
የዲፕሎማሲ ሥራ አንድ ሀገር ከሌላ ሀገር ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ለማሻሻል እና የጋራ ጥቅም ባላቸው መስኮች ላይ ትብብር ለማጠናከር ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ ዲፕሎማሲ በዓለም ላይ ሰላምን እና ደህንነትን ለመጠበቅም የሚያገለግል መሳርያ ነው። በዓለማችን ላይ የሚገኙ ዲፕሎማቶች የዲፕሎማሲ ሥራ ሲያከናውኑ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ።
ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ወይም ከተከሰቱ በኋላ ሳይባባስ እና ወደ ውጥረትና ጦርነት ሳያድግ የሚከላከሉበት ሲሆን በዋናነት ውይይትና ድርድር በማከናወን በስምምነት ይቋጩታል። በመሆኑም የዓለማችን ሰላምና ደህንነት በአብዛኛው በሀገር መሪዎች እና በዲፕሎማቶች እጅ ላይ የተቀመጠ ነው ቢባል ብዙም ማጋነን አይሆንም። የዚህ ፅሁፍ ዋና ትኩረት የመከላከል ዲፕሎማሲ ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን ለጽሁፌ ርዕስ የተጠቀምኩት በሀገራችን አባባል ያለውን “ሳይቃጠል በቅጠል” ዲፕሎማሲ (Preventive Diplomacy) የሚል ነው።
ሀገሮች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጦርነት ይገባሉ። ከእነዚህ ውስጥ በዋናነት የድንበር ጉዳይ፣ የዜጎች ሁኔታ፣ የድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች፣ በሀገር ውስጥ ጣልቃ ገብነት እና ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ውጥረቶች ወደከፋ ሁኔታ እንዳይደርሱ በመከላከል ዲፕሎማሲ አማካኝነት ማስቆም ይቻላል። አስቀድሞ የሚደረግ የመከላከል ዲፕሎማሲ ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት የሚወሰድ የሰላም እርምጃ ነው።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት የመከላከል ዲፕሎማሲ ማከናወን እና ጦርነት ከተነሳ በኋላ ሰላም ለመፍጠር የሚሰራውን ሥራ ጊዜና ገንዘብ በሁለት ወገን አድርገን ስንመዝነው ግጭት መከላከል አነስተኛ ወጪ ያለው መሆኑን ይገልጻሉ። የመከላከል ዲፕሎማሲ የሚያከናውን መንግሥት ሌላ አገር ወደጦርነት እንዳይገባ ወይም የእራሱ መንግሥት ከሌላ መንግሥት ጋር ወደውጥረትና ጦርነት እንዳይገባ ለመከላከል ሊሆን ይችላል።
የመከላከል ዲፕሎማሲ የሚከናወነው የግጭቶች ፍንጭ ሲታይ እና ሁኔታዎቹ (trends) ወደ ከፋ ችግር ሊያመሩ እንደሚችሉ በቂ መረጃ ሲኖር ነው። በዲፕሎማሲ ሥራ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት መከላከል ወደፊት ሀገር ልትከፍለው የምትችለውን ከፍተኛ የሕይወት፣ የገንዘብና የማቴሪያል ዋጋ ይታደጋል። በመሆኑም ዲፕሎማቶች አሁን ያለውን ብቻ ሳይሆን ወደፊት ምን ሊከሰት ይችላል በሚለው ጉዳይ ላይ አበክረው ማሰብና መተንተን አንዱ ኃላፊነታቸው ነው።
