ሜጋ ፕሮጀክቶች ያለማቋረጥ መገንባት የኢትዮጵያ ልዕልና ማረጋገጫ

ትዮጵያ በፈጣን የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ያለች ሀገር ነች። ከ70 በመቶ በላይ ወጣት የሆነ የሕዝብ ብዛት ያላት፣ እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና የማደግ ሕልም ያላት ሀገር ነች። ይሁን እንጂ ይህንን አቅም በሙሉ ኃይል ለመጠቀም እና ካደጉት ሀገራት የመመደብ ራዕይን ወደ እውነት ለመቀየር ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ያስፈልጋታል። ፕሮጀክቶቹ የሥራ እድል ከመፍጠር፣ ኢኮኖሚውን ከማሳደግ እና ድህነትን ከመቀነስ ባለፈ እንደ ሀገር ከዓለም ኃያላን ተርታ የመሰለፍ የዘመናት መሻትን ያሳካሉ። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለዚህ አንፀባራቂ ምሳሌ ነው። ኢትዮጵያ ያለ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንኳን በራሷ ታላቅነትን ማስመዝገብ እንደምትችል ያሳያል።

ለዚህ ነው በዛሬው ርዕሰ ጉዳዬ ላይ ኢትዮጵያ ለምን እንደ ሕዳሴው ግድብ ያሉ ብዙ ፕሮጀክቶችን እንደሚያስፈልጋት በማንሳት ጥቂት የውይይት ሃሳብ ለመጫር የወደድኩት። ለምሳሌ ኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን፣ አውራ ጎዳናዎችን እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ ከኋላቀርነት ከማውጣት ባሻገር ከዓለም ተወዳዳሪ ሀገር መሆን ትችላለች። መንግሥት እነዚህን ራዕዮች እንዴት እውን እያደረገ እንደሆነ ለመመልከት ወድጃለሁ።

ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚኖርባት ከአፍሪካ ሁለተኛው የሕዝብ ብዛት የሚገኝባት ሀገር ነች። አብዛኛው ሕዝብ ደግሞ በእርሻ ላይ ጥገኛ ነው። ይሁን እንጂ ግብርና ብቻውን ሀገሪቱን ወደ ብልፅግና ሊወስዳት አይችልም። ኢትዮጵያ ለመልማት ኢንዱስትሪዎች፣ የተሻሉ መሠረተ ልማቶች እና ዘመናዊ የኃይል አማራጮች ያስፈልጓታል። ሜጋ ፕሮጀክቶች ብዙ ችግሮችን በአንድ ጊዜ ይፈታሉ፤ የሥራ እድል ይፈጥራሉ፣ ከተማዎችን ያገናኛሉ ከውጭ በከፍተኛ ምንዛሬ የሚገቡ እቃዎች ጥገኝነትን ይቀንሳሉ፡፡ ለብዙ አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያ የውጭ ዕርዳታና ብድርን ስትጠብቅ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ከጥገኝነት የሚያላቅቅና ወደ እድገት የሚወስድ መፍትሔ አልነበረም።

እንደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ (GERD) ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግን ኢትዮጵያ የወደፊት እድሏን በራሷ መወሰንና መበልፀግ እንደምትችል አረጋግጧል። ይህ ግድብ ከሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጋር ሲደመር ያለ ምንም ጥርጥር ኢትዮጵያን ከአደጉት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍና ድህነትን ከታሪክ ገፅ ላይ ለመፋቅ ሁነኛ ምሳሌ ይሆናል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአፍሪካ ትልቁ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነው። በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ግድብ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ቤቶች እና ፋብሪካዎች ኃይል ይሰጣል። ፕሮጀክቱ አስደናቂ የሚያደርገው መጠኑ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ይህንን ግድብ ገንብቶ ለማጠናቀቅ እንዴት እንዳሳካችው ነው የሄደችበት ርቀት ነው። ዓለም አቀፍ ባንኮችና ባለጸጋ ሀገሮች ፕሮጀክቱን ለመደገፍ ብድር ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ኢትዮጵያውያን በራሳችን አቅም አሳክተነዋል።

