አስተያየት ሌላ ሰው እንዳያይባቸው ያጠፉታል። ለሃሳብ ያለን ርቀት ይህን ያህል ነው።
እነዚህን ነገሮች ያስታወሰኝ ሰሞኑን አንድ ጓደኛዬ የነገረኝ ገጠመኝ ነው። ይህ ጓደኛዬ አንድ የመንግሥት ከፍተኛ ተቃዋሚ የሆነ ፖለቲከኛ ከአንድ ሚዲያ ጋር ያደረገውን ቆይታ ይከታተላል። አንድ የሥራ ባልደረባው ገርሞታል ለካ! ጠጋ ብሎ በሹክሹክታ ‹‹አንተ ይሄን ሰውዬ ትከታተላለህ እንዴ! ኧረ እንዳያዩህ!›› ብሎ አለቆቹ እንዳያዩት ማስጠንቀቂያ መሳይ ምክር ሰጠው። ያንን ሰው መከታተል የሰውዬውን ንግግር አምኖ እንደመቀበል፣ ሃሳቡን እንደመደገፍ ስለቆጠረው ማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለሃሳብ ያለን ርቀት ይህን ያህል ነው። እንድገረም ያደረገኝ ይህ ጓደኛዬ ለዚያ ፖለቲከኛ ያለውን አመለካከት ስለማውቅ ነው፤ ‹‹አሁን እነዚህ ሀገር ቢሰጣቸው ምን ሊያደርጉት ነው?›› እያለ የፖለቲካ አካሄዳቸውን የሚቃወም ነው።
እንዲህ ዓይነት ነገሮችን አለመላመዳችን ነው የፖለቲካ ባሕላችንን የተበላሸ ያደረገው። አንድ ሰው የማያምንበትን ነገር፣ የማይወደውን ነገር ደጋፊው ነህ ሲባል ወደ እልህ ይገባል። አንድ የራሴ ገጠመኝ አስታውሳለሁ። በ2008 ዓ.ም ገና ሥራ የጀመርኩበት ዓመት ነበር። በሥራ አጋጣሚም ይሁን በሕይወት ልምድ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የመከታተል ልምዱ አልነበረኝም። ሆኖም ግን በዚያን ዓመትና በ2009 ዓ.ም ኢህአዴግ አንድ ማስጠንቀቂያ ይሰጥ ነበር። የሚዲያዎችን ስም እየጠቀሰ እነዚያን ሚዲያዎች የሚከታተል ሰው እንደ ወንጀለኛ እና እንደ ጥፋተኛ ይታይ ነበር። የሚገርመው ነገር እነዚያን የጠቀሳቸውን ሚዲያዎች አልወዳቸውም ነበር። በኋላ ግን ‹‹ምን ቢኖራቸው ነው?›› ብዬ መከታተል ጀመርኩ። አትከታተሏቸው ባይባል ኖሮ ትዝ አይሉኝም ነበር ማለት ነው፡፡
‹‹ፍረጃ›› የሚባል አደገኛ ነገር ሥር ሰዶብናል። በብዙዎች ላይ የምታዘበው ነገር እነርሱ የማይፈልጉትን ነገር የሚከታተል ሰው ራሱን ችሎ የሚያስብ አይመስላቸውም። አንድ ከ30 ዓመት በላይ የሆነ ሰው ‹‹ይህን አትይ፣ ይህን አትከታተል…›› ሊባል አይገባውም። አንብቦም ሆነ ተከታትሎ መረዳት የሚችል ነው። ልጅ እያለን እንዳናነባቸው የምንከለከላቸው መጽሐፎች ነበሩ። ከሃይማኖት እንዳያጋጩን፣ ወደ አልባሌ ነገር እንዳይወስዱን መሆኑ ነው። በልጅነት አዕምሮ መከልከላችን ትክክል ነው፤ ምክንያቱም ዙሪያ ገባውን እና ክፉ ደጉን የመለየት አቅም አልነበረንም። ዕድሜ ልካችንን እንደዚያ መገደብ ግን ራሳችንን ችለን እንዳናስብ ማድረግ ነው።
አንድ የምንሰማው ተደጋጋሚ ምክር አለ። ይሄውም ‹‹ከእገሌ ጋር አትዋል፤ ከእሱ ጋር አትታይ፣ ያበላሽሃል…›› እንባላለን። ልጅ እያለን ቢሆን ችግር አልነበረውም፤ ነፍስ ካወቅን በኋላ ግን አግባብ አይመስለኝም። ምክንያቱም ክፉ ደጉን ለይተን እናውቃለን። የራሴን የሕይወት ተሞክሮ ልናገር።
አንድ ጠጪ ጓደኛ አለኝ። የትኛውንም የአልኮል መጠጥ(ለዚያውም እየቀላቀለ ሁሉ) ይጠጣል። በቤተሰብም በጓደኛም ተመክሮ ተመክሮ ሊተወው አልቻለም። እኔ እንደማልጠጣ ጓደኞቼ ያውቃሉ። ከሚጠጡ ጓደኞቻችን በበለጠ ከዚህ ጠጪ ጓደኛችን ጋር አብረን የምንሆን ከእኔ ጋር ነው። መጠጣቱን ለምጀዋለሁ፤ አለመጠጣቴን ያከብራል። ከዚህ ጓደኛዬ ጋር አረቄ ቤት ቁጭ ብለን ብዙ ሰዓት እናሳልፋለን። ከማይጠጡ ቢጤዎቼ በተለየ ጨዋታውና ለዛው ይመቸኛል። እሱም በራስ መተማመን ስላለው የእኔ አለመጠጣት አይረብሸውም፤ ‹‹ሙዴ ይበላሻል›› ከሚሉት ወገን አይደለም።
ከዚህ ጓደኛዬ ጋር ይህን ያህል ዓመት ስንቆይ እኔን ጠጪ ሊያደርገኝ አልቻለም። አንዳንድ ቀን ሞቅ ሲለው ወይም ወፈፍ ሲያደርገው ‹‹ጠጣ!›› ይለኛል፤ በቀልድም በቁም ነገርም ቆጣ እያልኩ እንደማልጠጣ እነግረዋለሁ። ስለዚህ በዚህ ልዩነት ውስጥ የጠበቀ ወዳጅነት ኖረን ማለት ነው፡፡
ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው በአንድ ወቅት አንድ ጥያቄ ተጠየቀ። ‹‹ለመሆኑ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንደዚያ ዱላ ቁረሽ ጭቅጭቅ ስትጨቃጨቁ ቆይታችሁ ውጭ ስትገናኙ ሰላም ትባባላላችሁ ወይ?›› ተብሎ ተጠየቀ። የአቶ ልደቱ መልስ፤ ‹‹እንዲያውም ከአንዳንዶቹ ጋር ተቃቅፈን እንቀላለዳለን ሁላ›› ብሎ የተናገረውን አስታውሳለሁ። በራስ መተማመን ማለት ይህ ነው! የራስን ወጥ አቋም ይዞ ሰዋዊ በሆነው ጉዳይ ላይ ደግሞ በነፃነት ጓደኛ መሆን ማለት ነው።
የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ቤተሰቦች ሲናገሩ እንደሰማነው፤ ኮሎኔል መንግሥቱ እና አባታቸው ተቃራኒ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት የነበራቸው ናቸው። አስቂኙ ነገር ደግሞ የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወንድም ደርግን የሚቃወሙ ኃይሎችን ትደግፋለህ ተብሎ በዘመነ ደርግ ታስሮ ነበር። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንኳን ልዩነት ይኖራል ለማለት ነው።
ተቃራኒ ሃሳብ ያለውን ሰው እንደ ጠላት የማየት አባዜ አለቀቀንም። ከዚያ ሰው ጋር ወዳጅ የሆነውን ሁሉ እንደ ጠላት የማየት ኋላቀር አመለካከት ነው ያለን። አንዳንድ ሰዎች ከሆነ ሰው ጋር ሲኳረፉ፤ ከዚያ ካኮረፉት ሰው ጋር ጓደኛ የሆነውን ጓደኛቸውን ሁሉ ይቀየሙታል፤ እንዴት እኔ ካኮረፍኩት ሰው ጋር ጓደኛ ይሆናል? በሚል ነው። ይህ ልማዳችን አድጎ ትልቅ ኃላፊነት ስንሸከምም የፖለቲካ ልማዳችን እኔ የጠላሁትን ጥላ፤ እኔ የወደድኩትን ውደድ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በልዩነት ውስጥ ወዳጅነትን እንላመድ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም