‹‹ባለፉት ሰባት ዓመታት አዲስ አበባ እንደ አዲስ ተወልዳለች ›› አቶ ሞገስ ባልቻ

አቶ ሞገስ ባልቻ-የአ.አ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ

የኢሕአዴግ መንግሥት በሕዝብ ቅቡልነት ማጣትን ተከትሎ በ2010 ዓ.ም አዲስ የለውጥ መንግሥት በኢትዮጵያን እውን ሆነ። ይህንን ተከትሎ ባለፉት ሰባት ዓመታትም የለውጡ መንግሥት ሀገሪቱ ለዘመናት የገጠማትን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስብራት መጠገን የሚያስችሉ ርምጃዎችን እየወሰደ ዛሬ ላይ ደርሷል። በተለይ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች ደግሞ የለውጡ ማሳያ ሆነው ዘልቀዋል።

የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ሕዝቡን ለውጥ እንዲመጣ ያነሳሱት ገፊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? የለውጡ መነሻ ምክንያቶች ምንድን ነበሩ ? ከለውጡ በኋላስ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ የተደረጉ ጥረቶች ምን ይመስላሉ? ስንል ከአዲስ አበባ ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ከአቶ ሞገስ ባልቻ ጋር ቆይታ አድርገናል። አቶ ሞገስ አዲስ አበባ ከለውጡ በፊት እና በኋላ ምን እንደምትመስል ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተውናል፤ መልካም ንባብ

አዲስ ዘመን፡ከዛሬ ሰባት ዓመታት በፊት ሕዝቡን ለለውጥ ያነሳሱ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ሞገስ፡አንድ ቋሚ ነገር በምድር ላይ ቢኖር ለውጥ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በሀገራችን ከሰባት ዓመታት በፊት በነበረው ሁኔታ፤ ሕዝቡ ለውጥ ፈላጊ ነበር። ሰፊ አዲስ ነገር የመሻት ፍላጎት ነበር። በዋናነት በወሳኝ መልኩ በወቅቱ የነበረው መንግሥት ላይ የነበሩ ጉድለቶች እንዲታረሙ እና አለፍ ሲለም እንዲቀየሩ ፍላጎት ነበር። ከእነዚህ ፍላጎቶች ውስጥ ተጠቃሽ ሊሆኑ የሚችሉት የፍትሃዊነት እና የአሳታፊነት ጉዳዮች ናቸው።

የፖለቲካ ስርዓቱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የማሰለፍ እና የማሳተፍ ችግሮች ነበሩ። ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ያገባኛል በሚል ስሜት እንዳይንቀሳቀሱ የመገደብ እና ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የመከልከል እሳቤ ነበር። ይህ ጉዳይ በእሳቤ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአደረጃጀት ጭምር የታገዘ ነበር። ይህንን አካሄድ የተገነዘበው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅሬታውን በተለያዩ መንገዶች ሲያሰማ ቆይቶ በመጨረሻም በሀገሪቱ ላይ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል።

በኢኮኖሚ ረገድም ሕዝቡ ባለው ሀብት ልክ እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚያደርጉ በስልት የተደገፈ አሰራር ነበር። ዜጎች እኩል ሀብት የማፍራት እና የመጠቀም መብት አልነበራቸውም። ይህ ደግሞ ሕዝቡን ለለውጥ አነሳስቶታል። እነዚህ ኢፍትሃዊ አካሄዶችም አግባብ እንዳልሆኑ በኢሕአዴግ ውስጥ ይነሱ ነበር። ነገር ግን እነዚህን ሀሳቦች ተቀብሎ የማስተካከል ፍላጎት አልነበረም። ይህን ተከትሎ ሕዝቡ በስርዓቱ ላይ ቅሬታ እንዲገባው እና ወጣቶችም ለአመጽ እንዲነሱ አድርጓቸዋል።

ዴሞክራሲን ከማስፈን አንጻርም ሰፊ ክፍተቶች ነበሩ። የሕዝቡ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች የሚታፈኑበት፤ የመደራጀት ጥያቄዎች የሚነፈጉበት እና በሕግ መንግሥቱ ጭምር የተቀመጡ የዴሞክራሲ መብቶች የሚነፈጉበት ስርዓት ተፈጥሮ ቆይቷል። የፖለቲከ ምህዳር መጥበብ እና ዜጎች በፖለቲካ አቋማቸው ለእስር መዳረግ የተለመዱ አሰራሮች ነበሩ።

