
ለመጀመሪያ ጊዜ በተከናወነው የግራንድ ስላም ትራክ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በስኬታማነት አጠናቀዋል። በተለያዩ ርቀቶች የዓለም ምርጥ አትሌቶች የሚካፈሉበት ይህ ውድድር በጃማይካዋ ከተማ ኪንግስተን ለሦስት ቀናት ያህል ተከናውኗል። አትሌቶች በሁለት ርቀቶች በሚያስመዘግቡት ነጥብ መሠረት ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል እጅጋየሁ ታዬ እና ድርቤ ወልተጂ ቻምፒዮን ሊሆኑ ችለዋል።
34 የፓሪስ ኦሊምፒክ ሻምፒዮናዎችን ጨምሮ በጥቅሉ 96 አትሌቶችን በ48 ውድድሮች ያሳተፈው የግራንድ ስላም ትራክ ውድድር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢካሄድም በአትሌቶች መካከል ያለው ፉክክርና በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ያገኘው ተቀባይነት መልካም የሚባል ሆኗል። በቀድሞው አሜሪካዊ የአጭር ርቀት ሯጭ ሚካኤል ጆሃንሰን መሥራችነት የሚደረገው ውድድሩ አራት ዙሮች አሉት። በአንድ ግራንድ ስላም አሸናፊ የሚሆኑ አሊያም ከፍተኛ ነጥብ የሚያስመዘግቡ አትሌቶች ደግሞ የ100ሺ ዶላር ተሸላሚዎች ይሆናሉ።
የመም ውድድሮችን የማበረታታት ዓላማ ይዞ በተነሳው ሩጫም አምስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳታፊዎች ነበሩ። በመካከለኛና ረጅም ርቀት በነበራቸው ተሳትፎም ከሻምፒዮናነት እስከ ደረጃ ተሸላሚነት በመብቃትም ብቃታቸውን ማስመስከር ችለዋል። በሴቶች ረጅም ርቀት 3ሺ እና 5ሺ ሜትር በተፎካካሪነት (በተጋባዥነት) የተካፈለችው አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ሁለቱንም ርቀት በአሸናፊነት ያጠናቀቀች አትሌት ልትሆን ችላለች። እአአ በ2023ቱ የቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያጠለቀችው አትሌቷ በሳምንታት ልዩነት የ5ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሻምፒዮናም የነሐስ ሜዳሊያ ለሀገሯ ማስገኘት የቻለች ምርጥ አትሌት ናት። በቡድን ሥራ የተመሰገነችው አትሌቷ በተፎካካሪነት በገባችበት ውድድር በበላይነት በማጠናቀቅ ብቃቷን ማረጋገጥም ችላለች። አትሌቷ የ5ሺ ሜትር ውድድር በአሸናፊነት ያጠናቀቀችበት ሰዓትም 14፡54፡88 ሆኖ ተመዝግቦላታል፡፡
ሀገሯን ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ውድድር በ3ሺ ሜትር የወከለችው እጅጋየሁ በ2022ቱ የቤልግሬዱ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላ ነበር። በዚህ ርቀትም ምርጥ ተፎካካሪ የሆነችው አትሌቷ የግራንድ ስላም ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቃለች። ርቀቱን ለመሸፈን የፈጀባት ሰዓት ደግሞ 8፡28.42 ሆኖ ተመዝግቦላታል። በዚህም 24 ነጥብ በማስመዝገብ የመጀመሪያው ግራንድ ስላም ሻምፒዮን በመሆን የ100ሺ ዶላር ሽልማቱን የግሏ ልታደርግ ችላለች።
በዚሁ ርቀት ዋና ተሳታፊ የነበረችው አትሌት ጽጌ ገብረሰላማ ደግሞ በሁለቱም ርቀት ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ፈጽማለች። የጎዳና እና የሀገር አቋራጭ ውድድሮች ተሳታፊ አትሌቷ በ5ሺ ሜትር 15፡24.62 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ በሦስተኛነት ውድድሯን ስታጠናቅቅ፤ በ3ሺ ሜትር ደግሞ 8፡38.15 በሆነ ሰዓት ልትገባ ችላለች። በአጠቃላይም 12 ነጥብ በማስመዝገብ የ30ሺ ዶላር ተሸላሚ ሆናለች።
በወንዶች በኩልም በተመሳሳይ በዚህ ርቀት አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት በዋና ተወዳዳሪነት፤ አትሌት ጥላሁን ኃይሌ ደግሞ በተፎካካሪነት ተሳትፈው ነበር። ከፍተኛ የአሸናፊነት ተስፋ የተጣለበት ጠንካራው አትሌት ሐጎስ በታወቀበት የ5ሺ ሜትር 4ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀው። በዚህ ርቀት የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮና የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚውና የሪዮ ኦሊምፒክ ባለ ነሐስ ሜዳሊያ አትሌቱ ባለፈው ዓመት የዓለም ክብረወሰንን ለመስበር ከጫፍ ደርሶ እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህም አትሌቱ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ባስመዘገበው 14፡40.20 የሆነ ሰዓት አራተኛ ደረጃን ሊያስመዘግብ ችሏል። በሁለተኛው የ3ሺ ሜትር ሩጫ ግን የቀድሞ ስህተቱን አርሞ በመሮጥና ከሀገሩ ልጅ ጥላሁን ኃይሌ ጋር በመተጋገዝ አስቀድሞ መውጣቱ አሸናፊ አድርጎታል። የገባበት ሰዓትም 7፡51.55 ሆኖ የተመዘገበለት ሲሆን፤ የሰበሰበው 17 ነጥብም የ50ሺ ዶላር አሸናፊ አድርጎታል። አብሮት የሮጠው ተፎካካሪው ጥላሁን በበኩሉ 25ሺ ዶላር አግኝቷል።
በሴቶች አጭር ርቀት (800 እና 1ሺ500 ሜትር) ደግሞ በብቸኝነት ኢትዮጵያዊቷ አትሌ ት ድርቤ ወልተጂ ተሳታፊ ትሆናለች። በቅርቡ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና 1ሺ500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው አትሌቷ፤ ባለፈው ዓመት በተደረገው የዓለም ሻምፒዮናም ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። ጠንካራዋ አትሌት በሁለቱም ርቀት አሸናፊ በመሆኗ ሽልማቷን ከሻምፒዮናዎቹ ጋር ተጋርታለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም