መላኩን ከባሻገር

ስምን መልዓክ ያውጣው፤ ስሙም “መላኩ አሻግሬ” ሆነ:: መላኩም ወዲያ አሻግሮ ጥበብን አየ:: ገና ብዙዎች ያልተዋወቁትን ቲያትር በአንቀልባው አዝሎ፣ ከአንደኛው የዘመን ጋራ ወደ ሌላኛው አሻገረ:: ታዲያ ከዚህ በላይ የተቀደሰ ማሻገር ምንስ አለ? ዳሩ ግን መላኩ ያልተነገረለት ያልተዘመረለት የሠገነቱ ድልድይ ነው:: አሻግሮ ሳያበቃ ጥበብን ከሠገነቱ ከፍ አድርጓታል:: መላኩ ማለት በቲያትር ጥበብ ባደረበት ሱስ ምክንያት ትዳሩንም ያጣ ሰው::

ያኔ እርሱ ብቅ ሲል፤ ቲያትር ቤት ገና ማለዳ ነበር:: ገና ዘመን ራሱ አልዘመነም:: እሳት ነዶ፣ ጥበብ ተጥዶ፣ ግዙፉ የቲያትር መሶብ ከማዕድ ጠረጴዛው ላይ አልተቀመጠም ነበር:: በዚህ ሰሞን ላይ የመላኩ የቲያትር ጥበብ ምናልባትም ከውስጡ ተከድኖ ሲበስል ነበር:: እርሱን የሚያውቁ ዲያቆን ሆኖ ድቁናውን ሲደቁን ነው:: ከቀጨኔ መድኃኒዓለም ተነስቶ አራዳ ጊዮርጊስ፣ በዮሐንስ አድርጎ ወደ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ያዳርሰዋል::

ድምጹን ግን ብዙዎች ይወዱለታል:: ዜማን የተማረ ብቻ ሳይሆን አዚያዜሙም የሚሰረቀረቅ ነው:: የሚያዩት የሚሰሙት ሁሉ በምናብ ወደፊቱን አሻግረው እንደምን ያለው ሊቀ መዘምራን ሊወጣው እንደሚችል ይገምቱለታል:: ይሄው መላኩ ግን ምርጡ ጥበብ አፈራሽ ቲያትረኛ ሆነ:: ድንገት ባጋጣሚ አንድ የስቅለት ቲያትርን በዝማሬው ሊያጅብ የወጣበትን የቲያትር መድረክ ግዛቱ አድርጎት ምናቡም ከዚያው አልወርድ አለ:: ከዚያን ጊዜ በኋላ የጥበብ ሠራዊት የሆኑ ሥራዎቹን ይዞ ግዛቱን በወረራ እንደሚያስፋፋ ንጉሥ ከአንዱ ወደ አንዱ ይዘለዋል:: መሄድ መሻገር ማሻገር ነው ልማዱ::

የቲያትር ጥበብ ዋናተኛው መላኩ አሻግሬ፤ ውልደትና ሞቱ በ1925 እና በ1985ዓ.ም ሆኖ ሰፍሯል:: በቀድሞው በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ተወለደ:: ያኔ አባቱ አቶ አሻግሬ ወርቅነህ አዲስ አበባ ላይ ከትመው ነበር:: ወላጅ እናቱ ወይዘሮ ወርቅነሽ ይዘኸዋልም ጨቅላውን ልጃቸውን ይዘው እናታቸው ወደሚገኙበት ጅሩ ሄዱ:: መላኩም ሰባት ዓመት እስኪሞላው ድረስ በዚያው ነበር::

ድንገት ግን አዲስ አበባ የነበሩት ወላጅ አባቱ ማረፋቸው ተሰማ:: እናትዬው አሁንም መላኩን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ገሰገሱ:: አባቱ ከሕይወት ወደ ሞት በተሸጋገሩበት መጥፎ አጋጣሚ፣ መላኩና እናቱም ከክፍለ ሀገር ከተማ ተሻግረው ላይመለሱ ጉለሌ ላይ ከተሙ:: እናት ልጃቸው በቤተ ክርስቲያን ትምህርትና በመንፈሳዊ ዕውቀት አድጎ እንዲበስልና የሰጣቸውን አምላክ እንዲያገለግለው በልብ ሳይሳሉት አይቀርም፤ ምናልባትም እንደ ፍቅር እስከ መቃብሩ በዛብህ:: መላኩም እንዲያው ያለውን የልጅነት ጉዞ ለመጀመር፣ ቀድሞ ያቀናው ወደ ቀጨኔ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ነበር:: በዚያው ከሰንበት እስከ ዳዊት፣ አልፎ ዜማን ተማረ:: ድቁናና ዘማሪነቱን ይዞ ከአንዱ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላኛው ሲሾር የነበረውም ከዚሁ በመጀመር ነው::

ድንገት በፍቅር ወጥመድ ተይዛ እንደተሰቃየችው እንደ በዛብህ ልብ፤ በመላኩም ልብ ግራ ቀኝ የምትላወስ የጥበብ ዘር ነበረች:: በአንዲቷ አጋጣሚ ተጠምቆም ይህችኑ ጥበብ ሲያሳድጋትና ሲያገለግላት መኖሩን ጀመረ:: ጊዜው ልክ እንደ ሰሞኑ የትንሳኤው በዓል ከፊት እየመጣ፣ ስቀለቱም ተቃርቦ ነበር:: በወቅቱ የማዘጋጃ ቲያትር ቤት ተዋንያን በአሁኑ የአዲስ አበባ የባሕል አዳራሽ ውስጥ በልምምድ ላይ ናቸው:: እያዘጋጁት ባለው በዚህ የስቅለት ቲያትር ላይ ዘማሪ ያስፈልገው ነበርና ተፈለገ:: መረዋው የመላኩ ድምጽ ዝናው በየት በኩል ሾልኮ እንደደረሰ ባይታወቅም እርሱ እንዲሆን ተደረገ:: ቀድሞውኑ አንዳች የሚጠራውን ድምጽ ሲጠባበቅ ነበርና ለመድረስ ጊዜ አልፈጀበትም:: ከቲያትሩም ሆነ ከቲያትር አባላቱ ጋር ለመዋሃድ አልተቸገረም:: በድንቅ ብቃት መወጣት በመቻሉም አዘጋጆቹን አስደስቷቸዋል:: ኋላ ቲያትሩ የመድረክ እይታውን አጠናቆ ብዙ ሳምንታትና ወራት ቢሄዱም፤ መላኩ ግን ከዚያ ቲያትር ቤት ንቅንቅ አላለም:: አንድ ጊዜ በከበሮ መቺነት፣ ሌላ ጊዜም በድምጻዊነት እያለ እዚያው ለመቀጠር ቻለ::

ውስጡ ላይ እየተንቀለቀለች መቀመጫ ያሳጣችው አንዲት የጥበብ ዘር የነበረች ቢሆንም፤ መላኩ ዓይኑን ጨፍኖ ወደዚህ ውሳኔ እንዲገባ ያስገደደው ሌላ ነገርም ነበር:: ቀደም ሲል ከአገልግሎቱ ጎን ለጎን፣ በተፈሪ መኮንን እና በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አስኳላውንም ሲያስኬድ ነበር:: ነገር ግን፤ በቤት ውስጥ ከእናቱ ጋር እየኖሩ ያሉበት ሁኔታ በችግርና በማጣት ነው:: ቲያትር ቤቱ ውስጥ የነበረውን ጊዜያዊ ቆይታን ለውጦ መልካሙን አጋጣሚ መፍጠሩ፣ በቤተክርስቲያን የነበረውን ብቻ ሳይሆን ትምህርቱንም ጥሎ ነበር:: በማዘጋጃ ቤት ተቀጥሮ መሥራት ከጀመረ በኋላ፤ የቆየው ለስድስት ወራት ብቻ ነበር:: ሌላ መሸጋገሪያ አግኝቶ ተሻግሮ ሄዷል::

ሁለተኛው መዳረሻው ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ሆነ:: በጊዜው ቲያትር ቤቱን ሲያስተዳድር የነበረው ማቴዎስ በቀለ፣ በጥሩ ተቀብሎ በጥሩ መንገድ ያስቀጥለው ጀመረ:: ራሱ ማቴዎስም ቲያትሮችን ይደርስ ነበርና በቲያትሮቹ እንዲሳተፍም ያግዘዋል:: በእንዲህ ሳሉም፤ የአዲስ አበባው ሀገር ፍቅር ዳርቻውን አስፍቶ ሐረርጌ ገባ:: ወዲያ ካቀኑት መካከልም ኃላፊው ማቴዎስ አንደኛው ሲሆን፣ መላኩንም ጭምር ይዞት ሄደ:: ሐረርጌ ከተሻገሩ በኋላ መላኩ በዚያ የቆየው አሁንም ለ6 ወራት ብቻ ነበር::