እነዚህ የስርዓቱ ሕጸጾች በውስጥም፤ በውጭም ቅሬታዎችን ስለፈጠሩ የኢሕአዴግ አገዛዝ አጣብቂኝ ውስጥ ወደቀ። በድርጅቱ ውስጥ ለውጥ ፈላጊ አመራሮች እየተበራከቱ በመምጣታቸው የመንግሥት ለውጥ እውን ሊሆን ችሏል።

አዲስ ዘመን፡የመንግሥት ለውጥ ከመጣ በኋላ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ የተሞከረው እንዴት ነው ?

አቶ ሞገስ፡ በእርግጥ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የለውጥ ፍላጎት እንጂ፤ ምንፈልገው ምን አይነት ለውጥ ነው የሚለውን ብዙዎቻችን አልተረዳነውም ነበር። የጋራ ስምምነት ሁሉም ጋር ተፈጥሯል ማለት አይቻልም። ነገር ግን ለውጡን የሚመራው ኃይል ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ሆኖ የቆየው ጉዳይ ምንድን ነው ? መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው ? የሚሉትን ጉዳዮች በዝርዝር ሲያጠና ቆይቷል። በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበዓለ ሲመታቸው ላይ ይፋ እንዳደረጉት እና ሁላችንም እንደተደመምንበት የኢትዮጵያ ችግሮች ፍንተው ብለው ለመውጣት ችለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር በስጋት ውስጥ የነበረችን ሀገር ሊያረጋጋ እና ዜጎችንም ሊያሰባስብ የቻለ፤ አንድነታችንን እና አብሮነታችን ያጠናከረ ነበር። በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የተጎዳውን የሕዝብ ስሜት ያከመ እና ኢትዮጵያውያንን ወደ አንድ መድረክ የሰበሰበ ነበር።

ይህ ንግግር ለበርካታ ሥራዎቻችን መነሻ ነበር። በቀጣም የእዚሁ እሳቤ ማብራሪያ እና በቀጣይ ያሉ አካሄዶችንም ያመላከተ ‹‹መደመር›› መጽሃፍ በጠቅላይ ሚኒስትራችን አማካኝነት ሕዝብ ጋር ደረሰ። መደመር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መጽሃፍ ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት በኢትዮጵያ ውስጥ የለውጥ ፍላጎት እንጂ የሚያስፈልገው ምን አይነት ለውጥ ነው? የሚለውን የመለሰ አካል አልነበረም። በርካታ ኃይሎችም ለውጥ እንዲመጣ ተሳትፎ አድርገዋል እንጂ፤ በለውጡ ላይ የጋራ መግባባት አልነበራቸውም። አንዳንድ ኃይሎችም ለውጡን በራሳቸው እሳቤ የመቃኘት ፍላጎት ነበራቸው።

ሆኖም ለውጡ በአግባቡ ካልተቃኘ እና ካልተመራ እንደ ሀገር የባሳ ውድቀት ሊያጋጥም የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነበር። የብዙዎችን ፍላጎት እና እሳቤ ወደ መድረክ መጥቶ ለውጡ ካልተመራ በስተቀር የባሰ ችግር ሊያጋጥም ይችልም ነበር። የመደመር መጽሃፍ እና እሳቤ እነዚህን ስጋቶች የቀረፈ እና ከሞላ ጎደል ያግባባ ነበር። የመደመር እሳቤ ከነበርንበት አጠቃላይ የፖለቲካ ፤ የኢኮኖሚ እና የማሕበራዊ ስብራቶቻችን በአግባቡ ማከም የሚያስችል እና ያሉንንም ሀገራዊ ወረቶች በአግባቡ በመጠቀም በአዲስ ጎዳና እንድንጓዝ ብርሃን ሆኖ የሚያገልግል ነው።

ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ታሪክ ያላት ሀገር ነች። ይህቺ ሀገር የጥንታዊነቷን ያህል በርካታ ወረቶች እና በዘመናትም የወረሰቻቸው ችግሮች ያሉባት ሀገር ነች። ስለዚህም የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን በአግባቡ የተረዳ ነው። ይህቺ ጥንታዊት አገር ከችግሮቿ እንድትላቀቅ እና ያሏትን ወረቶች እንድትጠቀም ለመጀመርያ ጊዜ እሳቤዎችን ያፈለቀ ነው። እነዚህ እሳቤዎች ባለፉት ሰባት ዓመታት ሕዝቡ በሰፊው የተወያየባቸው እና ወደ መሬትም ወርደው መተግበር የጀመሩበት ናቸው።

ባለፉት ሰባት ዓመታት የተደረገው ለውጥ ስህተቶችን የሚያርም እና ያሉ ጠንካራ ጎኖችን ይዞ የሚጓዝ እንጂ፤ ሁሉንም ነገር በዜሮ የሚያባዛ የአብዮት እሳቤ አይደለም። ስለዚህም ለውጡ ያሉንን ጠንካራ ጎኖች ያስቀጠለ እና ዳካማ ጎኖችንም እያረመ የሚሄድ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ አንጻር የተከናወኑት በጥቂቱ መመልከት ይቻላል።

ከፖለቲካ አንጻር ለውጡን በሁለት መልኩ ከፍሎ መመልከት ይቻላል። አንደኛው በራሱ በፓርቲው ውስጥ የተካሄደው ለውጥ ነው። በፓርቲው ውስጥ የነበሩ የእሳቤ፤ የአደረጃጀት እና የአሰራር ግድፈቶችን በማረም የተደረጉ ለውጦች አሉ። እነዚህ ለውጦች ሲደረጉ በጥናት ላይ በመመስረት እና በርካታ ታዋቂ ምሁራን ጭምር በማሳተፍ ነው። አግላይ እና ከፋፋይ የነበረውን የፖለቲካ አደረጃጀት እና እሳቤ በመቀየር ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያለ ገደብ እንዲሳተፉበት የሚያስችል አደረጃጀት ተፈጥሯል።

ከዚህ ቀደም በአንድ ሀገር ውስጥ እየኖርን አንዱ ባለቤት ሌላው አጋር የነበረበት የተዛባ እሳቤ እና አደረጃጀትን በመለወጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ እንዲወያይ እና እንዲወስን የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ሆኗል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማንነቱ ተከብሮለት በሀገራዊ ጥላ ስር እንዲኖር እና እኩልነት እንዲሰፍን የሚያደርግ አካሄድም ዕውን ሆኗል።

ይህ የፓርቲ ሪፎርም በውስጥ የነበሩ ጡዘቶችን እና መጓተቶችን ያስቀረ እና ተባብሮ የመስራት ባሕልን ያመጣ ነበር። ሆኖም ይህ ለውጥ ያልተመቻቸው እና የቀድሞው አሰራር እንዲቀጥል የሚፈልጉ ግለሰቦች እና ቡድኖችም ነበሩ። ይህ እሳቤያቸውም አግባብ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ቢነገራቸውም ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ወደ አላስፈላጊ ግጭት ተገብቷል። ሆኖም አብዛኛው ኢትዮጵያውያን መንግሥት እየሄደበት ያለውን መንገድ የሚደግፉ ስለሆኑ ለውጡን ከመቀጠል ያቆመው አንዳችም ኃይል አልነበረም።

በሁለተኛ ደረጃ የተደረገው ከፓርቲ ውጭ የተደረገ ለውጥ ነው። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የፖለቲካ ምህዳሩ በአዋጅ፤ በአሰራር እና በጉልበት ጭምር እንዲጠብ ተደርጎ ቆይቷል። ለዓመታት ታፍኖ የቆየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህንን ሊያስተነፍስ እና የዲሞኪራሲ ምህዳሩን ሊያሰፋ የሚችል ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ያስፈልግ ነበር። ከዚህ በመነሳትም በርካታ አዋጆች እንዲሻሻሉ እና እንዲወጡ ተደርገዋል። የተሻሻሉት አዋጆች እና አሰራሮች ፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋታቸውም በሻገር በፖለቲካ እሳቢያቸው ምክንያት ወደ ሀገር እንዳይገቡ ተገድበው የቆዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አመራሮች ወደ ሀገር ገብተው በፖለቲካ ውስጥ በሰላም እንዲሳተፉ በሩ ተከፍቶላቸዋል።