ዜጎች ለግድቡ ፋይናንስ ሲሉ ቦንድ ገዝተዋል። የመንግሥት ሠራተኞች ከደሞዛቸው ቆርጠው ድጋፍ አድርገዋል፤ ገበሬዎች ሰብል ሸጠው አዋጥተዋል። ዲዛይኑን ኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች መርተዋል የሀገር ውስጥ ሠራተኞች አስቸጋሪ የአየር ፀባይና ሁኔታዎችን ተቋቁመዋል። ግብፅና ሱዳን እንቅፋት ለመሆን ቢሹም ኢትዮጵያ ወደፊት ገፍታ ግድቡን በድል አጠናቅቃለች። ይህ ስኬት ሕዝብ በአንድነት፣ በመስዋዕትነት እና በራሱ እምነት ጥሎ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ከተሳተፈ ምን ሊያሳካ እንደሚችል ማሳያ ነው።

ልክ እንደ ሕዳሴው ግድብ ሁሉ ሌሎች ሀገራት ባደረጉት ተጋድሎ በሜጋ ፕሮጀክቶቻቸው ኢኮኖሚያቸውን ለመለወጥ ችለዋል። ለምሳሌ የቻይና ‹‹ሶስቱ ጎርጅ›› እየተባለ የሚጠራው ግድብ በብዙ ውጣ ውረድ የተገነባ ቢሆንም ዛሬ ላይ 10 በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ኤሌክትሪክ ያቀርባል። በውጤቱም ኢንዱስትሪዎችን በማጎልበት እና ሚሊዮኖችን ከድህነት በማውጣት የቻይና የጀርባ አጥንት ሆኗል። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ግድብ የኃይል አቅርቦትን ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን ኃይል ላኪ አድርጎ ያስቀምጣታል፤ ኢኮኖሚዋንም ያሳድጋል የምንለው።

የማዳበሪያ ፋብሪካዎች

ኢትዮጵያ ከሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ማግሥት ትኩረት ልታደርግበት የሚገባው ሌላው የሜጋ ፕሮጀክት የማዳበሪያ ምርት መሆን አለበት። ይህንን ጉዳይ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴርም ለሕዝብ እንደራሴዎች እቅዳቸውን ባቀረቡበት ወቅት አንስተውታል።

እንደሚታወቀው ግብርና 70 በመቶ በሚሆን ሕዝብ የሚሸፈን ነው። አርሶ አደሩ ግን ለዓመታት አነስተኛ ምርት ለማግኘት ሲታገሉ ይስተዋላል፤ ለምርቱ መቀነስም ከውጭ በሚገቡ ማዳበሪያዎች ውድ መሆን አንዱ ምክንያት ነው። ይህን አዙሪት ለመስበር ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ማዳበሪያ ምርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይጠበቅባታል።

በዓመት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ለማምረት አልሞ የነበረው የድሬዳዋ ማዳበሪያ ፋብሪካ ጨዋታን የሚቀይር የነበረ ቢሆንም አፈፃፀሙ ግን እጅግ ደካማ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ጥረት ዳግም መቀጠል ይጠበቅበታል። ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ ማምረት ለገበሬዎች ወጪን ይቀንሳል፣ የሰብል ምርትን ይጨምራል፣ አንድ ጊዜ ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ይቆጥባል።

በመሆኑም መንግጭት ከሀገር ውስጥ ኩባንያዎች እና የሰለጠኑ መሐንዲሶች የቴክኒክ እውቀትን በማስተባበር ልክ እንደ ሕዳሴው ገድብ ሁሉ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታን በስኬት ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል። ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን በምግብ ምርት ራሷን እንድትችል ስትራቴጂካዊ አቅም የሚፈጥር ነው።

በማዳበሪያ ምርት ላይ ሌሎች ሀገሮችም ተመሳሳይ መንገዶችን ተከትለዋል። ለምሳሌ ህንድ በ1960ዎቹ የማዳበሪያ ምርትን በማሳደግ እና የግብርና ቴክኒኮችን በማሻሻል አረንጓዴ አብዮትን አድርጋለች። ይህም ሀገሪቷን ከምግብ አስመጪነት ወደ ዓለም አቀፋዊ የግብርና ምርት ማዕከልነት እንድታድግ አግዟታል። ኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች በመገንባት እያደገ ለሚሄደው ሕዝቧ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ይህንን ስኬት መድገም ይቻላል።