ከስድስት ወር በኋላ ማቴዎስ ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ፣ ይዞት የሄደውን መላኩንም ይዞ ነው:: በመንፈስ የተሞላውን ክርስቶስን ሲከተል እንደነበረው ጴጥሮስ፤ መላኩም የጥበብ መሪ አባቱ አድርጎ ለተቀበለው ማቴዎስ፣ እንደ ደቀመዝሙርም ይመስላል:: ማቴዎስ የሐረርጌውን ትቶ አዲስ አበባ ሲመለስ፣ “አንድነት ቴአትር ማኅበር” የሚል አንድ ማኅበር አቋቋመ:: ከቡድኑ አባላት መካከል አንደኛው መላኩ ነበር:: ታዲያ አንድ ጊዜ ላይ፤ ሥራዎቻቸውን አሰናድተው ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አቀኑ:: እዚያ ሳሉም በቡድኑ መካከል አይሁኑ ሁኔታ ተፈጥሮ፣ ለግጭትና አለመግባባት ተዳረጉ:: መላኩም የሰለባው አካል ሆኖ ከሥራው ተባረረ:: እሱ ግን አዲስ አበባ ሳይመለስ በዚያው ወደ ጅማ ሄደ:: በጅማ ማዘጋጅ ቤትም በጸሐፊነት መሥራት ጀመረ:: መላኩ አሻግሬ ግን አሁንም መሻገር ወይ አሻግሮ መመልከቱን አያቆምም:: “መሄድ መሄድ አለኝ” የሚለው ዘፈን ልክክ ብሎ የሚሄድበት በርሱ ነው::

መላኩን የት ነው ቢሉት፤ እርሱ ተመልሶ ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ገብቷል:: እንደምን ያለው ዕድለ ለምለም ይሁን፤ ከአዳዲስ ስፍራ ቃኝቶም ሆነ ከነበረበት ናውዞ ቢመለስ መግቢያ አያጣም:: በተዋናይነት መቀጠሩን ግን ሲመለስ አላገኘውም:: የተሰጠው ቦታ “የኢትዮጵያ ድምጽ” በተሰኘው የማኅበሩ ጋዜጣ ላይ የጋዜጠኝነት ግብር መከወን ነው:: ቀስ እያለ በሌሎች አስተዳደራዊ ሥራዎችም ይሳተፍ ነበር:: በዚሁ ሁኔታ ከ1946ዓ.ም እስከ 1949ዓ.ም፤ ለሦስት ዓመታት ያህል ከሠራ በኋላ አሁንም መሄድ አሰኘው:: ምክንያቱም ስንቱን ነገር እርግፍ አድርጎ የመጣበት ጉዳይ ይህ አልነበረም::

ከክብር ዘበኛ ቤት ደጃፍ ደርሶ፣ የሙዚቃ ባንዱን ተቀላቀለ:: ወታደር ባይሆንም ሲቪል ሆኖ ከውጭ ተቀላቀለ:: እዚህም ያገኘው በሀገር ፍቅር ትቶ ከመጣው ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም፤ የምኞቱን ለማሳካት የተሻለ አማራጭና ቀረቤታ ነበረው:: ሾልኮ ለመግባት የሚችልባትን ቀዳዳ አስቀድሞ ተመልክቷት ነበር:: በተሰጠው የሥራ ድርሻ “ወታደርና ጊዜው” የተሰኘውን ጋዜጣ ቀኑን ጠብቆ ለሕትመት እያበቃ ኃላፊነቱን ይወጣል:: በሀገር ፍቅር እያለ ለዚህ የሚሆነውን በቂ ዕውቀትና ክህሎት አካብቶ ነበርና አልተቸገረበትም:: ቀጥሎም በጎን የሙዚቃና የቲያትር ዝግጅቶችን በማሰናዳቱም ተጠመደ::