በዓለማችን ላይ በታሪክ ከ10000 ያላነሱ ጦርነቶች እንደተከናወኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ከእነዚህ ጦርነቶች ውስጥ 1500 የሚሆኑት ትልልቅ ጦርነቶች እና ብዙ ውድመት ያደረሱ ናቸው። እነዚህ በታሪክ ሂደት የተከሰቱ ጦርነቶች ቆይታ አጭር ወይም ረጅም ሊሆኑ ይችላሉ። ለአብነት ያክል ጣልያን በዓድዋ ጦርነት ስትሸነፍ ጦርነቱ የተከናወነው ለሰዓታት ብቻ ነው። በዓለማችን ላይ ሰባት የሚሆኑ ጦርነቶች ደግሞ ከመቶ ዓመታት በላይ እንደወሰዱ መረጃዎች ያሳያሉ። ከእነዚህም ውስጥ ስፔንና ቺሊ ከ270 ዓመታት በላይ የተዋጉ ሲሆን እንግሊዝና ፈረንሳይ ደግሞ ለአንድ መቶ አስራ ስድስት ዓመታት (1337-1453) ተዋግተው በፈረንሳይ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በአሁኑም ወቅት በርካታ ጦርነቶች እየተካሄዱ ሲሆን በዋናነት የሩስያና ዩክሬን፣ እስራኤልና ሃማስ፣ የሳህል ሀገራት ይጠቀሳሉ። ከዚህም በተጨማሪ በአንድ ሀገር ውስጥ በርካታ እርስ በእርስ የሚደረጉ ጦርነቶች ይካሄዳሉ። የመከላከል ዲፕሎማሲ ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ በርካቶቹ ጦርነቶች ባልተከናወኑ ነበር።
በዚህ መልኩ በተከናወኑ ጦርነቶች ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል፣ ከፍተኛ የሆኑ የሰብአዊ ቀውሶች የንብረት ውድመቶች አስከትለዋል። ኢኮኖሚውንም የሚጎዳ እንደመሆኑ መጠን ልዕለ ሀያል የነበረው አገር በሌላ ልዕለ ሀያል እንዲተካ አድርጓል። ለአብነት ያክል የዓለም ጦርነቶች ከመከሰታቸው በፊት እንግሊዝ በሁለንተናዊ መልኩ ዓለምን ትመራ ነበር። ብዙም የጦርነት ተሳትፎ ያልነበራት አሜሪካ የዓለም ጦርነት ሲያበቃ የእንግሊዝን ቦታ ይዛ አንደኛ ልዕለ ሀያል ሀገር ለመሆን በቅታለች።
እንደሚታወቀው የመከላከል ዲፕሎማሲ ባለመከናወኑ አንደኛ ዓለም ጦርነት ተካሄደ። ከዚህ ያልተማሩ ሀያላን መንግሥታት ሁለተኛውን የዓለም ጦርነትንም አስተናገዱ። ቀጣይ ውድመት እንዳይከሰት የመከላከል ዲፕሎማሲ በዓለም ደረጃ ትኩረት የሚሻው የዲፕሎማሲ ዘርፍ ነው። በአሁኑ ሰዓት በዓለማችን ላይ በርካታ አይነት የጦር መሳሪያዎች እየተሰሩ ነው፤ ብዙ ጦርነቶች እየተከናወኑም ነው፤ በርካታ ሰዎች እየሞቱ ነው፤ ከፍተኛ ቀውሶች እየደረሱ ነው።
ጦርነት ሲበዛ መሰረተ-ልማትም ይወድማል፣ የሽብርተኝነት መስፋፋት እድል ይጨምራል፣ የኢንቨስትመንት ፍሰት ይቀንሳል፣ የዋጋ ግሽበት ይጨምራል፣ ድህነት ይስፋፋል፣ የአካል ጉዳተኛ ቁጥር ይጨምራል፣ የሕግ የበላይነት ይጠፋል፣ የስደተኞች ቁጥር ይጨምራል ወዘተ። ይህንን ችግር በሙሉ መቅረፍ ቢያስቸግርም መቀነስ የሚቻለው በመከላከል ዲፕሎማሲ ነው።
የመከላከል ዲፕሎማሲ ፅንሰ ሀሳብ የቆየ ቢሆንም ለመጀመርያ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትኩረት እንዲያገኝ ያስቻሉት የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ በመሆን ያገለገሉት ዳግ ሀመርሾልድ (Dag Hammarskjöld) ናቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን ሲገልፁ እንዳሉት ግጭትን ከመፍታት ይልቅ መከላከል ቀላል እና ብልህነት ነው ብለዋል። ሀመርሾልድ በኮንጎ ተከስቶ የነበረውን ችግር ለመቅረፍ በአውሮፕላን ሲጓዙ አደጋ ገጥሟቸው እ.ኤ.አ 1961 በዛምቢያ የሞቱ የስዊድን ዜጋ ነበሩ። እርሳቸው ከሞቱ በኋላ በዚያው ዓመት የሰላም የኖቬል ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል (posthumously awarded)።
