አገራችን በሁለት አማራጮች መካከል ተወጥራለች፡፡ የመጀመሪያው፣ አብዛኛው ዜጋ የሚመርጠውና የሚያቀነቅነው ጎዳና ብሩህ ተስፋን ያመላክታል፡፡ ጎዳናው ሰላም፣ እኩልነት፣ ፍትህ፣ ብልጽግናና ወንድማማችነትን ሰንቋል፡፡ ይህ ባለፉት ስምንት ወራት ከታየው ለውጥ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው መነቃቃት ዜጎች በአዲስ መንፈስ የተሻለ ነገን እንዲያልሙ ምክንያት በመሆኑ በብዙዎች እንደ አይን ብሌን ይጠበቃል፡፡
በሌላኛው ጥግ በማወቅም ባለማወቅም የተሰለፉ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው እንስሳ የጥፋት መንገዱ ያዋጣል ብለው መርጠዋል፡፡ የቁጥራቸው ማነስና የመንገዳቸው ጠማማነት የጎላ ተጽእኖ ይፈጥራል ተብሎ ባይታሰብም፤ እኩይ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው የብዙዎችን ቀና ልብ እየመረዘው ይገኛል፡፡ ይህ የጥፋት ጎዳና አንዱ ጋር በረደ ሲባል ሌላ ጋር የሚለኮስ ግጭት እየፈጠረ ነው፡፡
ብዙዎችን በሚያማልል ብሩህ ተስፋና ጥቂቶችን ‹‹ደስታ›› በሚሰጣቸው ግጭት መካከል የምትዋልለው ኢትዮጵያ ይህን ፈተና አልፋ በማይቀለበሰው የለውጥ መንገድ እንደምትጓዝ ጥርጥር የለውም፡፡ እስከዚያ ግን አቅደው፣ በስሌት ግጭት በመለኮስ ብሎም በማራገብ አትራፊ ለመሆን የሚሞክሩትን ሀይሎች ሴራ በጋራ መመከት ይገባል፡፡ ሳያውቁ በስሜት እየተከተሉ ነገር የሚያራግቡትንና የሚማገዱትን ስርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ይህ የለውጡ ሂደት ብዙ ዋጋ ሳያስከፍል በመንታ መንገድ የምትገኘውን አገር በቀናው ጎዳና እንድትጓዝ ያደርጋልና፡፡
በአሁኑ ወቅት ግጭት በመለኮስና በማራገብ ረገድ ቅድሚያውን የሚወስዱት የማህበራዊ ሚድያ የጥፋት ሰልፈኞች ናቸው፡፡ በሃሰት በተከፈቱ አካውንቶች በርካታ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ የሀሰት መረጃዎች ከአንዱ ጥግ ይወረወራል፡፡ ተልእኮ የተሰጣቸው ሌሎች ደግሞ ይቀባበሉታል፡፡ ነገሮችን ማመዛዘን የተሳናቸው በስሜት የሚመሩ አንዳንድ ዜጎች ተቀብለው እውነት ነው ብለው ያሰራጩታል፡፡ በዚህ መንገድ በግለሰቦች ተፈጥረውና ተሰራጭተው የህይወት ዋጋ ያስከፈሉ የሀሰት መረጃዎች ባለፉት ጊዜያት ታይተዋል፡፡
ግጭት የሚለኩሱና የሚያራግቡ የማህበራዊ ድረገጽ የጥፋት ሰልፈኞች ጊዜያዊ ችግር መፍጠር ቻሉ እንጂ ዘላቂ ትርፍ እንዳላገኙ የእስካሁኑ ጉዟቸው ያሳብቃል፡፡ ህብረተሰቡ እያደር እውነታውን ሲረዳ እያንገዋለለ እየተዋቸው ነው፡፡ ሌላ አካል ይጎዳል ብለው ያሰራጩት የሃሰት መረጃ መልሶ እራሳቸውን ሲለበልባቸውና የበተኑትን መሰብሰብ ሲቸገሩም ታይተዋል፡፡ ለሌላ የሳሉት ቢላዋ የገዛ ወገናችን የሚሉትን ሲቆርጥም ጸጸት ያተረፉ አይጠፉም፡፡ይህም ግጭት በመለኮስም ሆነ በማራገብ አትራፊ መሆን እንደማይቻል ያሳያልና ጥፋትን አምኖ መቀበል፤ በይቅርታ መታከም ይገባል፡፡
በማህበራዊ ድረገጾች በብዙዎች ዘንድ በአክቲቪስትነት የሚታወቁ ግለሰቦችም የሚያሰራጯቸውን መረጃዎች ይዘት ቢያጤኗቸው መልካም ይሆናል፡፡ የማይካደው እውነታ ቀደም ብሎ ለውጡን ለማምጣት ይደረግ በነበረው ሂደት በትጋት የመረጃ ሰጪነትና ህብረተሰብን የማንቃት ሚና ማበርከታቸውን ነው፡፡ ለለውጡ ጉልበት ሆነውታል፡፡ አሁንም ቀጣይ ይሆን ዘንድ ከእነርሱ ብዙ ይጠበቃል፡፡
አሁን አሁን በርካታ አክቲቪስቶች በልጆች ብሽሽቅ አይነት አተካራ ተጠምደው መታየታቸው ግን ያስተዛዝባል፡፡ አንዳንዶቹም በባላንጣነት የፈረጁትን አካል ለማሳጣት ከእውነታ የራቁ መረጃዎች እየፈጠሩና እየተቀበሉ ያሰራጫሉ፡፡ ያልተረጋገጠ መረጃ ያስተጋባሉ፡፡ ብዙዎቹ አክቲቪስቶች ቀላል የማይባል ተከታይ ስላላቸው ከግጭት የተጠቀመ አገር የለምና ተቀባይነታቸውን ለበጎ አላማ ቢያውሉት የለውጡ ቀኝ እጅ መሆናቸውን በተግባር እያስመሰከሩ መሄድ ይችላሉ፡፡ ጥፋተኛንና በዳይን በአደባባይ የማጋለጡ ነገር ተጠናክሮ መቀጠል ያበት ሲሆን፤ ብሽሽቁ ግን መወገድ አለበት፡፡ ይልቅ በሃሳብ መሟገት በእውቀት መከራከር አገር ይገነባልና ትኩረት ሊሠጠው ይገባል፡፡
በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው ግጭት አንዱ መንስኤ ከሚሰራጩት የሀሰት መረጃዎች ጋር የተያያዙ ስለሆነ የህዝብና የግል መገናኛ ብዙሃን ስነ ምግባሩን ጠብቀው በጥንካሬ እንዲቀጥሉ ማገዝ ይገባል፡፡መገናኛ ብዙሃኑ ተአማኒና ተደራሽ እንዲሁም መረጃን በፍጥነት ለህብረተሰቡ የሚያደርሱ እንዲሆኑ ማስቻል አስፈላጊ ነው፡፡ ለእዚህም በመረጃ ድርቅ እንዳይመቱ የሚመለከታቸው አካላት የያዙት መረጃ የእነርሱ ሳይሆን የህዝብ መሆኑን ተገንዝበው ቀና ትብብራቸው ሊጓደል አይገባም፡፡ በዚህ መልኩ በሚፈጠር ቅንጅት ለህብረተሰቡ በወቅታዊ መረጃ ማዳረስ ከተቻለ የአሉባልታ የግጭት መቀስቀሻና ማባባሻ መንገድ ይዘጋል፡፡ ለውጡም በአስተማማኝ ጎዳና ይጓዛል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 5/2011