መላኩ ትክክለኛውን ሽግግር ያደረገው ይሄኔ ነበር:: ሰንዳ አድርጎ ማዘጋጀቱን ብቻ ሳይሆን፣ ራሱም ቲያትርና አጫጭር ተውኔቶችን መጻፍ ጀመረ:: አሀዱ ብሎ በመጀመሪያ “ሴት አረዳችኝ” የሚል ተውኔት ጻፈ:: ከላይም ሆነ ከታች ተውኔቱን ያነበባላቸው ወደዱለት:: እንዲሠራም ተደረገ:: ለመድረክ በቃና መድረክ ላይም ይታይለት ጀመር:: ይህ እንዳለም እንደገና “ሰይጣን ለወዳጅ ቅርብ ነው” ሲል ሌላ ተውኔት አከለበት:: ሁለተኛው ተውኔቱም ተሠርቶ፣ ተወዶለት ይታይ ነበር:: ችግሩ ግን፤ ተውኔቶቹ የሚታዩት በውጭ ሳይሆን እዚያው ባሉ የሠራዊቱ አባላት ነው:: እንዲህ ብቻ መሆኑ ለመላኩ ምቾት አልሰጠውም፤ ደስታውን ቀነሰበት:: አሻግሮ ተመለከተናም አንድ መላ ዘየደ::

መላኩ ከክብር ዘበኛ ሆኖ፣ አሻግሮ የተመለከተው የማዘጋጃ ቤቱን አዳራሽ ነበር:: “ሴት አረዳችኝ” የሚለውን ተውኔቱን ይዞ፣ ተዋንያኑን ከኋላው አስከትሎ ከማዘጋጃ ቤቱ አዳራሽ፣ ከመድረኩ ላይ ወጣ:: ተውኔቱን ለሕዝብ የማሳየት ጥሙን አረካ:: ወዲያው ግን፤ ዳናውን እየተከተለ ከበስተጀርባው ሲገሰግስ የነበረው መዘዝ ዱላውን ጨብጦ ከተፍ አለ:: ተዋንያኑ ተይዘው ወደ እሥር ቤት ተወረወሩ:: መላኩ ግን እንደ ምንም ብሎ አመለጠና በዚያው ደብዛውን አጠፋ:: ለዚህ የተዳረጉት፤ ተቀጣሪ አባል ሆነው ሳለ ያለ ክቡር ዘበኛ ፈቃድ ሥራውን በውጭ በማቅረባቸው ነበር:: የክቡር ዘበኛ ሆነው፣ ከክቡር ዘበኛ ዕውቅና ውጭ መንቀሳቀሳቸው እንደ ክህደትም ጭምር የሚያስቆጥር ነው:: ለተወሰኑ ጊዜያት ተሰውሮ የቆየው መላኩ፣ ከዚያን ጊዜ በኋላ የክቡር ዘበኛን ደጅ ሳይረግጥ በዚያው ቀረ::

ሸሽቶ የሄደው መላኩ ወንዙን ተሻግሮ ከማዶ ታየ:: ከጉብታው ላይ ተቀምጦ ብዙ አሰበ:: እናም ገንዘብ ተበድሮ በቲያትር ጥበብ የተነደፉ ጀማሪያንን አሰባስቦ አሠለጠናቸው:: ቀድሞ የጻፋቸውን ጨምሮ ሌሎችንም እየጻፈም አለማመዳቸው:: ለመድረክ ብቁ መሆናቸውን እርግጠኛ ሲሆን ቀድሞ ወደሚያውቃት ጅማ ይዟቸው ሄደ:: ጅማ ላይ ባሰናዱት መድረክ፣ ከታዳሚው የመግቢያ ትኬት የተሰበሰበው ቀላል የማይባል ገንዘብ ነበር:: ቅሉ ግን፤ እዚያው እንዳሉ ገንዘብ ሰብሳቢው ብሩን ይዞ ተሰለበ:: ይህ መድረክ የተዘጋጀው በብድር ነበርና ለመላኩ “መሬት ተሰንጥቀሽ ዋጪኝ” የሚያስብል ነው:: በኋላ የመመለሻ ገንዘብ እንኳ አጥተው፣ ትሬንታ ኳትሮ ለምነው፤ እንደሌላኛው መረጃም በሀገር አቋራጭ የጭነት መኪና ታጭቀው አዲስ አበባ ገቡ::