መሠረተ ልማት-አውራ ጎዳናዎች

የኢትዮጵያ ተራሮች እና ሰፊ መልክዓ ምድሮች የምርት መጓጓዣን አዝጋሚ እና ውድ አድርገውታል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ አውራ ጎዳናዎች በሀገሪቱ እየተስፋፉ ከተማና ክልል አማራጭ መንገዶች እየተገነቡ ይገኛሉ። ለምሳሌ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው ዘመናዊ አውራ ጎዳና የሆነው የአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ በዋና ከተማው እና በዋና ዋና የኢንዱስትሪ ከተማ መካከል 85 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው።

በቅርቡ የሚጠናቀቀው ከሀዋሳ አዲስ አበባ የሚደርሰው መንገድም እንዲሁ ሌላ ምሳሌ ነው። በቅርቡ ፕላናቸው የተጠናቀቁ የፍጥነት መንገዶችም ጥሩ ጅምር መኖሩን ያሳያሉ። የመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች መወጠናቸውና ተግባራዊ መደረጋቸው አርሶ አደሮች እቃቸውን በፍጥነት ወደ ገበያ ማጓጓዝ እንዲችሉ ኢንቨስተሮች የተሻለ ትስስር ወዳለባቸው አካባቢዎች እንዲሳቡ ስለሚያደርግ ሜጋ የመንገድ ፕሮጀክቶች እውን መሆን ይኖርባቸዋል።

አውራ ጎዳናዎች ለብዙ ሀገራት እድገት ምክንያት ናቸው። በ1950ዎቹ የተጀመረውን የዩናይትድ ስቴትስ ኢንተርስቴት ሀይዌይ ሲስተም ምሳሌ ማድረግ ይቻላል። ንግድን፣ ቱሪዝምን እና የከተማ መስፋፋትን በማበረታታት ትንንሽ ከተሞችን የኢኮኖሚ መናኸሪያ እንዲሆኑ ትልቅ ድርሻ ነበረው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ ያለው የኢትዮጵያ የመንገድ አውታር ተመሳሳይ ጥቅሞችን እንደሚሰጥ ጥርጥር የለውም። የገጠር አርሶ አደሮችን ከከተሞች ጋር ከማስተሳሰር ባሻገር በግንባታ እና በአገልግሎት ዘርፍ የሥራ እድል እንደሚፈጥር መታወቅ አለበት።

ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ

ኢትዮጵያ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማውጣት እንደ ስኳር፣ ጨርቃጨርቅ እና ማሽነሪ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ታስገባለች። ይህ የውጭ ምንዛሪ ያሟጥጣል፤ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን ያዳክማል። ይህንን አዝማሚያ ለመቀልበስ ኢትዮጵያ በትኩረት እየሠራች መሆኑ ይታወቃል። ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ከመግዛት ይልቅ በሀገር ውስጥ በማምረት ከፍተኛ ወጪ መቀነስ ይቻላል። የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ሜጋ ፕሮጀክት ነው።

ከ20 ሺህ በላይ ሠራተኞች (በአብዛኛው ሴቶች) ተቀጥረው ይሠራሉ፤ እንደ ካልቪን ክላይን ያሉ ዓለም አቀፍ ብራንዶች ልብስ እያመረቱ ነው። እነዚህን እቃዎች በሀገር ውስጥ በማዘጋጀት ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መቀነስ ትችላለች፤ ኤክስፖርት በማድረግም ገቢ ማግኘት ትችላለች። በመሆኑም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት አስፈላጊ ነው።

ደቡብ ኮሪያ በ1970ዎቹ ፈጣን ኢንዱስትሪላይዜሽን ውስጥ በነበረችበት ወቅት ተመሳሳይ ስትራቴጂ ተጠቅማለች። የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት እና ኤክስፖርትን በማበረታታት በጦርነት ከታመሰች ሀገር ወደ የቴክኖሎጂ ግዙፍ ሀገርነት ተቀይራለች። የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ለአምራቾች የሚደረጉ የግብር ማበረታቻዎች እና የሙያ ስልጠና መርሃ ግብሮች ይህንን ሞዴል መድገም አለባቸው።

