ጅማ ያነቃቃው የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር

ጥንታዊቷ ታሪካዊ የንግድ ከተማ ጅማ ከአስራ አንድ ዓመት በፊት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚያዘጋጀውን አንድ ውድድር የማስተናገድ እድል ነበራት። ከዚያ በኋላ ግን አትሌቲክስ ወዳዱ የጅማ ከተማ ሕዝብ መሰል ውድድሮችን በከተማው የማየትም ሆነ የመሳተፍ አጋጣሚ አግኝቶ አያውቅም። ከትናንት ጀምሮ ግን ይህ ታሪክ ታድሷል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአራት ከተሞች የሚያዘጋጀው ዓመታዊ የ ”ልወቅሽ ኢትዮጵያ” የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር አካል የሆነ ፉክክርን ጅማ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ትናንት አስተናግዳለች። የከተማው ሕዝብም ከልጅ እስከ አዋቂ በውድድሮ በመሳተፍ ለአትሌቲክስ ያለውን ፍቅር አሳይቷል። ቱሪዝምን ከአትሌቲክስ ጋር ያቆራኘው ይህ ውድድር የንግዷን ከተማ ይበልጥ ያነቃቃ ሆኖም ታይቷል።

“2017 ኢትዮ ቴሌኮም ታላቁ ጅማ ሩጫ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ውድድር ከ15 ሀገራት የተውጣጡ 100 የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ በርካቶችን በአስራ አምስት ኪሎ ሜትር አፎካክሯል። ከአስራ አንድ ዓመት በታች የሆኑ ስድስት መቶ ህፃናት የሚሳተፉበት ውድድርን ጨምሮ 2500 የጤና ሯጮች በአምስት ኪሎ ሜትር ተወዳድረዋል።

መነሻውን ጅማ አባጅፋር ቤተመንግሥት መጨረሻውን ደግሞ በፈረንጅ አራዳ ባደረገው የ15 ኪሎ ሜትር ውድድር በወንዶች ጋዜጠኛና አትሌት ደሳለኝ ዳኜ በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ፣ ጃፋር ጀማልና አቢዮት ሞገስ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ፈፅመዋል። በሴቶች ደግሞ የግሌ እሸቱ ቀዳሚ ስትሆን፣ ሃና ዓለማየሁ ሁለተኛ፣ አና ላውረን ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።

ከ 11 ዓመት በታች የታዳጊ ህፃናት ወድድሩን በፍቅር ሙሉ በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ፣ ዮሴፍ መኮንንና አቤኔዘር ማሙሽ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነዋል። በሴቶች ደግሞ አርሴማ ምትኩ ቀዳሚ በመሆን ስታጠናቅቅ ፣ ዳግማዊት ቢኒያም ሁለተኛ፣ ማህደር ዳዊት ሦስተኛ ሆነው በመፈፀም የማበረታቻ ሽልማት ከከተማው ከንቲባ ተቀብለዋል። በኤሊት ወንዶች አትሌት ለታ ኦሊ ቀዳሚ ሆኗል፣ አትሌት ቀነኒሳ ቶፋና አትሌት አብዶ ሱራ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል። በተመሳሳይ በሴቶች አትሌት ማህሌት ሙሉነህ ቀዳሚ ስትሆን፣ አትሌት ሉቢና ኒዜሙ ሁለተኛ፣ አትሌት መዲና ረሻድ ሦስተኛ አጠናቀዋል።

በታሪዊቷ ጅማ ከተማ የተካሄደው ታላቁ ሩጫ ውድድር የከተማውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከማነቃቃት አንፃር ፋይዳው የጎላ መሆኑን የውድድሩ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል።

ውድድሩን በተመለከተ ከትናንት በስጢያ በተሰጠው መግለጫ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጅማ ከተማ ከንቲባ ጣሃ ቀመር፣ ጅማ ውድድሩን በማስተናገዷ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው “የምንፈልገው ነገር ነው፣ ዝግጅቱም የጋራ ጉዳያችን ነው፣ ለውድድሩ የመጡ እንግዶችም ተደስተው እንደሚመለሱ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት ተናግረዋል። ከንቲባው ከቱሪዝም ሚኒስቴር የውድድር አዘጋጅነት ባጅም ተረክበዋል።

በቱሪዝም ሚኒስቴር ኮንቬንሽን ቢሮ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ግዛው፣ ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም አቅም ቢኖራትም ባለፉት 60 ዓመታት የማህበራዊ ቱሪዝምን ብቻ ስትጠቀም እንደኖረች በማስታወስ ዘርፉን ለማሳደግ ይህን መቀየር እንደሚገባ ተናግረዋል። ወደ ቱሪዝም ቢዝነስ ለመግባትም ስፖርት ትልቁ መሣሪያ መሆኑን ጠቁመው፣ “ታላቁ ሩጫ በዚህ ረገድ ቀድሞ ነቅቷል” ብለዋል። ቱሪዝም ሚኒስቴርም ይህን የመጠቀም በአዋጅ የተሰጠው ሥልጣን ስላለ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር አብሮ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

በውድድሩ ለመካፈል ጅማ የተገኙ ተሳታፊዎች ባለፈው አርብ በሆራይዘን ፕላንቴሽን የኮሳ የቡና ምርምር ማዕከል በመገኘት የቡና እርሻ ጎብኝተዋል። ቅዳሜ ደግሞ በጅማ ከተማ 1900 ሜትር ከፍታ ላይ በመገኘት የ 5 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ በማድረግ በእድሳት ላይ የሚገኘውን ታሪካዊውን የአባ ጅፋር ቤተመንግሥት መዳረሻ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ እንደ አዲስ እየተጀመሩ ካሉ ኢንሼቲሾች አንዱ የስፖርት ቱሪዝም ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ላለፉት ዓመታት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፉት ከሃያ ዓመታት በላይ እስከ ሃምሳ ሺህ ሰው የሚሳተፍበትና በአዲስ አበባ ከተማ ከሚያካሂደው ዝነኛው የአስር ኪሎ ሜትር በተጨማሪ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ “ቅድሚያ ለሴቶች” አምስት ኪሎ ሜትር የሴቶች ብቻ የጎዳና ላይ ውድድር ለረጅም ዓመት እያከናወነ ይገኛል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ስፖርትን ከቱሪዝም ጋር በማቆራኘት ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የአትሌቶች ምድር በሆነችው የበርካታ ከዋክብት መፍለቂያ በቆጂ የጎዳና ላይ ውድድር እያከናወነ ይገኛል።

የብርቅዬ ከዋክብት አትሌቶች መፍለቂያ የሆነችው ኢትዮጵያን የስፖርት ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመሆን በተለያዩ ከተሞች ውድድሮችን በማድረግ ከተሞቹ ያላቸውን የባህልና የቱሪዝም ፀጋዎች በማስተዋወቅ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ እድሎች ለመፍጠር እየሠራ ይገኛል።

የዚሁ ውድድር አካል የሆነ የጎዳና ላይ ሩጫ ባለፈው የካቲት 02/2017 ዓ.ም “የሃዋሳ ሐይቅ ግማሽ ማራቶን” በሚል ስያሜ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ በቀጣይም በቆጂና አርባ ምንጭ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You