የእዳ ገንዘቡ መዘዝ ፊቱን አሹሎ ከቤቱ ሲገባ፣ ከባለቤቱ ትፍስህት አያሌው ጋር የቀለሱት የትዳር ጎጆ መናጋት ጀመረ:: በሽማግሌ ምልጃ ተማጽኖ እንደምንም ተረፈ እንጂ፤ ችግሩ የገዘፈ ነውና በመለያየት መንገድ ላይ ነበሩ:: ከዚህ በኋላ መላኩ ቲያትር በዞረበት ላይዞር በሽማግሌዎቹ ፊት ተገዘተ::

ከዚያ በኋላ፤ በ1950ዓ.ም በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚንስቴር ውስጥ ተቀጥሮ ቃሉን በተግባር መፈጸሙን አሳየ:: ወደተለያዩ ትምህርት ቤቶች እየሄደም በመምህርነት ማገልገሉን ቀጠለ:: ቤተሰቡም ሆነ በፊታቸው የተገዘተላቸው ሽማግሌዎች የሚያውቁት ይህንኑ የማስተማር ሥራውን ነበር:: መላኩ ግን የውስጡ እሳት እየተንቀለቀለበት በድብቅ የቲያትር ሥራውን ይሠራል:: ከ3 ዓመታት በኋላ በ1954ዓ.ም መላኩ፤ ከቲያትር ባለሙያው ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ ጋር ተጣምሮ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ቤት ሥራቸውን አቀረቡ::

ቀደም ሲል “ክህደት የኑሮ መቅሰፍት” የተሰኘውን የተስፋዬ ገሠሠን ተውኔት፤ “ዓለም ጊዜና ገንዘብ” በሚል ተቀይሮ በአዲስ መልክ ታየ:: ከመጀመሪያው መድረክ በኋላ ግን፣ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ተውኔቱ ታገደ:: ከኪሳራ የከፋው ኪሳራ ደግሞ፤ ባለቤቱ የበኩር ልጃቸውን አስከትላ ተለየችው:: የቲያትር ፍቅሩ ለእዳ፣ ትዳሩንም ለአደጋ አሳልፎ ሰጠው:: የባለቤቱን ማምረርና መሄድ ሲመለከት ግን “ዓርብ ጥላኝ ሄደች” የምትል ተውኔት ጻፈ::

የመላኩ አበዳሪዎች ገንዘባቸውን እንዲመልስ አንገት ይዘው መተንፈሻ አሳጡት:: በሕግ ፊት ቀርቦም ወደ ዘብጥያ መውረዱ የማይቀር ነበር:: በደህናው ጊዜ ከተውኔትና በሌላውም ሲሯሯጥ ትንሽ የማይባል ገንዘብ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም፤ አቦቸር ነውና ላገኘው ሁሉ ሲሰጥ ጨርሶታል:: በዚሁ መልካምነቱ በአንድ ወቅት ለቀይ መስቀል የሚሆን 11 ሺህ ስድስቶ መቶ 70 ብር እንደለገሰም ይነገርለታል:: አናቱ ላይ እዳ ተቆልሎ እንኳን የሚያስበው ስለሌላው መሆኑ በእጅጉ የሚያስገርም ነው::

በቅርበት የሚያውቁት ዶክተር ከበደ ሚካኤልም ወደ ንጉሡ ቀርብ ብለው፣ የመላኩን ሁኔታ አስተዛዝነው ነገሯቸው:: ጃንሆይም አዘኑና 2 ሺህ ሁለት መቶ ብር ሰጥተው መላኩን ከእዳ ቀንበር ነፃ አወጡት:: በ1952ዓ.ም በአንድ ሰው እርዳታና አማላጅነት ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ቤት ተዘዋወረ:: እንደገና ወደነበረበት ትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚንስቴር ተመልሶ፣ የድራማ ክፍል ኃላፊ ተደረገ:: የእርሱ መዘዋወር ማብቂያ የለውምና በ1956ዓ.ም በቀለመ ወርቅ ት/ቤት ውስጥ የቴአትርና መዝሙር መምህር ሆነ:: ለተማሪዎቹ ጎበዝ አስተማሪ ቢሆንም አሁንም ግን ከላይ ማስጠንቀቂያ መጣለት::