የገንዘብ ድጋፍ-መፍትሔዎች

እንደሚታወቀው ሜጋ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ማድረግ ትልቅ እንቅፋት ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የገጠማትን ፈተና መወጣት ችላለች። አዳዲስ እቅዶችንም ተግባራዊ በማድረግ ለሕዳሴው ግድብ ዜጎች በቦንድ ግዥ እና በፈቃደኝነት መዋጮ አድርገው ፕሮጀክቱ እውን ሆኗል። የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትብብርም ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። የግል ኩባንያዎች የክፍያ መንገድ የመሰሉ መሠረተ ልማቶች ላይ ተሳትፈው ተመልክተናል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከቡና፣ ከአበባ እና ከጨርቃጨርቅ የምታገኘውን ገቢ ለልማት መጠቀም ትችላለች።

እዚህ ጋር ቻይናን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። በተለይ በመሠረተ ልማት እና በማኑፋክቸሪንግ ላይ ኢንቨስት በማድረግ በተጨማሪም የውጭ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ 18 ትሪሊየን ዶላር ኢኮኖሚ ገንብታለች። ኢትዮጵያ በመንገድ፣ በኃይል ማመንጨት እና በፋብሪካዎች ላይ የሰጠችው ልዩ ትኩረት በተመሳሳይ መልኩ ለረጅም ጊዜ እድገት መሠረት ሊጥል ይችላል። በመሆኑም መሰል ስልቶችን ተጠቅሞ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ይገባል።

የመንግሥት አመራር- ራዕይ እና አፈፃፀም

ጠንካራ አመራር ለኢትዮጵያ እድገት ወሳኝ ነው። መንግሥት ግልጽ ግቦችን ማውጣት አለበት። ተቋማትን ማስተባበር፣ ሕዝቡንም ማሳተፍ ይጠበቅበታል። ለምሳሌ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ የተመራበት መንገድ ግንባታውን የሚቆጣጠር፣ ግልጽነትና ቅልጥፍናን የሚያረጋግጥ ተቋምና ፕሮጀክትን ጀምሮ የመጨረስ እሳቤ ትምህርት ይሰጣል። አዘውትሮ ማሻሻያ ማድረግ፣ ለዜጎች በፕሮጀክቱ ዙሪያ መረጃ እንዲሰጥ ማድረግ፣ ብሔራዊ ኩራትን እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማበረታታት የመንግሥትን የመሪነት ሚና የሚያሳይ ነው። ይህ ስኬት በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይም መቀጠል አለበት።

ለምሳሌ በድህነት ቅነሳ የቬትናም ስኬት የአመራርና አስተዳደርን ብስለትን ያሳያል። በመሬት ማሻሻያ እና በመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶች ቬትናም በ1990ዎቹ ከ60 በመቶ የድህነት ምጣኔ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ከ5 በመቶ በታች አድርሳለች። የኢትዮጵያ መንግሥት ደፋር ቁርጠኝነት የሚጠይቁ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማስተባበርና በመምራት ተመሳሳይ መንገድ መከተል ይኖርበታል።

ተግዳሮቶች

ሜጋ ፕሮጀክቶች ያለ እንቅፋት እውን አይሆኑም። የገንዘብ እጥረት፣ የክህሎት እጥረት እና የፖለቲካ አለመግባባቶች እድገትን ሊያዘገዩ ይችላሉ። በመሆኑም መንግሥት ቁርጠኛ በመሆን እነዚህን ፕሮጀክቶች መገንባት ደረጃ በደረጃ እውን ማድረግ ይኖርበታል። ለምሳሌ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ገጥመውት ከአሥር ዓመታት በላይ ሊወስድ ቢችልም በመጨረሻ እውን ሆኗል።

የክህሎት ክፍተቶችን ለመቅረፍ መንግሥት ተማሪዎችን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ለቴክኒክ ሥልጠና እና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የሀገር ውስጥ እውቀት እንዲያዳብሩ ማድረግ አለበት። የፖለቲካ ተግዳሮቶችንም ቢሆን በውይይት መፍታት ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ የወደፊት ዕቅዶች የበለጠ ተስፋ ሰጪ ናቸው። በኦሞ ወንዝ ላይ ያለው የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ሁለት ሺህ 160 ሜጋ ዋት ኃይል ይጨምራል። የባቡር ሐዲድ የሚያገናኝ ፕሮጀክቶች፣ የኮሪደር ልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች እና ሌሎችም ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መፃኢ እድገት እውን እንደሚያደርጉ እሙን ነው። በመሆኑም በፍፁም ቅንነት ራዕይ ሰንቀን ህልም አንግበን በጋራ ታላቋን ኢትዮጵያን ለመገንባት እንበርታ። ሰላም!!

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You