ለፖለቲካ ምህዳሩ ዋስትና ሊሰጡ የሚችሉ የፖለቲካ ተቋማትን የማጠናከር እና የማደራጀት ሥራዎች ተከናውነዋል። ከእነዚህ ተቋማት አንዱ እና ወሳኙ ምርጫ ቦርድ ነው። ምርጫ ቦርድን በአደረጃጀቱ፤ በአሰራሩ እና በሰው ኃይሉ እንዲጠናከር በማድረግ የተጣለበትን ሀገራዊ ግዴታ እንዲወጣ በሚችልበት ቁመና ላይ ለማድረግ ተሞክሯል። ምርጫ ቦርድ እንደዚህ ቀደሙ ለአንድ ወገን ያደላ ሳይሆን ገለልተኝነቱን ሊያረጋግጥ በሚችል እና ሁሉንም የፖለቲካ አመለካከቶች በእኩል መልኩ ሊያገልግል በሚችልበት ቁመና ላይ እንዲገኝ ተደርጓል። ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እምነት የሚጥሉበት ተቋም ለማድረግ ተሞክሯል።

በተመሳሳይ የሚዲያ ተቋማት፤ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ እንባ ጠባቂ ተቋም እና የመሳሰሉት በዚሁ ሒደት ውስጥ እንዲያልፉ ተደርገዋል። የእነዚህ ተቋማት መጠናከር የፖለቲካ ምህዳሩን ለማሰፋት እና ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ረድተዋል። በርካታ የፖለቲካ ኃይሎች በነጻነት እንዲሳተፉ እና ልዩነቶች በሰላማዊ ሁኔታ ሊፈቱ የሚችሉበት አሰራር ተፈጥሯል ማለት ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎን በአዋጅ እና በአሰራር ብቻ ሊፈቱ የማይችሉትን በተደጋጋሚ የፖለቲካ ውይይት ጭምር እንዲፈቱ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራባቸው ይገኛል። ለአብነት የወሰን እና የማንነት ጉዳዮች በአዋጅ እና በአሰራር ብቻ ሊፈቱ ስለማይችሉ በተለየ መንገድ መፍትሄ የሚያገኙ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ጽንፍ የረገጡ የፖለቲካ እሳቤዎች ሀገሪቱን ዋጋ ሲያስከፍሏት ቆይተዋል።

አንደኛው ፍጹም አክራሪነት ላይ የተመሰረተ አንድነት  የሚል ነው። ይህኛው ሁሉም ነገር አንድ አይነት መሆን አለበት ብሎ ሙጭጭ የሚል ነው። ሁሉንም መልኮች በመደፍጠጥ አንድ እሳቤ ብቻ ሀገር እንዲገዛ የሚፈልግ እሳቤ ነው። በሀገራችን ውስጥ ያለውን ብዝሃነት ከግምት የማያስገባ፤ ሕብረብሄራዊነትን ታሳቢ የማያደርግ እሳቤ አንዱ የፖለቲካ ብልሽታችን ነው።

ሁለተኛው ለእዚህ እሳቤ ምላሽ የሚሰጥ እና ልዩነት ላይ የሚያተኩር አካሄድ ነው። ብዝሃነት ላይ ብቻ ያተኮረ፤ ማንነት ላይ ብቻ የሚያጠነጥን፤ ሀገራዊ ሁኔታን የሳተ እሳቤም የፖለቲካ አንዱ ገጽታችን ሆኖ ቆይቷል። በዚህም ዘርፍ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲደራጁ ሆኗል።

ብዙዎቹ ፓርቲዎችም የራሳቸውን ቁስል እና ሕመም ብቻ እያጎሉ የሚሄዱ እና ዋና ምሶሶ የሆነውም ሀገር የምንለውን እሳቤ የሳቱ ለመሆን ችለዋል። ይህ ደግሞ አንድነታችን እንዲላላ እና እርስ በእርስ የነበረን ግንኙነት ችግር እንዲገጥመው አድርጓል።