ነጮች ሲተርቱ በሽታን መከላከል ከመዳን ወይም ከመፈወስ የተሻለ ነው “Prevention is better than cure’’ ይላሉ። ይህ አባባል በሕክምና ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ፣ በሰላም ግንባታ እና በውጭ ጉዳይ ሥራዎችም ውስጥ አግባብነት ያለው ነው። እንደሚታወቀው አንድ ሰው ከታመመ በኋላ በርካታ መድሀኒቶችን በመውሰድ፣ ወይም በሕመም ከተሰቃየ በኋላ ሊድን ይችላል።
መድሃኒቱም ከበሽታው ያድነው እንጂ ሌላ ተጓዳኝ ሕመም ሊያመጣበት ይችላል፤ ወይም ሊሞትም ይችላል። ይህ ሂደት የሚወስደው ጊዜና ገንዘብ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይም ሁለት አገሮችን ወደ ጦርነት ሳይገቡ በዲፕሎማሲ ጥበብ ግጭቱን ማስቀረት ማለት አገርም እንደበሽተኛው ሰውዬ እንዳትማቅቅ ወይም እንዳትፈርስ ይታደጋታል።
የችግሮችን ምንጭ ለማድረቅ የተሰራ የመከላከል ዲፕሎማሲ ውጤታማ ሲሆን አገሮች ከግጭት ይልቅ ወደ ትብብር እንዲመጡ ያግዛል። ከላይ እንደተገለጸው የመከላከል ዲፕሎማሲ በመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአፍሪካ ሕብረት እና በመሳሰሉት የሚከናወን ነው።
በዓለም ላይ ያሉ ሁሉም መንግሥታት ጋር ተግባብቶ ለመሥራት አስቸጋሪ የሚሆንበትም ጊዜ አለ። መንግሥታት ይህንን ዲፕሎማሲ እየተከተሉም ሌላ መንግሥት በጦርነት “ይዋጣልን” ብሎ ገፍቶ ከመጣ ምርጫ ስለሌለ ወደ ጦርነት ሊገባ ይችላል፤ አገር መከላከል የግድ ስለሚል፡ በአንድ ወቅት አንድ ጉምቱ ዲፕሎማት ከግብፅ ጋር ስላለው የዓባይ ውሀ ድርድር ላይ እኛ ከ80 ፐርሰንት በላይ የናይል ውሀ አመንጭ ሆነን እንዴት ተጠቃሚ መሆን የለብንም? ለሚለው የኢትዮጵያ ጥያቄ ግብፆች የሚሉት ቢያጡ ዝናብ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመዝነቡ በፊት በሰማይ ላይ ያለው ደመና (cloud) እኮ የጋራችን ነው አሉ ብለውኛል። እንደዚህ አይነት ሚዛን የማይደፋ መከራከርያ ይዘው ከመሚመጡ ወገኖች ጋር በጋራ የመከላከል ዲፕሎማሲ ሥራ ለመስራት አይቻልም ባይባልም ፈታኝ ግን ያደርገዋል።
ዲፕሎማሲ በዋናነት የሚሰራው አገሮች ወደ ጦርነት ከማምራታቸው በፊት እና ጦርነቱን ከአጠናቀቁ በኋላ ነው። የመከላከል ዲፕሎማሲ ደግሞ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የሚሰራ ሲሆን ጦርነቱ ከአበቃ በኋላ የሚደረገው የድርድር ዲፕሎማሲ ነው። በዚህ ድርድር ለአሸናፊው ወገን ያደላ ስምምነት የመፈጸም እድሉ ከፍተኛ ነው።
የመከላከል ዲፕሎማሲ ሥራ በግጭትና በጦርነት መሀከል በአለ ጊዜ ውስጥ ሊሰራ የሚችል ነው። የመከላከል ዲፕሎማሲ ለማከናወን የሶስተኛ ወገን ዲፕሎማቶችና የአገር መሪዎች በሚያደርጉት ምልልስ እና ውይይት (Shuttle Diplomacy) የችግሮችን ምንጭ ለማግኘትና ግጭቶች ሳይባባሱ ለመፍታት ያግዛቸዋል። የመከላከል ዲፕሎማሲ ሥራ ሊሳካ ወይም ላይሳካም ይችላል። ከተሳካ ብዙ እልቂትና ውድመት ይታደጋል፡ ካልተሳካ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል።
በአንድ መቶ ቀናት ውስጥ 800,000 ሰዎች በሩዋንዳ ሲያልቁ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቀያቸውን ለቀው ወደሌላ አገሮች ተሰደዋል። ይህ ችግር ከመከሰቱ በፊት የመከላከል ዲፕሎማሲ ሥራ በተባበሩት መንግሥታት አለመሰራቱ እንደሆነ እና ድርጅቱም እንደውድቀት የተቀበለው ጉዳይ ነው። የአፍሪካ ሕብረትም ማድረግ የነበረበትን ሥራ ባለማድረጉ ነው። ግጭቱ ሊነሳ እንደሚችል የሚዲያዎች እኩይ ሥራ ምልክት የሰጠ ቢሆንም በመዘናጋት ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። የሩዋንዳ ሕዝብ እና የዓለም ሕዝብ በእጅጉ ያዘኑበት እና ቀድመን ይህንን አድርገን ቢሆን ኖሮ ይህ አይሆንም ነበር የሚል ትልቅ የዓለማችን የታሪክ ጠባሳ ጥሎ ሄዷል። ይህ የሚያሳየው የመከላከል ዲፕሎማሲ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ነው።
የመከላከል ዲፕሎማሲ ለመሥራት ይቻል ዘንድ ስጋት በአለበት ቦታ ላይ በመገኘት መረጃ መሰብሰብና የቢሆን ትንተና መሥራት አስፈላጊ ነው። በተለይም አሰላሳይ ተቋማት ይህንን ተግባር በጥናትና ምርምር በመደገፍ የዲፕሎማሲውን ሥራ ማገዝና የሀገር ሰላምና ደህንነት፣ የኢኮኖሚ እድገትና የዜጎችን ተጠቃሚነትን እንዲረጋገጥ ማድረግ ይገባቸዋል።
ይህ የቢሆን ትንተና ጥናት ግጭቱ አሁን በአሉበት ሁኔታ ቢቀጥልስ? ግጭቱ ተባብሶ ወደ ብጥብጥና ጦርነት ቢያመራስ? ሁኔታውስ ወደ ሰላም ቢያመራ የሚሉ ቢሆኖችን (Best and Worst Scenarios) በማንሳትና ለእያንዳንዱ ክስተት ተጓዳኝ ምላሽና የስትራቴጂ ዝግጅት በማስቀመጥ የሚከናወን ነው። በመሆኑም የቢሆን ትንተና የተሰራበት ጉዳይ ወይም ጭብጥ አንዱ አማራጭ ቢከሰት የተቀመጠውን ስትራቴጂ መዘዝ አድርጎ መተግበር ብቻ ነው። ይህ ለነገሮች ክስተት መደናገጥና መረበሽን ያስቀራል። በመሆኑም የመከላከል ዲፕሎማሲ ለመሥራት የቢሆን ጥናቶች ከፍተኛ ጥቅም አላቸው።
የመከላከል ዲፕሎማሲ ከቢሆን ትንተና በተጨማሪ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ኔትወርክ በሥራ ላይ ሲውል ይታያል (Early warning system)። ይህ አሰራር በተባበሩት መንግሥታት፣ በአፍሪካ ሕብረት እና የኢኮኖሚክ ኮሚኒቲ/ለምሳሌ ኢጋድ/እየተሰራበት ይገኛል። በአብዛኛው የሚነሳው ጉዳይ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ለሚመለከተው አካል እንዲከላከል ግብዓት ሆኖ የሚደርሰው ችግሩ ከተከሰተ በኋላ መሆኑ ነው። ይህም ማለት አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደበት የመከላከል ዲፕሎማሲ ብዙም ፍቱን መድሀኒት ላይሆን ይችላል፣ ከጊዜ ወይም ከፍጥነት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ።
የአፍሪካ ሕብረት፣ የምሥራቅ አፍሪካ እና ሌሎች የአፍሪካ ቀጠናዊ ተቋማት (RECs) የሀገር ሽማግሌዎች መማክርትም አቋቁመዋል። የእነዚህ መማክርት ዋና ዓላማ የግጭትና ጦርነት የመከላከል ዲፕሎማሲ ለማከናወን እና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ለማድረግ በማሰብ ነው። ጥያቄው ግን ምን ያህል ፋይዳ አምጥተዋል ነው።
የቀድሞ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋም የአፍሪካ መሪዎች ስለድንበር ሰፊ ውይይት አድርገው ነበር። ወደፊት ሊመጣ የሚችል ግጭትን እና ጦርነትን መከላከል ይቻል ዘንድ ቅኝ ገዢዎች በዘፈቀደ ያሰመሩት የአገራት ድንበር እንዲጸና ተስማምተዋል። ይህ ውሳኔ በወቅቱ በርካታ ግጭቶች እንዳይከሰቱ ቢከላከልም በሂደት ግን ታሪክ እና ጎሳ እየተመዘዘ የድንበር ግጭቶች ተከናውነዋል፤ አሁንም የቀጠለ ችግር ነው። እንደዚህ አይነት እልባት ያልተገኘላቸው ችግሮች ወደለየለት ጦርነት እንዳያድጉ የመከላከል ዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወን ተገቢ ነው።
የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ምግብ ፣ መጠለያ እና ልብስ ነው ቢባልም ሰላም ከሌለ ግን መሰረታዊ ፍላጎቶች ቢሟሉም ሊተገበሩ አይችሉም። በመሆኑም ሰላም ከመሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ውስጥ ሊካተት ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ምሁራን እንደሚሉት ግጭት ተፈጥሮአዊ ነው ፤ በአግባቡ ከተያዘ ለመልካም ሥራ ሊውል ይችላል ፤ በአግባቡ ካልተያዘ ግን ወደውጥረትና ብጥብጥ አድጎ የጥፋት መሰረት ይሆናል።
የጦር መሳሪያ የሚያመርቱ ካምፓኒዎች እና ሀገራት አትራፊ የሚሆኑት በተለያዩ ሀገሮች ጦርነቶች ሲኖሩና ተዋጊ ቡድኖች መሳሪያዎቻቸውን ሲገዙላቸው ነው። ሰላም ሲኖር የሚከስሩ፤ ጦርነት ሲኖር አትራፊ የሚሆኑ እነርሱ ናቸው። በሀገሮች መሀከል ግጭትና ጦርነት ሲነሳ ለእነርሱ ትልቅ የሚያስደስት ዜና ነው። ሰላም ከሆነማ ካምፓኒዎቹ ይከስራሉ፡ የመዘጋት እድልም ይገጥማቸዋል፤ ሰራተኞቻቸውን ይበትናሉ። ከብዙ ግጭቶች ጀርባ የጦር መሳርያ በገፍ የሚያመርቱ ካምፓኒዎችና ሀገራት ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚችል እንዲሁ በግርድፉ መገመት ይቻላል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ሂደት ጀምሮ እስካሁን የተለያዩ የመከላከል ዲፕሎማሲ ተግባራት አከናውናለች፤ ሌሎች ሀገሮችም ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ጥረት አድርጋለች። አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለጎረቤት አገሮች ቅድሚያ ይሰጣል። ለሀገራችን እድገት የጎረቤት ሀገሮች ሰላምና ደህንነት ወሳኝ ከመሆኑም በላይ፤ አብሮ ለማደግ ሰላም አስፈላጊ ነው። በጎረቤት ሀገሮች የሚከናወኑ ጦርነቶች የጎንዮሽ ጉዳት ስለሚያመጣ እና የአካባቢውንም ሰላም ስለሚያደፈርስ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም እንዲሆን በርካታ የመከላከል ዲፕሎማሲ ሥራ አከናውናለች፤ የተሳካም፤ያልተሳካም። በተለይ በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች መካከል የተከናወነው ግጭት እንዲቆም የመከላከል ሥራ መስራቷ የሚጠቀስ ነው፤ ምንም እንኳን አሁንም ችግሩ ያልተፈታ ቢሆንም።
በጎረቤት አገራት ጦርነት ከተነሳ በርካታ ስደተኞች ወደ ሀገራችን ይገባሉ፤ የሁለትዮሽ ንግድ እና ሌሎች የኢኮኖሚ ሥራዎች ማከናወን አይቻልም፤ ሕገወጥ የመሳርያ ዝውውር በድንበር አካባቢ ይስፋፋል፤ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውሶች ይከሰታሉ። በተመሳሳይ እኛ ሀገር የሚከሰት ግጭት ሌሎች ጎረቤት አገሮችንም የሚጎዳ ነው። እነዚህን መሰል ችግሮች ለመፍታት ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የትብብር፤ የቅንጅት እና የጋራ የመከላከል ዲፕሎማሲ መሥራት ወሳኝ መሆኑን እየገለጽኩ ሳይቃጠል በቅጠል እላለሁ።
መላኩ ሙሉዓለም ቀ.
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስልጠና ዳይሬክተር ጄኔራልና ተመራማሪ
melakumulu@yahoo.com
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም