ታናሽ እና ታላቅ፣ ቀይ እና ጥቁር፣ ሙስሊም እና ክርስቲያን፣ ደግ እና ክፉ፣ የሰው ልጅ እና እንሰሳ የሚባል መከፋፈያ መስፈርት አይታሰብም። አንዱ ጠግቦ ሌላኛው ተርቦ፤ አንዱ ተደስቶ ሌላኛው አዝኖ የሚያድርበት ስርዓት በዛች ከተማ አይታወቅም- በሀረር፡፡
ብዙዎች የምስራቅ ጸሐይ፣ የስልጣኔ መነሻ፣ የጎብኝዎች መዳረሻ ይሏታል። ለዘመናት ከፍተኛ የንግድ ማዕከል ሆና አገልግላለች። ከመሃል ሀገር፣ ከአፍሪካ ቀንድ እና ከአረብ ሀገራት ጋር በንግድ መንገዶች ተገናኝታለች። ወደሃበሻ ምድር የረገጠ ሀገር ጎብኚ ሁሉ እርሷን ሳይረግጥ አላለፈም። በእስልምና ሃይማኖት ‹‹4ኛዋ የተቀደሰች ቦታ›› ተብላም ስትታወቅ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ መስጊዶችና የቀብር ቦታዎች ይገኛሉ። ከአዲስ አበባ በ525 ኪ.ሜትር ገደማ ርቀት ከትማለች።
ጥንታዊቷ የሃረር ከተማ። ዝናዋ ዓለምን አዳርሷል። ጅብ ሰርቆ ሳይሆን ተለምኖ በግላጭ ስጋ ይበላባታል። በማያውቁት ሀገር ሳይሆን በሚያውቁት ጎረቤቶቹ ቁርበት አስነጥፎ ይቀመጣል። ማደሪያው ጫካ መዋያው ዋሻ ሳይሆን በፍቅር ከተሞሉት ሰዎች በሰላም ሲኖር ይታያል። የገና እና የፋሲካ ስጋ፤ የረመዳን እና የመውሊድ ገንፎ በክብር ተጠርቶ ይጋበዛል።
ሐረር በአነስተኛ የመሬት ስፋት በርካታ ጎብኝዎችን ከሚያስተናግዱ ጥቂት የዓለማችን ከተሞች አንዷ ናት። ሀረር በሰባተኛዉ እስከ ዘጠነኛዉ ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተቆረቆረች ይነገርላታል። ከ1ሺ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የከተማዋ ታሪክ ቅርሶቿ እንዲበዙ እድል ፈጥሮላታል። የጀጎል ግንብና አምስቱ በሮች፣ የወርቅ ሳንቲሞች፣ ረጅም እድሜን ያስቆጠሩ መስጊዶች ፣ የስነ-ሕንፃ፣ የታሪክን አሻራ የሚያንፀባርቁ የቤት ውስጥ ዕቃዎች ቱሪስትን ከሚስቡት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። በውስጧ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት
እና በዙሪያዋ የሚገኘው ቁልቢ ገብርኤል ሌላኛው የቱሪስት መዳረሻ ነው።
በፈረንሳዊው ጸሃፊ አርተር ራምቦ የተሰየመው ሙዚየም ሌላው አስገራሚ ቅርሷ ነው። በሙዚየሙ ከረጅም ዓመታት በፊት የተነሱ የሐረር ከተማ ፎቶዎችና በከተማዋ ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን ያካተቱ ክፍሎች አሉበት። አርተር ራምቦ በ1880 ወደ ሃረር ከተማ በመሄድ በ11 ዓመት ቆይታው ለ120 ዓመታት መቆየት የቻሉ ፎቶዎችን አንስቷል። የዚህ ሙዚየም ግንባታ ጂዋጅ በሚባል ህንዳዊ እንደታነጸ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በ16ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በሼክ አሚር ኑር ሙጃሂድ አማካኝነት እንደተገነባ የሚነገርለት የጀጎል ግንብ የሃረር መገለጫ ነው። የጀጎል ግንብ የሐረሪዎች መኖርያ ቤት ነው ይባላል። ይህ ግንብ ከምድር አራት ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን ወርዱ ደግሞ ከ50 እስከ 75 ሴንቲሜትር ይሰፋል። ግንቡ አምስት በሮች ያሉት ሲሆን ውሃ ያለበትን አቅጣጫም ለማመልከት የተሰሩ ናቸውም ይባላል።
የበሮቹ ስያሜም አሰሱም በሪ፣ አርጎ በሪ፣ በድሮ በሪ፣ አስመአዲን በሪ እና ስቁጣት በሪ ይባላሉ። ግንቡን ያሰሩት አሚር ኑር እጅግ ከተከበሩት የሐረር ሼሆች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ናቸው። ኡመር ከሌሎች በርካታ ሼሆች ጋር በመሆን ከሂጅሪያ (1216 እ.አ.አ) ተነስተው ሐረር ከገቡ በኋላ በአካባቢው የጎሣ እና ኃይማኖት መሪዎች ተመርጠው ዒማም እንደሆኑ ይነገራል።
በኢትዮጵያ ጅብ ተከብሮ ስጋ ጎርሶ፤ ገንፎ ተገንፍቶ ቀርቦለት የሚኖረዉ ሐረር ከተማ ብቻ ነው። ከጥር ስምንት እስከ 10 የሐረሬ ጅቦችና የከተማዋ ነዋሪዎች አንድ ላይ የሚያከብሩት አሹራ የሚባልም በዓል እንዳላቸው ይነገራል። ከምስራቅ አፍሪቃ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ በመሆን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) ተመዝግባለች። ‹‹አባድር ጦም አያሳድር›› የሚባልላት የሀረር እና የሐረር እንብርት፤ የተለያዩ እሴቶችን አድሏታል። ህዝቧም ተቻችሎ ይኖርባታል።
የሀረር ህዝብ ታሪክ ፣ ባህል እና ማንነት ከሀረር ከተማ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ሀረሪዎች በረዥም ዘመን የስልጣኔ ታሪካቸው ያፈሯቸው ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀሱ እንዲሁም የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶች ባለቤት ናቸው። ሀረር ከፍተኛ የስልጣኔ እድገት ደረጃ ላይ በደረሰችበት በ16ኛው ክፍለ ዘመን በምስራቅ አፍሪካ የእስልምና ሀይማኖት ትምህርት እና የንግድ ማዕከል ሆናም አገልግላለች። ይህም የበርካታ ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል።
የጀጎል ግንብ የሀረሪ ህዝብ የኪነ ህንፃ ችሎታውን የሚያስመሰክር የታሪክ እና የጥበብ መዘክር ነው። ይህ ግንብ በርካታ ጎብኝዎችን የሳበ ባህር አቋርጠው ዳዋ ጥሰው እንዲያዩት ያስገደደ ውብ ታሪክ ነው። ሀረር ከተማ መቻቻል ያለባት የውበትና የጥበብ መዲና ናት። የኢትዮጵያ ኢስላማዊ ኪነ ህንጻና ባህል ማንንም ሳይመስል፤ ሃይማኖታዊ መሰረቱን ሳይጥል የነገሰባት መዲና ናት።
ለቱሪስት መስብዕነት ሀረሪ ላይ ጅብ ባለውለታ ነዉ ይባላል። ለምን ቢሉ ከሃረር ውጪ በየትኛውም ሀገር ጅብ እና ሰው አብሮ ስለማይኖር ነው። በከተማዋ ለጅብ ስጋ ማብላት የተጀመረዉ የጀጎል ግንብ ሲገነባ ነው ይባላል። ለከተማዋ ንፅህና ሲባል ከየቤቱ የሚወጣውን የምግብ ትርፍራፊ እና ቆሻሻ እንዲለቃቅም ሲባል ነበር መመገቡ የተጀመረው። በግንቡ ዙሪያ ለጅብ መግቢያ ተብሎ የተሸነቆረዉ ቀዳዳ ወረባ ኑድል ይባላል። ብቻ ሃረር ታይታ የማትጠገብ ልርሳት ቢባል ልትረሳ የማትችል ውብ እና አስደናቂ ከተማ ነች።
እርስዎም ይጎብኞት ውብ እና አስደናቂ ነገር አይተው ይመለሳሉ። ኢትዮጵያ በአንድነት የተመሰረተች የብዙ እምነቶች በረከት ያረፈባት የብዙ ጀግኖች ደም እና አጥንት ያነጻት ድንቅ ሀገር ናት። ኢትዮጵያ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የሰላም እና የጥበብ ሀገር ናት። ነኪ ሳይኖራት ተከብራ ለዛላለም ትኑር። ለእማኝነት አቤጅ የተሰኘው በሃረሪ ምክር ቤት የታተመው መጽሃፍ እና ልዩ ልዩ ሰነዶችን ተጠቀምን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2011
አብርሃም ተወልደ