ስለዚህም እነዚህን ሁለት ጽንፎች ይዞ ሀገር መምራት ስለማይቻል የለውጡ መንግሥት መካለለኛውን መንገድ በመምረጥ ሚዛኑን የሚጠብቅ የፖለቲካ እሳቤ እውን እድርጓል። እሳቤው ነባራዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ነው። ከእዚህ አንጻር በምርጫ ያላሸነፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ሀገር የሚያስተዳድሩበት እድል አግኝተው ከገዢው ፓርቲ ጋር እየሰሩ ይገኛሉ። ይህ እንደ ሀገር አዲስ እሳቤ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ለዘመናት የቆዩ የፖለቲካ እሳቤዎችም በተወሰኑ ዓመታት ጥረት ብቻ ሊፈቱ ስለማይችሉ በምክክር እና ውይይት ዕልባት እንዲያገኙ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከተገባ ሶስት ዓመታት አልፈዋል። በአጠቃላይ የፖለቲካ ሪፎርሙ ለግጭት እና አለመግባባት የሚዳርጉንን ታሪካዊ እና አሁናዊ ሁኔታዎችን በዘመነ እና በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።

ከኢኮኖሚም አንጻር የተደረጉ ለውጦች የሕዝቡን ጥያቄዎች መሰረት ያደረጉ ናቸው። ሕዝቡ በአካባቢው ጸጋ እንዲጠቀም እና ፍትሃዊነት እንዲሰፍን የሚያስችሉ አካሄዶች ተግባራዊ ተደርገዋል። ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመቅረጽ በኢትዮጵያ ያሉ የኢኮኖሚ ጸጋዎች ወደ ሀብትነት እንዲለወጡ ማድረግ ተችሏል። ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ስር ነቀል የሚባል ለውጥ ውስጥ ገብታለች። ሀገሪቱ ከሴራና ከመገፋፋት ፖለቲካ ወጥታ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት ካደረገችው ጥረት ባሻገር በኢኮኖሚ ዘርፉም በርካታ መሻሻሎች ተመዝግበዋል።

ከለውጡ በፊት በነበሩ ዓመታት ኢትዮጵያ ስትከተለው የነበረው የኢኮኖሚ ስርዓት የውጭ ብድርና ዕርዳታን መሰረት ያደረገ ስለነበር፤ ሀገሪቱን ከፍተኛ ለሆነ የብድር ዕዳ ጫና ዳርጓታል። በርካታ የልማትና የሥራ ዕድል ጥያቄ ባለባት ሀገር ውስጥ ለትውልድ የሚተላለፍን ዕዳ እያከማቹ መሄድ በቀጣይ ሀገሪቱ የማትወጣው አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከታት መንግሥት በመረዳቱ በአፋጣኝ በአይነቱ አዲስ የሆነ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊስ በመተግበር እንደ ሀገር ከተገባበት አጣብቂኝ ውስጥ ኢትዮጵያን ለማውጣት ተችሏል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚው ማሻሻያው ሀገር በቀል እሳቤን በመያዝ ዜጎች ያላቸውን ሃብት እንዲያለሙ፤ ኢትዮጵያ ስትከተለው የነበረውን ከፍተኛ ብድር እንድታቆም የሚያስገድድና የውጭ ባለሃብቶችን በስፋት እንዲገቡ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። የኢኮኖሚ ማሻሻያው መተግበር የነበረውን ዕድገት እንደገና እንዲያንሰራራ ከማድረጉም ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ ትልቁን የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር ያስቻለ ነው።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በውስጣዊ ችግሮችና ውጫዊ ጫናዎች ከፍተኛ ፈተና ገጥሟት የነበረ በኢሆንም፤ ኢኮኖሚው ዕድገት ከማስመዝገብ ወደ ኋላ አላለም። ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ወቅት እንኳን ኢትዮጵያ 6 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ኢኮኖሚዋን መታደግ ችላለች። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት በርካታ ቁሳዊና ሰብአዊ ጉዳት ቢያስከትልም ቀደም ሲል ለፈተና የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባቱ እንደ ሀገር የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ችግሩን ማለፍ ተችሏል።

በማሕበራዊ ዘርፎችም ትምህርት እና ጤና የማስፋፋት፤ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ችግሮች የመቅረፍ እና ድሃ ተኮር አካሄዶችን የመከተል አሰራር ስንከተል ቆይተናል።

አዲስ ዘመን፡ለውጡ ለአዲስ አበባ ከተማ ይዞ የመጣውን ትሩፋት ቢያብራሩልን?

አቶ ሞገስ፡አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፤ የአፍሪካ መዲና፤ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እና ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ከተማ ናት። ስለዚህ አዲስ አበባ ከሀገር አልፎ እንደ ዓለም አቀፍ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባት ከተማ ነች። ስለዚህም ይህንን ኃላፊነትዋን እና ታሪኳን ሊመጥን የሚችል ሥራ መሰራት አለበት። በአዲስ አበባ የመጣው ለውጥ በዋነኛነት የእሳቤ ለውጥ ነው።

አንደኛው አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ ነች የሚል ነው። አዲስ አበባ የሁላችንም ቤት ነች። ከኢትዮጵያውያን አልፎ የአፍሪካውያን ከተማ ነች። ከኒዮርክ እና ጄኔቫ ቀጥላ የዲፕሎማሲ ከተማ ነች። ሆኖም ይህቺ የዲፕሎማሲ መናኸርያ ስሟና ግብሯ ለዘመናት ተራርቆ ቆይቷል። ከተማዋ ከምስረታዋ ጀምሮ በዘመናዊ ማስተር ፕላን የተቆረቆረች ባለመሆኗ እና ለዘመናትም አስታዋሽ አጥታ በመቆየቷ በእርጅና ብዛት ለመፍረስ ተቃርባ ነበር። የመሰረተ ልማት ዝርጋታዋም ሆነ አረንጓዴ ሽፋኗ አንድ ከተማ ሊያሟላ ከሚገባው ዝቅተኛ መስፈርት በእጅጉ የራቀ ሆኖ ቆይቷል።

ሆኖም የመንግሥትን ለውጥ ተከትሎ ከተማዋ ባገኘችው ትኩረት አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብ አበባ የመሆን እድል አግኝታለች። ስሟን እና ክብሯን የሚመጥን ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግ በመታመኑ፤ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስ እናደርጋታለን በሚል መርህ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ተወዳዳሪ ከተማ እንድትሆን በርካታ ሥራዎች በመተግር ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብሎም የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ አዲስ የሆኑ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑባት ናቸው። ከተማዋን ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት የሚያበቋት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችና የመዝናኛ ስፍራዎች በስፋት እየተከናወኑባት ይገኛሉ። የአንድነት ፓርክ፤ የወዳጅነት አደባባይ፤ እንጦጦ ፓርክ የመሳሰሉት የቱሪስት መዳረሻዎች ከተማዋ እንደገና እንድታንሰራራ አድርገዋታል።

በጀመርነው ዙር የአዲስ አበባን ገጽታ ከመሰረቱ የሚለውጥ የኮሪደር ልማት በአምስት አቅጣጫዎች ተተግብሮ አዲስ አበባን ውበት አላብሷታል። በአሁኑ ወቅትም ሁለተኛው ዙር ኮሪደር ልማት በመፋጠን ላይ ይገኛል። የኮሪደር ልማቱ የተጎሳቆለውን የአዲስ አበባ ገጽታ ለመቀየር ከማስቻሉም በላይ አዲስ አበባ ከአቻ ከተሞች ጋር መሳ ለመሳ እንድትቆምና የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ማዕከል የመሆን እድል አግኝታለች። አስገራሚ በሆነ መልኩም የኮንፈረንስ ቱሪዝም መናኸርያ ለመሆን በቅታለች።

የኮሪደር ልማቱ ትሩፋቶች የሆኑት የዓድዋ ሙዚየም፤ ልዩ ልዩ የመስህብ ቦታዎች እና ማራኪ እይታዎች እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ለኮንፈረንስ እና ለቱሪዝም የምትመረጥ ከተማ እንድትሆን አድርጓታል። በአጠቃላይ ያለፉት ሰባት ዓመታት አዲስ አበባን እንደ አዲስ የወለዱ ዓመታት ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡በከተማዋ የተከናወኑ ሰው ተኮር ተግባራትን እንዴት ይገልጿቸዋል?

አቶ ሞገስ፡እንደ አጠቃላይ በአዲስ አበባ የሚከናወኑ ተግባራት ሰው ተኮር ናቸው። እየተሰራ ያለው ከበጀት አደላደል ጀምሮ እስከ ትግበራ ድረስ የእያንዳንዱን ነዋሪ ሕይወት በሚጠቅም መልኩ ነው። ሰው ተኮር ተግባራት ስንል ከሥራ ፈጠራ አንስቶ አቅም የሌላቸውን ሰዎች መደገፍ ጭምር የሚያካትት ነው። በተለይም ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ተማሪዎች እና አረጋውያን ሰው ተኮር ተግባራችን የትኩረት እቅጣጫዎች ናቸው። የሥራ ዕድልም ከመፍጠር ጎን ለጎን የከተማ አስተዳደሩ አቅም የሌላቸውን ዜጎች ለመደገፍ በዓመት ወደ 12 ቢሊየን ብር ድጎማ ያደርጋል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል። ለእነዚህ ዜጎች የመስርያ ቦታ በመስጠት፤ ስልጠና በማመቻቸት፤ ብድር በማቅረብ፤ ሼድ በመስጠት፤ መሬት በማቅረብ ፤ ብድር በማቅረብ ሁሉ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

ከሥራ ፈጠራው ጎን ለጎን አቅም ደካማ የሆኑ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በየዓመቱ ወደ 1 ሚሊዮን ለሚጠጉ ተማሪዎች የትምህርት ግብዓት በነጻ እንዲያገኙ ይደረጋል። 850 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ደግሞ በቀን ሁለት ጊዜ እንዲመገቡ እያደረግን እንገኛለን። ይህ ትምህርት ቤት ምገባ ለተማሪ ወላጆች ትልቅ እፎይታ ከመፍጠሩም በሻገር ትውልድ የመገንቢያ አንዱ መንገድ ነው።

አቅም ደካማ የሆኑ እናቶችን ለመደገፍ እየተደረገ ባለው ጥረት በሴፍትኔት ተደራጅተው ወደ 200 ሺ የሚጠጉ እናቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ሕይወታቸውን እየመሩ ይገኛሉ። ከዚሁ ጎን ለጎንም የከተማዋ አስተዳደር ለሴቶች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ለጎዳና ተወዳዳሪነት እና ለሴተኛ አዳሪነት የተጋለጡ ሴቶችን ከጎዳና በማንሳት እና አሰልጥኖ ሥራ ለማስያዝ የነገዋ የሴቶች ማዕከልን የመሳሰሉት ተቋማት ተገንብተው ፍሬያማ ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። በነገዋ የሴቶች ማዕከል በሶስት ዙር ወደ 1 ሺ የሚጠጉ ሴቶች በ17 አይነት ሙያ ዘርፎች ሰልጥነው ወደ ሥራ መሰማራት ችለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ እያከናወናቸው ካሉ ሰው ተኮር ተግባራት አንዱ አቅም የሌላቸው አረጋውያን በምግብ እጦት እንዳይቸገሩ የሚያደርጉ የምገባ ማዕከላት በስፋት ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል። በአሁኑ ወቅት 24 የሚደርሱ የምገባ ማዕከላት በሁሉም ከተማዋ አካባቢዎች አቅም የሌላቸውን አረጋውያን ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ እየመገቡ ይገኛሉ።

ከዚሁ ጎን ለጎንም በተጎሳቆሉ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ አረጋውያንን በመለየት በለውጡ ዓመታት ባለሃብቶችን በማስተባበር 37ሺ522 ቤቶችን በዘመናዊ መልኩ በማደስ አረጋውያን ቀሪ ዘመናችውን በደስታ እንዲኖሩ ለማድረግ ተችሏል።

አዲስ ዘመንአዲስ አበባ የስኬቷን ያህል ያልተፈቱ ችግሮች ያሉባት ከተማ ነች። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በቀጣይ ምን ታስቧል?

አቶ ሞገስ፡እውነት ነው። አዲስ አበባ በስኬት ብቻ የታጀበች ከተማ አይደለችም። ለዘመናት የተከማቹ እና ወቅትም የሚፈጥሯቸው ችግሮችም ያሉባት ከተማ ነች። የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር፤ የኑሮ ውድነት እና የመሳሰሉት አሁንም እየፈተኑን ያሉ ችግሮች ናቸው። የሥራ እድል ፈጠራውም ቢሆን ገና ብዙ መስራት የሚጠይቀን ነው። ስለዚህም በቀጣይም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ጠንክረን የምንሰራባቸው ይሆናሉ።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራርያ እናመሠግናለን።

አቶ ሞገስ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You