በማስተማሩ ሂደት ላይ ዋነኛ ትኩረቱን በትወና ከማድረጉም፣ ተማሪዎቹን ይዞ ወደተለያዩ ከተሞች ጉዞ ያደርግ ስለነበረ፣ ይህን እንዲያቆም ትዕዛዝ ደረሰው:: እርሱ ግን ልጆቹን አሠልጥኖ ብቁ ለማድረግ፣ በጊዜና ቦታ ሳይገደብ፣ መብራት በሌለበት በሻማና ፋኖስ እየሠራ ሲከፍል የነበረው መስዋዕትነት ትልቅ ነበር:: በዚህ ሁሉ እያለፈ ካፈራቸው ጋር ወደ ክፍለ ሀገሮች እየሄደ ሲያደርጋቸው በነበሩ እንቅስቃሴዎቹ ውስጥ ባሳየው ነገር፤ አለቆቹም ሆኑ ሌላው፣ ሳይወዱ እንዲያደንቁትና እንዲገረሙበት ተገደዋል::

ከመላኩ ሕይወት ባሻገር፣ ከወዲያ ማዶ ካልተመለከቷቸው የጥበብ ሥራዎቹ መካከል፤ ሽፍንፍን ቁ1 እና 2 በ1959ዓ.ም፣ ማሪኝ በ1960ዓ.ም፣ አዬ ሰው በ1962ዓ.ም፣ የለሁም ብለው ጉድ ፈላ በ1969ዓ.ም፣ ምን ዓይነት መሬት ናት? በ1972ዓ.ም እንዲሁም ክህደት፣ ማጣትና ማግኘት፣ የኑሮ መቅሰፍት፣ ዓለም ጊዜና ገንዘብ…የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው:: በመጨረሻ የሠራት “አንድ ጡት” የምትለዋን ተውኔቱን በብሔራዊ ቲያትር ለማሳየት ችሏል::

መላኩ አሻግሬ ሳይነገርለት በዝምታ የታለፈና ያለፈ ስለመሆኑ ሁሉንም የሚያስማማ ነው:: ከአንዱ ወደሌላው መሸጋገርና መሄድ የማይታክተው የተውኔት መንገደኛ፣ የመጨረሻውን የሥራ ቅጥር ያደረገው በ1969ዓ.ም በብሔራዊ ቲያትር ሲቀጠር ነበር:: ከአሥራ አንድ ዓመታት በኋላ በ1981ዓ.ም በጡረታ ገለል ብሎ የተጫጫነውን ሕመምና ድካሙን ማስታመም ጀመረ:: በአራተኛው ዓመት፣ ሰኔ 1 ቀን 1985ዓ.ም ግን ድካሙ ረታውና ለዘለዓለም እንቅልፍ አሸለበ::

መላኩ አሻግሬ ትልቁን የጥበብ ጀብዱ ከሠራባቸው ውስጥ “ቴዎድሮስ የቴአትር ክበብ” አንደኛው ነው:: አዳዲስ ተዋንያንን እየመለመለ፣ እያሠለጠና እያስተማረ በርካቶችን ወደ ሙያው አምጥቷቸዋል:: አዳዲሶችን እየቀረጸ ብዙዎችን ከማፍራቱ ጎን የመድረክ ሥራዎችንም እያዘጋጀ ያሠራቸው ነበር:: ቲያትሮችንና አጫጭር ተውኔቶችን እየጻፈና እያዘጋጀ፣ ራሱም ይተውናል:: በዚህ ባደራጀው ድርጅት ውስጥ ያፈራቸውን አባላቱን ይዞ፣ በአራቱም አቅጣጫ ያልደረሰበት የሀገራችን ክፍል የለም:: ይህን ሁሉ በሚንቀሳቀስበት ወቅት የቲያትር ጥበብ እንኳንስ በክፍለ ሀገር፣ በአዲስ አበባም ቢሆን ጎልቶ የወጣበት ጊዜ አልነበረም:: በእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ውስጥ እየገባ፣ የቲያትርን ጥበብ እንዲያውቁና እንዲወዱት ያደረገ ባለውለታ ነው:: ቲያትርን ከማሳወቁም፣ ትምህርታዊና ግንዛቤ አስጨባጭ ሥራዎችን እያቀረበ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ማኅበረሰቡን ሲያነቃ ነበር::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You